Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልዩኔስኮ የደረሰው የጥምቀት ክብረ በዓል ሰነድ

ዩኔስኮ የደረሰው የጥምቀት ክብረ በዓል ሰነድ

ቀን:

በሔኖክ ያሬድ

በኢትዮጵያ በድምቀት በአደባባይ ከሚከበሩት ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው የጥምቀት ክብረ በዓል ነው፡፡ በዓሉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የውጭ አገር ዜጎችንም ቀልብ የገዛ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ የፌስቲቫሎች መድበል የአፍሪካ ኤጲፋኒያ/ጥምቀት (The African Epiphany) እየተባለ የአክሱሙ፣ የጎንደሩ፣ የላሊበላው፣ የአዲስ አበባው የሌላውም አካባቢ የጥምቀት አከባበር በዓለም የክብረ በዓላት (Festivals) ድርሳን ላይ በየጊዜው የሚተዋወቀው፣ ቱሪስቶችም እየመጡ የሚያደንቁት አንዳንዶችም ‹‹የጥምቀት ክብረ በዓልን ለምን በዓለም አቀፍ ቅርስነት አላስመዘገባችሁም?›› እያሉ ሠርክ የጠየቁበት ነገር ዘንድሮ ወደ መቋጫው እያመራ ነው፡፡

በብሔራዊ ደረጃ ጥር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. የተመዘገበው ነው የጥምቀት ክብረ በዓልን በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት) በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity)  የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በይፋ እንቅስቃሴ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች  ያደረገውን ጥናት አጠናቆ  ከቀነ ገደቡ ከመጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በፊት ለዩኔስኮ ልኳል፡፡

የባለሥልጣኑ የባህል አንትሮፖሊጂስቱ አቶ ገዛኸኝ ግርማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ከባለሙያዎችና ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጋር ሙያዊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ነው ሰነዱ የተላከው፡፡ የጥምቀት በዓልን ለማስመዝገብ ከባለሥልጣኑ ጋር ተባብረው የሠሩት በመንበረ ፓትርያርክ የቅርስ ጥበቃና የቤተ መጻሕፍት የሙዚየም መምሪያ ኃላፊው መልአከ ሰላም ሰሎሞን ቶልቻ፣ የማስመዝገቢያው አንዱ መሥፈርት የይመዝገብልን ፊርማ በመሆኑ የምዕመናንና የካህናት ፊርማ ከነማመልከቻው ተያይዞ መቅረቡን  አስረድተዋል፡፡

መልአከ ሰላም ሰሎሞን የክብረ በዓሉን አንድምታ እንዲህ ይገልጹታል፡፡ ‹‹በርካታ በዓላት አሉን፡፡ ጥምቀት የሚለይበት ከሃይማኖታዊ መሠረትነቱ ባሻገር የአደባባይ በዓል መሆኑ ነው፡፡ ሕፃንና አዋቂ፣ ሽማግሌም ደካማውና ብርቱው የሚታይበት ሃይማኖታዊና ባህላዊ መገለጫዎቹም ለየት ያሉ ናቸው፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር የሚያስተሳስሩ፣ የኢትዮጵያዊነት ወዝ ያላቸው፣ ጠቀሜታቸው የጎላና እኛነታችንን የሚገልጹ ብዙ ባህሎች አሉበት፡፡ በሃይማኖታዊነቱ የጌታ መጠመቅ ለእኛ አርዓያ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ መጠመቁን የምናይበት ትልቁ በዓላችን ነው፡፡ ለክርስትና ሕይወት የጥምቀት በዓል መሠረታዊ በዓል ነው፡፡›› የማስመረጫ ሰነዱ የተላከለት ዩኔስኮ እ.ኤ.አ. ለ2019 በዕጩነት እንደሚያቀርበው ታውቋል፡፡

በዓለ ጥምቀቱ ሲገለጽ

በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥር 11 ቀን 31 ዓ.ም. (5531 ዓመተ ዓለም) በአጥማቂው ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ ነው፡፡ ‹‹ኤጲፋንያ›› በመባልም ይታወቃል፡፡ ጥር 10 ቀን በከተራ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወደየባሕረ ጥምቀቱ የሚያደርጉት ጉዞና መንፈሳዊ አዳር በማግስቱ የጥምቀት ዕለት ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ›› ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀን ይዞ የሚኖረው ያሬዳዊ ዝማሬ የበዓሉ ገጽታ ነው፡፡ ሥዕላዊ ከሆነው ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አከባበሩ በተጓዳኝም ባህላዊ ገጽታው ይታያል፡፡ ወጣቶች የሚተጫጩበት የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት አጋጣሚዎችን ከመፍጠሩም ባለፈ በከተማም ሆነ በገጠር ሰውን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡ በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው፣ በየባሕረ ጥምቀቱ የሚከበሩ በመሆናቸው፣ አገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብነትን በመጎናጸፉ፣ ቱሪስቶችን እንደሳበ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ላሊበላ፣ ከአክሱም እስከ ጎንደር፣ ከሐዋሳ እስከ ጅማ፣ ከአሶሳ እስከ ጋምቤላ በሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ ዓይነት ደምቆ ይከበራል። የምእመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ  በሚማርኩ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁልጊዜ አዲስ ነው። ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደያመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ።

ሊቃውንቱ እንደሚናገሩት፣ ዘመነ አስተርእዮ የሚባለው፣ ከጥር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ (ለዘንድሮ እስከ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም.) ያለው ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ‹‹አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ፣ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሠርግ ላይ የመጀመሪያው ተዐምር በመፈጸሙ፣ አምላካዊ ኃይሉ መገለጡ›› እየታሰበ ምስጋና ይቀርባል።

 ይህ ኩነት ኢትዮጵያ ብሂልን ከባህል ጋር አዛምዳ ከሌላው የክርስቲያን ዓለም በተለየ አከባበር በዓሉን ማክበሯ፣ አያሌ ቱሪስቶችን ለመሳብ አስችሏታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...