Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገሪቱን የገቢ ዕቃዎች እንደታቀደው ማስገባት አልተቻለም ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ትራንስፖርተሮች በሥራ ዕጦት መማረራቸውን ገልጸዋል

የአገሪቱን የዘጠኝ ወራት የትራንስፖርት ጉዳዮች የተመለከቱ አፈጻጸሞችን ለሕዝብ ክንፍ በማስመደጥ ውይይት ያደረገው የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ካቀረባቸው ጉዳዮች አንዱ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችና ጭነቶችን የተመለከተው ይገኝበታል፡፡

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከውጭ እንደሚገባ የታቀደው 15 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ጭነት ቢሆንም፣ 5.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ጭነት ወደ አገር ውስጥ እንደገባ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ የትራንስፖርት ማኅበራት ይህንኑ አኃዝ በማጣቀስ በድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት መስክ የሚታየውን ከፍተኛ የሥራ መቀዛቀዝ ለማሳየት ተጠቅመውበታል፡፡

ይሁንና ይህ አፈጻጸም የደረቅ ጭነት ብቻ እንደሆነ፣ ይህም ቢሆን በአሁኑ ወቅት ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን መጠጋቱን በማረም ምላሽ የሰጡት የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም ናቸው፡፡ አቶ ካሳሁን በሰጡት ማብራሪያ መሠረት፣ በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ከውጭ ይገባል የተባለው የደረቅ ጭነት መጠን 12 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሆን፣ አፈጻጸሙም 78 በመቶ ነበር ብለዋል፡፡ የ1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ አብዛኛው እንዳልገባ ግን አልሸሸጉም፡፡ ከ800 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ስንዴም የግዥ ሒደት ላይ እንዳለ ገልጸው፣ ጭነቶቹ ወደብ እንደደረሱ በቶሎ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል ቢሉም፣ አብዛኛው ጭነት ግን በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ መጓተቱን ጠቅሰዋል፡፡

የትራንስፖርት ማኅበራቱም እንደ ቀድሞው ጊዜ በርካታ ጭነቶችን ወደ አገር ውስጥ ማስባት እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ በወር አንድ ጊዜ ወደ ጂቡቲ እስከመሄድ እንደደረሱ፣ በዚህ ሳቢያም ሠራተኞችን ለመቀነስ እንደተገደዱ የገለጹም ነበሩ፡፡ የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት ማኅበራት ተወካዮች ሲገልጹ እንደተደመጡት፣ በአሁኑ ወቅት በወር አንድ ጊዜ እንኳ ወደ ጂቡቲ መሄድ አዳጋች እየሆነ በመምጣቱ ሾፌሮች ለሥራ አጥነት እየተዳረጉ ነው፡፡

ሾፌሮች በሚከፈላቸው ደመወዝ ሳይሆን በሚያገኙት አበል እየተደጎሙ እንደሚተዳደሩ የገለጹት የማኅበራቱ ተወካዮች፣ እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ሥራ በማጣታቸው ሳቢያ ለችግር መዳረጋቸውን መንግሥት እንዲያውቀው ጠይቀዋል፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት ግን ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባ በሚደረገው ምልልስ ጥቂት ግለሰቦችና ኩባንያዎች ጭነት እንደ ልብ ማጓጓዝ የቻሉበት የሞኖፖል አሠራር እንደሚታይም ለትራንስፖርት ሚኒስቴርና ለተጠሪ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

ሥራ አጥተናል ለሚለው የጭነት ትራንስፖርት ማኅበራቱ ጥያቄዎች ከተሰጡ ምላሾች ውስጥ በትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አብዲሳ ያዴታ የተሰጠውና አገሪቱ ያሳለፈችው የፖለቲካ ቀውስ አንዱ ምክንያት እንደሆነ የጠቀሱበት አግባብ ነበር፡፡ ‹‹ሥራ ጠፍቷል ለሚለው የሰላው ትልቁ ዋጋ ይሄው ነው፡፡ ምርት የለም፡፡ ንግድ የለም፡፡ ነገሮች ሲከፉ የት ድረስ እንደሚደርሱ፣ በእኛ አገር ይደርሳሉ፣ ይሆናል ብለን የማናስባቸው ነገሮች ሆነው ዓይተናል፡፡ ገቢያችሁ መቀነሱ ታይቷል፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

ከዚህ በተጓዳኝ በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ላይ ተደጋግመው የሚደመጡ ቅሬታዎችም ሲሰነዘሩ ተደምጠዋል፡፡ አዋጅን በመመርያ በመሻር ማኅበራትን የማይደግፉ አሠራሮች እንደሚታዩ፣ የአንበሳ አንድነት አገር አቋራጭ የደረቅ ጭነት ማኅበርን በመወከል የተናገሩት አቶ ብርሃኔ ዘሩ የተባሉ ሰው ናቸው፡፡ እንደ አቶ ብርሃኔ ቅሬታ ከሆነ፣ አዋጅ ቁጥር 968/97፣ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ለተቋቋሙ የጭነት ትራንስፖርት ማኅበራት ትልቅ ድጋፍ የሚሰጥ ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ በመመርያ እየሸረሸራቸው ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ‹‹ከትራንስፖርት ባለሥልጣን ጋር ያሉብንን ችግሮች ለመነጋገር መድረክ ይያዝልን፤›› በማለት ለትራንስፖርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ችግሮች ካሉብን፣ የምናነሳቸው ጥያቄዎችም ስህተት ከሆኑ ስህተት ናችሁ በሉን፣ አድምጡን፤›› ያሉት አቶ ብርሃኔ፣ የጭነት ትራንስፖርት ማኅበራት በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በኩል በደል እንደሚደርስባቸው፣ ‹‹ለምን ተናገራችሁ፣ አመጸኞች፣ ተቃዋሚዎች የሚሉ ስሞች እየተሰጡን ነው፡፡ ባለድርሻዎች ነን፡፡ በር አትዝጉብን፤›› በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

አቶ ካሳሁን በበኩላቸው ከጭነት ትራንስፖርት ማኅበራት ጋር ያለው አለመግባባት አንድ ጉዳይ ላይ ብቻ እንደሆነ፣ እሱም በቦርድ ሊቀመንበር አሠራር ላይ እንደሆነ በመጥቀስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹የቦርድ ሊቀመንበር የኦፕሬሽን ሥራ ውስጥ እየገባ ስምሪት አይስጥ ነው ያልነው፡፡ የቦርድ አመራር ከሁለት ጊዜ በላይ እንዳይመረጥ የሚከለክል ሕግ ነው ያወጣነው፡፡ ይህ የመብት መጣስ አይደለም፡፡ መከራከር ግን እንችላለን፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ይህ የተደረገው ማኅበራቱ እንደ ኩባንያ እንዲንቀሳቀሱ ተፈልጎ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የጭነት፣ የሕዝብ ማመላለሻ እንደሌላው አገር በኩባንያ ደረጃ ስላልተደራጁ፣ በልዩ ሁኔታ መንግሥትን በማሳመን በአዋጅ እንዲደራጁ መደረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም ማኅበራቱ የንግድ ባህርይ ያለው ሥራ እንዲሠሩ ማለትም የራሳቸው ነዳጅ ማደያ እንዲገነቡ፣ መለዋወጫ ለራሳቸው ፍጆታ ከውጭ እንዲያስገቡ የሚፈቅድ አዋጅ ፀድቆ ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም በአዋጁ የተጠቀሰው ይህ መብት በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ እንዲሁም በንግድ ሚኒስቴር ሳይቀር እንደማይከበርላቸው፣ ማደያም ለማቋቋምም ሆነ ከውጭ መለዋወጫ ለማስገባት ሲጠይቁ ለማኅበራት እንዲህ ያለው ሥራ አልተፈቀደም እየተባሉ እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያሉት ችግሮች የተደመጡበት መድረክ፣ በመጪው ሰኔ ወር አብዛኞቹ ችግሮች ላይ ምላሽ ይዞ እንደሚቀርብ፣ በአጭር ጊዜ ምላሽ የሚሰጥባቸውን መፍትሔ ሰጥቶ፣ በረዥም ጊዜ ለሚመለሱትም እንዲሁ ስትራቴጂ ቀርፆ እንደሚቀርብ አቶ አብዲሳ ገልጸዋል፡፡ በዚሁ መድረክ ወቅት የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ተዋናዮች ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች መዘገባችን ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች