Wednesday, October 4, 2023

ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት አዲሱ ስያሜውን ከማግኘቱ በፊት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተብሎ በሚጠራበት ወቅት፣ ለአኅጉራቱ አጠቃላይና ሙሉ ነፃነት መስፈን ከፍተኛውን ድርሻ እንዲጫወትና በአኅጉሪቱ የሚገኙ አገሮችም በጋራ ቅኝ ግዛትንና ጭቆናን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስወግደው በነፃነትና በኅብረት እንዲሠሩ ለማድረግ በማሰብ የተቋቋመ ነበር፡፡

ምንም እንኳን ድርጅቱ ስለአንድነት በመስበክ የአኅጉሪቱን ችግር ለመቅረፍና ነፃ ለማውጣት የተለያዩ ዕቅዶችን በማውጣት ለማስፈጸም ቢውተረተርም፣ የታቀዱት ነፃነቶችና አኅጉራዊ የጋራ ዕድገቶች ግን ሊተገበሩ ያልቻሉ ተስፋና ዕቅዶች እንደነበሩ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት በተሸጋገረበት ወቅት ለኅትመት የበቁ በርካታ የታሪክና የምርምር ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡

ለአኅጉሪቱ የተተለመውን ነፃነት፣ ሰላም፣ አንድነትና መረጋጋት ማምጣት ተስኖት የነበረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዕቅዶቹን ለማስፈጸም ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖበት የነበረው ደግሞ፣ ድርጅቱ የራሱን የገንዘብ ወጪና በጀት በራሱ መሸፈን አለመቻሉ ነው፡፡ ድርጅቱ ለሚያቅዳቸውና በአኅጉሪቱ ለማሳካት ለሚያቅዳቸው ተግባሮች የገንዘብ ምንጩ ከአፍሪካያን ሳይሆን፣ ከሌሎች የአውሮፓና የአሜሪካ አገሮች መሸፈን ነበር፡፡

ይህንን ተገንዝበናል ያሉ የአፍሪካ መሪዎች የድርጅቱን መዋቅር በማሻሻልና የተሻለ የገንዘብ ምንጭም እንዲኖረው ለማስቻል በማቀድ፣ ድርጅቱን ወደ ኅብረትነት አሸጋገሩት፡፡ ምንም እንኳን የአፍሪካ ኅብረትም ተመሥርቶ ከ15 ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም፣ ኅብረቱን በአባል አገሮች የገንዘብ መዋጮ የመደገፍ ጉዳይ አሁንም ከፍተኛው ራስ ምታት ነው፡፡ ኅብረቱም እንደ ቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሁሉ ዕቅዱን ለማሳካት፣ አሁንም በሌሎች ከኅብረቱ ውጪ ባሉ የገንዘብ ምንጮች ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ለዚህም ይመስላል የአፍሪካ ኅብረት በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ፣ የኅብረቱን ገቢ ለመሸፈን የሚያስችሉ አዳዲስ ማሻሻያዎች ተፈጻሚ ለማድረግ በመሥራት ላይ የሚገኘው፡፡ በሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ የሚመራው የአፍሪካ ኅብረትን የማሻሻል ሥራዎች በዋነኛነት የኅብረቱን የገንዘብ ምንጭ በአባል አገሮች እንዲሸፈን፣ አባል አገሮችም ያለምንም የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ ተላቀው ዕቅዶቻቸውን እንዲፈጽሙ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ በአኅጉሪቱ የሚገኙና የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ እንዲሁም በመንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኙ ተቋማት በአኅጉሪቱ ተዋናዮች እንዲከናወን የታቀደውን ኅብረቱን ማሻሻል አጀንዳ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እየተከናወኑ ነው፡፡

ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ ለመስጠት ከተቋቋሙት በመንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ከሚገኙ አደረጃጀቶች መካከል የሚጠቀሰው ጣና ፎረም ሲሆን፣ ፎረሙ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ የአኅጉሪቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ የፖሊሲና የመፍትሔ ሐሳቦችን ለማፍለቅ እንደ አንድ መድረክ እያገለገለ እንደሆነ ይገለጻል፡፡

በዚህም መሠረት የፎረሙ ሰባተኛ ዙር ውይይት ቅዳሜ ሚያዝያ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. እና እሑድ ሚያዝያ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ተከናውኗል፡፡

የዘንድሮው የፎረሙ መሪ ቃልና የውይይት አጀንዳም በአፍሪካ ኅብረት ማሻሻያዎችና በአኅጉሪቱ ሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

የአፍሪካን የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች በባለቤትነት የመያዝ፣ የመቆጣጠርና የማስተዳደር፣ እንዲሁም የኅብረቱን የገንዘብ ምንጭ በባለቤትነት የመያዝ ጉዳይ የዘንድሮው ጣና ፎረም ዋነኛው የመወያያ አጀንዳ ነበር፡፡

ለሁለት ቀናት በባህር ዳር የተካሄደው ውይይትም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አትኩሮቱን አድርጓል፡፡ የተለያዩ ሪፖርቶችን በማድመጥም ውይይት ተካሂዷል፡፡ በዚህ ውይይት ላይ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጎንደርና ከባህር ዳር ነዋሪዎች ጋር ያደረጉትን ውይይት አጠናቀው በመገኘት የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ አዳራሹ ሲገቡ ሞቅ ያለ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፣ እርሳቸውም በንግግራቸው አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት አኅጉሪቱ ያሉባትን ችግሮች ለመቅረፍ በምታደርገው ጥረት የኅብረቱን የገቢ ምንጭ ከአፍሪካውያን ማድረግ ዋነኛውና ቁልፍ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡

እንደ ጣና ፎረም ያሉ ተነሳሽነቶች ደግሞ አኅጉሪቱ የራሷን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለማስከበር የሚረዱ ሐሳቦች የሚነሱበት የሐሳብ አደባባይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

‹‹ጥልቅና ሰፋፊ ሐሳቦች የአዕምሮ ነፃነት ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የጣና ፎረም አንዱና ትልቁ ማሳያ ነው፡፡ የአኅጉሪቱ ተቋማትም ከመረዳት ባህል ወጥተው ራሳቸው የመዋዕለ ንዋይ ምንጭ ሊሆኑ ይገባል፤›› በማለት፣ እንደ ጣና ፎረም ያሉ ሌሎች በአኅጉሪቱ ሰላም፣ ደኅንነትና ሁለንተናዊ ብልፅግና ላይ ያተኮሩ መነሳሳቶች ለአኅጉሪቱ አጠቃላይ የለውጥና ዕድገት ትልሞች አቅጣጫዎችን ለማመላከት ሚናቸውን እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከሰባት ዓመታት በፊት የተመሠረተው የጣና የሰላምና የደኅንነት ፎረም ምንም እንኳን ከተመሠረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም፣ በአኅጉሪቱ የሰላምና የደኅንነት ፈተናዎችን ለመቋቋምና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለፖሊሲ አውጪዎችና ለመሪዎች አማራጭ ሐሳቦችን በማቅረብ ሚናውን እየተጫወተ እንደሆነ በመግለጽ፣ እንዲህ ያሉ አኅጉር በቀል እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

ጣና ፎረም እንዲህ ያሉ ታላላቅ ሐሳቦችንና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመጠቆም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ቢሆንም ግን፣ አንዲህ ያሉ መነሳሳቶችን አጠናክሮ ለመቀጠል የአኅጉሪቱ መሪዎች ውጤታማና የተጠና አመራር መስጠት እንዳለባቸው፣ የገቢው ምንጭም ከአኅጉሪቱ መሆን እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በአኅጉሪቱ ለሚካሄዱ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችና የአፍሪካ ኅብረት ለሚያቅደው አዲስ አሠራር በአኅጉሪቱ የሚገኙ ሀብቶችን ማሰባሰብና ማደራጀት ካልተቻለ አኅጉሪቱን ለማሻሻል፣ እንዲሁም ሰላምና ደኅንነትን ለማስፈን የሚገቡ ቃላት ህልም ሆነው እንደሚቀሩ በመግለጽ፣ የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካውያን የገንዘብ ምንጭነት መፍታትና መታገል ለነገ የሚባል እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኅብረቱን የማጠናከርና የማሻሻል ሥራዎች እንዲሁ በአኅጉሪቱ የሚገኙ ተቋማትን ከማጠናከርና ከማሻሻል በአንድ ላይ መሆን እንዳለበት፣ እያንዳንዱ የኅብረቱ አባል አገር ኅብረቱንና በየአገሪቱ የሚገኙ ተቋማትን ለማጠናከርና ለማሻሻል ተግቶ እንዲሠራ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም በአኅጉር ደረጃ እየተካሄዱ ያሉ የማሻሻያ ሥራዎች በአባል አገሮች አመራር ደረጃም መተግበር እንደሚገባቸው፣ አመራሮችም ኃላፊነት በሚሰማውና ግልጽና ተጠያቂነትን ባሰፈነ መንገድ ለተግባራዊነቱ መረባረብ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ጊዜ የማይሰጠው ዓብይ አጀንዳ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የዚህ ሁሉ ማጠንጠኛ ደግሞ ራስን በገንዘብ አቅም መቻል እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ የአኅጉሪቱን የሰላምና የደኅንነት መዋቅር ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ማድረግ፣ ባለቤትነትና የገንዘቡ ምንጭ መሆን በሁሉም አባል አገሮች ዘንድ አሳሳቢና ቅድሚያ የሚሰጠው መሆን እንደሚኖርበትም አውስተዋል፡፡

በዘንድሮ የጣና ፎረም ውይይት ላይ የተለያዩ ዝግጅቶችና የተከናወኑ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የአርብቶ አደሮችን የሕይወት የኑሮ ሁኔታና በግሎባላይዜሽን፣ እንዲሁም አገሮች በማከተሏቸው የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የተነሳ እየደረሰባቸው ያለውን ጫና የሚያትት የመጽሐፍ ምረቃም የዝግጅቱ አካል ነበር፡፡

መጽሐፉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አማካይነት ለኅትመት የበቃ ሲሆን፣ የኢትዮጵያና የናይጄሪያ ምሁራን ጥናቱን ለማከናወንና ለመጽሐፉ ዕውን መሆን ሚናቸውን ተጫውተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በመለስ ዜናዊ ፐብሊክ ሌክቸር ሲሪስ ላይ ደግሞ፣ የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ጋማል አብዱል ናስር የፓን አፍሪካኒስትነትና የአመራር ጥበብና ብቃት ላይ ያተኮረ ውይይትም ተካሂዷል፡፡

ለውይይቱ የመነሻ ሐሳብ ያቀረቡት የመጀመርያው የጋና ፕሬዚዳንትና ግንባር ቀደሙ ፓን አፍሪካኒስት ኳሜህ ንኩርማህ ልጅ ሳሚያ ንኩርማህ ናቸው፡፡

ሳሚያ ንኩርማህ ባቀረቡት ሐሳብ ላይ አፅንኦት ሰጥተው እንዳስረዱት፣ የፓን አፍሪካን እንቅስቃሴና የዓረብ አንድነት በአዲስ መልክ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ለዚህም እንደ ምሳሌ የኳሜህ ንኩርማህና የጋማል አብድል ናስር ለፓን አፍሪካኒዝም መጠናከር አብረው መሥራታቸውን በመጥቀስ፣ አሁንም እንዲህ ያሉ ትስስሮች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸውና አፍሪካና የዓረብ አፍሪካ አገሮች ትስስር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በባህር ዳር ከተማ የተካሄደው የጣና ፎረም ላይ የተለያዩ በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ላይ የሚሠሩ ተቋማት ተወካዮችና ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህማትን ጨምሮ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች ተገኝተው በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት መዋቅሮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

የጣና ፎረም ቦርድን ላለፉት ሰባት ዓመታት የመሩት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ለአዲሱ አመራር ለቀድሞው የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ዳራማኒ ማህማ ኃላፊነታቸውን አስረክበዋቸው፣ የሁለት ቀናት የፎረሙ ዝግጅቶች ተቋጭተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -