Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየእግር ኳስ ፌዴሬሽን ዝምታና የፊፋ የምርጫ ሕግ

የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ዝምታና የፊፋ የምርጫ ሕግ

ቀን:

ከወራት በፊት ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ተወካዮች በአዲስ አበባ ቆይታ አድርገው፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮችንና ዕጩ ተወዳዳሪዎችን አነጋግረው መመለሳቸው አይዘነጋም፡፡ ተወካዮቹ የፌዴሬሽኑን ቀጣይ አመራሮች ለመምረጥ የነበረውን ሒደትና ላለፉት ሰባት ወራት ያህል ሲከናወን ለቆየው ሽኩቻና ትርምስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት፣ ፊፋ በተለይ የምርጫ ደንብና መመርያ እንዴትና በምን አግባብ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ምክረ ሐሳቡን ይሰጥ ዘንድ፣ መረጃ ለመሰብሰብ ወደ ኢትዮጵያ የላካቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዚህ መሠረት ፊፋ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀጣይ ምርጫ የሚከናወንበትን የምርጫ ሥነ ምግባር ሕግ ከአፈጻጸሙ ጭምር ከሰሞኑ ለፌዴሬሽኑ ልኳል፡፡ ይኼው የምርጫ ሕግ የፌዴሬሽኑ ሕጋዊ የምርጫ መመርያና ደንብ ሆኖ እንዲቀጥልና ጠቅላላ ጉባዔውም እንዲያፀድቀው፣ ለሚያዝያ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡ ይሁንና ይኼ ዘገባ እስከተጠናቀረበት  ዓርብ ሚያዝያ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ሌሊት ድረስ፣ የጉባዔው የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከስብሰባው በፊት ተልኮላቸው ተዘጋጅተው እንዲመጡ የምርጫ ሕጉ እንዳልደረሳቸው ታውቋል፡፡ ክልሎችም ሆኑ ክለቦች ፊፋ የላከው የምርጫ ሕግ ለፌዴሬሽኑ መድረሱ በመገናኛ ብዙኃን ከተነገረበት ቀን ጀምሮ ኮፒ ተደርጎ እንዲላክላቸው በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

የሪፖርተር ዝግጅት ክፍል ይኼንኑ የክልሎችና የክለቦችን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ፌዴሬሽኑን ለማነጋር ጥረት አድርጓል፡፡ ይሁንና የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰሎሞን ገብረ ሥላሴ ጉዳዩን በስልክ እንዲያብራሩ ተጠይቀው፣ ‹‹ስብሰባ ላይ ነኝ›› በማለት ተጨማሪ አስተያየት ሳይሰጡ ግንኙነቱን አቋርጠዋል፡፡

- Advertisement -

 በሌላ በኩል የምርጫ ሕጉ ደርሷቸው ዝርዝሩን የተመለከቱ አንዳንድ ወገኖች፣ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ አስተዳዳሪ (ፊፋ)፣ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሰሞኑን የላከው የምርጫ ሕግ እንዳለመታደል ሆኖ እንጂ፣ ተዘጋጅቶ መቅረብ የነበረበት በኢትዮጵያዊያን የዘርፉ ባለሙያዎች ነበር፡፡ ይኼ ባለመሆኑ የሚቆጨን ሰዎች ብንኖርም አሁንም  ከፊፋ የመጣውን የምርጫ ሕግ ለአገሪቱ እግር ኳስ ሲባል ትኩረት አግኝቶ ተግባራዊ ቢደረግ ጥሩ ነው በማለት ለመልዕክቱ ያላቸውን በጎ ምላሽ ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ጀምሮ በተለያዩ የፍትሕ አካላት ውስጥ ለዓመታት በማገልገል የሚታወቁት የሕግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ኃይሉ ሞላ፣ ከእነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ አቶ ኃይሉ ፊፋ ለፌዴሬሽኑ ‹‹ላከው›› የተባለውን የምርጫ ሕግ በዝርዝር እንደተመለከቱት ጭምር ያስረዳሉ፡፡

ዓለም አቀፉ ተቋም እ.ኤ.አ. በታኅሳስ 2007 ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከላከው የምርጫ ሕግ ጋር የአሁኑ ብዙም ልዩነት እንደሌለው የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ አሁንም የምርጫ ሕጉ ከተፈጻሚነት ወሰኑ ጀምሮ መርሆዎቹና ግዴታዎቹ ሲታዩ በጥሩ ጎኑ ሊወሰዱ የሚገባቸው መሆኑን ያምናሉ፡፡ በተለይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዴት መከናወን እንዳለበትና በዚሁ መሠረት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ምን ምን መሥራት እንዳለበት አመለካች ነገሮችን በዝርዝር አካቶ የያዘ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡

የሕግ ባለሙያው ሲቀጥሉ፣ ‹‹ፊፋ የምርጫ ሕጉን በ27 አንቀጽ በመከፋፈል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ልኳል፡፡ በአንቀጽ ሁለት የተመለከተው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀደም ሲል ምርጫ ሲካሄድ የማይታወቁ አዳዲስ የሕግ አካሄዶች ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በሚያካሂደው ምርጫ በእጅጉ የሚያጨቃጭቀውና የሚያወዛግበው ጉዳይ ሳይቀር ግልጽ በሆነ ቋንቋ ሰፍሮ ይገኛል፤›› ይላሉ፡፡

በዚሁ አንቀጽ ክፍል ሁለት የተቀመጡት የምርጫ አካሄድና ሕጎች ደግሞ፣ አስመራጭ ኮሚቴ የሚባለው አካል ሊኖሩት ስለሚገባው ሥልጣንና ኃላፊነት በግልጽ መሥፈሩን የሚያክሉት የሕግ ባለሙያው፣ የምርጫ ሕጉ ወደ ክፍል ሦስት ንዑስ አንቀጽ አንድ ሲቀጥል፣ ‹‹አስመራጭ ኮሚቴ የሚያደራጀውም ሆነ የሚመለከተው በዚሁ ሕግ መሠረት በመሆኑ ከምርጫ ጋር የሚገናኙ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ፣ በዚህ አስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ በአሁኑ ወቅትም ሆነ ቀደም ሲል በፌዴሬሽኑ ውስጥ በምንም መንገድ የነበሩ ሊካተቱ እንደማይገባ ይደነግጋል፤›› ብለው፣ በአንቀጽ ሦስት ንዑስ አንቀጽ ሦስት ላይ ደግሞ የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት መሆን የሚገባቸው በተቻለ መጠን ገለልተኛ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ያስገነዝባል፡፡

በዚሁ የፊፋ የምርጫ ሕግ አስመራጭ ኮሚቴውን በተመለከተ የተቀመጠው የማያከራክርና የማያወላዳ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፣ ከዚህ ውጪ  የሚመረጠው አስመራጭ ኮሚቴ መታጨት (መቅረብ) ያለበት በፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ነው፡፡ ለአመራርነት የሚታጩት የሚመረጡት በዚህ የምርጫ ሕግ መሠረት መሆኑን እንደሚያስረዳ በግልጽ መቀመጡንም ይናገራሉ፡፡

የጊዜ ገደቡን በተመለከተ የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ከሚያደርገው ምርጫ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ መሰየም እንዳለበት በዝርዝር መቀመጡን የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ በምርጫ ሕጉ አንቀጽ አምስት ደግሞ ይኼው አስመራጭ ኮሚቴ በምን ያህል የሰው ኃይል መዋቀር እንዳለበት ጭምር ያብራራል፡፡ በንዑስ አንቀጽ አንድ አባላቱ አምስት ሲሆኑ፣ በንዑስ አንቀጽ ሁለት አንድ ዋናና በአንድ ምክትል ሊቀመንበርና ሦስት አባላት መሆን እንዳለባቸው አስቀምጦ ምናልባት በሚል ሦስት ተጠባባቂዎች እንደሚካተቱ ያስረዳል፡፡

እንደ ሕግ ባለሙያው ከሁሉም በላይ በምርጫ ሕጉ አንቀጽ ስድስት የተቀመጠው፣ አስመራጭ ኮሚቴው ምን ምን ሥራዎች እንደሚሠራ በዝርዝር መቀመጡ ትልቁ ነገር ሲሆን፣ ለሥራው ማስኬጃ የሚሆኑ ወጪዎች ደግሞ በፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት የሚሸፈኑ እንደሚሆንም ያስረዳል፡፡ በአንቀጽ ሰባት የአስመራጭ ኮሚቴ ስብሰባ እንዴትና በምን አግባብ እንደሚካሄድ፣ የድምፅ አሰጣጡ ሁኔታና በውሳኔ ጊዜ የተለያዩ አቋሞች ቢንፀባረቁ መፍትሔውም አብሮ መካተቱ ተመልክቷል፡፡

ቀጥሎ በምርጫ ሕጉ የተቀመጠውና በተለይም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ የውዝግብና የልዩነት መንስዔ ለሆነው ለፕሬዚዳንታዊና ሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ዕጩ ሆነው የሚቀርቡ አባላት ጉዳይ፣ በአንቀጽ ዘጠኝ እንዳስቀመጠው የተገቢነቱ ጉዳይ የሚወሰነው በፌዴሬሽኑ መተዳዳሪያ ደንብና መመርያ ብቻ መሆኑን ያሳያል፡፡

ይሁንና እስከ ዛሬ በነበረው የፌዴሬሽኑ የምርጫ ሒደት፣ በመንግሥት አካሉ የሚዘጋጀው ማኅበራት የሚደራጁበት መተዳደሪያ ደንብ እንደ ማመሳከሪያ እየተወሰደ ጥቅም ላይ የሚውልበት አጋጣሚ የነበረ ስለመሆኑ አቶ ኃይሉ አልሸሸጉም፡፡

በአንቀጽ 11 የተቀመጠው የምርጫ ሕግ፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውዝግብ መንስዔ ሆኖ ለቆየው አስመራጭ ኮሚቴው የዕጩዎች የተገቢነት ጉዳይ የሚያጣራበትን ይመለከታል፡፡ በሒደቱም እነማን ተገቢ ናቸው? እነማን ተገቢ አይደሉም? ብሎ በመለየት ውሳኔ የሚያሳልፍበት አሠራር በግልጽ መቀመጡንና  መብራራቱን የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፣ ‹‹በአንቀጽ 12 በሒደቱ ችግሮች ቢፈጠሩ በምን ዓይነት የይግባኝ ሥርዓት መፍታት እንደሚቻል፣ የይግባኝ አባላቱ እነማን እንደሆኑ፣ ሦስት በዋናነት ሁለት በተጠባባቂነት የሚኖሩ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባላት መሆናቸው፣ ይግባኝ የሚል አካል ቢመጣ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ይግባኙ መታየት እንዳለበት፣ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሚወስነው ውሳኔ ማንም ጣልቃ ሳይገባ መንግሥትን ጨምሮ በፍጹም እንደሚከለክል በግልጽ የደነገገ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በምርጫ ሕጉ በአንቀጽ 13 የተቀመጠው የመጨረሻዎቹ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ዝርዝር እንዴት ይፋ እንደሚደረግ ግልጽ ማድረጉን የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፣ በአንቀጽ 15 ደግሞ ምርጫውን በተመለከተ የአስመራጭ ኮሚቴው ኃላፊነትና ግዴታ በዝርዝር መቀመጡን ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ሒደት እስከ አንቀጽ 18 ድረስ የተቀመጡ ድንጋጌዎች የምርጫ ሁኔታና የአፈጻጸም ቅደም ተከተልን የሚያሳዩ ስለመሆናቸው ጭምር ያስረዳሉ፡፡

በአንቀጽ 19 ደግሞ የምርጫውን አጠቃላይ አካሄድና በእነ ማን እንደሚመራ፣ የድምፅ አሰጣጥ፣ ቆጠራና ሌሎችንም በዝርዝር አካቶ መያዙን የሚያክሉት የሕግ ባለሙያው፣ የምርጫ ሕጉን በአጠቃላይ በ27 አንቀጾች ከፋፍሎ በማስቀመጥ የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎችን ሳይቀር አጠቃሎ የያዘ ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ የፊፋ የሕግ ድንጋጌዎች በምንም መመዘኛ ከአገሪቱ አቅም በላይ እንዳልነበሩ የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፣ በአጠቃላይ ግን ፊፋ በዚህ አጋጣሚ የእግር ኳሱን ምርጫ ለማካሄድ ይኼንን የምርጫ ሕግ በመቀበል ትምህርት መውሰድ ለዘርፉም ሆነ ለተቋሙ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ያምናሉ፡፡ የምርጫ ሕጉ ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ባለሙያዎች አለመዘጋጀቱ የሚያስቆጭ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገር ግን የምርጫ ሕጉ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚስማማ፣ እግር ኳሱ ከገባበት ውዝግብና ንትርክ እንዲወጣ የሚረዳ፣ በሒደት ግን በዘርፉ ባለሙያዎች አማካይነት መሻሻል የሚገባው ካለ መሻሻል የሚችል ግልጽ የሕግ አካሄድን የሚያስተምር እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...