Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ18 አገሮች የተውጣጡ ኩባንያዎች የሚታደሙበት ዓውደ ርዕይ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፌርትሬድ የተሰኘው የጀርመኑ ኩባንያ ከአገር በቀሉ ፕራና ኤቨንትስ ኩባንያ ጋር በመተባበር በቋሚነት ማዘጋጀት በጀመረው የግብርና፣ የምግብና መጠጥ ማቀነባበሪያ እንዲሁም የፕላስቲክ ኅትመትና ምርት ማሸጊያዎች የንግድ ዓውደ ርዕይ ላይ ከ18 አገሮች የተውጣጡ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት ተገለጸ፡፡

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ከሚያዝያ 25 እስከ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ስለሚጠበቀው ዓውደ ርዕይ የፌርትሬድ ኩባንያና የፕራና ኤቨንትስ ኃላፊዎች ከመንግሥት ተቋማት ተጠሪዎች፣ ከጀርመንና ከፈረንሳይ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተጠሪ ቆንስላዎች ጋር ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 16 ቀን 2010 ዓ.ም.  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ከ60 በላይ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት በሚጠበቀው በዚህ የንግድ ዓውደ ርዕይ የፕላስቲክ ማሸጊያዎች፣ የፕላስቲክ ውጤቶች፣ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያዎችና ልዩ ልዩ ማምረቻዎች ይተዋወቃሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ከ14 አገሮች የተውጣጡ ኩባንያዎች መሳተፋቸውን የገለጹት፣ የፌርትሬድ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፖል ማርዝ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ምርቶች ፍጆታ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ በመጣበት ወቅት የሚካሄደው ይህ ዓውደ ርዕይ ላይ በዘርፉ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች ይሳተፉበታል፡፡ በኢትዮጵያ ከዓመት ዓመት የነፍስ ወከፍ የፕላስቲክ ፍጆታ እያደገ መጥቷል፡፡ ከውጭ የሚገቡ የምግብ ውጤቶች በ21 በመቶ መጨመራቸውንና ከእነዚህም ውስጥ የወተት ምርቶችና የጣፋጭ ምግቦች የገቢ ንግድ ከፍተኛውን ደረጃ እንደያዘም ማርዝ ይጠቅሳሉ፡፡ በምግብ ሸቀጦች ረገድ፣ እ.ኤ.አ. በ2009 የኢትዮጵያ የምግብ ምርቶች የገቢ ንግድ መጠን 866 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ሲጠቀስ፣ ከሦስት ዓመት በፊት በነበረው መረጃ መሠረት የገቢ ንግድ መጠኑ ወደ 2.74 ቢሊዮን ዶላር ማደጉ ታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአማካይ የ21 በመቶ ዕድገት እያሳየ እንደመጣም መረጃዎቹ ይጠቁማሉ፡፡

 በምሥራቅ አፍሪካና በመካከለኛው አፍሪካ ቀጣና ከሚገኙ አገሮች ሁሉ ኢትዮጵያ የግብርና ማቀነባበሪያ ማሽነሪዎችን ከውጭ በገፍ ከሚያስገቡ አገሮች ሁለተኛዋ ስለመሆኗ የጠቀሱት ማርዝ፣ የፕላስቲክ፣ የማሸጊያና የኅትመት መሣሪያዎችንም በከፍተኛ መጠን ከሚያስገቡ የምሥራቅና የመካከለኛው አፍሪካ አገሮች መካከል ሁለተኛዋ ስለመሆኗም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚታየው የፕላስቲክ ምርቶች ፍጆታ አማካይ በ15 በመቶ ዕድገት እያሳየ እንደሚገኝ ሲጠቀስ፣ ባለፈው ዓመት የነበረው ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ፍጆታም 2.4 ኪሎ ግራም እንደነበር ተወስቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020ም የነፍስ ወከፍ ፍጆታው ወደ 3.2 ኪሎ ግራም እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡ በአገር ደረጃም የፍጆታው መጠን ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረበት የ44 ኪሎ ቶን ወይም የ44 ሺሕ ቶን የፕስቲክ ፍጆታ ወደ 220 ኪሎ ቶን ወይም ወደ 220 ሺሕ ቶን አሻቅቧል፡፡ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥም ወደ 308 ኪሎ ቶን ወይም ወደ 308 ሺሕ ቶን እንደሚያድግ ትንበያዎች ይጠቁማሉ በማለት ማርዝ አብራርተዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ፕላስቲክ ባታመርትም፣ የፕላስቲክ ውጤቶችን በማቀነባበርና ከውጭ በማስገባት ግን በትልቁ ከሚጠቀሱ አገሮች ተርታ ተጠቃሽ ሆናለች፡፡

የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳዬሳ ለታ እንደጠቀሱት፣ የወረቀት፣ የፕላስቲክ፣ የጠርሙስና መሰል ምርቶችና ማሸጊያዎች ለግብርናም ሆነ ለሌሎች ዘርፎች ወሳኝ ሚና ቢኖራቸውም፣ አንዳንዶቹ ማሸጊያ ምርቶች ከዋናው ምርት በላይ ከፍተኛ ዋጋ ይጠይቃሉ፡፡ በመሆኑም ተቋሙ ለምርት ማሸጊያዎችና ለኅትመት ኢንዱስትሪዎች ትኩረት እንደሚሰጥ ሲጠቅሱም፣ በአሁኑ ወቅት በዓመት 10.4 ሚሊዮን ቶን የፒፒ ፕላስቲክና ሌሎች ተለጣጭ ምርቶችን የሚያመርቱ 46 ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ቢመረትም ካለው ፍላጎት አኳያ በቂ እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡ የወረቀት ማሸጊያዎችና የኅትመት ውጠቶችን የሚያርቱ 21 ድርጅቶችም በዓመት ከ900 ሺሕ ቶን ያላነሰ ምርት ያቀርባሉ ብለዋል፡፡ ይህም ሆኖ ከፍተኛ ፍላጎት በመኖሩ ከውጭ ማስገባት ግድ ብሏል፡፡

የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲውቲካልስ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ መኩሪያ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ 70 የምግብና የመጠጥ ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙ አስታውሰዋል፡፡ ይህም ሆኖ የምግብ ሸቀጦችና መጠጦች ከውጭ በገፍ ይገባሉ፡፡ የእነዚህን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማስፋፋት ከሚጠበቁት ውስጥ 17 የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና በውስጣቸው የሚሰማሩ ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙበት አብራርተዋል፡፡ በፋርማሲውቲካል ረገድም ከ530 ሚሊዮን ዶላር ያላነሱ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

እንዲህ ያሉ አገርኛ ጉዳዮች የሚስተናዱበት ዓውደ ርዕይ ከሚያሳትፋቸው መካከል የኦስትሪያ፣ የቻይና፣ የዴንማርክ፣ የፈረንሣይ፣ የጀርመን፣ የህንድ፣ የጣልያን፣ የቱርክ፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ የአሜሪካ፣ የኬንያ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኩባንያዎችና የሌሎችም አገሮች እንደሚገኙበት ይጠቀሳሉ፡፡

የፕራና ኤቨንትስ ኩባንያ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ የዘንድሮው ዓውደ ርዕይ ከዓምናው የተሻለ የውጭ ተሳታፊዎች ቢመዘገቡበትም፣ የአገር ውስጥ ተሳታፊዎች ቁጥር ግን ከግማሽ በላይ መቀነሱን ገልጸዋል፡፡ ዓምና 18 የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ቢሳተፉም ዘንድሮ ወደ ሰባት ዝቅ ብለዋል፡፡ 

አብዛኞቹ የምግብና የፕላስቲክ ውጤቶች አስመጪዎችና አምራቾች በውጭ ምንዛሪ ዕጦት ሳቢያ እንደ ወትሯቸው ከውጭ ማስገባት አለመቻላቸው ዋናው ምክንያታቸው እንደሆነ አቶ ነብዩ አብራርተዋል፡፡ ከአገር ውስጥ ተሳታፊዎች ባሻገር በኢትዮጵያ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ ላይ ከሚጠበቀው አኳያ መጠነኛ ቅናሽ እንደታየ ጠቅሰዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1991 የተመሠረተው ፌርትሬድ ኩባንያ በቤሰተብ የንግድ ተቋምነት የሚተዳደር ሲሆን፣ በሰሜንና ከሰሃራ በታች በሚገኙ አፍሪካ አገሮች፣ በምሥራቅ አውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ በርካታ የንግድ ዓውደ ርዕዮችን በማዘጋጀት ይታወቃል፡፡ ፕራና ኤቨንትስ በበኩሉ ከ10 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ፣ በንግድ ዓውደ ርዕይና በተለያዩ የቢዝነስ ክንዋኔዎች አዘጋጅነት ሲሳተፍ የቆየ አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች