Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከሕዝብ ፈቃድ ውጪ መሆን ለማንም አያዋጣም!

የአዲሱን ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ/አደረሰን የምኞት መግለጫ በመለዋወጥ፣ በዓሉ በተጠናቀቀ ማግሥት በቀጥታ ወደ አንገብጋቢው የአገር ጉዳይ መመለስ ተገቢ ነው፡፡ ከዳር እስከ ዳር የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሩ ሰላም እንዲሰፍን፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ኖሮ ፍትሕ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን፣ በአገሩ ጉዳይ በነፃነት ተሳታፊ ሆኖ የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትኖረው ይፈልጋል፡፡ መጠራጠርና መፈራራት የሌለበት፣ ከአሉባልታና ከሐሜት የፀዳ፣ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲዳብር፣ የመወያየትና የመደራደር ባህል እንዲሰፍን፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ የጋራ እሴቶች እንዲከበሩና ለግጭት የሚዳርጉ አላስፈላጊ ድርጊቶች እንዲገቱ ወገብን ጠበቅ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች፣ ሰፋፊ ለም መሬቶች ያሉዋት፣ በሥነ ምግባርና በሞራል እንዲሁም በማስተዋል ታላቅ አክብሮት ያተረፈ ሕዝብ ያላት ትልቅ አገር ናት፡፡ ይህንን ፀጋና በረከት ማስተዋል እያቃተ ሕዝብን ግጭት ውስጥ የሚከቱ ድርጊቶችን ማየት ያስከፋል፡፡ ከምንም ነገር በላይ ሕዝብ በችላ ባይነት ሲጎዳ ማየት ያሳምማል፡፡ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይም የማይሽር ጠባሳ ያሳርፋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ግን ለሕዝብ ፈቃድ መገዛት ይገባ ነበር፡

ደግመን ደጋግመን የምንለው ከሕዝብ የሚበልጥ የለም ነው፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ በፖለቲካው ዙሪያ የሚገኙ ወገኖች ደጋግመው ማሰብ ያለባቸው፣ በተሳሳቱ ውሳኔዎችና ያላግባብ በሚደረሱ ድምዳሜዎች ምክንያት ሕዝብ ላይ አደጋ እንዳይደርስ ነው፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን ኃላፊነት በጎደላቸው ውሳኔዎችና ድምዳሜዎች ሳቢያ ሕዝብ ይሞታል፣ ለአካል ጉዳት ይዳረጋል፣ ከቀዬው ይፈናቀላል፣ የአገር ሀብት ይወድማል፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው አስከፊ ድርጊት ሊገታ ይገባል፡፡ ለዘመናት በክፉና በደግ ጊዜያት አብሮ የኖረ ሕዝብ መሀል ለግድያ የሚያደርስ ችግር መፈጠር አልነበረበትም፡፡ ችግር ቢፈጠር እንኳ በፍጥነት መፈታት ነበረበት፡፡ አሁን እየተሰማ ያለው ግን ነባሩን የሕዝብ አብሮነትና ወንድማማችነት የሚንድ ነው፡፡ ይህንን ድርጊት በፍጥነት አስቁሞ የእርማት ሥራ ማከናወን ተገቢ ነው፡፡ ሕዝቡን በተለምዶ የግጭት አፈታት ሥርዓቱ አስማምቶ ቁስሉን ማከም የአርቆ አሳቢዎች ተግባር ነው፡፡ ፖለቲከኞች ደግሞ ከአጉል እልህ ውስጥ ወጥተው ሕጋዊውን መንገድ በመከተል ችግራቸውን መፍታት አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያዊያን ነባሩና ቱባው የጋራ ባህል ቅድሚያ የሚሰጠው ለእርቅና ለይቅር ባይነት ነው፡፡ ይቅር ተባብሎ የተፈጠረውን ስህተት ማረም የአገር ባህል ነውና በዚህ መሠረት ችግሮች ይፈቱ፡፡ ለሕዝብ ፈቃድ መገዛት የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ አውዳሚ ተግባር ውስጥ መግባት የተከበረው ሕዝባችን ፍላጎት አይደለም፡፡ ይህ ይሰመርበት፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ ተከባብሮና ተስማምቶ መኖር የቻለውና እስካሁንም የዘለቀው፣ ከሚለያዩት ይልቅ አንድነቱን የሚያጠናክሩ የጋራ እሴቶቹ ስለሚበልጡ ነው፡፡ ይህ ለአፍ ልማድ ወይም ለወሬ ማጣፈጫ የሚነገር ቀልድ ወይም ማስመሰል አይደለም፡፡ ወይም አንዳንድ ማስተዋል የጎደላቸው ወገኖች እንደሚሉት፣ በሕዝብ መካከል መቼም ቢሆን ቂም በቀል ኖሮ እርስ በርሱ ሲጋጭ አይታወቅም፡፡ ይልቁንም በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ ወራሪዎችን በጋራ የመከተውና ደሙን ለአገሩ ያፈሰሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ የአውሮፓን ኮሎኒያሊስት ኃይል አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ የዓለም ጥቁር ሕዝቦችን አንገት ቀና ያደረገው ይህ ታላቅና ጀግና ሕዝብ ነው፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝም መመሥረት ምክንያቱ እሱ ብቻ ነው፡፡ አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነፃ ለመውጣት ሲታገሉ፣ ዘመን አይሽሬ አስተዋጽኦ ያበረከተው ይህ ምሥጉንና ኩሩ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ጀግና ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በተዘረጋው መልክዓ ምድር ውስጥ በፍቅር የሚኖር ነው፡፡ ይህ ሕዝብ በአፍሪካ ምድር እንደ አንበሳ እያገሳ በነፃነት የኖረ የነፃነት ቀንዲል ነው፡፡ በዘህ ዘመን እርስ በርሱ ተጋጨ ሲባል አያሳዝንም? አያሳፍርም? ይህ ኩሩ ሕዝብ ይከበር፡፡

በተለያዩ ጎራዎች ቢሠለፉም የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ አገር የምትኖረው ሕዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት ይፈልጋል፡፡ ፍትሕ ይፈልጋል፡፡ በእኩልነት መኖር ይፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተገንብቶ አገሩ እንድትበለፅግና ሰላም እንድትሆንለት ይፈልጋል፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ተከብረውለት የሥልጣኑ ትክክለኛ ባለቤት መሆን አለበት፡፡ የፈለገውን የመሾም ያልፈለገውን የመሻር መብት የእሱ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ምኞት ዕውን መሆን የሚችለው ደግሞ በሁሉም አቅጣጫ መደማመጥ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የአገሪቱ ፖለቲካ የቧልተኞችና የራስ ወዳዶች መጠቃቀሚያ ከመሆን ወጥቶ፣ ለእውነተኛ ውይይትና ለድርድር ጥርጊያ ጎዳናው ሊመቻች ይገባል፡፡ የራስ ወዳዶችና የግብዞች ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ዲስኩር ይበቃል፡፡ ለሥልጣን ብቻ በሚደረግ የእልህ ሽኩቻ ዴሞክራሲ አይገነባም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጤነኝነት የጎደለው አካሄድ ትርፉ የአገር ውድመት ነው፡፡ ሕዝብን ለዕልቂት መዳረግ ነው፡፡ ሕዝብን ማዕከል ያላደረገ በቅዥት የሚመራ ፖለቲካ አገርን ከማጥፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያው ውስጥ የመሸጉ የጠላት ተላላኪዎች አገርን ለማፍረስና ሕዝብን ለማተራመስ የሚያደርጉት መሯሯጥ፣ በሰከኑና አርቆ አሳቢ ዜጎች ይብቃ መባል አለበት፡፡ ሌላውም እንዲሁ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ ከሕዝብ በላይ ማንም የለምና፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ ለአገራቸው ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ልምዳቸውንና አለን የሚሉትን ነገር በሙሉ ፈቃዳቸው ለመስጠት ዝግጁ የሆኑ አኩሪ ዜጎች ብዙ ናቸው፡፡ ትውልድን ከመኮትኮት ጀምሮ ለአገር ዕድገትና ብልፅግና ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጁ እነዚህ አኩሪ ወገኖች ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልጋሉ፡፡ ከአድርባይነትና ከአጉል ይሉኝታ ርቀው የሰላ ሒስ በማቅረብ ስህተትን የሚያርሙና ቀናውን ጎዳና የሚያሲዙ በሻማ ብርሃን ጭምር መፈለግ አለባቸው፡፡ ከራሳቸውና ከመሰሎቻቸው ጥቅም ባሻገር የአገር ጉዳይ ደንታ የማይሰጣቸው እንዲታረሙ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር እያጋጩ ሰላም የሚያደፈርሱና የአገር ሀብት እየዘረፉ የሚፎልሉ በሕግ እንዲጠየቁ፣ ሥርዓተ መንግሥቱ በሕግ የበላይነት ሥር እንዲሆንና ሕዝብ እንዲከበር ይፈለጋል፡፡ ይህ ፍላጎት ዕውን መሆን የሚችለው ደግሞ በመፈክር ጋጋታና በአስመሳይነት አይደለም፡፡ አዲሱ ዓመት በርካታ የተንከባለሉ ጥያቄዎችን አዝሎ የመጣ በመሆኑ፣ በኃላፊነት ስሜት መመራት ተገቢ ነው፡፡ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የተገፉ ዜጎች ሳይቀሩ በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ምኅዳር መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ያገኘ መብት ነው፡፡ ሕዝብ ይህ መብት እንዲከበር ይፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት፡፡ የአፍሪካውያን መሰባሰቢያቸውም ናት፡፡ ለአፍሪካውያን ጭምር የጋራ ቤት የሆነችው ይህች ኩሩና የኩሩዎች አገር፣ ከደረጃዋ ወርዳ መገኘት የለባትም፡፡ ሕዝቧ አርዓያነቱ ከአድማስ እስከ አድማስ በዓለም የታሪክ መዝገብ ህያው ሆኖ ሰፍሮ እያለ፣ በወሰንና መሰል ጉዳዮች ተጋጨ ሲባል ተቃርኖ ይፈጥራል፡፡ ይህ በአስቸኳይ  ታርሞ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በይፋ መገለጽ አለበት፡፡ የ76 ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ መኖሪያ በሆነችው አገር ውስጥ እርስ በርስ መጠራጠርና መፈራራት እንዳይፈጠር፣ በዚህ ክፍተት ደግሞ የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ሰተት ብለው ገብተው ትርምስ እንዳይፈጥሩና የሕዝባችንን የአብሮነት ደማቅ ታሪክ እንዳያበላሹ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡  ለጊዜያዊ ጥቅምና ሥልጣን ሲባል ብቻ የሕዝባችንን ታሪክ ማበላሸትና አገሪቱን የማትወጣው ችግር ውስጥ መክተት ይቅር የማይባል ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በጨዋነት፣ በአርቆ አሳቢነት፣ በአስተዋይነት፣ በይቅር ባይነትና በጀግንነት የጋራ እሴቶቹ እስካሁን ያቆያትን አገር በመከባበርና በመተሳሰብ ማስቀጠል ይገባል፡፡  ለአገር ሲባል መደማመጥ የግድ ነው፡፡ መወያየትና መደራደር ባህል መሆን አለበት፡፡ አገርን ትርምስ ውስጥ ከከተቱ በኋላ ጥርስ ማፋጨትና መፀፀት በመካከለኛው ምሥራቅና በአካባቢው ያደረሰውን ውድመት አልቀለበሰውም፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለስደትና ለሰቆቃ የዳረገው የሌሎች ጥፋት ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡ አገራቸውን የሚያፈቅሩ ይህንን ይረዱታል፡፡ የጥፋት አባዜ የተጠናወታቸው ደግሞ ይሳለቁበታል፡፡ አሁን ጊዜው የቀልድና የቧልት አይደለም፡፡ የአገርና የሕዝብ ህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ይቅርታና ፍቅር ይቅደም፡፡ ሕዝብን የሚያስደስተው ይኼ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከሕዝብ ፈቃድ ውጪ መሆን ለማንም አያዋጣም መባል ያለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...