Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ67ኛው የኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ

67ኛው የኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ

ቀን:

በኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ማኅበር ፓርክ ከስድስት አሥርተ ዓመታት በፊት በኮሪያ ልሳነ ምድር ለተሰዉ ጀግኖች በቆመው መታሰቢያ ሐውልት ዙሪያ፣ የኢትዮጵያን ጨምሮ የ11 አገሮች ሰንደቅ ዓላማዎች ሲውለበለቡ ነበር ያረፈዱት፡፡ በሐውልቱ ፊት ለፊት በኢትዮጵያ የሚገኙና በኮሪያ ዘመቻ የተሳተፉት የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮችና ሚሊታሪ አታሺዎች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና የመከላከያ ሚኒስቴር ተወካይ ተገኝተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው በዚህ የመታሰቢያ በዓል ላይ በግዳጅ አፈጻጸማቸው ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው የተሸለሟቸውን ልዩ ልዩ የኒሻን ሜዳሊያዎችን በደረቶቻቸው ላይ ያንጠለጠሉ የኮሪያ ዘማች አረጋውያንም የክብር እንግዶች ሆነው ተገኝተዋል፡፡

የፖሊስ ሠራዊት የማርሽ ባንድ ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማሰማት ለድባቡ ድምቀትን ሲሰጥ፣ በአገር ባህል ልብስ ያሸበረቁ ወይዛዝርት ለዝግጅቱ ታደሚዎች የአበባ ስጦታ በማበርከት፣ በመስተንግዶ ሥራ ተጠምደው ደፋ ቀና ሲሉ ነበር፡፡ ታዳጊዎችም በሙዚቃ የታጀበ የኢትዮጵያና የደቡብ የኮሪያ ሕዝብ መዝሙር አሰምተዋል፡፡ ፕሮግራሙ የተዘጋጀው 67 ዓመታት ያስቆጠረውን የኮሪያ ዘመቻን ለማስታወስ ሲሆን፣ የተለያዩ ጉዳዮችን አንስቷል፡፡

የክብር ዘበኛ ቃኘው ሻለቃ ጦር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዕዝ ሥር ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ኮሪያ ሲንቀሳቀስ በወቅቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ከነበሩት ከግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እጅ የጦር መመሪያ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማና የጦሩን ዓርማ በአደራ ተቀብሏል፡፡ የክብር ዘበኛው ጦር ዓለም አቀፍ ግዳጁን በድል አጠናቆ ሲመለስ ለንጉሠ ነገሥቱ መልሶ ያስረከበበትን ዕለት በመሆኑ ተዘክሯል፡፡

በተጨማሪም በወቅቱ ተልዕኮአቸውን ሲፈጽሙና በጀግንነት ሲዋጉ የወደቁ 122 ጀግኖችን ለማሰብና አጽማቸውም ወደ እናት አገሩ ተመልሶ በክብር ያረፈበትን ዕለት በትዝታ ለመዘከር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የቃኘው ሻለቃ ጦር በተሠማራበት የውጊያ ወረዳ ሁሉ ድል ባስመዘገበ ቁጥር የተረከበውን ሰንደቅ ዓላማና የጦሩን ዓርማ በክብር ከፍ አድርጎ በማውለብለብ የአገሩን ስም ማስተዋወቁን ለማስታወስ ነው፡፡

ኢትዮጵያ አስቀድማ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል፣ በኋላም የተመድ መሥራች አባል እንደመሆኗ መጠን ከዓለም አቀፉ ድርጅት በደረሳት ጥሪ መሠረት ከሌሎቹ ኃያላን መንግሥታት ጎን ተሠልፋ የኮሪያን ሪፐብሊክ ከወራሪ ኃይል በመከላከል ለጥሪው ምላሽ ሰጥታለች፡፡ ለዓለም ሰላም አሥጊ በነበረው በዚሁ የኮሪያ ጦርነት ውስጥ ተዋጊ እግረኛ ጦሯን አሠልፋ ያስመዘገበችው አኩሪ ድል፣ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ተልዕኮ ብቁ ሆና እንድትገኝ አድርጓታል፡፡ ለዓለም ሰላም መከበር ያላትንም እምነት አስመስክራለች፡፡

አሁንም ቢሆን በአፍሪካ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ማዕከል ስትሆን፣ በየዓመቱም ከሚያዝያ 6 ቀን ጀምሮ በኮሪያ ዘማቾች ብቻ የሚከበረው መታሰቢያ በአገር አቀፍ ደረጃም ጭምር እንዲከበር ለማድረግ ተወጥኗል፡፡ በዚህም ተተኪው ትውልድ የዓለም ሰላም ተልዕኮን አጀማመርና የአባቶቹን የጀግንነት ገድል የሚማርበትና አጋጣሚ እንደሚፈጥርለት ተገልጿል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ማኅበሩ ጠብቆ ያቆያቸውን ቅርሶች ሁሉ ለሚመለከተው አካል ለማስረከብ ዝግጁ እንደሆነ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መለስ ተሰማ ተናግረዋል፡፡

በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ዘመን ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣሊያን ጦር መወረሯ ብቻ ሳይሆን፣ ወረራውን ለመከላከል ባካሄደችው እንቅስቃሴ ወራሪው ጠላት ሕጋዊ ባልሆነና በተከለከለ የጋዝ መርዝ ጥቃት መፈጸሙ የትናንት ትዝታ ነው፡፡ ይህንንም ሕገወጥ ተግባር ለተመድ ብታሰማም፣ በቸልታ መታለፏ የሚታወስ ነው፡፡ በጀግኖች አርበኞች ወራሪውን ጦር ድል አድርጋ ነፃነቷን ከተጎናፀፈች ከጥቂት ዓመታት በኋላም፣ ከተመድ የቀረበላትን የጦር ዕርዳታ ጥያቄ ሳታወላውል በመቀበል አጋርነቷን አሳይታለች፡፡

ይህ አኩሪ ዘመቻ ደግሞ በኢትዮጵያና በኮሪያ ሪፐብሊክ መካከል የወዳጅነት መሠረት የተጣለበት ዕለት እንደሆነ፣ በኮሪያ ዘመቻ ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች ምትክ የማይገኝለትን ሕይወታቸውን በመስጠት ከኮሪያ ሕዝብ ጎን እንደተሠለፉ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከድህነት አረንቋ ለመውጣት ደፋ ቀና በምትልበት በአሁኑ ወቅት የኮሪያ ሪፐብሊክ ከጎኗ በመቆም የልማት አጋርነቷን በማሳየት ላይ ትገኛለች፡፡

በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚስተር ሊም ሆን ሚን፣ ‹‹ለኢትዮጵያ የምንከፍለው ብዙ ዕዳ አለብን፣ በተለይ በታላቁ ችግራችን ጊዜ የደረሱልን የኢትዮጵያ ዘማቾች፣ ለሁለቱ አገሮች ወዳጅነት መመሥረት ምትክ የማይገኝለት አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ስለሆነም ውለታችሁን የመክፈል እንቅስቃሴያችንን እንቀጥላለን፤›› ብለዋል፡፡

የኮሪያ ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስቴር የጤና መድኅን ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ሊዋንቺን ኮን፣ ‹‹በኮሪያ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ የተመድን ጥሪ በመቀበል ወታደሮቿን ያዘመተች ከአፍሪካ የመጀመሪያዋና ከደቡብ ኮሪያ ሕዝብ መንግሥት በደም የተሳሰረች ብቸኛዋ አገር ነች፤›› ብለዋል፡፡

በጦርነቱ ወቅት ስማቸው ‹‹አሸንፍ፣ አስተካክል›› የሚል ትርጉም ያለው የቃኘው ሻለቃ ጦር ዘማቾች ከ200 በላይ በሚሆኑ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆኑ ጦርነቶች ተካፍለዋል፡፡

ኮሪያ በኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች መስዋዕትነት ከዓለማችን በኢኮኖሚ ኃያል ከሆኑ አሥር አገሮች ውስጥ አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥትና ዘማቾች የተደረገላትን ውለታ በትንሹም ቢሆን ለመመለስ ጥረት ታደርጋለች፡፡ ዘማቾች የበጎ አድራጎት ማዕከል ለመገንባት የመሠረተ ድንጋይ መጣሉ በዕለቱ ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ካሳ ወልደ ሰንበት ከዛሬ 67 ዓመት በፊት በተካሄደው የኮሪያ ጦርነት ኢትዮጵያ 6,037 የቃኘው ሻለቃ ጦር አባላትን እንዳሠለፈች፣ በውጊያውም 122ቱ ሲሰዉ፣ 536 ወታደሮች ደግሞ እንደቆሰሉ ተናግረዋል፡፡ ከዘማቾቹ መካከል ግን አንድም የተማረከ ወታደር እንዳልነበርና ይህንንም አኩሪ ገድል የወቅቱ የዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማት የመነጋገሪያ አጀንዳ አድርገውት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በደም የተሳሰረው የደቡብ ኮሪያና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ ለተያያዘችው የህዳሴ ጉዞ ስኬት ደቡብ ኮሪያ አጋርነቷን በተግባር በማረጋገጥ የበኩሏን ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች፡፡ አዲስ አበባ ከደቡብ ኮሪያዋ ቹንቺን ከተማ ጋር የመሠረተችው የእህታማማቾች ግንኙነትም ተስፋ ሰጪ የትብብር ሒደት እየታየበት መሆኑን አቶ ካሳ አውስተዋል፡፡        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...