Monday, May 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የለውጥ ሒደቱን መደገፍ የለውጥ አካል መሆን ነው!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢሕአዴግ ሊቀመንበር እንዲሆኑ ከተመረጡና በፓርላማ ከተሰየሙ ጊዜ ጀምሮ፣ አገሪቱ ላይ አንዣቦ የነበረው የሥጋት ደመና እየተገፈፈ ነው፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመገኘት ከሕዝብ ጋር እያደረጉ ባሉት ውይይትም ይህ እውነታ በሚገባ ተንፀባርቋል፡፡ እሳቸው እያስጀመሩ ያሉትን የለውጥ ሒደት በመደገፍ ሕዝብ በግልጽ እየተናገረም ነው፡፡ ለውጡ ስኬታማ እንዲሆንም ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ መተማመኛ እየሰጠ ነው፡፡ የአገሪቱ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት እንደሆነ የሚታሰበው ሕዝብ የለውጡ አካል ለመሆን ቁርጠኝነት ሲያሳይ፣ የለውጡን ሒደት ለማደናቀፍ መሞከር ፀቡ ከሕዝብ ጋር ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ የኖረችው፣ አሁንም ያለችው፣ ወደፊትም የምትኖረው በታታሪና በምሥጉን ልጆቿ አለኝታነት እንጂ፣ ከውጭ እንደ ሸቀጥ በሚገቡ ርዕዮተ ዓለሞች አይደለም፡፡ አሁን ኢትዮጵያን ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልጋት ልጆቿ በእኩልነት ሊያኖራቸው የሚችል ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ብቻ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህ ጠንካራ አንድነት ልዩነቶችን እያስተናገደ በሰላምና በፍቅር የሚኖሩበት መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ አንድ ርዕዮተ ዓለማዊ መስመር ላይ ተገትሮ ወይ ንቅንቅ ማለት የአምባገነንነት ባህሪ ነው፡፡ ልዩነትን የማያከብር ከመሆኑም በላይ አንዱን ወዳጅ ሌላውን ጠላት እያለ የሚፈርጅ በሽታ ነው፡፡ ለለውጥም ደንቃራ ነው፡፡

አሁን ዋናውና መሠረታዊው ጉዳይ በተጀመረው የለውጥ ሒደት አማካይነት አገርን ከአደጋ እየተከላከሉ ሁሉን አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንጂ፣ የአንድ ጎራን ርዕዮተ ዓለም ለመከላከል ሲባል ሌላ ትርምስ ማስነሳት አይደለም፡፡ አገር ከምንም ነገር በላይ ስለሆነች ለተጀመረው ለውጥ ቢቻል ደጋፊ መሆን፣ ካልተቻለ ደግሞ አደብ መግዛት ይመረጣል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለሙን ለማስረፅ ሲፈልግ የሕዝቡን ወቅታዊ ስሜት ማጤን ካልቻለ እንደ አሮጌ ሸክላ ይጣላል፡፡ የተጣለ ሸክላ ደግሞ ዕጣ ፈንታው መሰባበር ብቻ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ራሳቸውን እየለወጡና እያዘመኑ መሄድ ሲገባቸው፣ እንደ ድንበር ድንጋይ አንድ ቦታ ተገትረው ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም፡፡ ‹‹በድሮ በሬ ያረሰ የለም›› እንዲሉ፣ በድሮ ቅኝት እያላዘኑ አደባባይ መውጣት መሳቂያ ያደርጋል፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በአዲሱ ትውልድ አስተሳሰብ እየታገዘ መዘመን አለበት እንጂ፣ ከዘመኑ ጋር መራመድ በማይችል አሮጌ ቀኖና ወንዝ አይሻገርም፡፡ ጊዜው የለውጥ እንደ መሆኑ የለውጡ ባቡር ላይ መሳፈር መቼም ቢሆን ሊታለፍ የማይገባ እውነታ መሆን አለበት፡፡

በተለይ ኢሕአዴግ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› አድርጌ እየታደስኩ ነው ሲል፣ ወደ አሮጌው አስተሳሰብ ሊመልሱት የሚፍጨረጨሩትን ጭምር መታገል ይጠበቅበታል፡፡ ከለውጡ ጋር መራመድ የተሳነው ካለም ወይ ራሱን ማደስ ይኖርበታል፣ ካልሆነም አደናቃፊ እንዳይሆን መቆጠብ አለበት፡፡ የኢሕአዴግ አራቱ ብሔራዊ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ከወራት በፊት በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ለ17 ቀናት በተደረገው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግምገማና ውሳኔ መሠረት ኢሕአዴግ በአገሪቱ ለተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ ዋናው ምክንያት መሆኑን አምነው ነበር፡፡ ‹‹ከሰማይ በታች ያልተነጋገርንበት ጉዳይ የለም›› በማለትም በተለይ አመራሩ ያደረሰውን ጥፋት በጥቅሉ ተናግረዋል፡፡ ይኼንንም መነሻ በማድረግ ከፖለቲካ ጋር በተገናኘ የተፈረደባቸው እስረኞች እንዲፈቱ፣ በክስ ላይ የነበሩ እንዲቋረጥላቸው፣ ማዕከላዊ ምርመራ የሚባለው የሰቆቃ ተቋም ተዘግቶ  ሙዚየም እንዲሆን፣ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚረዱ የተለያዩ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ መወሰኑንም አስታውቀው ነበር፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አሠራር ጠፍቶ በርካታ ችግሮች መድረሳቸውን ተናግረው፣ ተሃድሶው በጥልቀት እንደሚቀጥል ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡ በውሳኔው መሠረትም እስረኞችን ከመፍታት ጀምሮ መልካም ጅምሮች ታይተዋል፡፡ በኋላም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአገሪቱ በደረሰው ቀውስ ምክንያት በገዛ ፈቃዳቸው ከሥልጣናቸው ለቀዋል፡፡ ይህ መጠነኛ ማሳያ በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረውን ችግር ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም በኢሕአዴግ ውስጥ በተደረገ እልህ አስጨራሽ ትግል አማካይነት ለሥልጣን መብቃታቸው፣ በራሱ የለውጡ ሒደት መነሻ መሆኑን ያመለክታል፡፡ አገርን ከገባችበት ዙሪያ ገብ ቀውስ ለመታደግ አዲስ ምዕራፍ መሆኑ ብዙዎችን አግባብቷል፡፡

ይኼንን ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት ተስፋ የሰነቀ የለውጥ ጉዞ ለማሰናከል መሞከር ከሕዝብ ጋር ያጋጫል፡፡ ለእናት አገሩ ከፍተኛ ፍቅር ያለው ሕዝብ አገሩ ለሦስት ዓመታት ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ለመውጣት ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እያየች በመሆኑ፣ ከዳር እስከ ዳር ደስታውን እየገለጸ ነው፡፡  አገር ላይ ያንዣበበው ሥጋት ተገፎ ኢትዮጵያዊያን መጪውን ጊዜ ለማሳመር በቀና መንፈስ በአንድነት ለመነሳት መልካም ፈቃዳቸውን ሲያሳዩ፣ ለሕዝብ በማይገባ አሰልቺ ፕሮፓጋንዳ ወደኋላ ለመመለስ የሚፍጨረጨሩ ካሉ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እየታደስኩ ነው ብሎ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች ከታዩ በኋላ ወደ ኋላ ለመመለስ ማንገራገር ዕርባና ቢስ ብቻ ሳይሆን፣ ከሕዝብ ጋርም የመረረ ፀብ ውስጥ ይከታል፡፡ አንድ ርዕዮተ ዓለማዊ መስመር ብቻ ነክሶ እሱ ላይ መቆዘምና የተሃድሶውን እንቅስቃሴ ማደናቀፍ ለድርጅቱም አይረባም፡፡ ከዚህ ይልቅ እስካሁን የነበሩትን ብልሹ አሠራሮች ሙሉ በሙሉ በማስወገድ፣ በሕግ የበላይነት ሥር የምትተዳደር አገር እንድትፈጠር ከልብ መነሳት ይገባል፡፡ የተወላገደውን አስተካክሎ ለውጡን ማስቀጠል የሚጠቅመው ለአገር ነው፡፡ ከአገር በላይ ምንም የለም፡፡

ለውጡ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አስተማማኝ አንዲሆን ደግሞ መደጋገፍ ይገባል፡፡ ይኼ መደጋገፍ ጥቅም ያስገኛል፡፡ የአገሪቱን አንፃራዊ ሰላም ይመልሳል፣ የሕዝቡ ጥያቄዎች በቅደም ተከተል እንዲመለሱ ይረዳል፣ የሕዝቡን በአንድነት የመኖር ፀጋ ያጠናክራል፣ ለአገር ዕድገትና ለጋራ ጉዳዮች መግባባት ይፈጥራል፣ የነገውን ቀና ጎዳና በኅብረት ለመተለም ዕገዛ ያደርጋል፡፡ ለዚህ ስኬት አገሪቱ የተረጋጋ አመራር እንዲኖራት ያስፈልጋል፡፡ መምራት ማለት መራመድ ሲሆን፣ አንድ ቦታ ቆሞ ለመምራት መሞከር አይታሰብም፡፡ አመራሩን አላንቀሳቅስ የሚሉ እንከኖች ሲፈጠሩ ለውጥ ይደናቀፋል፡፡ በፓርቲ ውስጥም ሆነ በአገር ደረጃ ለለውጥ የሚደረጉ ጥረቶችን መደገፍ ሲገባ፣ እንቅፋት መሆን አገርን ለሌላ ዙር ቀውስ ማመቻቸት ነው፡፡ ቁማር እንደተበላ ቁማርተኛ እየተነጫነጩ የለውጥ ሒደቱን መራገምና ጨለምተኛ መሆን ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ሕዝብ ‹እኔ ብቻ አውቅልሃለሁ› የሚባለውን አሰልቺ ነጠላ ዜማ ማዳመጥ እንደማይፈልግ በግልጽ ተናግሯል፡፡ አሁን የሕዝቡን ቴርሞ ሜትር በሚገባ መለካት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ መደረሱን መገንዘብ ይገባል፡፡ ይኼም የለውጥ አካል ለመሆን ይረዳል፡፡

አሁን ወሳኙ ሥራ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ሕገወጥ ድርጊቶችን ማምከን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው እንዲረጋገጥ፣ በሕገወጥ ድርጊት ውስጥ መሳተፍ በሕግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል መተማመን እንዲፈጠር፣ በሕግ ዋስትና ያገኙ መብቶች በተግባር ሥራ ላይ እንዲውሉ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጥሱ አፋኝ ሕጎች እንዲሻሻሉ፣ ፓርላማው አስፈጻሚውን አካል በሚገባ እንዲቆጣጠር፣ የዳኝነት አካሉ በነፃነት እየሠራ፣ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ አስፈጻሚው አካል በከፍተኛ ትጋትና ብቃት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው የጋራ ጉዳዮች ተሳታፊ የመሆን መብታቸው እንዲከበር፣ ከማንነት ብዝኃነት በተጨማሪ የሐሳብ ብዝኃነት ተግባራዊ ዕውቅና እንዲሰጠው፣ በጠላትነት የሚያፈራርጁ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች እንዲወገዱ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ ወዘተ ከልብ መሥራት ለውጡን የበለጠ ያፋጥነዋል፡፡ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያዊያንም በያሉበት ከተሰማሩበት የሥራ መስክ አስተዋፅኦ በተጨማሪ፣ ለውጡ ስኬታማ ሆኖ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ዕገዛ ያድርጉ፡፡ የለውጥ ሒደቱን መደገፍ የለውጥ አካል መሆን ነውና!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...