Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክየማንነት ጥያቄ አወሳሰን በሕገ መንግሥቱ ወልቃይት በምሳሌነት

የማንነት ጥያቄ አወሳሰን በሕገ መንግሥቱ ወልቃይት በምሳሌነት

ቀን:

በዘላላም እሸቱ

በቅርቡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መቐሌ ላይ ያደረጉትን ንግግር ተመርኩዞ የወልቃይት ጥያቄ አጀንዳ ሆኗል፡፡ እንግዲህ በአገራችን የተመሠረተው ፌዴራላዊ ሥርዓት ብሔርን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የብሔር ጉዳዮችን ለመፍታት ከሄዱበት መንገድ የተለየና ድፍረት የተሞላበት ስለመሆኑ በርካቶች ይስማማሉ፡፡

የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ ዋና አጀንዳ ሆኖ ለዘመናት በመቆየቱ ሕገ መንግሥቱ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ብዙ ርቀት በመሄድ ብሔርን ለፌዴራል ሥርዓቱ መነሻ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም የብሔር ብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ ዕውቅና በመስጠት ከተማሪዎች ዘመን ጀምሮ ይዘመርለት ለነበረውን የብሔር ጥያቄ መልስ ለመስጠት ሞክሯል፡፡ የራሳቸው የሆነ የተለየ ክልል የሌላቸው ብሔሮችም ወደፊት ክልል የመመሥረት መብታቸውን ክፍት በማድረግ፣ አዳዲስ ክልሎች የሚመሠረቱበትን ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ሥር ደንግጓል፡፡

- Advertisement -

ባለፉት ዓመታት ውስጥ የተተገበረው ኅብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት በርካታ ፈተናዎች ያጋጠሙት ሲሆን፣ ከማንነት ጋር ተያይዘው የተነሱና የሚነሱ ጥያቄዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ የስልጤ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ፣ የቅማንት ሕዝብ የማንነት ጥያቄና ወቅታዊው የአማራ ሕዝብ የወልቃይት ጥያቄን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የዚህ ጹሑፍ ዓላማም የማንነት ጥያቄን ምንነት? የአንድን ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄ መወሰን ያለበት ማነው? የሚወሰንበት ሥርዓት ምን መሆን አለበት? እነዚህ ሥርዓቶች ለወልቃይት ጉዳይ ያላቸው አግባብነት ምን ድረስ ነው? የሚሉ ጉዳዮችን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት በማድረግ ማሳየት ሲሆን፣ ጹሑፉ የወልቃትን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ይዳስሳል፡፡

 1. የማንነት ጥያቄ ምንነት

አንድ ብሔር በመሠረቱ በታሪክ ሒደት የተገነባ ማኅበረሰብ ሲሆን፣ ይህ  ማኅበረሰብ ሰፋ ያለ የጋራ ፀባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች፣ የሚገለገልበት የጋራ ቋንቋ፣ የሥነ ልቦና አንድነት፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና (አለን ብለው የሚያምኑ) እና በአብዛኛው የተያያዘ መልክዓ ምድራዊ አሠፋፈር እንደ ጋራ ባህርያት የሚታይበት ስለመሆኑ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እንቀጽ 39(5) ያስረዳል፡፡

የማንነት  ጉዳይ  ከብሔርነት ጋር የተቆራኘ ሲሆን፣ የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ ብሔርን መሠረት ያደረገ አስተዳደራዊ መዋቅር ከማቋቋምና ሌሎች ተያያዥ መብቶችን ከመጠየቅ መቅደም ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ማንነት ዕውቅና ከማግኘቱ ጋር ተያይዘው የሚገኙ ትሩፋቶች ናቸው፡፡ በኢትየጵያ ውስጥ የሚነሱ  የማንነት ጥያቄዎችን ምንነት ለመረዳት መነሻው አንቀጽ 39(5) ሲሆን በዋናነት  ብሔር ተብሎ ለመፈረጅ መሟላት ያለባቸውን መሥፈርቶች በመጥቀስ፣ አንድ ማኅበረሰብ እንደ ብሔር ዕውቅና እንዲሰጠው እና (ወይም) ከዚህ ጋር የተያያዙ ለምሳሌ የመገንጠል፣ ክልል የመመሥረት፣ የራስን አስተዳደራዊ መዋቅር የማቋቋም፣ የራስን ቋንቋንና ባህልን የመጠቀም፣ የማሳደግ፣ እንዲሁም በክልልና በፌዴራል የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ተገቢውን ውክልና የማግኘት መብቶች እንዲከበሩለት የሚያነሳው ጥያቄ የማንነት ጥያቄ ይባላል፡፡ ይህ እንደ ብሔር ዕውቅና ማግኘትና (ወይም) ከዚሁ ጋር የተያያዙ መብቶች እንዲከበሩ የሚቀርብ ጥያቄ የተለያየ መልክ ሊኖረው እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ይዘት በተለይም አንቀጽ 39፣ 47፣ 50(4) 52(2)(ሀ)፣ 62(3)፣ በተግባር ያጋጠሙ እውነታዎችንና በፌዴሬሽን ምክር ቤትና ክልል ምክር ቤቶች የተሰጡ ውሳኔዎችን መነሻ በማድረግ የማንነት ጥያቄዎችን ይዘት በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

ከመገንጠል ጥያቄ ጋር የሚያያዝ የማንነት ጥያቄ

  1. መገንጠል የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አካል ተደርጎ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ዕውቅና በመሰጠቱ፣ አንድ ብሔር ከፌዴራል ሥርዓቱ በመውጣት የራሱን ነፃ መንግሥት የመመሥረት መብቱን ለመጠቀም ከመገንጠል ጋር የተያያዘ የማንነት ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፡፡ አንቀጽ 39(4) አንድ ብሔር የሚያነሳውን የመገንጠል ጥያቄ ለመመለስ መከተል ስለሚገባው የአፈጻጸም ሥርዓት ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሠረት የክልል ምክር ቤቶች፣ የፌዴራል መንግሥቱ (ፌዴሬሽን ምክር ቤት) እና በሕዝበ ውሳኔ የሚሳተፈው ማኅበረሰብ የጋራ ሚና ይኖራቸዋል፡፡
  2. ክልል ከመመሥረት ጋር የሚያያዝ የማንነት ጥያቄ

በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚገኙባት ኢትዮጵያ በዘጠኝ ክልሎች የተዋቀረች ሲሆን፣ በአንድ ክልል ውስጥ በርካታ ብሔሮች እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡  ለምሳሌ በትግራይ ክልል ውስጥ ትግሬ፣ ኩናማና ኢሮብ ሲገኙ፣ በደቡብ ክልል ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ሐዲያና ሌሎች በርካታ ብሔሮች ይገኛሉ፡፡ ይኼን በመገንዘብ ይመስላል የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ከዘጠኙ ክልሎች በተጨማሪ ሌሎች ክልሎችን መመሥረት የሚቻልበትን አጋጣሚ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሳው የማንነት ጥያቄ አንድ የብሔር አማናዊ ማንነቱ ታውቆ በአንድ ክልል ውስጥ የሚኖር ማኅበረሰብ የራሱን ክልል ለማቋቋም የሚያቀርበው ሲሆን፣ ይኼም ብሔሩ በሚገኝበት ክልል ምክር ቤት ውሳኔና ይኼን ተከትሎ በሚዘጋጅ ሕዝበ ውሳኔ እንደሚፈጸም አንቀጽ 47(3) ያስረዳል፡፡  

  1. የራስን ዕድል በራስ ከመወስን ጋር የተያያዘ የማንነት ጥያቄ

ብሔር ለመባል የሚያስፈልጉትን በአንቀጽ 39(5) ላይ የተቀመጡ መሥፈርቶችን ያሟላሁ ስለሆነ፣ እንደ ብሔር ዕውቅና ተሰጥቶኝ የተለየ ማንነቴ ይታወቅልኝ፡፡ ከዚህም ጋር የተያያዙ ቋንቋና ባህልን የማሳደግ፣ የራስ አስተዳደር (ወረዳ፣ ልዩ ወረዳ፣ ዞንና ልዩ ዞን) የመመሥረት መብት ሊረጋገጥልኝ ይገባል በማለት የማንነት ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል፡፡ በተጨማሪም አንድ እንደ ብሔር ተለይቶ የታወቀ ማኅበረሰብ የወረዳ/ዞን  የመሆን የራስን ዕድል በራስ ከመወስን ጋር የተያያዙ የማንነት ጥያቄዎች ሊያነሳ ይችላል፡፡ በደቡብ ክልል የኮንሶ ሕዝብ የልዩ ወረዳ/ዞን የመሆን ጥያቄን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር ተያይዘው የሚነሱ አድሎዎችንና የመብት መሸራረፎችን በተመለከተ አንድ ማኅበረሰብ ጥያቄዎች ሊያነሳ ይችላል፡፡ እነዚህን ዓይነት ጥያቄዎች በአጠቃላይ የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን ጋር የተያያዙ የማንነት ጥያቄዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሔረ ማንነቴ ይታወቅልኝ በማለት የሚነሱ ጥያቄዎችን መስማት በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለአብነትም የስልጤን፣ የቅማንትን፣ የአርጎባን ሕዝብ የማንነት ጥያቄዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች የሚያሳዩት የማንነት ጥያቄ ያቀረበው ማኅበረሰብ በተለምዶው ከሚታወቅበት ማንነት በመውጣት የራሱን የተለየ አማናዊ ማንነትን ለማረጋገጥና ዕውቅና ለማግኘት ያቀረባቸው/የሚያቀርባቸው መሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ የስልጤና የቅማንትን የማንነት ጥያቄዎች ብንመለከት ‹‹እኔ ጉራጌ ሳልሆን ስልጤ ነኝ፤›› ‹‹አማራ ሳልሆን ቅማንት ነኝ፤›› በማለት አዲስ ብሔረ ማንነት ለማግኘት የቀረቡ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡

 1. የማንነት ጥያቄን ማን ይወስን?

ከመገንጠልና አዲስ ክልል ከመመሥረት አኳያ የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎችን ለመወሰን ሥልጣን ያላቸውን አካላት ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(4) እና 47(3) ላይ አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሠረት ከመገንጠል ጋር የተያዘው የማንነት ጥያቄ  በየደረጃው ያሉ ክልል ምክር ቤቶችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚኖራቸው ተሳትፎና በሕዝበ ውሳኔ ሊፈጸም እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡ ብሔረ ማንነቱ ታውቆ በአንድ ክልል ውስጥ የሚኖር ማኅበረሰብ የራሱን ክልል ለመመሥረት የሚያቀርበው ጥያቄ በክልል ምክር ቤቱ በኩል ዕልባት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡

ይሁንና የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን ጋር ተያይዞ የሚቀርበውን የማንነት ይታወቅልኝ (ዕውቅና ይሰጠኝ) ጥያቄዎችን መወሰን የማን ሥልጣን ነው? የሚለው በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ የስልጤ የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ በቀረበበት ወቅት (1990) ጥያቄውን ማን ይወስን? በምን ሥነ ሥርዓት ይወሰን? የሚለው ጉዳይ በጣም አከራካሪ እንደነበረ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ቃለ ጉባዔ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚያን ወቅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 52(2) (ሀ) እና 62(3) አጣምሮ በማየት የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄው በመጀመርያ ጉዳዩን ያነሳው ማኅበረሰብ በሚገኝበት ክልል ምክር ቤት መታየት ይኖርበታል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በክልል ምክር ቤቱ ቅር የተሰኝ አካል ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ እንደሚችልም ይኸው ውሳኔ ያስረዳል፡፡

ይህን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከር፣ ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር የወጣው አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 20 የራስን ዕድል በራስ ከመወስን ጋር የተያያዘ የማንነት ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከመቅረቡ በፊት በክልሉ ያሉ መፍትሔዎችን አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም ማንነቴ ይታወቅልኝ የሚለውን ጨምሮ የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን ጋር የተያያዘ የማንነት ጥያቄ በመጀመርያ ጉዳዩን ያነሳው ማኅበረሰብ በሚገኝበት ክልል ምክር ቤት መታየት ይኖርበታል፡፡

 1. የማንነት ጥያቄ የሚወሰንበት የሥነ ሥርዓት ሕግ

የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን ጋር በተያያዘ የሚቀርብ የማንነት ጥያቄ ለሚመለከተው ክልል ምክር ቤት በጽሑፍ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ የሚቀርበው ማመልከቻ ይዘት የጥያቄውን ዝርዝር ምንነት የሚያስረዳ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም ከኗሪው ወይም ከብሔረሰቡ ቢያንስ አምስት ከመቶ የሚሆነውን ሰው ስም፣ ፊርማና አድራሻ በአባሪነት በማያዝ ጥያቄው የሕዝብ/የብሔሩ መሆኑን ማሳየት ይኖርበታል፡፡ ጥያቄውን ለምክር ቤቱ የሚያቀርበው ግለሰብ ወይም ግለሰቦች ከሕዝብ/ከብሔሩ የተወከሉ ለመሆናቸው በቂ ማረጋገጫ ማቅረብ እንደሚኖርባቸው አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 21 ይደነግጋል፡፡ በዚህ መልኩ አቤቱታ የቀረበለት ምክር ቤት ጉዳዩን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መልስ መስጠት እንደሚገባው በዚሁ አዋጅ ላይ ተቀምጧል፡፡

 1. የወልቃይትና የጠ(ፀ)ገዴ የማንነት/ድንበር ጥያቄዎች ምንነት በአጭሩ 

የማንነት ጥያቄን ለመፍታት የተዘረጋው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ከዚህ በላይ የቀረበው ሲሆን፣ እነዚህን ድንጋጌዎች የወልቃት ጥያቄን ለመፍታት ያላቸውን ፋይዳ ከማየታችን በፊት የወልቃይት ጥያቄን ይዘት በአጭሩ መዳሰስ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

ወልቃይት በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሀገር ሥር የነበረ አካባቢ ሲሆን፣ ማኅበረሰቡ አማርኛ፣ ትግረኛና ዓረብኛ ይናገራል፡፡ የደርግ ሥርዓት መውደቅን ተከትሎ የፌዴራል ሥርዓት ሲዋቀር አብዛኛው ሕዝብ ‹‹ትግረኛ ተናጋሪ›› ነው በሚል  አካባቢው (ወልቃይት) ያለ ሕዝቡ ፈቃድ በትግራይ ክልል ሥር እንዲካለል ተደርጓል፡፡ ይኼን በመቃወም ከዚያን ወቅት ጀምሮ ቅሬታዎች የነበሩ ቢሆንም፣ ጥያቄው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ‹‹የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔረተኝነት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ›› ተዋቅሮ በተጠናከረ መልኩ ሊቀርብ ችሏል፡፡ 

የጥያቄው ይዘት የወልቃይት ሕዝብ ታሪኩ፣ ባህሉና ሥነ ልቦናዊ ትስስሩ ከአማራ ሕዝብ ጋር መሆኑ እየታወቀ ያለ ሕዝብ ፈቃድ ወልቃይት ወደ ትግራይ ክልል እንዲካለል መደረጉ አግባብ እንዳልነበር በመግለጽ፣ የወልቃይት ሕዝብ በአማራነቱ ታውቆ አከላለሉ እንዲስተካከል የሚጠይቅ ሲሆን፣ አቤቱታውም ለአማራ ክልል፣ ለትግራይ ክልልና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረበ ስለመሆኑ የኮሚቴው አባላት በተለያየ ወቅት ከሰጧቸው መግለጫዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ኮሚቴው እስከ ሃያ ሺሕ የሚደርስ የሕዝብ ፊርማ አሰባስቦ ያቀረበ መሆኑን በመግለጽ፣ በትግራይ ክልል በኩል ‹‹እናንተ የሕዝብ ተወካይ አይደላችሁም፤›› በሚል ለጉዳዩ መልስ ካለማግኘታቸው በተጨማሪ ማዋከብ፣ ማስፈራራትና አፈና የተፈጸመባቸው ስለመሆኑ የኮሚቴ አባላት ይገልጻሉ፡፡ 

ኮሚቴው ይኼንኑ በመግለጽ ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረበ ሲሆን፣ ምክር ቤቱም የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ጠቅሶ፣ በቅድሚያ በክልል የሚገኙ መፍትሔዎችን አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ በማስገንዘብ፣ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ ዕልባት እንዲሰጥ መጋቢት 26 ቀን  2008 ዓ.ም. በደብዳቤ ክልሉን አሳስቧል፡፡ ትግራይ ክልልም ‹‹ጉዳዩ የሕዝብ ጥያቄ አይደለም፣ የኮሚቴ አባላትም ሕጋዊነት የላቸውም፤›› በማለት ጉዳዩ እንዳልቀረበ በመቁጠር ነገሩን ችላ ያለው በመሆኑ ለጥያቄው መልስ ሳይሰጠው ቆይቷል፡፡ አማራ ክልልም አሁን ባለው ፌዴራላዊ ሥርዓት አካባቢው (ወልቃት) በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኝ መሆኑን በመገንዘብ በጉዳዩ ላይ ያቀረበው ምንም ዓይነት ኦፊሴላዊ ጥያቄ የለም፡፡ የወልቃት ጉዳይ ሙሉውን የሚመራው በኮሚቴው በኩል ነው/ነበር፡፡ 

ሁለተኛው ጉዳይ የጠ(ፀ)ገዴ የድንበር ውዝግብ ሲሆን፣ ይህ ጉዳይ የቀረበው በኮሚቴው በኩል አይደለም፡፡ የቀድሞው ጠገዴ ወረዳ 28 ቀበሌዎች ያሉት ሲሆን፣ የፌዴራል ሥርዓቱ ሲዋቀር ትግረኛ ተናጋሪ የሆኑት ቀበሌዎች ወደ ትግራይ፣ ቀሪዎቹ  ቀበሌዎች ደግሞ ወደ አማራ ክልል እንዲካለሉ ተደርገዋል፡፡ እዚህ መሀል ሁለት ቀበሌዎች ማለትም ግጨውና ጉቤ አከላለል ዙሪያ፣ ወደ አማራ ክልል ሊካለሉ ይገባል/አይገባም በሚል በሁለቱ ክልሎች መካከል ውዝግብ ሊፈጠር ችሏል፡፡ በተጨማሪም ማር – ዘነብ በመባል በሚታወቀው ቆላማ ለም መሬት ላይ ትግራይ ክልል  የይገባኛል ጥያቄ በማንሳቱ በክልሎቹ ወሰን መካከል አለመግባባት ሊፈጠር ችሏል፡፡ በእነዚህ ጠ(ፀ)ገዴና ማር ዘነብ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ በክልሎቹ በራሳቸው የተነሱ የወሰን አለመግባባትና የቦታ ይገባኛል ጥያቄዎች መሆናቸውን ከሁኔታዎችና ከተሰጡት መግለጫዎች መረዳት ይቻላል፡፡

 1. የወልቃይት ጥያቄ የሚፈታበት ሥርዓት፣ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ

የወልቃይት ጥያቄ የቀረበው በአማራ ክልል በኩል ቢሆን ኖሮ፣ ጉዳዩ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 መሠረት የሚፈታ፣ የክልሎችን ወሰን አከላለል ለውጥን የሚመለከት የድንበር ጥያቄ ብቻ ይሆን ነበር፡፡ አፈታቱም በሁለቱ ክልሎች የጋራ ስምምነት መሠረት ይሆናል፡፡ ይሁንና ይኼ ባለመሆኑና ጥያቄው የቀረበው በአካባቢው ማኅበረሰብ ወኪል በሆነው በወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔረተኝነት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ በኩል መሆኑ ጉዳዩን የማንነት ጥያቄ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ 

የወልቃይትን ጉዳይ ከጠ(ፀ)ገዴ በይዘቱ የሚለየው ነገር የለም፡፡ የጠ(ፀ)ገዴም ሆነ የማር ዘነብ የድንበር ጥያቄ በሁለቱ ክልሎች ስምምነት ካልተፈታ የሚመለሰው በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሠፋፈርን መሠረት ባደረገ ጥናት ወይም ሕዝበ ውሳኔ እንደሆነ ካለው የሕግ ማዕቀፍ መረዳት ይቻላል፡፡ ይኼም ብሔርን በዋናነት ቋንቋን መሠረት አድርጎ የሚፈጸም በመሆኑ አከራካሪ በሆኑት ቦታዎች የሚኖረው ማኅበረሰብ ትግሬ ነው ወይስ አማራ? የሚለውን ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የድንበሩ ጥያቄ የማንነት ጥያቄን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይሁንና በሁለቱ ጉዳዮች በይዘታቸው ተመሳሳይ ቢሆኑም የአማራ ክልል መንግሥት በወልቃት ላይ በይፋ ያቀረበው  የይገባኛል ጥያቄ የለም፡፡ ጥያቄው የተነሳው በማኅበረሰቡ ሲሆን የድንበር ማካለል ጉዳይ ደግሞ በሕዝብና በክልል መንግሥት መካካል ሊኖር አይችልም፡፡ በመሆኑም ማኅበረሰቡ ‹‹አማራ ስለሆንን ወደ አማራ ክልል ልንካለል ይገባል?›› በማለት ያቀረበው ጥያቄ በይዘቱ የድንበር አከላል ለውጥ ጥያቄ ቢሆንም የጥያቄ አቀራረቡ የወልቃይትን ጉዳይ  የማንነት ጥያቄ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህም ምክንያት የድንበር ጥያቄ የሆነውን የወልቃይትን ጉዳይ እንደ ማንነት ጥያቄ ለመፍታት የምንሄድበት መንገድና የምንከተለው ሥርዓት የራሱ የሆነ ችግር ይገጥመዋል፡፡ ለድንበር ጉዳይ የማንነት ጥያቄ አፈታት የሕግ ማዕቀፍን ተግባራዊ ማድረግ መፍትሔ አያመጣም፡፡  

ከዚህ በላይ እንደተገለጸው የወልቃይት ጉዳይ አቀራረቡ ጥያቄውን የማንነት ስላደረገው አፈታቱ በዚሁ አግባብ ያለሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ ወይም በሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ በትግራይ ክልል ምክር ቤት በኩል ሊፈታ እንደሚችል ይታመናል፡፡ ይሁንና እነዚህን በሕግ የተቀመጡ መፍትሔዎችን በአገራችን የተገነባው ዴሞክራሲ ካለበት ደረጃና አጠቃላይ ፖለቲካዊ ሁኔታ አንፃር ስንፈትሻቸው ለወልቃይት ጥያቄ መልስ ያመጣሉ ተብለው አይገመቱም፡፡ በመጀመርያ ትግራይ ክልል ጉዳዩ በወልቃይት ማኅበረሰብ እንደቀረበና ጥያቄውም ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው የሕዝብ ጥያቄ  አድርጎ ለመውሰድ ፍላጎቱ የለውም፡፡ ለዚህም ነው ሥነ ሥርዓታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ጥያቄውን ተቀብሎ ላለማየት ጥረቶች ሲደረጉ የሚስተዋለው፡፡ ‹‹ጥያቄው እስካሁን አልቀረበም፣ ሲቀርብልን እናያለን፤›› በማለት በክልሉ መስተዳድር የተሰጠውን መግለጫ ለአብነት መውሰድ ይቻላል፡፡ ይኼንንም የሚያደርጉት ከማንነት ጥያቄው ጀርባ ያለውን ‹‹ታሪክን የማስተካከል›› ፍላጎት በመገመት ይመስለኛል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው የድንበር አከላለል ያለቀለት ጉዳይ (A Settled Matter) ተደርጎ እንዲታሰብ ይፈልጋሉ፡፡

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ጥያቄውን ቢቀበለው እንኳን ጉዳዩን  የወልቃይት አካባቢ ለክልሉ ካለው ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታና ባለፉት 25 ዓመታት ከታየው ዴሞክራሲያዊ ቁርጠኝነት (Commitment for Democracy) አንፃር ክልል ምክር ቤቱ ነፃ፣ ገለልተኛና ሙያዊ በሆነ መልኩ ጉዳዩን አስጠንቶ ቀጥተኛ ባልሆነ የሕዝብ ተሳትፎ  ለጥያቄው ዕልባት ይሰጣል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ ጉዳዩ በሕዝበ ውሳኔ መሠረት ይፈታ ቢባልም ባለፉት 25 ዓመታት አካባቢው ከፍተኛ የሕዝብ እንቅስቃሴ (የሠፈራ ፕሮግራሞች፣ መፈናቀሎች) የተደረገበት በመሆኑ የሕዝበ ውሳኔ ውጤቱ ለችግሩ ፍትሐዊ የሆነ መፍትሔ ያመጣል ተብሎ አይገመትም፡፡ በአጠቃላይ የወልቃይትን ጉዳይ የማንነት ጥያቄ አድርጎ በመረዳት መፍትሔ ለማምጣት የምንከተለው መንገድ በችግሩ ዙሪያ ከመሽከርከር የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡  

 1. እና ምን ይደረግ? የማጠቃላያ ሐሳብ   

የወልቃይት ጉዳይ ምንም እንኳን አቀራረቡ የማንነት ጥያቄ ቢያደርገውም ይዘቱ  የድንበር ጉዳይ ነው፡፡ የወልቃይት ጉዳይ የድንበር ግጭት ነው፡፡ በአማራና በትግራይ ክልል መካከል ያለ የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ነው፡፡ በይዘቱ ጥያቄው በአማራ ክልል በኩል አለመቅረቡ ነው ወልቃይትን የማንነት ጥያቄ ያደረገው፡፡ በአማራና በትግራይ ክልል መካከል ያለው የክልል አከላለል ያለቀለት ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ምንም እንኳን ጥያቄው በአማራ ክልል በኩል ባይቀርብም፣ የወልቃይት ጥያቄ የድንበር ጉዳይ መሆኑን በመረዳት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46(2) እና 48 መሠረት በሁለቱ ክልሎች ስምምነት (Re-negotiation) ዕልባት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከዚህ በመለስ አቀራረቡን ብቻ በመከተል ወልቃይትን የማንነት ጥያቄ አድርጎ በመውሰድ የሚሰጥ ውሳኔ ችግሩን አይፈታውም፣ የሕዝቡንም ጥያቄ አይመልስም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...