Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤት ፕሮግራም ሲፈተሽ

የተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤት ፕሮግራም ሲፈተሽ

ቀን:

በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በሶማሌና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የልማት ምጥጥኑን ለማስጠበቅ የሚያስችል ልዩ ድጋፍ የመስጠቱ ሥራ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ውሎ ቆይቷል፡፡ ድጋፉን ቅንጅት በተሞላበት መንገድ በመስጠት ላይ ያሉት ስምንት የሴክተር መሥሪያ ቤቶች መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ሴክተር መሥሪያ ቤቶቹ ድጋፉን የመስጠቱን ሥራ የሚያካሂዱት የክልሎችን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ተቋማዊ በሆነ መንገድ በመገንባት ነው፡፡ በዚህ መንገድ የሚካሄደው የግንባታ ሥራዎች ማኅበረሰቡ የትምህርት ቤት፣ የጤና ኬላ፣ ዘመናዊ የግብርና ዘዴ፣ ወዘተ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ነው፡፡

ማኅበረሰቡ በእነዚህ ልማቶች ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በቅድሚያ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የተለመደውን የተበታተነ አኗኗር ዘይቤ ማኅበረሰቡ ወደ ጎን ብሎ  በአንድ በተወሰነ ሥፍራ መኖር እንዲችል ማድረግ ግድ ነው፡፡ በዚህ መሠረትም መንግሥት ማኅበረሰቡን በመንደር የማሰባሰብ ሥራ አካሂዷል፣ እያካሄደም ይገኛል፡፡

የአቅም ግንባታ በማካሄድ ድጋፍ የመስጠቱን ሥራ በቅንጅት ከሚያካሄዱት ሴክተር መሥሪያ ቤቶቸ መካከል የትምህርት፣ የጤና ጥበቃ፣ የግብርናና ሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤቶች ተጠቃሾች ሲሆኑ፣ ፌዴራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር ደግሞ ቅንጅቱን የማስተባበር ሥራ ይሠራል፡፡

በአራቱም ክልሎች ልዩ ድጋፍ የሚካሄደው የልማት ምጥጥናቸው እስከ 2020 ዓ.ም. ድረስ ከሁሉም ክልሎች ጋር ተመጣጣኝ/እኩል እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡ ምጥጥኑ በተጠቀሰው ዓመተ ምሕረት የተጠበቀው ደረጃ ላይ መድረሱና አመራሩና ባለሙያው እየበቃ መሄዱ ሲረጋገጥ ግን ልዩ ድጋፉ ይቋረጣል፡፡

የልማቱንም አፈጻጸም በየሦስት ወሩ የሚገመግም፣ የልዩ ድጋፍ ቦርድ በፌዴራልና በክልል ደረጃ እንደተቋቋመ፣ በፌዴራል ደረጃ በተቋቋመው ቦርድ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልል ደግሞ የየክልሎቹ ርዕሳነ መስተዳድሮች እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአራቱ ክልሎች ከሚደረግላቸው ድጋፍ መካከል በትምህርት ዘርፍ የተሰጠው ድጋፍ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ አቶ ተክላይ ገብረ ሚካኤል፣ በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ድጋፍና አካቶ ትምህርት ዳይሬክተሩ በእያንዳንዱ ክልል እስከ ቀበሌ ድረስ አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት የሚሰጥበት፣ እስከ አራተኛ ክፍል ያለው ትምህርት ቤት መቋቋማቸውን ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቤቶቹ የተቋቋሙት በዛፍ ጥላ ሥር፣ በዳስና በጎጆ ውስጥ ሲሆን፣ ያቋቋሙትም የየወረዳው ማኅበረሰቦች ናቸው፡፡ ከማኅበረሰቦቹ የተውጣጡና የሠለጠኑ መምህራን በየትምህርት ቤቶቹ ተመድበዋል፡፡ የመማርና ማስተማር ሒደቱን የሚያሳልጡ መጻሕፍትም ተሠራጭተዋል፡፡ በሶማሌ ክልል ብቻ 1,168 አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት ቤቶች እንዲቋቋሙ ተደርጓል፡፡

በዚህ መንገድ የተጀመረው የመማር ማስተማሩ ሥራ እየተጠናከረና ውጤታማ እየሆነ ሲመጣም በእያንዳንዱ ወረዳ ካሉት አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት ቤቶች መካከል 15 ከመቶ ያህሉ ወደ መጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲያድጉ ተደርጓል፡፡

ሁሉም አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት ቤቶች ወደ መጀመርያ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድል ያላገኙት እንደ ወንበር፣ ጠረጴዛና ጥቁር ሰሌዳ  የመሳሰሉት መሠረታዊ የትምህርት ቤት መገልገያ ግብዓቶችን የመግዛትና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችን የማሟላቱ ሥራ አቅምን የሚፈታተን በመሆኑ ነው፡፡

አሥራ አምስት ከመቶ ያህሉ ክልሎች አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት ቤት ወደ መጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከፍ ካሉ ወዲህ የተማሪዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ እንደመጣ፣ ለአብነት ያህልም በጋምቤላ ክልል የተማሪዎች ቁጥር ከ100 ፐርሰንት በላይ እንዳደገ ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

ይህም ሆኖ ግን ከጊዜ በኋላ በአንዳንድ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ልጆች እየተበራከቱ መምጣታቸው አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በተለይም በሶማሌና በአፋር ክልሎች የማቋረጡ ሁኔታ በስፋት እየታየ ነው፡፡ በአፋር ክልል ብቻ ገና የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርት ሳይጀመር ከሰባት ሺሕ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡

ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ድህነት መሆኑንና ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ችግሩ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ጉዳዩን አስመልክቶ የተሠራው ጥናት ያሳያል፡፡ ስለሆነም ለችግሩ ብቸኛው መፍትሔ የትምህርት ቤት የምግብ ምገባ ፕሮግራም ማስጀመር እንደሆነ ጥናቱ ይመክራል፡፡

ለ1.4 ሚሊዮን ተማሪዎች የምግብ ፕሮግራም ለማስጀመር ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ዓመት 289 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ገንዘቡ ፈሰስ የተደረገው ከመጠባበቂያ የመንግሥት በጀት ነው፡፡ እንደ አቶ ተክላይ ገለጻ፣ የምገባ ፕሮግራም እየተካሄደ ያለው በአብዛኛው በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ሲሆን፣ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ደግሞ በሙከራ ደረጃ እየተከናወነ ይገኛል፡፡  

በአራቱም ታዳጊ ክልሎች በመካሄድ ላይ ያለው የመማር መስተማሩ ሥራ የትምህርት ጥራት ፓኬጆችን መሠረት ያደረገ ግምገማ፣ ግብዓት የማሟላትና የሰው ኃይል የማሠልጠኑ ሥራ እንደቀጠለ ነው፡፡ ግምገማው ካተኮረባቸው ነጥቦች መካከል የትምህርት ቤቶች ተደራሽ መሆንና ምቹ የማድረግ መርሐ ግብሮች እንደሚገኝበት ከዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

አቶ ብርሃኔ ሞረዳ የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ናቸው፡፡ እንደ አማካሪው ማብራሪያ፣ በታዳጊዎች ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም ክልሎች የሚተገበሩ ስድስት የጥራት ፓኬጆች አሉ፡፡  እነርሱም የሥርዓተ ትምህርት፣ የመምህራን ልማት፣ የትምህርት አመራርና አስተዳደር፣ የትምህርት ቤት መሻሻል፣ የትምህርት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት መርሐ ግብሮች ናቸው፡፡

እነዚህን መርሐ ግብሮች በውስጣቸው ያቀፉት ፓኬጆች የአተገባበር ሁኔታ ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ አዲስ አበባ ላይ አሁን እየተተገበሩ ያሉበት ሁኔታ ምናልባትም በታዳጊ ክልሎች ላይ በሚፈለገው ልክ እየተተገበሩ ላይሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር የጠበቀ ክትትልና ድጋፍ የሚጠይቅ ሥራ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

በታዳጊ ክልሎች ያሉ ሕፃናት በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸው ሊያቋርጡ ይችላሉ፡፡ ከምክንያቶቹም መካከል ድርቅ ያስከተለው ችግር፣ ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀሱ፣ ትምህርት ቤቶች ምቹና ተደራሽ አለመሆንና ድህነት፣ እንዲሁም መምህሩ ሕፃናቱን በአግባቡ ያለመያዝ ችግርና ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸው መስተጋብር የጠነከረ አለመሆኑ፣ ከንድፈ ሐሳቡ ባሻገር ፔዳጎጂካልና ማኅበራዊ ክህሎቶቻቸው አናሳ መሆንና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ የጥራት ፓኬጆች በትክክል ከተተገበሩ ግን የተጠቀሱት ችግሮች ተወግደው ሕፃናትን ወደ ትምህርት ቤት መልሶ ማቆየት እንደሚቻል ነው አማካሪው የተናገሩት፡፡   

ከብት አረቢ ማኅበረሰቦች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ቀደም ሲል ሲካሄድ የነበረው የተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤት (ሞባይል ስኩል) ይዞታ በአገር ውስጥና በውጭ ኮንሰልታንቶች በመጠናት ላይ ይገኛል፡፡

አቶ ተክላይ እንደገለጹት፣ በጋምቤለ፣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሚገኙ በእነዚህ አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ ትምህርቱ እንዲጠና ያስፈለገበት ምክንያት ውጤታማ ሆኖ ባለመገኘቱ ነው፡፡

ለጥናቱ ሥራ የሚውለውን በጀት በመደገፍ ወይም በመሸፈን የተባበረው ብሪቲሽ ካውንስል ሲሆን፣ ጥናቱ በቅርቡ ተጠናቅቆ ለሚመለከተው አካል ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...