ጉዞ ለመጀመር ታክሲ ተራ ደርሰናል፡፡ በፌስቡክ ላይ ያነበብኩት ግን አስፈግጎኛል፡፡ ሰውየው ‹‹አሞኛል›› ብሎ ለወዳጁ ቢያጫውተው፣ ወዳጅ ተብየውም፣ ‹‹ዋናው ሆስፒታል አለመሄድህ ነው፤›› በማለት በሆስፒታሎችና በጤና ተቋማት ላይ የተሳለቀው ሳያንሰው፣ ‹‹ሆስፒታል ካልሄድክ ምንም አትሆንም፤›› በማለት ይቀልዳል፡፡ አንድ ሰው ከተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ ስልክ እያወራ ነው፡፡ በምሬት፣ ‹‹አሁኑኑ ውጪ! በቃ ምንም ድምፅ ሳታሰሚ ውጪ ብዬሻለሁ፤›› እያለ ይቆጣል፡፡ ሁላችንም የጠረጠርነው ነገር ቢኖር ምናልባት ውድ ባለቤቱ አንድ አደጋ የተከሰተበት ቦታ እንደተገኘች ነው፡፡
ምናልባትም ይህች የተባለችው ሴት የጊዮርጊስ ወይም የቡና ደጋፊ ሆና ስቴዲየም ገብታበትም ይሆናል ብለን ጠርጥረናል፡፡ ታዲያ የሚጠይቅ ሰው አይንሳችሁ፡፡ የሰውየው ጭንቀት ጭንቅ ያላት ቢጤ፡፡ ሰውየውን ብትጠይቀውስ? መቼስ ምን ይባላል? አፋችን ቁርጥ ይበልልሽ ከማለት ውጪ ምን እንላለን፡፡ የክብሩ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ንግግር የሰማ ሁሉ ‘አፌ ቁርጥ ይበልልዎት’ ያላቸው የእኔም ጩኸት ይኸው ነበር፣ የእኔም ጥያቄ ይኼው ነበር በማለትም አይደል እንዴ፡፡ እኛም ዘንድ የተፈጠረው ነገር ይኼው ነው፡፡
ልጅት እጅግ ተጨንቃ፣ ‹‹ምን ውስጥ ገብታብህ ነው? ወይስ የእሳት አደጋ የተነሳበት ቦታ ነው ያለችው?›› በማለት ጥያቄያችንን ጠየቀችልን፡፡ ምናልባት የሁላችንንም ጥያቄ ይወክላል ለማለት እደፍራለሁ፡፡ መቼም እኔ ይህንን ጥያቄ ጠይቅ ብባል ኖሮ፣ ‹‹አይዞህ ተረጋጋ፣ ዳሩ ግን ምን ጉድጓድ ውስጥ ገብታብህ ነው?›› ብዬ የምጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ከመገናኛ ስቴዲየም እየሄድንም ስለነበር ነው መሰለኝ አብዛኞቻችን ስቴዲዮም ገብታ ነበር የመሰለን፡፡
‹‹ይኼ ሁሉ ወጣት ለኳስ ያለውን ፍቅር ለአገር በጎ ግንባታ ቢያውለው ኖሮ፣ ይኼኔ አገራችን ኢትዮጵያ በእግር ኳስ እነ ህንድ የደረሱበት ታላቅ ቦታ ላይ በደረሰችልን ነበር፤›› በማለት አንዱ አስተያየት ሲሰጥ ወያላው ክትክት ብሎ ሳቀበት፡፡ ወያላው፣ ‹‹እንዲያው ፖለቲካ ሲባል ግን በጣም አሳዛኝ ጨዋታ ነው፤›› በማለት ጨዋታውን ጀመረ፡፡ ይኼኔ ሙሉ መረጃውን ለመስማት አሰፈሰፍን፡፡ ደግነቱ ሁሉም ወሬ ውስጥ ጥልቅ እያለች የምትጠይቅ ምርጥ ተሳፋሪ ይዘናል፡፡ ታዲያ የመጀመሪያው ጥያቄ በአግባቡ ሳይመለስ ድጋሚ ወያላውን ጠየቀችው፡፡ ‹‹ለምንድነው ፖለቲካ አሳዛኝ የሆነው?›› በማለት ጥያቄዋን ወደ ወያላው ሰነዘረች፡፡
ያው እንዳልኳችሁ እኔ ብሆን ኖሮ ይህን ጥያቄ የጠየቅኩት፣ ‹‹እስቲ በእናትሽ አንዱን አሳዛኝ የፖለቲካ ጨዋታ አጫውቺን?›› ነበር የምለው፡፡ ብቻ ልጅት ጥያቄያችንን ጠይቃልናለች፡፡ ወያላው የወጣቷን ጥያቄ ለመመለስ ተሽቀዳደመ፣ ‹‹እስቲ እንዲያው አሁን እግዜር ያሳይሽና እግር ኳስንና አገርን ምን አገናኛቸው? አንዳንድ ካድሬዎች ታክሲ ድረስ እየመጡ ኳስ ስለወደዳችሁ ብቻ አገራችሁን አትወዱም፣ ኳስ ስሜታዊ ስላደረገን ብቻ አገር የከዳን ያህል ለጠላት መመከቻ ተብለው በሕዝብ ሀብት በሠለጠኑ ቴኳንዶዎች መቀጥቀጥ አለብን እንዴ?›› በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መለሰላት፡፡ ወያላው በሰውየው አስተያየት አልተደሰተም ነበር፡፡
በወያላው አስተያየት ብዙ ያልተስማማው አንድ ወጣት ወሬውን ተቀላቀለ፡፡ ‹‹መቼ ነው ኳሱን ሜዳ ውስጥ ጨርሰን የምንወጣው?›› በማለት ጥያቄ አቀረበ፡፡ ማንም መልስ የሰጠው አልነበረም፡፡ መልስ በማጣቱም በእግር ኳሱም የበገነ ይመስላል፡፡ ‹‹በጣም አዝናለሁ፡፡ እዚህ ግባ ለማይባል እንኳንስ የውጭ ተከታታይ ሊያፈራ ይቅርና እዚህ አገር ውስጥ እንኳን በቂ ተከታይ የሌለው እግር ኳስ፣ ለምን በፀብ እንደሚታጭ አይገባኝም?›› በማለት ለማልቀስ ሩብ ጉዳይ ዓይነት አስተያየት ሰጠ፡፡ ዝም ብሎ መሪውን ሲዘውር የነበረው ሾፌር አሁን ገና ለመጀመርያ ጊዜ ወሬያችንን ተቀላቀለ፡፡ ‹‹ፍርጃ እኮ ነው! ይህ እርግማን ነው፡፡ ለምንድነው የተሸነፈው መሸነፉን በፀጋ የማይቀበለው? ለምንድነው አሸናፊውስ ቢሆን ተሸናፊን ሳያንጓጥጥ ደስታውን ማጣጣም የሚችለው?›› በማለት ብሶቱን ገለጹ፡፡
በሾፌሩ ወሬ የተነካችው ሌላ ወጣት ደግሞ፣ ‹‹አይገርማችሁም እነዚህ አሸነፉ የተባሉት ቡድኖች ተጫዋቾች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቢጠሩ አብረው አገርን ወክለው አንድ ማሊያ ለብሰው የሚጫወቱትን ወንድሞቻቸውን ሳይሆን፣ ዓድዋ ላይ ጣሊያንን ድል የነሱ እኮ ነው የሚመስሉት!›› በማለት ድንቅ ሐሳብ አመጣች፡፡ እውነትም! እውነትም!›› የሚል የተወሰነ ጉምጉምታ ታክሲ ውስጥ ተሰማ፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ዑራኤል ደርሰናል ስንል የእስጢፋኖስ መንገድ ተዘጋጋቶ ዑራኤል ደርሷል፡፡ ያው ኳስ ለመመልከት በተሰባሰቡት ፖሊሶች መሀል በተፈጠረውም ውጥረት ጭምር ነው፡፡
በዚህ መሀል መጀመሪያ ስልክ ሲያወራ የነበረው ሰውዬ ስልክ ድንገት ጮኸ፡፡ ሁላችንም እንደተነጋገረ ሰው ፀጥ ብለን ማዳመጥ ጀምረናል፡፡ ምናልባት ቅድም ውጪ ካላት ቦታ ወጥታ ይሆን፡፡ ወይስ ሳትወጣ አደጋ ደርሶባት ይሆን? የሁላችንም ጥያቄ ይመስል ነበር፡፡ በዚህ መሀል ሰውዬው ስልኩን አንስቶ ‹‹ሄሎ!›› ሲል፣ ሁላችንም ዘንድ በግልጽ ይሰማ ነበር፡፡ መረጃው እንደሚያመልጠን በተመስጦ እያደመጥነው ነበር፡፡ መቼም ለወሬ ሟች ነኝ ያሉ ሰዎች ተጠራርተው የከተሙባት ታክሲ ነበር የምትመስለው፡፡
‹‹ወጣሽ?›› የሚል ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ በግምት ከመልሱ እንደተረዳነው ‹አዎን ወጥቻለሁ› ያለች ይመስላል፡፡ ‹‹ተመስገን! እንኳን በሰላም ወጣሽልኝ . . . ›› በማለት እግዜሩን ካመሠገነ በኋላ፣ ‹‹እባክሽን አትዋሽኝ፣ ምንም የወጉሽ ነገር የለም አይደል?›› በማለት ድጋሚ ጥያቄውን አቀረበላት፡፡ ይኼኔ ታክሲዋ በሳቅ ተሞላች፡፡ ለደቂቃዎች ተነስታ የነበረችው ጥያቄ አሁን መልስ ያገኘች ይመስላል፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ለካስ ነፍሰ ጡሯ ባልተቤቱ ሳታማክረው ለምርመራ ብላ ሆስፒታል ሄዳ ነው መሀል የጦርነት ቀጣና ውስጥ የገባች ያህል እንድትወጣ ሲያስጨንቃት የነበረው፡፡
‹‹ሰዎችን ለማዳንና ለማከም የተመሠረቱት የጤና ተቋማት ነፍስ የሚጠፋባቸው ቦታዎች ሲሆኑ፣ ሰው ወደ ሆስፒታል መሄድ ቢፈራ ምን ይገርማል?›› ያለን ደግሞ ሌላ በሆስፒታሎችና በጤና ተቋማት የተማረረ የሚመስል ወጣት ነው፡፡ አክሎም ይህ እንደ አዋቂ የሚያደርገው ሰው፣ ‹‹በዓለም ላይ አስከፊ ከተባለው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ ካለቁት ሰዎች በላይ፣ በየሆስፒታሉ በጤና ባለሙያዎች በውርጃ ሰበብ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ይበልጣል፤›› በማለት አስገረመን፡፡
ጥያቄ የምትጠይቅ የነበረችው ወጣት አሁን ደግሞ መልስ ቢጤ ይዛ ሳትመጣ አትቀርም፡፡ እንዲህም በማለት ሐሳቧን አስቀመጠች፡፡ ‹‹መቼም እነዚህ የጤና ባለሙያዎች የስንቱን ሕይወት በየቀኑ ከሞት ሲታደጉ፣ የስንቱን እስትንፋስ ቀጥለው ሕይወትን ሲዘሩ ማንም ዘምሮላቸው አያውቅም፡፡ ዳሩ ግን አንድ ሰው አንድን ስህተት ሠራ ተብሎ ሁሉም በአንድ ተደፍጥጠው ይረገማሉ፤›› እያለች ሐሳቧን አብራራች፡፡ ከኋላ ያሉ ሁለት ሰዎች ‹ነርስ ናት አይደለችም› የሚል ክርክር ውስጥ ገቡ፡፡
ወያላው በልጅቷ ሐሳብ የተስማማ አይመስልም፡፡ ‹‹የጤና ባለሙያዎች ሰው ቢያድኑ ምን ይገርማል? ሥራቸውም አይደል አንዴ? ቃለ መሃላ ፈጽመው ወደዚህ ኃላፊነት ውስጥ የገቡት ሰውን ለማዳንም አይደል እንዴ?›› ወያላው ወሬውን ገና አልጨረሰም፡፡ ‹‹የሮናልዶ ጎል ማግባት ምን ይገርማል? የሚገርመው ጎል ሥር ኳስ ተሰጥቶት ቢስት ነበር ኳስ አፍቃሪው ሁሉ አይ ሮናልዶ አርጅቷል እኮ እያለ የሚሳለቅበት . . . ›› እያለ የወጣቷን ሐሳብ ሞገተ፡፡
‹‹በእርግጥም ሕክምና ከምንም በላይ ታላቅ ትኩረትን የሚፈልግ የሙያ ዘርፍ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ዳሩ ግን ሆስፒታሎቻችን የመዳኛ ሥፍራዎች ብቻ እንዲሆኑልን የዘወትር ፀሎታችን ነው፡፡ የጤና ተቋሞቻችንን የመፈወሻ ማዕከላት ብቻ እንዲሆኑልን፣ የጤና ባለሙያዎቻችንም ቢሆኑ ሰው አንዴ ካመለጠ አይመለስምና ሰባት ጊዜ እየለኩ አንድ ጊዜ መቁረጥን፣ ማለቴ አንድ ጊዜ መውጋትን እንዲማሩልንና እንዲያስተውሉልን ማሳሰብ አለብን . . . ›› እያለ አንድ ጎልማሳ ሲናገር፣ አንድ ለግላጋ ወጣት፣ ‹‹እንደ አፍህ ያድርግልን . . . ›› እያለ ሲናገር ‹‹መጨረሻ›› ተብለን ተሰነባበትን፡፡ በዚህ መሀል ነበር አንድ ነገር ብልጭ ያለልኝ፡፡ እሱም ክቡር ለሆነው የሰው ሕይወት መጨነቅ፡፡ ሰው መሆን ይቅደም አይደል የሚባለው? መልካም ጉዞ!