Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሒልተን ሆቴል ሽያጭ ዋጋ ትመና ጥናት ተጠናቀቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ሆቴሉ ጨረታ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል

የሒልተን አዲስ አበባ ሆቴልን ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር ሲደረግ የነበረው የዋጋ ትመና ጥናት መጠናቀቁን ታወቀ፡፡

      የዋጋ ትመና ጥናቱን ሲያካሄድ የነበረው የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት የተባለ መንግሥታዊ አማካሪ ተቋም ጥናቱን አጠናቆ፣ ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ማቅረቡን የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

      የመጀመሪያውን ዙር የጥናት ውጤት ጨርሶ የሰጠው አማካሪ ድርጅቱ፣ ከሚኒስቴሩ በጥናቱ ላይ የተሰጡ ግብረ መልሶችን አካቶ የመጨረሻው የጥናት ውጤት ያስረክባል ተብሏል፡፡ የሆቴሉ መነሻ የንብረት ግምት ዋጋና ሌሎች ተያያዥ ግኝቶች በጥናቱ ይፋ ይሆናሉ፡፡ በዚህም መሠረት ሒልተን ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ይዞታነት በጨረታ ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

      ሒልተን ሆቴል መንግሥት በዘንድሮ በጀት ዓመት ወደ ግል ይተላለፋሉ ብሎ ይፋ ካደረጋቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡

      በዚህ ዕቅድ መሠረት ሚኒስቴሩ የአሰላ ብቅል ፋብሪካን በ1.34 ቢሊዮን ብር፣ በብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት ላይ የነበረውን 30 በመቶ የመንግሥት ድርሻ በ434 ሚሊዮን ዶላር ባለፉት ወራት ውስጥ ወደ ግል ይዞታ ማዘዋወሩ ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም እንደ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ያሉ ተቋማትም ወደ ግል ይዞታ ለመዛወር ይፋ ጨረታ ወጥቶላቸው በሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡

      በባለፉት ስድስት ወራት ብቻ መንግሥት ወደ ግል ከተዘዋወሩ ተቋማት ሽያጭ ወደ 12.7 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ይታወሳል፡፡ ከሒልተን ሆቴል ሽያጭ ጋር በተያያዘ ብዛት ያላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ሊሳተፉ እንደሚችሉ ግምታቸውን የገለጹት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች፣ ሆቴሉ ካለው ስፋትና ከሚገኝበት ቦታ አንፃር ፉክክሩ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

      በእነዚህ ምክንያቶችና በሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮች የሆቴሉ የሀብት ዋጋ ከፍ ይላሉ ሲሉ አስተያየት የሰጡት የፌርፋክስ ግሎባል ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ እሳቸው የሚመሩት ተቋም ከተለያዩ አገር ባለሀብቶች ጋር በመሆን ግዥው ላይ እንደሚሳተፍ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

      የዋጋ ትመና ጥናቱን ከተጠናቀቀ በኋላ ጨረታው በቀጣይ ወራት ውስጥ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች