Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናለአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ከፍተኛ ሥልጣን የሚሰጥ አዋጅ ፀደቀ

ለአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ከፍተኛ ሥልጣን የሚሰጥ አዋጅ ፀደቀ

ቀን:

  • ባለሥልጣኑ በከተማው ሠራተኛ አስተዳደር አዋጅ አይገዛም

ላለፉት ሰባት ዓመታት በፌዴራል መንግሥት ሥር ሲተዳደር ቆይቶ ታኅሳስ 2010 ዓ.ም. በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተመለሰው ገቢዎች ባለሥልጣን፣ ከፍተኛ ሥልጣን የሚሰጥ አዋጅ ፀደቀ፡፡

ከሰኞ ሚያዝያ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ቀናት በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ስብሰባ የከተማው ገቢዎች ባለሥልጣን፣ በሠራተኞቹ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዲኖረው የሚያደርግ አዋጅ አፀድቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈጻሚና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካላት ለማቋቋም እንደገና በተዘጋጀ ረቂቅ ሕግ ላይ ከአንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 2 በመቀጠል፣ ‹‹አንቀጽ ሦስት›› እንዲጨመር በረቂቁ ተመልክቷል፡፡

- Advertisement -

አንቀጽ 3 በያዘው ዋና ነጥብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 8/2000 ቢኖርም ይልና ሦስት ጉዳዮችን ያስቀምጣል፡፡ የመጀመርያው ባለሥልጣኑ ለሠራተኛው አመቺ የሆነ አደረጃጀትና መዋቅር እያጠና በሚመለከተው አካል ሲፀድቅ በሥራ ላይ ሊያውል ይችላል ይላል፡፡

ሁለተኛው የገቢዎች ባለሥልጣን ሠራተኞች አስተዳደር የከተማው ካቢኔ በሚያወጣው ደንብ መሠረት ይመራል ይላል፡፡ ሦስተኛው የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ልዩ የደመወዝ ስኬልና ጥቅማ ጥቅም ክፍያ ሥርዓት አጥንቶ ለከተማው ከንቲባ ያቀርባል፣ ሲፈቀድም ተግባራዊ ያደርጋል የሚል ነው፡፡

የዚህን አንቀጽ አስፈላጊነት በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ሲያብራሩ፣ የአዋጁ አስፈላጊነት መነሻ ገቢዎች ባለሥልጣን የተለየ ባህሪ ያለው ተቋም መሆኑ ነው፡፡

‹‹የታክስ አስተዳደር ሥርዓት የተለየ ባህሪ ስላለው ዘርፉ በልዩ የሕግ ማዕቀፍ መመራት ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ የምንፈልገውን ውጤት ማምጣት አንችልም፤›› ሲሉ አቶ አባተ አስረድተዋል፡፡

አቶ አባተ ጨምረው የኢትዮጵያ ጉምሩክና ገቢዎች ባለሥልጣን ለየት ያሉ የሕግ ማዕቀፎች አሉት፡፡ ሠራተኞችን የሚያስተዳድረውም ከሲቪል ሰርቪስ ሕግጋት በተለየ ነው በማለት፣ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አዲስ አዋጅ ከፌዴራል መንግሥት የተቀዳ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 155/2000 ለኢትዮጵያ ጉምሩክና ገቢዎች ባለሥልጣን የሰጠው ሥልጣን በወጣበት ወቅት አነጋጋሪ ነበር፡፡

ይህ ደንብ፣ ‹‹በሌላ ሁኔታ የተደነገገ ቢኖርም የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በሙስና የተጠረጠረና እምነት ያጣበትን ማንኛውም ሠራተኛ፣ መደበኛውን የዲሲፒሊን ዕርምጃ አፈጻጸም ሥርዓት ሳይከተል ከሥራ ማሰናበት ይቻላል፤›› ይላል፡፡

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት ከሥራ የተሰናበተ ሠራተኛ፣ በየትኛውም የፍርድ ቤት አካል ውሳኔ ወደ ሥራ የመመለስ መብት አይኖረውም በማለት ይደነግጋል፡፡

ለምክር ቤቱ የቀረበውና የፀደቀው አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህንን ዓይነት ደንብ እንዲያወጣ ሥልጣን እንደሰጠ ሁሉ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤትም ለካቢኔው ይህንን ሥልጣን እንዲሰጥ አድርጓል፡፡

በወቅቱ በምክር ቤት አባላትና በአስፈጻሚ ባለሥልጣናት መካከል የተነሳው ነጥብ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 8/2000 ቢኖርም፣ ይህንን ትቶ በአንቀጽ አዲስ ድንጋጌ መጨመሩ ነው፡፡

የምክር ቤት አባላት፣ ‹‹ቢሆንም›› የሚለው ቃል ቀርቶ አዋጅ ቁጥር 8/2000 ዓ.ም. ‹‹እንደተጠበቀ ሆኖ›› በሚለው ሊቀየር ይገባል የሚል ጠንከር ያለ መከራከርያ አቅርበዋል፡፡

ነገር ግን የከተማው ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ወርዶፋ ይህንን መከራከርያ አልተቀበሉትም፡፡ አቶ ሙሉነህ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ  ባለሥልጣን በፌዴራል ሠራተኞች አዋጅ አይተዳደርም፡፡ ፓርላማው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣቱ የባለሥልጣኑ ሠራተኞች በወጣው ደንብ ይተዳደራሉ፡፡

‹‹በአዲስ አበባም እንዲሁ ምክር ቤቱ ለካቢኔው ሥልጣን ይሰጥና ካቢኔው በሚያወጣው ደንብ የከተማው ገቢዎች ባለሥልጣን ይተዳደር ነው ጉዳዩ፤›› በማለት አቶ ወርዶፋ አስረድተዋል፡፡

‹‹እንደተጠበቀ›› የሚለው ቃል አይሆንም፣ ‹‹ቢሆንም›› የሚለው ቃል ነው ሊሆን የሚገባው በማለት አቶ ሙሉነህ አብራርተዋል፡፡

የከተማው ምክር ቤት ይህንን ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ ባይቀበለውም፣ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርጎ አዋጁን በድምፅ ብልጫ አፅድቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...