Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ከእለታት አንድ ቀን በአንድ አገር ንጉሡ ሕዝብ ስለሳቸው ምን እንደሚል ለማወቅና የተለያዩ ትኩስ ወሬዎችን ለመስማት በማሰብ አንድ ዕቅድ ያወጣሉ፡፡ በዕቅዳቸው መሠረት ሕዝቡ ውስጥ የሚነገሩትን ነገሮች በሙሉ ልቅም አድርጎ የሚያመጣላቸው ሰው ይሾማሉ፡፡ የእሳቸው ዋነኛ ዓላማ የሚባለውን መስማትና በዚያ ላይ ተመሥርተው፣ መንግሥታቸው የሕዝቡን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ይኼንን ፍላጎታቸውን በሚገባ አስረድተው ሹሙን ወደ ሥራ ያሰማሩታል፡፡

ንጉሡ ለአንድ ወር ያህል ቢጠብቁ ከሹሙ በኩል የሚመጣ ወሬ የለም፡፡ ምናልባት የዕለቱንና የሳምንቱን አንድ ላይ አጠናቅሮ ሊያመጣልኝ ይችል ይሆናል ብለው በትዕግሥት ቢጠብቁም ጠብ የሚል ነገር ጠፋ፡፡ ቢቸግራቸው ሹሙን አስጠርተው ለማናገር ወሰኑ፡፡ ንጉሡ እንደ ወትሮው ጎርደድ እያሉ፣ ‹‹እስካሁን ብጠብቅህ ምንም ዓይነት መረጃ አላመጣህም፣ ችግሩ ምንድነው?›› አሉት፡፡ ሹሙ ሁለት እጆቹን አጣምሮ አንገቱን እንደ ደፋ፣ ‹‹ንጉሥ ሆይ ከሾሙኝ ጊዜ ጀምሮ ሰው ጭጭ ብሏል፤›› አላቸው፡፡ ንጉሡ በመገረም እያዩት፣ ‹‹ለምን?›› ሲሉት፣ ‹‹እኔ እንጃ ሁሉም ሰው እኔን ሲያየኝ የጀመረውን ወሬ አቋርጦ ዝም ይላል፤›› በማለት የገጠመውን ነገራቸው፡፡

‹‹በል ተወው!›› ብለው በሌላ መንገድ ነገሩን ለማጣራት በመፈለግ የአገር ሽማግሌዎችን ይሰበስባሉ፡፡ ከሽማግሌዎቹ ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ካደረጉና አቤቱታ ከተቀበሉ በኋላ፣ ‹‹ለመሆኑ ለምንድነው የእኔ ሹም ሲኖር ሕዝቡ ዝም የሚለው?›› በማለት ድንገተኛ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ከሽማግሌዎቹ መካከል አንዱ ብድግ ይሉና እንዲናገሩ እንዲፈቀድላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ንጉሡ ሲፈቅዱላቸው፣ ‹‹ንጉሥ ሆይ እኛ ከእርስዎ ጋር ባልሆነ ምክንያት መጣላት ስለማንፈልግ ነው፤›› አሏቸው፡፡ ንገሡ በመገረም፣ ‹‹ለምን ትጣሉኛላችሁ?›› በማለት ሲጠይቁ፣ ሽማግሌው አንዴ ንጉሡን ሌላ ጊዜ ሌሎቹን ሽማግሌዎች እያዩ፣ ‹‹ግርማዊነትዎ የላኩብንን ሹመኛ እናውቀዋለን፡፡ እኛ የምንፈልገውንና የምናምንበትን ሐሳባችንን ገልብጦ ካቀረበው በመጨረሻ ንጉሥና ሕዝብ ጠብ ውስጥ ልንገባ ነው፡፡ ስለዚህ እሱ ሲመጣ ዝም በማለታችን ቢያንስ ሰላም እንዳይደፈርስ አድርገናል፤›› ሲሉ ንጉሡ በመደነቅ ተመለከቷቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የሕዝቡ አስተያየት ከሽማግሌዎቹ ጋር በሚደረገው የምክክር መድረክ እንዲሰማ ወስነው ሽማግሌዎቹን አሰናበቷቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንግሥትና ሕዝብ በሚገባ መደማመጥ ጀመሩ ይባላል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማየው አሳሳቢ ሁኔታ ይኼንን ዕድሜ ጠገብ ምሳሌ አስታወሰኝ፡፡ ኢሕአዴግ በምርጫ 2007 የፓርላማ መቀመጫ መጠቅለሉን ሳስብ አንዳንድ ነገሮች ያሳስቡኝ ነበር፡፡ በወቅቱ  የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት አድርጎ እንደሚሠራ፣ የመረጠውንም ሆነ ያልመረጠውን ሕዝብ በእኩልነት እንደሚያገለግል፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአገር ጉዳይ ላይ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ጋር እንደሚመካከር፣ ስለተገኘው ድልም ‹‹እናመሰግናለን›› በማለት ብሔራዊ መግባባት እንደሚፈጥር ተስፋ ፈንጥቆ ነበር፡፡ በወቅቱ ግን የነበረውን የሕዝብ ኩርፊያ መቼም አልረሳውም፡፡ ዋል አደር ብሎ የመጣው ቀውስ የኩርፊያው ውጤት መሆኑን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡

እነሆ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያለፍንባቸው መከራዎች ብዙ አሳይተውናል፡፡ አንዳንድ ነገሮች ይላላሉ ሲባል የበለጠ ሲወጠሩ፣ የመቀራረብ ስሜት ሊፈጠር ነው ወይ ሲባል የመራራቅና የመጠላላት ግጭት ሲከሰት ለአገር ዕድገትና ብልፅግና የሁሉም ዜጋ ርብርብ ያስፈልጋል ሲባል በሩ ሲቀረቀር፣ ሰላም ሰፍኖ ልማት ሊጧጧፍ ነው ተብሎ ሲጠበቅ ጦርነት መሰል ውድመቶች አገሩን እያዳረሱ ነበሩ፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት የበለጠ ይጎለብታል የሚል ዘና የሚያደርግ መንፈስ ሲነቃቃ ይኼንን መብት የሚጋፉ አሉታዊ ጋጋታዎች በዝተው፣ በደል ደረሰ ተብሎ አቤቱታ ሲቀርብ አዳማጭ አልነበረም፡፡ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤቱ ምን እንዳስከተለ የታወቀ ስለሆነ ብዙ ማለት ጠቃሚ አይደለም፡፡

እነዚህንና የመሳሰሉትን ግራ የሚያጋቡ ነገሮች በአዕምሮዬ ውስጥ ሳወጣና ሳወርድ አንድ ቀን በወጣትነታችን አሜሪካ ከተማርን ጓደኞቼ ጋር ለምን አንነጋገርበትም አልኩ፡፡ በዚህ መሠረት ሁለቱን አግኝቼ ነገሩን ሳነሳላቸው ሁለቱም ‹‹ታክቶናል በቃን›› የሚል አስተያየት ሰጡኝ፡፡ በጣም ተናድጄ መፍትሔው ምን ይሁን ትላላችሁ ስላቸው፣ በቀልድ የሚታወቀው አንዱ ጓደኛችን፣ ‹‹እንደ ንጉሡ የሽማግሌ መካሪዎች እንዳልልህ ለዚህ የሚመጥኑ የሉም፣ ስለዚህ በአጉል መካሪዎች እንቀጥቀጥ፤›› ሲለኝ፣ ‹‹አዎ! ሽማግሌ የሌለው አገር እንዴት ይባረካል? ጥሩ መካሪ ከሌለስ ምን ይደረጋል?›› ብዬ ትቼው ነበር፡፡

አሁን ግን የተውኩትን ጉዳይ እንደገና እንዳነሳው የሚያስገድድ ወቅት ላይ ስለሆንን፣ ሽማግሌ ጠፋ ባልንበት አገር የልጅ ሽማግሌ ስለተገኘ አንድ ነገር ማለት አለብኝ ማለት ፈለግኩ፡፡ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቼና እህቶቼ የልጅ ሽማግሌውን አህመድ ዓብይን (ዶ/ር) የተባረከ ጅምሩን ደግፈን፣ አገራችንን ከገባችበት ማጥ እናውጣት፡፡ ይኼ ሰው በክፉ ጊዜ አገር ሊታደግ ከፈጣሪ የተላከ ያህል ይሰማኛልና በማስተዋል ውስጥ ሆነን እንደግፈው፡፡ የዳር ተመልካችነት እንኳን ምራቁን የዋጠ ሽማግሌ አሰላሳይ ወጣትንም ያጠፋብናል፡፡ አደራ በሰማይ አደራ በምድር፡፡

(የምሥራች መክብብ፣ ከአራት ኪሎ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...