Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከድንበር ጥያቄ ጋር በተገናኘ ከሱዳን ፕሬዚዳንት ጋር መከሩ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከድንበር ጥያቄ ጋር በተገናኘ ከሱዳን ፕሬዚዳንት ጋር መከሩ

  ቀን:

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያና ሱዳን ባልፈቱት የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተገናኘ፣ ከሱዳን ፕሬዚዳንት ጋር በባህር ዳር መምከራቸው ተሰማ፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ እሑድ ሚያዝያ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በተጠናቀቀው ጣና ፎረም ላይ ለመሳተፍ ከተገኙት የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር ጋር ሁለቱ አገሮች ጥያቄ በሚያነሱበት ድንበር ላይ የጎንዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በአማራ ክልል በመተማ በኩል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳበት ድንበር ዕልባት ስለሚያገኝበት፣ ይህ እስኪከናወን ድረስም መፍትሔ ሊሆኑ ይገባል ባሏቸው ሐሳቦች ላይ እንደመከሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ይሁን እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በሁለቱ መሪዎች ውይይት ወቅት የድንበር ጉዳይ አልተነሳም ብለዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች ለመጀመርያ ጊዜ በአካል እንደ መገናኘታቸው መጠን፣ የተዋወቁበትና በቀጣይ በሁለቱ አገሮች ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሠሩ የገለጹበት ውይይት መሆኑን ቃል አቀባዩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡  

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከሱዳኑ ፕሬዚዳንት ጋር ውይይት ከማድረጋቸው አስቀድሞ፣ በጎንደር ከተማ ከነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

  በወቅቱ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች መፍትሔ እንዲሰጣቸው ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ከሱዳን ጋር የሚያዋስነው የመተማ ድንበር ጉዳይ ይገኝበታል፡፡

  በወቅቱም፣ ‹‹ከሱዳን ድንበር ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጉዳይ መፍትሔ መስጠት አለበት ብዬ አምናለሁ፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ጉዳዩን በተመለከተም ለጣና ፎረም ስብሰባ ባህር ዳር ከሚገኙት የሱዳን ፕሬዚዳንት ጋር እንደሚወያዩ ተናግረው ነበር፡፡

  ‹‹በድንበሩ ላይ የሚገኙት የሁለቱም አገሮች ወታደሮች ከአካባቢው እንዲወጡና የሁለቱም ወገን ነዋሪዎች በሰላም እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ለጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በወቅቱ ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባነሱት በዚህ የመፍትሔ ሐሳብ ላይ ከሱዳን ፕሬዚዳንት ጋር ተወያይተው የደረሱበት ምን እንደሆነ አልታወቀም፡፡ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ጥያቄ ከሚነሳበት ድንበር በተጨማሪ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ መሆኑ ታውቋል፡፡

  ሁለቱ አገሮች የድንበር ይገባኛል ጥያቄውን ለመፍታትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለመተባበር የጋራ የድንበር ኮሚሽን አቋቁመው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ የድንበር ጥያቄውን ለመፍታት የድንበር ማካለል እንዲከናወን በድንበር ኮሚሽኑ ከዓመታት በፊት የተወሰነ ቢሆንም፣ እስካሁን ግን ወደ ተግባር አልተገባም፡፡ 

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ኢዜማ በምሥራቅ ወለጋ ዞን የንፁኃን ጭፍጨፋ አሳስቦኛል አለ

  በግጭት ቀጣና ውስጥ ያሉ ዜጎች ራሳቸውን ከጥቃት ለመጠበቅ መታጠቅ...

  ኦሲፒ አፍሪካ ጨዋማ መሬት ለማከም የሚረዳ ምርምር ይፋ አደረገ

  በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለአርሶ አደሩ የሚሠራጨውን የአፈር ማዳበሪያ በማቅረብ...

  የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በየዓመቱ አርባ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን እያስተዋወቀ መሆኑን ገለጸ

  የአገሪቱን የግብርና ልማት በምርምር የሚያግዙ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የማልማት፣ የግብርና...

  የተሽከርካሪ ባለንብረቶች በአክሲዮን ለመደራጀት የሚያስፈልጋቸውን የተሽከርካሪ ብዛት የሚወስን መመርያ ተረቀቀ

  የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ባለንብረቶች ከማኅበርነት ወጥተው አክሲዮን ሲቋቋሙ፣ ከሚጠበቅባቸው...