ኢዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ
በኢኮሚክስ ሙያ መስክ የካበተ ልምድና ተሞክሮ ያላቸውና በማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያነታቸው የሚታወቁት ኢዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ በፋይናስ መስክም የዓመታት ልምድና ዕውቀቱ አላቸው፡፡ ኢኮኖሚስቱ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ከመንግሥት የአምስት ዓመቱ ዕቅዶች አፈጻጸም ጀምሮ ስለዋጋ ግሽበት፣ ስለውጭ ምንዛሪ እጥረትና መንግሥት የምንዛሪ ተመን ማሻሻያ እንዲያውጅ ስለተገደደባቸው ችግሮች፣ በግብርናና በኢንዱስትሪ መካከል እንዲኖር ይገባው ስለነበረው ትስስር፣ የመንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ መሪም የበላይም ሆኖ ስለዘለቀባቸው ምክንያቶችና ሌሎችም መሠረታዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሙያዊ እሳቤና ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ቃለ ምልልስ የተንፀባረቀው ሐሳብ በግላቸው የሰጡት እንጂ፣ የሚሠሩበትን ተቋምም ሆነ ተቋማት እንደማይወክል በማሳሰብ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸው ትንታኔዎች እንደሚከተለው ተጠናክረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት የሚከተለው የልማታዊ መንግሥት አካሄድ የግል ዘርፉን አዳክሟል፣ ድህነትን በበቂ ሁኔታ የሚቀንስ የሥራ ዕድል አልፈጠረም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶ/ር ኢዮብ፡- በማንኛውም አገር ውስጥ መንግሥት ኢኮኖሚውን የመምራትና የማሳደግ ሚና አለው፡፡ መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ሚና የሚወስነው ኢኮኖሚው የሚገኝበት ደረጃ ነው፡፡ በዓለም ላይ የሚገኙ ሁሉም መንግሥታት የመሪነት ሚና ይዘው ነው ለኢኮኖሚያቸው ማደግ መሠረት የጣሉት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ አገሪቱ ሰፊ የልማት ጉድለት ካለባቸው አገሮች ውስጥ ትመደባለች፡፡ በተለያዩ የመንግሥት ሥርዓቶች ወቅት ሥር የሰደደው የሕዝብ ድህነት ሊቀንስ አልቻለም፡፡ ይህ መንግሥት ግን በመጀመሪያዎቹ አሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ የተከተለው ደሃ ተኮር የተባለው ስትራቴጂ ድህነትን ከመቅረፍና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ከማምጣት አኳያ አቅሙ ደካማ ነበር፡፡ መንግሥት አሁን እየተከተለ ያለው የልማታዊ መንግሥት አካሄድ እንደ ስትራቴጂ ሲታይ ትክክልና ተገቢነት ያለው ነው፡፡ ምክንያቱም ስትራቴጂው ድህነትን ለመቀነስና ጠንካራ አቅም ያለው ኢንዱስትሪ ለመፍጠር በማቀዱ ነው፡፡ በእርግጥ አከራካሪ ሊሆን የሚችለውና እየሆነ የመጣውም የመንግሥት የመሪነት ሚና እስከ ምን ይዘልቃል? የግሉ ዘርፍ ማዕከላዊ ሥፍራውን የሚይዘው መቼ ነው? መቼ ነው መንግሥት የመሪነት ቦታውን ለቆ የደጋፊነት ሚና ላይ የሚያተኩረው? የሚሉት ጥያቄዎች ስለሚነሱ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት እንከተል ቢባል፣ መጀመሪያ ገበያው መኖር አለበት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ገበያውን የሚያንቀሳቅሰው የገበያ ኃይል ወይም የግሉ ዘርፍ መኖር አለበት፡፡ ነፃ የገበያ ሥርዓት ለመፍጠር ምርትና የልማት ምሰሶዎች በሌሉበት ገበያ እንፍጠር ማለት ‘መጀመርያ ተኩስ ከዚያ ዒላማህን ፈልግ’ (First shoot then find the target) እንደ ማለት ነው፡፡ ሌላው ስትራቴጂው ድህነትን የሚቀንስ አይደለም ከተባለ፣ ነፃ ገበያ በሌለበት ከዚህ የተሻለ ስትራቴጂ ምን አለና ነው? የሚል ጥያቄ ያመጣል፡፡ መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ ትምህርት ቤትና የመሳሰሉት ድህነትን ለመቀነስ ወሳኝ ሚና ያላቸውን የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የግሉ ዘርፍ ሳይሆን መንግሥት የሚገነባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ስትራቴጂ ድህነትን ከመቀነስ አኳያ ውጤት የለውም ማለት በንድፈ ሐሳብም ሆነ በእውነታ ደረጃ ሲታይ አያስኬድም፡፡ ከልማት ስትራቴጂው ውጪ የሚቀር ነገር ቢኖር ‘የተራበን አጉርሱ፣ የታረዘን አልብሱ’ የሚለው የእማሆይ ቴሬዛ ስትራቴጂ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሞራል አኳያ ካልሆነ አዋጭ የድህነት መቀነሻ ዘዴ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም እንደተጠበቀው አልሆነም፡፡ የሁለተኛው ዕቅድም እንደታሰበው ይፈጸማል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በአጠቃላይ በዕቅዶቹ ላይ ምን ዓይነት አስተያየት አለዎት?
ዶ/ር ኢዮብ፡- ይህንን ጥያቄ በተሻለ ሊመልሱ የሚችሉት ዕቅዱን እንዲያስፈጽሙና እንዲከታተሉ የተሰየሙ ሰዎች ናቸው፡፡ መረጃውም ስለሌለኝ ስለአፈጻጸሙ መናገር አልችልም፡፡ ሆኖም በዕቅዶቹ ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተወጥነው የተሳኩ፣ በሁለተኛውም ዕቅድ እንደዚሁ የተገነቡና ወደ ሥራ የገቡ በዓይን የሚታዩ ተጨባጭ ነገሮች አሉ፡፡ ስላልተሳኩት ወይም በተለየ መንገድ ቢፈጸሙ ይሻል ነበር ስለመባሉ የዕቅዱ ክፍሎችና አፈጻጸማቸው መናገር ይችላሉ፡፡ አንድን ስትራቴጂ ስትከተል ወሳኙ ነገር ስትራቴጂውን ወደ ዕቅድነት፣ ዕቅዱንም ወደ ፕሮግራምነት፣ ፕሮግራሙን ወደ ፕሮጀክትነት የሚለውጥ የማስፈጸም አቅምና አደረጃጀት ሊኖርህ ይገባል፡፡ ፕሮጀክቶቹም በተመደበላቸው በጀትና በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሊጠናቀቁ እንደሚችሉ ማረጋገጫ የሚሰጥ የቁጥጥርና የክትትል ሥልት ሊኖርህ ይገባል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያነት የሚውል በቂ የገንዘብ ምንጭም ሊኖር ይገባል፡፡ እንግዲህ ይህን ስል የምትሠራቸውን ሥራዎች ቅደም ተከተል በመስጠት ዒላማ ብቻ ሳይሆን እንዴትና በማን፣ በምን ያህል ወጪ ይሠራሉ ብለህ በዝርዝር የማስፈጸሚያ ዕቅድ ሊኖርህ ይገባል፡፡ እስካሁን ያየናቸው የዕቅዶቹ ዳራዎች የሰፉ፣ የተለጠጡና አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ ሳይኖር የታቀዱ፣ የፈጻሚዎቹ አቅምና አደረጃጀት ደካማ በሆነበትና ችላ በተባለበት ሁኔታ ውስጥ እንዲፈጸሙ የታሰቡ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች በቅንነት ሊሳኩ ይችላሉ ተብለው የተጀመሩ ወይም የታቀዱ እንጂ፣ ውስጣዊና ውጫዊ የገንዘብም ሆነ የማስፈጸም አቅም ታይቶ የተጀመሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ አዋጭነታቸው በሚገባ ያልተፈተሹ ናቸው፡፡ በመሆኑም በመጀመሪያው ዕቅድ የታዩ ችግሮች አሁንም እየተንከባለሉ በመሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለሁለተኛው ዕቅድ ካነሳን የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደ ቀድሞው ዕቅድ የሌለው፣ ችግሮችን ለመለየትና ለማወቅ ዕይታው ደካማ የሆነበት ነው፡፡ ምናልባት ሌሎች ጉዳዮች የአመራሩን ትኩረትና ጊዜ በመውሰዳቸው ይመስለኛል ይህ የሆነው፡፡
ሪፖርተር፡- በተሻለ ሁኔታ ቢፈጸሙ የበለጠ ውጤታማ ይሆኑ ነበር ስላሉት ነገር ቢያብራሩልን?
ዶ/ር ኢዮብ፡- የማስፈጸም፣ የመፈጸምና የመከታተል፣ በቂ የገንዘብ አቅም በሚገባ ባልተሟላበት ሁኔታ ውስጥ ነው በአንድ ጊዜ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንዲፈጸሙ የተፈለገው፡፡ ከዚህ ይልቅ አንዳንዶቹን ፕሮጀክቶች ልምድና አቅም ያላቸው የውጭ ድርጅቶች ቢያከናውኗቸው የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጎን ለጎን እየተማሩባቸው ዕውቀት እያገኙ ቢሄዱ፣ ሌሎቹን ፕሮጀክቶች ደግሞ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በጥምረት ቢሠሯቸው፣ ወደፊት ዕውቀቱም ልምዱም ሲኖር የአገር ውስጥ ኩባንያዎች መሥራት ቢጀምሯቸው የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ይህ ግን በአገር ውስጥ አቅም የሚሠራው እየተሠራ ማለት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ፕሮጀክቶቹን በአመዛኙ መሥራት የተፈለገው በብድር ገንዘብ ነው፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ፋይናንስ አፈላልገው እንዲገቡ ነበር የተፈለገው፡፡ ይህ አካሄድ ግን አንደኛው አማራጭ እንጂ ብቸኛው አይደለም፡፡ አገሪቱ ዕዳ ሳይበዛባት በሌሎች የፋይናንስ ዘዴዎች ብዙ ፕሮጀክቶችን መገንባት ይቻል ነበር፡፡ ለምሳሌ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ወይም ‹‹ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርነሺፕ›› በሚባለው፣ በእሽሙር ወይም በ‹‹ጆይንት ቬንቸር››፣ በ‹‹ቢዩልድ ኦፐሬት ትራንስፈር››፣ ወዘተ. በርካታ አማራጮች ነበሩ፡፡ በግብርናውም በኢንዱስትሪውም የአገር ውስጥ ባለሀብት እንዲሳተፍ በማበረታታት የተሻለ ውጤት ሊገኝ ይችል ነበር፡፡ ለአብነት ያህል ስለሰፋፊ እርሻዎች የተባለውን አካሄድ ተመልከት፡፡ ውጤቱ ዜሮ ነው፡፡ ጨርቃ ጨርቅ ዘርፉን ውሰድ፣ ስንቱ ፋብሪካ ተዘግቷል፡፡ እነዚህ በሙሉ የውጭው ባለሀብት ተዓምር ይሠራል ተብለው የተሰጡ ነበሩ፡፡ በግብርናና በኢንዱስትሪ ጥምረት የመፍጠር ሁናቴ በዕቅዶቹ ውስጥ ቢኖርም በተግባር የታየው ግን በጣም አናሳ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የዕቅዶቹ ትኩረት መንገድ ከመዘርጋት፣ ግድብ ከመገንባት ባለፈ በሁለቱ ዘርፎች መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር ትኩረት መስጠት ተገቢ ይሆን ነበር፡፡ ኢንዱስትሪው ግብርናውን እያነሳ ካልሄደ የሚኖረው የኢንዱስትሪ ጉዞ አርቲፊሻል እንዳይሆን ያሠጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ሕዝቡ ስለሚያነሳው የዋጋ ግሽበት ጥያቄ እንነጋገር፡፡ በኢትዮጵያ በእርስዎ ዕይታ የዋጋ ግሽበት መቀስቀሱና ተባብሶ የመቀጠሉ መሠረታዊ ምክንያት ምንድነው?
ዶ/ር ኢዮብ፡- የዋጋ ግሽበቱ በተለይም በቋሚ ደመወዝና ጡረታ ገቢ የሚተዳደረውን የኅብረተሰብ ክፍል ክፉኛ እየተፈታተነው ይገኛል፡፡ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማለዘብ እየታገለ ቢሆንም ውጤቱ የተፈለገውን ያህል አልሆነም፡፡ በእኔ እምነት ለዋጋ ግሽበት መሠረታዊ ምንጩ የኢኮኖሚ ሞዴሉ ነው፡፡ ይህንን ላስረዳ፡፡ ለአንድ ኢኮኖሚ መነሻ መሠረቱ የመሠረተ ልማት መኖር ወይም መስፋፋት ነው፡፡ ኢኮኖሚስቶቹ ‹‹ካፒታል ፎርሜሽን›› ብለው ይጠሩታል፡፡ እነዚህ ለልማት ቁልፍ የሆኑ የመሠረተ ልማት ጉድለቶች ባሉባቸው የታዳጊ አገሮች እንደሚታየው መንግሥት ጉድለቱን ለመቀነስና ልማትን ለማፋጠን በታክስ፣ በብድር፣ በአገር ውስጥ ቁጠባ፣ በፕራይቬታይዜሽንና በሌሎችም መንገዶች የሚያገኘውን ገንዘብ (Marshaled Resources ይሏቸዋል) አሰባስቦ ልማት ላይ ለማዋል ሲነሳ፣ ያሰባሰበው ገንዘብ ከወጪው አንፃር ጉድለት ይኖረዋል፡፡ ይህንን ጉድለት ለመሙላት መንግሥት ፊቱን ወደ ማዕከላዊ ባንክ ያዞራል፡፡ ከማዕከላዊ ባንክ የተገኘ አዲስ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እንዲገባ ያደርጋል ወይም የበጀት ጉድለቱን ይሸፍንበታል፡፡ ይህ አካሄድ የበጀት ጉድለት ወይም ‘ዴፊሲት ፋይናንሲንግ’ ወይም ደግሞ ‘ኢንፍሌሽናሪ ፋይናንሲንግ’ ይባላል፡፡ መንግሥት በተለያየ መንገድ የሰበሰበው ገንዘብ በተወሰነ መልኩ ከማዕከላዊ ባንክ የተበደረው፣ እንዲሁም የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ከባንኮች የሚበደረው ተጨምሮ፣ ከውጭ በብድርና በሐዋላ የሚገባው ገንዘብ በአንድ ላይ የገንዘብ አቅርቦቱን ያሳድገዋል፡፡ የዋጋ ግሽበት አባባሽ በሆነው ‘ዴፊሲት ፋይናንሲንግ’ ወይም ‘ኢንፍሌሽናሪ ፋይናንሲንግ’ እሳቤ መሠረት ፍላጎት ሲጨምር አቅርቦትም የሚጨምር በመሆኑ፣ የዋጋ ግሽበት የአጭር ጊዜ ክስተት ይሆናል፡፡ ሆኖም አቅርቦት አዝጋሚና ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ የዋጋ ግሽበት ይተኮሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ኢኮኖሚው ይግላል፡፡ ይህ ነው ለኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ዋነኛ ምንጩ፡፡ ልማቱን ፋይናንስ ለማድረግ የተኬደበት መንገድ የዋጋ ግሽበትን የሚቀሰቀስ ነው፡፡ በመሠረቱ ይህ አካሔድ ‘ዎኪንግ ኦን ኤ ታይት ሮፕ’ የምትለው ዓይነት ነው፡፡ አካሄዱ ስህተት ባይሆንም፣ በተለይ ከድህነት በፈጣን ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችል አቅም ስለሚፈጥር የተሳሳተ መንገድ ነው ልትለው አትችልም፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰቡ ሊሸከመው የሚችለው የዋጋ ግሽበት መጠን ምን ያህል ድረስ ነው ብለህ ማወቅን ይጠይቃል፡፡ የዋጋ ግሽበት ሰይጣን ነው፡፡ ዕድገትን ለማምጣት ያለዋጋ ግሽበት ስለማይቻል፣ አስፈላጊ ሰይጣን ብለህ የምትቀበለው በመሆኑ፣ መጠኑን ለክተህ ካልሄድክ አደጋው የከፋ ነው፡፡ አቅርቦት እስካልጨመረ ድረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓመታዊው የዋጋ ግሽበት ከአሥር በመቶ በታች ይወርዳል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- የዋጋ ግሽበቱ መፍትሔ ሊበጅለት ያልቻለ እንቆቅልሽ ሆኖ እስከ መቼ ይቀጥላል?
ዶ/ር ኢዮብ፡- የዋጋ ግሽበት ዜሮ ወይም ከዚያ በታች ይሆናል ብሎ መመኘት ጉዳት አለው፡፡ ምርት እንዲመረት አምራቹን የሚስብ የገበያ ዋጋ እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ይህ የዋጋ ግሽበት ታክሎበት ለምርት የሚከፈል ዋጋ ነው፡፡ ሰውነት ሙቀት እንደሚያስፈልገው ሁሉ ኢኮኖሚም ልከኛ ሙቀት ያስፈልገዋል፡፡ ከአገር አገር ይለያይ እንጂ ኢኮኖሚ ሲቀዛቀዝ ወይም ሲዳከም መንግሥታት የወለድ ምጣኔን በመጠቀም የገንዘብ አቅርቦትን ከፍ በማድረግ፣ ከተመጠነ የዋጋ ግሽበት ጋር ኢኮኖሚው ከተዘፈቀበት ያነቃቁታል፡፡ ከተኛበት ይቀሰቅሱታል፡፡ ይህንን አካሄድ ‹‹ኳንቲቴቲቭ ኢዚንግ›› ይሉታል፡፡ አንዳንዶቹም ‹‹ሔሊኮፕተር መኒ›› እያሉ ይጠሩታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የልማት ስትራቴጂ ነድፎ ልማታዊ መንግሥት ነኝ ብሎ ኢኮኖሚውን ለማስፈንጠር የሄደበት መንገድ ቅድም እንዳልኩህ ‹‹ኢንፍሌሽናሪ ፋይናንሲንግ›› የሚባለው ነው፡፡ የገንዘብ አቅርቦት በመጨመሩ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ የፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ መጨመር በሚገባው መጠን በአቅርቦት መጨመር ባለመደገፉ ምክንያት የዋጋ ግሽበት ተቀጣጥሏል፡፡ የገንዘብ ፖሊሲውም ሆነ የአቅርቦት አዝጋሚ መሆን ለዋጋ ግሽበት መቀጣጠል ምክንያት ሆነዋል፡፡ የተለያዩ የገንዘብ መሣሪያዎችን በመጠቀም የዋጋ ግሽበቱን ፍጥነት ለመቀነስ የፖሊሲ ዕርምጃዎች ቢወሰዱም፣ አቅርቦት አዝጋሚነቱን በመቀጠሉ የዋጋ ግሽበት ገዥ መሬት ላይ እንዲቀመጥ አስገድዷል፡፡ የዋጋ ግሽበትን በኢትዮጵያ ልከኛ ወደ ሆነ ደረጃ ማውረድ የሚቻለው በምርት አቅርቦት በኩል ያለውን ችግር መቅረፍ ሲቻል፣ በተለይም ግብርናን የማዘመን ሥራ ሲኖር ነው፡፡ ኢኮኖሚው እያደገ የዋጋ ግሽበት ግን ለሰው እንቆቅልሽ የሆነበት ምክንያት የምርት አቅርቦቱ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመድረሱ ነው፡፡ እየፈጠንክ ስትሄድ ከፍተኛ ሙቀት ይሰማሃል፡፡ በዚህ ጊዜ ማድረግ የሚኖርብህ ፍጥነት መቀነስ ወይም የመጓጓዣውን ዓይነት መቀየር ነው፡፡ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ልክ ‹‹ላዳ›› ተብለው እንደሚጠሩት ተሽከርካሪዎች አድርገህ ልታየው ትችላለህ፡፡ ላዳ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ቢጓዝ ሞተሩ ይግላል፡፡ ውኃም ሊያፈላ ይችላል፡፡ በተቃራኒው ‹‹ቶዮታ ካምሪ››ን ብትወስድ ግን በከፍተኛ ፍጥነት ብትነዳውም ሞተሩ አይግልም፡፡ ስለዚህ በእጅህ ያለው ተሽከርካሪ ላዳ ከሆነ እስክትቀይረው ድረስ ፍጥነትን ቀንሰህ መጓዝ ነው፡፡ ይህም ካልተመቸህ የሚቀጥለው አማራጭ በባጃጅ መጓዝ ሊሆን ይችላል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ወደ ዜሮ ይጠጋ ካልክ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትህንም በዚያው መጠን ማውረድ ነው፡፡ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ የሚሻለው ግን ዕድገት እያስመዘገብክ አቅርቦትን ማሳደጉ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከወራት በፊት የብርን የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ ባንኩ ለተመኑ መዳከም የሰጠው ምክንያት የወጪ ንግድን ለማበረታታትና የንግድ ሚዛኑን ጉድለት ለማጥበብ የሚል ነው፡፡ የተወሰደው ዕርምጃ ውጤታማ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል?
ዶ/ር ኢዮብ፡- በመጀመርያ ደረጃ የምንዛሪ ተመን ከማክሮ ኢኮኖሚ ማስተዳደሪያ ቁልፍ መሣሪያዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የአንድ ወር የመገበያያ ገንዘብ ከንግድ ሸሪኮች የገንዘብ ተመን፣ ለምሳሌ ብር ከዶላር አኳያ ሲነፃፀር ውድ (Overvalued) ወይም ርካሽ (Undervalued) ይሆናል፡፡ ብር ውድ ነው ሲባል ዶላር የያዘ ነጋዴ፣ ቱሪስት ወይም ሌላ ሰው፣ ዶላሩን ወደ ብር ቢቀይረው የሚያገኘው አነስተኛ ገንዘብ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነጋዴው በርከት አድርጎ ወደ ውጭ እንዲልክ የምንዛሪ ተመኑን ቀይረህና ብሩን ከፍ አድርገህ ስጠው ነው ዋነኛ ትርጉሙ፡፡ የኢኮኖሚ ሳይንሱም የሚለው ይህንኑ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የብሔራዊ ባንኩን የተመን ማስተካከያ ስታየው ትክክል ነው፡፡ ወደ ገሃዱ ተጨባጭ ሁናቴ ስንመጣ፣ የምንዛሪ ተመን ለውጡ በኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን ጉድለትን የማጥበብ ኃይል ያለው ተዓምር ይሠራል ወይ ብትለኝ፣መልሱ አይደለም ነው፡፡ ምክንያቱም የብር የምንዛሪ ተመኑ የታሰበውን ያህል ውጤት እንዲያመጣ ከፈለግህ፣ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው የተትረፈረፈ ምርት ሊኖርህ ወይም የአንተ ምርት ለምሳሌ የቡና የምርት ሰንሰለት በዓለም የምርት ሰንሰለት ውስጥ ጉልበት ድርሻ ሊኖረው ሲችል ነው፡፡ አቅም ካለህ የዓለም ባንክም፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅትም ምክር ሳያስፈልግህ ራስህ የምንዛሪ ተመንህን ታስተካክላለህ፡፡ ገና ለገና ከአምስት ዓመት በኋላ ለሚደርስ ቡና ዛሬ ተመን ብትቀይር ግን የንግድ ሚዛን ጉድለቱ አይጠብም፡፡ ይልቁኑም ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው የካፒታል ዕቃም ሆነ የሸቀጥ ዋጋ ስለሚንር ጉድለቱ ይብሱን ይሰፋል፡፡ የኢኮኖሚው መዋቅራዊ ችግር እስካልተፈታ ድረስ የንግድ ሚዛኑም መስፋቱን አያቆምም፡፡ ብርም ተመኑን ከመቀነስ አያመልጥም፡፡
ሪፖርተር፡- ከጥቂት ዓመታት በፊት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለው መናገርዎ ይታወሳል፡፡ እንደ ተፈራውም የውጭ ምንዛሪው እጥረት ኢኮኖሚውን ክፉኛ እየተፈታተነው ነው፡፡ የእጥረቱ መነሻ ምክንያት ምንድነው?
ዶ/ር ኢዮብ፡- የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት በፍጥነት እያደገ እንደሚሄድ ምልክቶች ነበሩ፡፡ አንዳንድ መንግሥት ሊጀምራቸው ያሰባቸው ፕሮጀክቶች ለግንባታ ከሚያስፈልጋቸው ገንዘብ ከ50 እስከ 60 በመቶ የውጭ ምንዛሪ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ገምተን ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዶላር ይዘው ይመጣሉ ብሎ መንግሥት የተማመነባቸው የውጭ ኢንቨስተሮች ጭራሹኑ ከፍተኛ ዶላር ጠያቂ ሆነው ቀረቡ፡፡ በወቅቱ የመንግሥት ባንኮችን የውጭ ምንዛሪ ፍሰታችሁ ምን እንደሚመስል ሠርታችሁ አቅርቡ ስንል፣ የተለመደ ስላልነበር አስቸጋሪ ጥያቄ ሆኖባቸው ነበር፡፡ እንደ ምንም መረጃውን አሰባስበን የውጭ ምንዛሪ የማፍራት አቅማቸውን ስንፈትሽ፣ ከሚፈለገው የውጭ ምንዛሪ በጣም የወረደ ነበር፡፡ ወዲያውኑ በወቅቱ ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመግለጽ የተለያዩ የፕሮጀክት ፋይናንሲንግ መንገዶች እንዲፈለጉ፣ በአጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ላይ እንዲሠራ፣ ይህ ካልሆነ ግን ችግሩ እንደሚከፋ ማስታወሻ አቀረብን፡፡ ማስታወሻው አሁንም ድረስ አለኝ፡፡ ላሳይህ እችላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ያቀረባችሁት ማስታወሻና ማሳሰቢያ ተቀባይነት አገኘ?
ዶ/ር ኢዮብ፡- ጉዳዩ የሚመለከታቸውና የሚገባቸው ሰዎች ሐሳቡን ለመቀበል ትንሽ ሳይከብዳቸው እንዳልቀረ ሰምቻለሁ፡፡ ሆኖም በሒደት ለማየት የፈለጉት ይመስል ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ጉዳዩ የማይመለከታቸውና የማይገባቸው ሰዎች እኛ ቢፒአር እየተገበርን የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ እንዴት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ይከሰታል ይላል በማለት ይኼ ማጋነን ነው ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ አሉ፡፡ ቢፒአር የውጭ ምንዛሪ እንደ ልብ ያስገኛል ብለው ስላመኑ ይመስለኛል (ረዥም ሳቅ)፡፡
ሪፖርተር፡- የውጭ ምንዛሪ እጥረትን እንዴት መፍታት ይቻላል?
ዶ/ር ኢዮብ፡- ይኼ ትንሽ ከበድ ያለ ጥያቄ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝባቸው መንገዶች አንደኛ አስተማማኝ የወጪ ንግድ ነው፡፡ ሁለተኛ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ሦስተኛ በገንዘብ አስተላላፊዎች በኩል ከውጭ የሚላክ የሐዋላ ገንዘብ፣ አራተኛው ብድርና ዕርዳታ ናቸው ለውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሆኑት ዘዴዎች፡፡ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ መሠረታዊ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግር ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በዓመት ከሚፈለው የውጭ ምንዛሪ አንፃር አነስተኛ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ከአገሪቱ የ112 ዓመታት የንግድ ታሪክ ውስጥ የ110 ዓመታት ታሪኳ የንግድ ሚዛን ጉድለት የታየበት ነው፡፡ ቡናና ኮረሪማ ኤክስፖርት እያደረግህ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር የማይበልጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢ አገኘሁ ማለት አይቻልም፡፡ መፍትሔው ሥር ነቀል የሆነ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ሲሆን፣ እስከዚያው ግን ዘርፉን እንደገና መፈተሹ ተገቢ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ከቬትናም ብዙ መማር ይቻላል፡፡ ቬትናም 18 ቢሊዮን ዶላር የነበረውን የወጪ ንግድ ገቢ በሃያ ዓመታት ውስጥ 244 ቢሊዮን ዶላር አድርሳለች፡፡ እነሱ የሄዱበትን መንገድ ማየት ይጠቅማል፡፡ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው፡፡ በአጭር ጊዜም ባይሆን በሁለትና ሦስት ዓመት የአንዳንዶቹ ውጤት በመጠኑም ቢሆን መፍትሔ ሊያስገኝ ይችላል፡፡ ቱሪዝምና የሐዋላ ገቢ ላይ በተገቢው መንገድ የሚሠራባቸው ካለ፣ የውጭ ምንዛሪ ችግሩን ማስተንፈስ ይቻላል፡፡ ቱሪዝም ትልቅ ኢንቨስትመንት የማይፈልግ ዘርፍ ነው፡፡ በአዳዲስ ሐሳቦችና ቴክኒኮች (ኢኖቬቲቭ) ከተኬደበት በአጭር ጊዜ ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡ በዚህ ላይ የአየር መንገዱን ትልቅ አቅም መጠቀም ከተቻለ ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡ ከተመለደው ወጣ ብለው ማሰብ ለሚችሉ ሰዎች ኃላፊነቱን መስጠት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከማቃለል አኳያ ከውጭ አገር የሚላከው የሐዋላ (ሬሚታንስ) መጠን በአሁን ወቅት እየገባ እንደሆነ ከሚገጸለው አራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ማሳደግ አይቻልም?
ዶ/ር ኢዮብ፡- በመጀመሪያ አራት ቢሊዮን ዶላር ይገባል እየተባለ የሚነገረው መጠን ትክክለኛ አኃዝ አይደለም፡፡ ይህን አኃዝ እንደ መረጃ ያወጡት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ናቸው፡፡ እንዴት እዚህ አኃዝ ላይ ሊደርሱ እንደቻሉ ተነጋግረናል፡፡ እዚህ አኃዝ ላይ የደረሱበት አካሄድ ግምታዊና በስህተት የተሞላ ነው፡፡ ስለዚህ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩት ገንዘብ ከአራት ቢሊዮን ዶላር ሊበልጥም ሊያንስም ይችላል፡፡ ሁለተኛ በባንኮችና በገንዘብ አስተላላፊዎች በኩል በኦፊሴል የሚላከው ገንዘብ የዓለም ባንክም ሆነ የአይኤምኤፍ መረጃ እንደሚያሳዩት በአማካይ ከ700 ሚሊዮን ዶላር የማይበልጥ ነው፡፡ ወደ አገር ውስጥ ይገባል ከሚባለው ገንዘብ 75 በመቶው በባንኮች በኩል የሚያላክ አይደለም፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ከማቃለል አኳያ የውጭ ሐዋላ ብዙ ልፋትን የማይጠይቅ ወይም ‹‹low hanging fruit›› የሚባል ነው፡፡ የውጭ ሐዋላ አሁን ባለው አካሄድና ባንኮች በሚያደርጉት መፍጨርጨር ብቻ በፍጥነት ማሳደግ አይችልም፡፡ ከውጭ ሐዋላ የሚገኘውን ገንዘብ በፍጥነት ለማሳደግ ከተፈለገ ጉዳዩን ብሔራዊ አጀንዳ አድርጎ መነሳትን ይጠይቃል፡፡ በርካታ አገሮች የውጭ ሐዋላ ገቢን ብሔራዊ አጀንዳቸው በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ችለዋል፡፡ ከሰባት ዓመታት በፊት ፓኪስታን ከሐዋላ የምታገኘው ገንዘብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 ፓኪስታን ያገኘችው የውጭ ሐዋላ 19 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ፊሊፒንስ 29 ቢሊዮን ዶላር፣ ሜክሲኮም 30 ቢሊዮን ዶላር ያገኛሉ፡፡ ከመቶ ሺሕ ሕዝብ በታች ያላቸው የፓስፊክ አገሮች ማለትም እንደ ቶንጋ ሳሞአና ፊጂ ያሉት አገሮችም 50 በመቶ ለአገር ውስጥ ምርት ድርሻ የሚያበረክተው ሐዋላ ነው፡፡ ሐዋላን ለማሳደግ በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ከውጭ ሐዋላ የሚገኘውን ገንዘብ በፍጥነት ለማሳደግ ከተፈለገ፣ የሐዋላ ገንዘብ የሚላክባቸውንና “high value corridors” ተብለው የሚታወቁ አገሮችን ማለትም ሳዑዲ ዓረቢያ ሊባኖስ፣ እስራኤልና አሜሪካ የመሳሰሉት ላይ በማተኮር በአጭር ጊዜ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በኦፊሴል ማስገባት ይቻላል፡፡ እዚህ አገር ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትም መንገዱን ለማሳየትና ለማገዝ ዝግጁ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- የፋይናንስ ዘርፉ አሁን እየሰፋ ለመጣው የኑሮ ልዩነትና ሚዛናዊ ላልሆነው የሀብት ክፍፍል አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ይባላል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ ምልከታ ምንድነው?
ዶ/ር ኢዮብ፡- የፋይናንስ ዘርፉ ማለትም የባንክ፣ የኢንሹራንስና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለኢኮኖሚው ዕድገት የተፈለገውን እንኳ ባይሆን ለግሉ ዘርፍ ማበብ የጎላ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው አይካድም፡፡ በመሠረቱ የፋይናንስ ዘርፉ ልማታዊ በሆኑ አገሮች ውስጥ የሀብት ክፍፍልን ሚዛናዊ ለማድረግ ከሚጠቀሙባቸው ቁልፍ መሣሪያዎች መካከል በዋናነት የሚመደብ ነው፡፡ ልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚውን የሚያይበት መነጽር የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መነጽር ነው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ሀብት ሲፈጠር፣ የተፈጠረው ሀብት ለጋራ ተጠቃሚነት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል አለበት ብሎ ልማታዊ መንግሥቱ ስለሚያምን ጭምር ነው፡፡ ልማታዊ መንግሥት የግሉን ዘርፍ የማይተካ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽነት ሚና እንዳለው ስለሚያምን፣ የግል ባለሀብቱና ኢንቨስተሩ ኢኮኖሚውን ወደ ተሻለ ከፍታ እንዲያደርሱና የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ የተመቻቸ የብድር አቅርቦት፣ አቅም በፈቀደ መጠን የሚገኝ የውጭ ምንዛሪን ቅድሚያ የማግኘት መብት፣ አቅምን ያገናዘበ የታክስ ሥርዓት፣ ወዘተ. በመዘርጋት የግሉ ዘርፍ መንግሥት ቅድሚያ በሰጠባቸው የሥራ ዘርፎች ላይ እንዲሠማራ መንገዱን ያመቻቻል፡፡ በደቡብ ኮሪያ፣ በማሌዥያ፣ በሲንጋፖር፣ ወዘተ. መንግሥታት ኢኮኖሚያቸውን ያሳደጉት ለመንግሥት ያደሩ የፋይናንስ ዘርፎችን ተጠቅመው ነው፡፡ የተመቻቸ ብድርና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት የሚያገኙ ኩባንያዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ነው፡፡ የደቡብ ኮሪያው ሳምሰንግ ባለቤት ሥራውን የጀመረው የአትክልት፣ የዓሳ፣ ከዚያም የስኳር ሻጭ ከመሆን ተነስቶ ነበር፡፡ ይህን ሥራ በ30 ዶላር ነው የጀመረው፡፡ የወቅቱ ፕሬዚዳንት የፓርክ ቹንግ መንግሥት ሳምሰንግና መሰል ኩባንያዎችን ሰብስቦ ብድር እየሰጠ፣ የውጭ ምንዛሪ እያቀረበ አልፎ ተርፎም ዕዳ ያለባቸውን ዕዳቸውን እየሰረዘ ነው በሒደት ኢኮኖሚውን የገነባው፡፡
የእዚህ አገር የፋይናንስ ዘርፍ የሀብት ክፍፍሉን አዛብቷል በሚለው ላይ እኔም እስማማለሁ፡፡ የባንክ ብድር ለማግኘት መመዘኛው ምንድነው፡፡ ዋናው መመዘኛ የብድር ማስያዣ ነው፡፡ ማስያዣ ያለው ብድር ያገኛል፡፡ ዋስትናው የማይረባም ቢሆን ብድር ያስገኝለታል፡፡ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ የተሠማራው ብድር አገኘ ከተባለ እንጥፍጣፊ ቢደርሰው ነው፡፡ ባለሀብቱን ከወሰድክ በአብዛኛው በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሠማራ አይደለም፡፡ የሚያኘውን ትርፍ ወይ ዱባይ ያስቀምጠዋል አሊያም ሕንፃ ይሠራበታል፡፡ አበቃ፡፡ ለአንድ የቡና ነጋዴ አራት መቶ ሚሊዮን ብትሰጠው የማን ኑሮ ነው የሚሻሻለው? የአርሶ አደሩ ወይስ የነጋዴው? በሀብት ላይ ሀብት እንጂ ይጨምርለታል እንጂ ወደ ደሃው ብዙም አይወርድም፡፡ አብዛኛው የአገሪቱ ኢኮኖሚና ሕዝብ የት ነው ያለው? የብድር ፍሰቱስ ወዴት ነው ያመዘነው? በወሬ ደረጃ የምትሰማቸው አንዳንድ ነገሮች እውነት ከሆኑ፣ የኑሮ ልዩነት እንዲሰፋ የፋይናንስ ተቋማቱ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል ማለት ትችላለህ፡፡ ለምሳሌ በትዕዛዝ የሚሰጥ ብድርና የውጭ ምንዛሪ አለ ይባላል፡፡ እንዲሁም በአንድ የብድር ዋስትና ከሁለት ባንክ ብድር የወሰዱ አሉ ይባላል፡፡ በቀላሉ የሆቴል ባለቤት ሕጋዊ በሚመስል ነገር ግን በተቀነባበረ አሠራር በመያዣነት የተያዘ ሕንፃ የገዙ ሰዎች፣ ራሳቸው የጨረታ ሰነድ አዘጋጅተው ራሳቸው አሸናፊ እንደሚሆኑ፣ ወዘተ. ይሰማል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ በሒደት ቅሬታ ይፈጥራል፡፡ የኑሮ ልዩነት እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን በእዚህ አገር ልዩነት እንዲሰፋ ካደረጉ ነገሮች አንዱ መሬት ነው፡፡ አንዳንድ ሰው ሚሳይል የተገጠመለት እስኪመስል ድረስ በፍጥነት ይምዘገዘጋል፡፡ ይኼ መፍትሔ ካልተበጀለት አካታች የኢኮኖሚ ዕድገት የሚባለውን መርሳቱ ይሻላል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አሠራሩ የኢንቨስተሩን ፍላጎት ያላማከለ፣ የሚያወጣቸውም መመርያዎች እርስ በርስ የሚጋጩ፣ በሙስናና በአቅም ማነስ ባለሀብቶችን ያማረሩ ጉዳዮች እየተነሱ በስፋት ወቀሳ ይቀርብበታል፡፡ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶ/ር ኢዮብ፡– እኔ ከባንክ ዘርፉ ከወጣሁ ቆየሁ፡፡ አሁን ባንኩ ስላለበት ደረጃ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ያልካቸው ችግሮች በሙሉ በዚያን ጊዜም ነበሩ፡፡ እንዲያውም ፈረንጆች እንደሚሉት ‹‹Pandora Box›› የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ነገሮች ነበሩ፡፡ በወቅቱ የአሠራር ችግሮችን በተለይ በብድር አሰጣጥ ክትትልና አሰባሰብ፣ የፕሮጀክት አዋጭነት ትንተና፣ ወዘተ. ላይ በርካታ ችግሮችን ነቅሰን አውጥተን ብዙ ጦርነት አካደናል፡፡ ባንኩ እንደ አዲስ እንዲዋቀር የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አሳምነንና ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ሥራ ለመግባት ስናቅድ ሁናቴው ያላስደሰታቸው ሰዎች አከሸፉት፡፡ የመጀመርያውን የሥራ መልቀቂያ ያቀረብኩትም ወዲያውኑ ነበር፡፡ በቅርቡ ስለባንኩ በየአቅጣጫው ተነስቶ የነበረውን ውግዘት የምታስታውሰው ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ሥር የሰደደ ሙስና እንዲሁም የአቅም ችግር አለባቸው ይባላል፡፡ ቀደም ሲል ዘርፉን ይመሩ ስለነበር በዚህ ጉዳይ ላይ የሚገልጹልን ነገር ካለ? አሁንስ ድርጅቶቹ ያሉበትን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
ዶ/ር ኢዮብ፡- አሁን ገና ጣት የሚያስቆርጥ ጥያቄ አመጣህ፡፡ ጥያቄው መቅረብ የነበረበት 14 ዓመታት ሙሉ ሙስናን ሲዋጋ ለነበረው የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ነው፡፡ ከዘርፉ ስለራቅሁ ድርጅቶቹ ያሉበትትን ወቅታዊ ሁኔታ አላውቅም፡፡ ሥራቸውን አክብረው በታማኝነት የወር ደመወዝ እየጠበቁ ዓመቱን ሙሉ ቦነስ እየናፈቁ ደፋ ቀና የሚሉ በርካታ ሠራተኞች ያሉባቸው ድርጅቶች መሆናቸውን በወቅቱ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ከእነዚህ ውጪ በግለሰቦች ላይ በመንጠላጠል፣ እንዲሁም የፓርቲ ጭንብል በማጥለቅ ባልተገባ ተግባር የሚሳተፉ ደብተራዎችና ወይዛዝርት እንደነበሩ መረጃ ብቻ ሳይሆን ማስረጃ ለመንግሥት ቀርቦ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ዝርዝሩን የመንግሥት ሚስጥር ስለሆነና ስለማላስታውሰው ልነግርህ አልችልም፡፡ የአቅም ጉዳይ ከተነሳ በጣም ብዙ ባይሆኑም በጥቂቱ አቅም ያላቸው ነበሩ፡፡ ሌሎች አቅምም ወገብም የሌላቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ አሁንም ያሉ ይመስለኛል፡፡ አሁን በምንነጋገርበት ወቅት ሙስና ሥር ሰዶ ከሆነ እንደ እምቦጭ መጠራረግ ነው፡፡ አኮልኳይና ወጥ ቀማሹን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ዋናው ትኩረት መሆን የሚገባው ተቋማቱ የልማት ማስፈጸሚያ ዓይነተኛ መሣሪያዎች በመሆናቸው የሰው ኃይሉን የማብቃቱ ሥራ ላይ ነው፡፡ ችሎታ፣ ብቃትና ታማኝነትን (ለአገር ማለቴ ነው) መሠረት ያደረገ አሠራርና አደረጃጀት መኖሩን በድጋሚ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ በአጭሩ መንግሥት ሪፖርት በሚደረግለት ዓመታዊ ትርፍ ሳይዘናጋ ፍተሻ ቢያደርግ የሚያዋጣው ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- አገሪቱን ከፍተኛ የሥራ አጥነት፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተፈታተኗት ይገኛሉ፡፡ እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ዶ/ር ኢዮብ፡- ባለፉት ዓመታት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ያሳይ እንጂ በበቂ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ እያመነጨ የሥራ ዕድል እየፈጠረ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ኢኮኖሚው እየሸጋገረ የሚገኘው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ሳይሆን፣ ዝቅተኛ ምርትና ምርታማነት ካለው ግብርና ተመሳሳይ የምርትና ምርታማነት ወዳለው ሰርቪስ ሴክተር ነው፡፡ ኮንስትራክሽን፣ ሰርቪስ ሴክተር የሥራ ዕድል ከመፍጠርና የውጭ ምንዛሪ ከማፍራት አኳያ በጣም የተወሰነ አቅም ነው ያለው፡፡ አሁን የሚያስፈልገው አዲስ ምልከታ ነው፡፡ እንደነበረው ሊቀጥል አይችልም፡፡ አንድ ኢኮኖሚ በበቂ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ማፍራት ካልቻለና የሥራ ዕድል በአጥጋቢ መፍጠር ካልቻለ የኢኮኖሚ ስትራቴጂውንና ፖሊሲዎችን መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ በተለይም በግብርናና ኢንዱስትሪ መካከል ትስስር በበቂ ሁኔታ ካልታጠረ የሚፈለገው ውጤት ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ አበባ ሸጠህ ተመልሰህ ባገኘኸው የውጭ ምንዛሪ ከፓኪስታንና ከባንግላዴሽ ጥጥ እየገዛህ በጨርቃ ጨርቅ ሴክተር ከምታቀርብ፣ በባለሀብቱና በአርሶ አደሩ መካከል ጥምረት ፈጥረህ ለምሳሌ አርሶ አደሩ ዕዳ ውስጥ ሳይገባ ባለሀብቱ ግብዓት እያቀረበለት በኮንትራት ግብርና ጥጥ ቢያመርት፣ ግብርናውም ኢንዱስትሪውም ተያይዞ ማደግ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በግብርና ሜካናይዜሽንና በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ቢሠራ፣ የዋጋ ግሽበት ይለዝብና የውጭ ምንዛሪ ይገኛል፡፡ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የአገር ውስጥ ባለሀብት ተሳትፎ መጉላትና መሪ መሆን አለበት፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ የማክሮ ኢኮኖሚ በተለይም የገንዘብና የታክስ ፖሊሲዎች እስካሁን አገልግለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ወቅቱ በሚጠይቀው፣ ኢኮኖሚው በሚፈልገው መጠን ወርድና ቁመናቸው ሊስተካከል ይገባል፡፡ የግል ዘርፉን ጠፍረው የያዙ ሕጎች፣ አሠራሮችና ደንቦች ሊፈተሹና እንደ ፓስታ የተወሳሰበው ቢሮክራሲም ዳግም መቃኘቱ የግድ ነው፡፡ ቁልፍ የሆኑ ተቋማት ከፖለቲካ ነፃ ወይም ‘ዲ-ፖሊቲሳይዝድ’ መደረግ አለባቸው፡፡ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት በድጋሚ መታየት አለባቸው፡፡ በተለይም የቴሌኮምና የፋይናንስ ድርጅቶች፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳ፣ የኬሚካል፣ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎችና ማዕከላት በድጋሚ ሊታዩ ይገባል፡፡ የኤክስፖርት ዘርፉ አርባ ሺሕ ጫማ ላይ በሚገኝበት አግባብ መቀጠል ስለማይቻል፣ አፋጣኝ ለውጥ ማምጣት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው፡፡ እስካሁን የተኬደባቸው የሥራ ፈጠራ ዕድሎች መከለስ አለባቸው፡፡ ከሁሉ በላይ የኢኮኖሚ ልማት ያለ አዕምሮ ልማት የማይታሰብ ነው፡፡ የአዕምሮ ልማት ከባለ ሁለት አኃዝ ዕድገት በላይ ሊሠራበት የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡