Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ አስተዳደር በዘጠኝ ወር ውስጥ 21.6 ቢሊዮን ብር ሰበሰበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 23.8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 21.6 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ፣ የዕቅዱን 90.61 በመቶ ማሳካቱን አስታወቀ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ባለሥልጣኑ የታክስ ሥወራንና ማጭበርበርን ለመቆጣጠር፣ ብሎም ሕግ ለማስከበር ባካሄደው የምርመራ ኦዲት 483 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን የ2010 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በተያዘው በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ ርዕሶች 31.5 ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ ዕቅድ ይዟል፡፡

በዘጠኝ ወራት ውስጥ ደግሞ 23.8 ቢሊዮን ብር ሊሰበስብ ዕቅድ ቢያወጣም፣ ማሳካት የቻለው 21.6 ቢሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 90.61 በመቶ ነው፡፡

ይህ ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ3.6 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሲሆን፣ በወቅቱ የተሰበሰበው 17.9 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ነገር ግን የበጀት ዓመቱ ሊጠቃለል ሦስት ወራት ቢቀሩትም፣ ሙሉ ለሙሉ የዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት 9.9 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ይጠበቅበታል፡፡ ይህንን ዕቅድ ለማሳካት የተለያዩ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

ይህን ገንዘብ በመሰብሰብ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት አራዳ፣ አዲስ አበባ መካከለኛ ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት ቦሌ ቅርንጫፎች ናቸው ተብሏል፡፡

ባለሥልጣኑ በዘጠኝ ወራት ትልቅ ሥራ ለማከናወን ያሰበው የምርመራ ኦዲት ላይ ነበር፡፡ ባለሥልጣኑ በሪፖርቱ እንደገለጸው፣ የታክስ ሥወራንና ማጭበርበርን ለመቀነስ፣ የታክስ ሕግ ለማስከበርና የገቢ አሰባሰብ ሥጋት የሚሆኑ የሥራ ዘርፎችን፣ የትልልቅ ግብር ከፋዮች የሒሳብ መዝገብ ኦዲት በማድረግ የተደበቁ የወንጀል እንቅስቃሴዎች በመቀነስ ታቅዶ ነበር፡፡

‹‹ያልተከፈለ የመንግሥት ገቢ ለመሰብሰብ፣ የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎች በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ የኦዲት ሥራ ምርመራ ተሠርቷል፤›› በማለት የገለጸው የባለሥልጣኑ ሪፖርት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና በዋናው መሥሪያ ቤት በ142 ፋይሎች ላይ ኦዲት በማድረግ 639 ሚሊዮን ብር የኦዲት ግኝት ለመወሰን ታቅዶ አፈጻጸሙ፣ በ139 ፋይሎች ላይ ምርምር በማካሄድ 483 ሚሊዮን ብር መወሰኑን ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡

በታኅሳስ ወር ወደ አዲስ አበባ የተመለሰውን ገቢዎች ባለሥልጣን እንዲመሩ የቀድሞው የንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ ተሾመዋል፡፡ አቶ ሺሰማ ይኼን ተቋም እንዲመሩ ሐሙስ ሚያዝያ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በከተማው ምክር ቤት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፡፡

የከተማው ገቢ የመሰብሰብ አቅም እያደገ መሄዱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የከተማው ኢኮኖሚ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ሊያመነጭ እንደሚችል ጥናቶች የሚያሳዩ ሲሆን፣ ከዚህ አንፃር ባለሥልጣኑ ብዙ ርቀት ላይ እንደሚገኝ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች