በአባ ገንባው ዘቦሌ
የፖለቲካ በሉት፣ የአገር አስተዳደር፣ ወይም አገዛዝ፣ አንዳንድ ጊዜ በልጆ (ሕፃናት) ጨዋታ ይመስላል፡፡ ይህንን ተምሳሌታዊ ንፅፅር ያወጋኝ መሬት ይቅለለውና ባልንጀሬ በዓሉ ግርማ ነበር፡፡ ወጉ እንዲህ ነበር፡፡
ከ44 ዓመታት በፊት በ1966 ዓ.ም. ሕዝባዊው የኢትዮጵያ አብዮት ፈንድቶ፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላማዊ አመፅ ለአዲስ ሥርዓት ምሥረታ ይታገል በነበረበት ጊዜ፣ ከመለዮ ለባሽ ልዩ ልዩ ክፍለ ጦሮችና ብርጌዶች ተውጣጥቶ፣ የመንግሥትን መንበረ ሥልጣን ዕርካብ ለመርገጥ ተቃርቦ የነበረው ደርግ(ኮሚቴ) የሕዝባዊ አመፅ አስተባባሪ ነበር፡፡ በአስተባባሪነቱም ለጭቁኖች የቆመ ኃይል መሆኑን በይፋ ያውጅ ነበር፡፡
የጭቁን ሴቶችን መብት ማስከበር በተመለከተ ፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ እንዲሠራ የደርግ ማስታወቂያ ኮሚቴ ለመገናኛ ብዙኃን አመራር ይሰጣል፡፡የቤት ሠራተኞች(ገረዶች) ጉዳይ ቅድሚያ ይሰጠው ተባለና ‘የቤት ሠራተኛና ቀጣሪዋ የቤት እመቤት እኩል መብት አላቸው’ በሚል ርዕስ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ መግለጫ እንዲያዘጋጅ ጓድ በዓሉ ግርማ ይታዘዛል፡፡
ኅላፊነት የሚሰማው፣ ሥልጡኑ የሙያው ሰው – ጋዜጠኛ በዓሉ፣ ‹‹ይህማ እንዴት ይሆናል?! የመብትን ጥያቄ ወደ አላስፈላጊ ጠርዝ መግፋት ስለሚሆን ይታሰብበት?›› ይላቸዋል፡፡
‹‹ጓድ በዓሉ አንተ ያለብህ የታዘዝከውን መፈጸም ነው፤›› ይባልና ወደ ቢሮው ይመለሳል፡፡ በማግሥቱ ጽፎ ያቀረበላቸውን መግለጫ፣ እነሱ(ደርጎች) የድርሻቸውን ይበልጥ አስጩኽው በመገናኛ ብዙኃን እንዲታወጅና ልዩ ፕሮግራም እንዲሠራበት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በኩል ይተላለፋል፡፡
በዚያኑ ዕለት ከቀኑ ስድስት ሰዓት፣ ‹‹ከደርግ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ›› ተብሎ በቴሌቪዥንና በራዲዮ ይለቀቃል፡፡ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ የዕሪታ ማዕበል ይነሳል፡፡ አንዳንድ የደርግ አባላት ሚስቶች ጭምር እሪ ይላሉ፡፡ ገረዶች ለእመቤቶቻቸው ባለ መታዘዝ ‹‹አንቺም ሰው… እኔም ሰው …›› እስከ መባባል የደረሱም ነበሩ፡፡
በማግሥቱ ጧት ጓድ በዓሉ ደርግ ማስታወቂያ ቢሮ ይጠራና በቤት ሠራተኞችና በቤት እመቤቶች መካከል የቅራኔ ሞገድ ማስታገሻ (ማስተባበያ) ጽሑፍ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ ይታዘዛል፡፡ ያላንዳች እሰጥ አገባ በዓሉ እንደመሰለው ማስተባበያውን ጽፎ ያቀርብላቸውና በመገናኛ ብዙኃን ተደጋግሞ እንዲታወጅ፣ ተቃውሞውን ማርገቢያ አስተያየትና ልዩ ፕሮግራም እንዲሠራበት ይታዘዛል፡፡
ይህ የፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ቅሌት በተካሄደበት ምሽት ከሥራ ሰዓት ውጪ ደጃች ውቤ ሠፈር ‘መዲና ግሮሰሪ’ ደጃፍ፣ በጳውሎስ ኞኞ መኪና አምስት የሥራና የመለኪያም ጓደኛሞች በመጠጥ የታጀበ ወሬያችንን ስንደልቅ፣ ከአምስታችን አንዱ የነበረው ጓድ በዓሉ ከዚህ በላይ የተነገረውን ቅሌት ግሩም በሆነ ምሳሌ አሸግኖ አወጋን፡፡ ምሳሌው፣ ‹‹ደርግና አንዳንድ ሞገደኛ ሕፃናት ይመሳሰላሉ፡፡ ሕፃናት አቧራ እያቦነኑ እንዳይጫወቱ ሲከለክሏቸው እሺ አይሉም፡፡ ማቡነናቸውን ይቀጥላሉ፡፡ አቧራው ዓይናቸው ውስጥ ሲገባ፣ በአቧራ እንዳይጫወቱ ሲመክራቸው የነበረውን ሰው ‘እባክህ አቧራ ዓይኔ ውስጥ ገባ፣ እፍ በልልኝ’ በማለት ያስቸግራል፡፡››
‹‹ጓዶች! አለ በዓሉ››፣ ‹‹የገረዶች መብት ዕወጃና የዕወጃው ማስተባበያ የፖለቲካ አቧራ ማቡነን ይቅርብህ ሲባል አልሰማም ብሎ፣ ማቡነኑን ቀጥሎ፣ ማጣፊያው ያጠረበት ድኩም ፖለቲከኛን ያስታውሰኛል፤›› በማለት ወጋችንን አደራው፡፡
እስቲ ያንን የ44 ዓመታት የፖለቲካ ውዥንብር ከወቅቱ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ በንፅፅር እንዳስሰው፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ማጠፊያው ያጠረው የፖለቲካ ቀውስ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ወደ መፈታተን ደረጃ የተሸጋገረው ኢሕአዴግ፣ ‹‹ተው! ካለማስተዋል የወረወሩት ድንጋይ ተመልሶ ራስ ላይ›› እንዳይሆን በማለት የተለገሰውን ምክር ባለመቀበል፣ ሲያቦን የቆየው የፖለቲካ አቧራ ዳፋ መሆኑን ኢሕአዴግ ራሱ ያልካደው ሀቅ ሆኗል፡፡
በመንግሥታዊ መንበረ ሥልጣን ላይ ተቀምጦ አገርንና ሕዝብን መምራት ከባድ፣ እጅግ ከባድ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህን አባባል በተመለከተ ብዙዎች የምንጋራቸውን አንድ አስረጂ ልጥቀስ፡፡
‹‹እግዚአብሔር አምላክ፣ ሰለሞንን ‘እንድሰጥህ የምትፈልገውን ሁሉ ለምን’ ይለዋል፡፡
ሰለሞንም እንዲህ ሲል መለሰ፡፡ ‘አባቴ ዳዊት በፅድቅና በቅን ልቦና በፊትህ ስለተመላለሰ፣ ለባሪያህ ታላቅነት አሳይተኽዋል፡፡ ይህ ታላቅ ቸርነት እንዲቀጥል፣— በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተኽዋል፡፡
‘እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! ባሪያህ! በአባቴ እግር ተተክቼ እንድነግሥ አድርገሀል፡፡ እኔ ግን ገና ትንሽ ልጅ ስለ ሆንኩ፣ መውጫና መግቢያውን አላውቅም፡፡ ባሪያህ አንተ በመረጥከው፣ ከብዛቱ የተነሳ ሊቆጠር በማይችል ታላቅ ሕዝብ መካከል ይገኛል፡፡ ለዚህ መልካሙንና ክፉውን በመለየት ሕዝብህን ማስተዳደር እንዲችል ለባሪያህ አስተዋይ ልብ ስጠው፡፡ አለዚያማ ይህን ታላቅ ሕዝብ ማን ሊያስተዳድር ይችላል?››
ሰለሞን ይህንን በመለመኑ ጌታ ደስ አለው፡፡ “— ለራስህ ረጅም ዕድሜ፣ ብልፅግና እንድታገኝ፣ ወይም ጠላቶችህ እንዲጠፉልህ ሳይሆን፣ በትክክል ማስተዳደር እንድትችል ማስተዋልን ስለጠየቅህ፣ ይህንኑ አደርግልሀለሁ፡፡ ማንም የሚያገኘውን ጥበብና አስተዋይ ልቦና እሰጥሀለሁ፤›› በማለት እግዚአብሔር ሰለሞንን ባረከው፡፡ በዋጋ የማይተመን ታላቅ በረከት፡፡
ውድ አንባብያን በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበረ ሥልጣን ላይ የተሰየሙትን የዶ/ር ዓብይ አህመድ አመራርና አሠራር ስከታተል፣ እኚህ ሰው ይህን ታላቅ ሥልጣን የተቀዳጁት ሰለሞንን ኮርጀው ይሆን እንዴ የሚል ጥያቄ አጫረብኝ፡፡ በነገራችን ላይ ኩረጃ የማይፈቀደው በፈተና ላይ ላለ ተማሪ ብቻ ነው፡፡
የእስካሁን አነጋገራቸውን፣ አመራራቸውንና አሠራራቸውን፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ (ሁሉም አላልኩም፡፡ ጥቂት ጥቅማቸው የነጠፈባቸውና ፈር የለቀቀ አገዛዛቸው የታገተባቸው ወገኖች አይጋሩ ይሆናል የሚል ሥጋት አድሮብኝ ነው) ‹‹ይበል! ይበል!›› በማለት ቡራኬውን ሰጥቷል፡፡ እኔም ከእነዚህ መካከል አንዱ ሆኛለሁ፡፡
የ82 ዓመት አዛውንት ብሆንም፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ‹‹— ኢትዮጵያ አገራችን የሁላችን መሆኗን ተገንዝበን፣ የሁሉም ድምፅ የሚሰማበት፣ ሁሉንም የሚያሳትፍ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባቱን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን፤›› በማለት ያስተላለፉትን ጥሪ በመቀበል እኔም እንዳቅሜ እሠለፋለሁ፡፡ መቸም ሰው እንዳቅሙ እህል እንደ ቅርሙ ነውና፡፡
ይህ እንዳቅም ስለአገር የመሠለፍ በጎ ፈቃድ ከ40 ዓመታት በፊት አንድ የ85 ዓመት አዛውንት፣ በአንድ ሕዝባዊ ሸንጎ ላይ አስተንክረው የገቡትን ቃል ኪዳን አስታወሰኝ፡፡ ባጭሩ ላካፍላችሁ፡፡ ሸንጎው በወቅቱ ይካሄድ የነበረውን የሰሜን ግንባር ጦርነት ለማጠናከር የተደረገ ስብሰባ ነበር፡፡
አዛውንቱ ጥጥ የመሰለ ሽበታቸው ያጎናፀፋቸው ግርማ ሞገስ የታዳሚውን ዓይን መሳቡን ካረጋገጡ በኋላ፣ ባሉበት ቆነጥነጥ አሉና እንዲህ አሉ፡፡ ‹‹– እኔ እንደምታዩኝ የዓይን ብርሃኔ ደክሟል፣ ጉልበቴ ዝሏል፣ ክንዴ ልሟል፣ በጠመንጃ ተኩሼ ጠላትን የመግደል ብቃት የለኝም፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ እዘምታለሁ! አዎ እዘምታለሁ! የምዘምተው በደጀንነት ሳይሆን በአፍላ ቀማሽ ግንባር ቀዳሚ ተዋጊ በመሆን ነው፡፡
‹‹ከጠላት የሚተኮስ ጥይት በእኔ አካል ላይ እንዲያርፍ – ወገኔ ከመገደል እንዲተርፍ አደርጋለሁ፡፡ በዚህ ዓይነት የተቀደሰ መስዋዕትነት ለአገሬና ለወገኔ ያለኝን ፍቅር አንድ ጊዜ እንደ ገና ላስመስክር!›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ጓድ ሊቀመንበር ጥያቄህን ተቀብለናል፣ ትዘምታለህ ካላችሁኝ አልቀመጥም፤›› ብለው ቆሙ፡፡
እኔ የሸንጎው ሰብሳቢና ታዳሚውም ጥያቄያቸውን በእንባ አጅበን ተቀበልን፡፡ የዕለቱ ሸንጎ ከተጠበቀው አሥር እጥፍ በላይ ውጤት የተመዘገበበት ሆነ፡፡ የአዛውንቱ የተሳትፎ በጎ ፈቃድ እንደ አቅም ሳይሆን፣ ከአቅም በላይ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የእንደነዚህ ዓይነት ዜጎች አገር ነበረች፣ ባይበዙም ዛሬም ነች፡፡
በሪፖርተር ጋዜጣ ተደጋግሞ ያለ ሐኬት እንደ ተነገረው፣ በተለይም መጋቢት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ርዕስ አንቀጽ ውስጥ ‹‹—የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሩን ነፃነት ለማስከበር ያደረጋቸው ተጋድሎዎች፣ ለመብቱና ለነፃነቱ ያደረጋቸው ፍልሚያዎች፣ የማንነትና የሐሳብ ብዝኃነት ባለመስተናገዳቸው ሳቢያ የተፈጠሩ ግጭቶች፣ እንደዚሁም፣ ኢትዮጵያ ከሥልጣኔዋ ተለይታ ለድህነትና ለተመፅዋችነት አሳፋሪ ውርደት የታሪኳ አካል ናቸው—-›› የሚለው መሪ ሐረግ፣ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን የ85 ዓመት አዛውንት ኢትዮጵያዊ ደግነት፣ ጨዋነት፣ ማለፊያ ሰብዕና፣ ቆራጥነትና ደፋርነት ያረጋግጣል፡፡
ይህን ውርስና ቅርፅ መፈክር አድርገን ዛሬም እንደ ትናንት ኢትዮጵያችንን እንታደጋት፡፡ በሐዘን በአርምሞ ያሳለፍናቸውን የኢሕአዴግ አገዛዝ ዓመታት በቂም በቀል ሳይሆን በይቅርባይነት እያስታወስን፣ የታደሰው ኢሕአዴግ እያመቻቸ ባለው የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ግንባታ እንደየአቅማችን እንሳተፍ፡፡ ከጭፍን ጥላቻ ወይም ከከንቱ ውዳሴ፣ ከቂም በቀል፣ ከዘረኝነትና ከስግብግብነት ራሳችንን ብሎም ማኅበራሰባችንን ማፅዳት የተሃድሶ ተሳትፏችን ቀዳሚ የቤት ሥራ መሆን እንዳለበት አንዘንጋ፡፡ ይህን ካልኩ ዘንዳ፣ የተሃድሶው አመራርና አሠራር ምን ምንን እንዴት? ያካትት በሚለው ጭብጥ ላይ የድርሻዬን አንዳንድ ሐሳብ ልፈንጥቅ፡፡
በመወራረድ ላይ ስላለው የኢሕአዴግ የ27 ዓመታት አገዛዝ የፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ ዕድገትና ልማት ትርፍና ኪሳራ፣ ወደ ኋላ ተመልሼ የማጠነጥነው ዝክረ ታሪክ የለኝም፡፡ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ፣ ይህን የትርፍና ኪሳራ(የአሠራር አመራር ጥንካሬና ድክመት) ሥሌት ኢሕአዴደግ ራሱ፣ ራሱን በራሱ ገምግሞ (ኦዲት አድርጎ) የደረሰበትን ውጤት እየተናገረ ነው፡፡ ከመንገርም በላይ ስለድክመቱ ይቅርታ ጠይቋል፡፡
አንዳንድ ወገኖች፣ የኢሕአዴግን ይቅርታ ጥየቃ፣ ‹‹ሰይጣን ቢያረምም መንፈስ ቅዱስ ይመስላል›› ይላሉ፡፡ ይህን የጨለምተኞች አቋም አልጋራም፡፡ በአንፃሩ ኢሕአዴግ የችግሩ አካል እንደ ነበር ሁሉ፣ የመፍትሔውም ገንቢ ኃይል እንዲሆን ያልተቆጠበ ድጋፍና ትብብር ሊደረግለት ይገባል፡፡ አዎ! የተነጣጠለ ግድግዳ ቤት አይሆንምና የሕይወት መስዋዕትነት፣ የአካል ጉዳትና በቢሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ውድመት የተከፈለበት የሕዝብ አመፅ ውጤት ትንሣዔ ኢትዮጵያ ላይ የፈነጠቀው ብርሃን ቦግ እንዲል፣ የእያንዳንዱ ቅን ኢትዮጵያዊና እንዲሁም ገዥው ፓርቲና መንግሥት ተነጋግረው፣ ተደማምጠውና ተስማምተው መሥራትን ይጠይቃል፡፡
የተናጋውና ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት የሰላም ጥያቄ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን፣ በሕዝብም በመንግሥትም ግንዛቤ ማግኘቱ ይታያል፡፡ ከዚህ ጋር ጎን ለጎን መቀጠል ያለበት ዓብይ የቤት ሥራ፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ሥር ሰድዶ እርስ በርስ ሲያጠላልፋቸው የቆየውን አንጀኝነት በሰከነና ግልጥ – ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ፍትጊያ አፅድቶ፣ ‹‹ሲመክር ብርቱ፣ ለራሱ ከንቱ›› በመባል ሲታማ የነበረበትን ቅፅል ስም አስፍቆ፣ የሕዝብን ተዓማኒነት ለማትረፍ መቻል ይኖርበታል፡፡ አዎ ኢሕአዴግ አንዳንድ ሰው ተናጋሪ አንዳንድ ልብ ነባቢ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡
በዚህ እውነተኛና ጥልቅ የተሃድሶ ዘመቻ እነማን እስከ መቼ? እንዴት? በምን ደረጃ ይሳተፉ? የሚሉት ጥያቄዎች በዋዛ መታየት የለባቸውም፡፡ ‹‹ጅብ አህያ ጠብቅ›› ሲባል እምቢ አይልም፡፡ ትዕዛዙን እንደ ተቀበለ፣ ‹‹አህያው ቢጠፋብኝስ?›› የሚል ጥያቄ ያቀርባል አሉ፡፡
እስከ ዛሬ የበግ ለምድ የተጀቦኑ ተኩላዎች በበግ ጉሮኖ ውስጥ በመግባት የሠሩትን ሠርተዋል፡፡ የተሃድሶው ዘመቻ ሥምሪት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የዘረኝነት፣ የትምክህተኝነትና የጠባብነት ንክኪ ካላቸው ግለሰቦች ማፅዳቱ፣ ሌላው ዓብይ ተግባር ነው፡፡
ብሔራዊ ዕርቅን፣ የመልካም አስተዳደር ችግርን፣ ፍትሐዊ የአገር ሀብት ክፍፍልን፣ የማንነት ጥያቄን ማስተናገድንና የፖለቲካ ምኅንዳር ስፋትንና አሳታፊነትን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን የጀመርሁት የመረጃ ቅርሚያ እንደ ተሳካልኝ ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡ ለጊዜው ከመሰናበቴ በፊት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ዓሊ የተለየ ትኩረት ማድረግ ስላለባቸው ጥቂት፣ ነገር ግን ዓበይት ጭብጦችን እጠቁማቸው ዘንድ ይፈቀድልኝ፡፡
- አመሥጋኝ አማሳኝ ነውና በከንቱ ውዳሴ እንዳትታለል አደራ፡፡ ምሥጋና አያስፈልግም ማለቴ እንዳልሆነ ትረዳኛለህ፡፡
- ሌላው አትቸኩል፡፡ ሮም በአንድ ዠንበር አልቆረቆረችም፡፡ አንተም ኃላፊነትህንና የሥራ ድርሻህን በአንድ ዠንበር፣ በአንድ ሳምንት፣ በአንድ ወር፣ በአንድ መንፈቅ፣ በአንድ ዓመትና ከዚያም በላይ በሆነ ጊዜ ተምነህ፣ ለክተህና አቅደህ ሥራ፡፡
- እኛም መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማ ያደረግከውን ግሩም ድንቅ ንግግር በእንባ አጅበን ያዳመጥንህ ወገኖችህ፣ አቅም በፈቀደው ልክ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም ባለፍ (Byond The Call Of Duty) ቀበቷችንና መቀነታችንን አጥብቀን እያገዝን፣ ውጤቱን በኢዮብ ትዕግሥት እንጠብቃለን፡፡
- ‘የቸኮለ አፍሶ ለቀመ’ በሚሉ ጨለምተኞች ከንቱ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ እንዳትሆን አደራ፡፡
- ዶ/ር ዓብይ አህመድ ዓሊ የኢትዮጵያ፣ እንዲያውም የአፍሪክ ባራክ ሁሴን ኦባማ መሲህ (Redeemer) እስከመባል ተግባርን በጥበብ አከናውን፡፡ንበርንትወinion
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡