Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትበለንደን ማራቶን ቀነኒሳ ቅሬታ አድሮበታል

በለንደን ማራቶን ቀነኒሳ ቅሬታ አድሮበታል

ቀን:

  • አዘጋጁንና አሸናፊውን ወቅሷል

በለንደን ማራቶን ሲጠበቁ የነበሩ ታዋቂ አትሌቶች ተሸንፈዋል፡፡ የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮናው ቀነኒሳ በቀለና እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ በቅድመ ግምቱ ብዙ ሲባልላቸው ቢቆዩም፣ በውድድሩ ወቅት ለኬንያው ተወዳዳሪ እጅ ሰጥተዋል፡፡ በሴቶች ምድብም በትልቁ ሲጠበቁ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ ማሬ ዲባባና ጥሩነሽ ዲባባ በውድድሩ አልተሳካላቸውም፡፡

ኃያላኑ በተረቱበት በለንደኑ ማራቶን ውድድር ቀነኒሳ በቀለ ቅሬታ እንዳደረበት ገልጿል፡፡ አትሌቶቹ ከመነሻው ጀምሮ ዙሩን ሆን ብለው ማክረራቸው የውድድሩን ጣዕምና አጓጊነት ጭምር እንደ ገደለው፣ ለዚህም አዘጋጁንና የማራቶን ውድድሩን አሸናፊ ኬንያዊውን ኤሊዩድ ኪፕቾጌን ወቅሷል፡፡ ሆን ብለው የውድድሩን ሒደት በማዛባት እሱን ጨምሮ በሌሎች ተወዳዳሪዎች ላይ ጫና ፈጥረዋል ሲል ቀነኒሳ ቅሬታውን አሰምቷል፡፡

አትሌቱ ይህን ቢልም ቅሬታው ግን ብዙም ሚዛን እንደማይደፋ በዘርፉ ትልቅ ስም ያላቸው የአገር ውስጥ አሠልጣኞች ያስረዳሉ፡፡ እንደ አሠልጣኞቹ ከሆነ፣ የተወዳዳሪዎችን ፅናት በሚጠይቀው የማራቶን ውድድር ላይ ውጤት የሚወሰነው በተወዳዳሪው አቅምና ብቃት እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

- Advertisement -

‹‹ቀነኒሳ ወደ ጎዳና ሩጫ ከማቅናቱ በፊት፣ በረዥም ርቀት አምስትና አሥር ሺሕ ሜትሮች በኦሊምፒክም ሆነ በዓለም ዋንጫ ይህ ቀረው የማይባል ብቃቱን በማሳየት በርካታ ድሎችን ያስመዘገበ አትሌት ነው፡፡ በዚህም በዓለም የወርቅ መዝገብ ስማቸውን ካሰፈሩ ታላላቅ አትሌቶች አንዱ ነው፤›› የሚሉት አሠልጣኞቹ፣ የለንደን ማራቶን በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) በወርቅ ደረጃ ከሚመድባቸው የጎዳና ላይ ውድድሮች አንዱ እንደ መሆኑ መጠን፣ የውድድሩንና የተወዳዳሪዎችን አቅምና ብቃት በአግባቡ ማጥናትና መገመት ይጠበቅበት እንደነበር ይናገራሉ፡፡

ቀነኒሳ ከውድድሩ በኋላ ለቢቢሲ የአማርኛ አገልግሎት በሰጠው አስተያየት፣ ‹‹የለንደን ማራቶን አዘጋጆችና ኬንያዊው የርቀቱ አሸናፊ ኪፕቾጌ ውድድሩ የሚጠበቀውን ያህል አስደሳች እንዳይሆን አድርገውታል፡፡ ይህን ያደረጉበት ምክንያት ደግሞ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰንን በማለም ነው፡፡ በዚህ ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ ምክንያቱም አዘጋጁ ለሁሉም ሯጮች ፍጥነት ማዘጋጀት ነበረበት፤›› ብሏል፡፡

እሑድ ሚያዝያ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በተከናወነው የለንደን ማራቶን፣ ኬንያውያኑ በሁለቱም ፆታ አሸናፊነቱን ተቀዳጅተዋል፡፡ ቀነኒሳና ሞ ፋራህ በተሳተፉበት የወንዶች ምድብ ወቀሳ የቀረበበት ኤሊዩድ ኪፕቾጌ አንደኛ በመውጣት ሲያሸንፍ፣ አትሌቱ ርቀቱን ለማጠናቀቅ፣ 2 ሰዓት 04 ደቂቃ 15 ሰከንድ ፈጅቶበታል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሹራ ኪጣታ 2 ሰዓት 04 ደቂቃ ከ48 ሰኮንድ በመሮጥ ሞ ፋራህን በሁለት ደቂቃ ገደማ ቀደሞ ሁለተኛ ሆኗል፡፡ ሞ ፋራህ 2 ሰዓት 06 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ በመግባት ሦስተኛ ሆኗል፡፡ ቀነኒሳ በቀለ ሰባተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል፡፡

በሴቶች መካከል በተደረገው የማራቶን ውድድር፣ ኬንያውያኑ ቪቪያን ቼሪዮትና ብሪጂድ ካስጌይ፣ ርቀቱን 2 ሰዓት 18 ደቂቃ 30 ሰከንድ እና 2 ሰዓት 20 ደቂቃ 13 ሰከንድ በማጠናቀቅ አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ሲገቡ፣ ኢትዮጵያዊቷ ታደለች በቀለ 2 ሰዓት 21 ደቂቃ 40 ሰከንድ በማጠናቀቅ ሦስተኛ ወጥታለች፡፡ በውድድሩ ሰፊ ግምት ከተሰጣቸው ኢትዮጵያውያኑ መካከል ማሬ ዲባባ ርቀቱን ሰባተኛ በመሆን ስታጠናቅቅ፣ ጥሩነሽ ዲባባ ውድድሩን ማቋረጧ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...