Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በክብር ተሸኙ

  የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በክብር ተሸኙ

  ቀን:

  የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ባለቤታቸው ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ በሥልጣን ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ በይፋ የክብር አሸኛኘት ተደረገላቸው፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም አገሪቱ ከፍተኛ ደረጃ ያለው የክብር ሜዳሊያና ዲፕሎማ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተበረከተላቸው፡፡

  ማክሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተደረገው የአሸኛኘት ሥነ ሥርዓት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ዲፕሎማቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

  ለአቶ ኃይለ ማርያም ከመስከረም 1 ቀን 2005 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ላበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዲፕሎማ፣ እንዲሁም በመንግሥት መሪነት ላበረከቱት መልካም አገልግሎት የክብር የወርቅ ሜዳልያ ተበርክቶላቸዋል፡፡

  ለቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬም የዕውቅና ምስክር ወረቀትና የወርቅ ሀብል ተበርክቶላቸዋል፡፡

  በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ለአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የሁሉም ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡

  ‹‹የነበርኩበት ኃላፊነት በጣም ከባድ ነበር፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለሚጠብቃቸው ፈተና ትዕግሥትና የሁላችንም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

  ‹‹እኔ ከልምዴ ተነስቼ ከመተቸት በፊት ድጋፍ እንድታደርጉላቸው አደራ እላለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት የለውጥ ንፋስ እየነፈሰ ነው፡፡ ለውጡ የሁላችንንም ፍላጎት ያማከለ እንዲሆን ልንረባረብ ይገባል፡፡ ነገር ግን ይህን ጥሩ የለውጥ ንፋስ አቅጣጫ የሚያስቀይር ከሆነ ወደ አስከፊና የማንወጣበት ነገር ሊያስገባን ይችላል፤›› ሲሉ አቶ ኃይለ ማርያም አሳስበዋል፡፡

  ሕዝቡም አስተዋጽኦ እንዲያደርግና በትዕግሥትና በድጋፍ እንዲቆይ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በኃላፊነት ወቅት አብረዋቸው ለነበሩ የሥራ አጋሮቻቸው ማለትም የካቢኔ አባላት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የመከላከያ ሠራዊትና የሌሎች ፀጥታ አካላትን ያመሠገኑት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ከሁሉ በላይ ግን ቤተሰቦቻቸውን በአፅንኦት አመሥግነዋል፡፡

  ‹‹ከዚህ በፊት እንደ ድርጅት ነፃና ግልጽ ሆነን ስለቤተሰቦቻችን፣ ስለውስጥ ስሜቶቻችን የመግለጽ ባህል የለንም፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የዚህን ልምድ መጋረጃ ቀደው ጥለዋል፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹እኔም አሁን አልገመገም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ውድ ባለቤቴንና እህቴን ሮማን ተስፋዬን በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት እንዳመሠግናት ፍቀዱልኝ፤›› ብለዋል፡፡

  ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ ልጆቼ በታክሲ ዩኒቨርሲቲ ይሄዱ ነበር፤›› ሲሉ ያስታወሱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ሦስት ልጆቻቸውንም አመሥግነዋል፡፡

  በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም አቶ ኃይለ ማርያምን፣ ‹‹እጅግ ንፁህ የሆኑና ሌብነትን የሚፀየፉ ናቸው፤›› ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል፡፡ ‹‹አቶ ኃይለ ማርያም ብዙ ነገሮችን አስተምረውናል፡፡ ሥልጣንና ወንበር የሕዝብ ማገልገያ እንጂ፣ የግል መገልገያ መሆን እንደሌለበት ያስተማሩም ናቸው፤›› በማለት አመሥግነው፣ ባለቤታቸውን ወ/ሮ ሮማንም ምሥጋና አቅርበውላቸዋል፡፡ 

  ለሰዓታት በቆየው ሥነ ሥርዓት ላይ አዲስ የተሾሙትን የካቢኔ አባላትን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም ከክልል ባለሥልጣናት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድን ጨምሮ፣ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ተገኝተዋል፡፡   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...