Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  ኢምባሲዎቻችን የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ለመቅረፍ ምን እየሠሩ ነው?

  ስለአንድነትና ስለኢትዮጵያዊነት እየሰማን ነው፡፡ ስለፍቅርና ይቅር ባይነትም ሰምተናል፡፡ አንድ እንሁን አንድነታችን ‹‹ተደምሮ›› ወደ መልካም ጐዳና ይወስደናል የሚል መልዕክት ያላቸው አንደበቶችን ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተደጋጋሚ እየሰማን ነው፡፡ የሁላችንም ምኞት ይህ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ካለው መልዕክቶቻቸው ባሻገር በየንግግሮቻቸው አካትተው ሲገልጹ የነበረው የመልካም አስተዳደር ችግርን ነው፡፡ በአገሪቱ ያለውን አማራሪ የአገልግሎት አሰጣጥ ለመቀየር ቃል ገብተዋል፡፡ ‹‹ቃል›› ይከበር ብለዋልና ይህንን ቃላቸውን ይተገብራሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ሙስናን ወይም ዶ/ር ዓብይ አህመድ በተደጋጋሚ ሌብነት ጽዩፍ መሆኑን ለማስረዳት የተለዩ ምሳሌዎችን እያስቀመጡ እጃችሁን ሰብስቡ ብለዋል፡፡

  በዚህ ድርጊት መሳተፍ ቀይ መስመር ስለመሆኑ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በአጭር ጊዜ በተለያዩ መድረኮች ካሰሙት ንግግር ውስጥ የአገራችን ዲፕሎማቶችን በተመለከተ ጨረፍ አድርገው የጠቆሙትም ነገር ነበር፡፡ በአጭሩ ዲፕሎማቶቻችን ኢትዮጵያን ለመሸጥ ወይም ኢትዮጵያን ለሌሎች ለማስተዋወቅ እየሠሩ አለመሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ ይህ እውነት ስለመሆኑ ይታመናል፡፡

  ቡናችንን፣ አበባችንን፣ ሰሊጣችንን፣ ቆዳችንን ግዙን ብለው በያሉበት አገር ቀስቅሰዋል፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚደግፍ ጉልህ ተግባር ፈጽመዋል ማለትም ይከብዳል፡፡ ቢሆን ኖሮ የአገራችን የወጪ ንግድ ባለበት ባልቆመ ነበር፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መልካም ሥራ የሠሩ ዲፕሎማቶች እንዳሉን ሁሉ፣ እንዲህ ያለውን ተግባር ያልፈጸሙ በርካታ ዲፕሎማቶች እንዳሉን እንገነዘባለን፡፡

  በእርግጥ በሌሎች የዲፕሎማሲ ሥራዎቻቸው መልካም ተግባር ፈጽመዋል ሊባል ቢቻልም፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ሊያስገኙ የሚችሉ ሥራዎቻቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ብዙዎቻችን እንደምንስማማው ኤምባሲዎቻችን የቱንም ያህል ሥራ ቢኖራቸው፣ ዋነኛ ተግባራቸው ኢትዮጵያን ማስተዋወቅና ለኢትዮጵያ ምርቶች ገበያ መፈለግ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ በተለይ አገር በውጭ ምንዛሪ እጥረት በተቸገረችበት በዚህ ወቅት ዋነኛ ሥራቸው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ በሆነ ነበር፡፡

  በዚህ ዓብይ ሥራ ዙሪያ ምን ያህል ኤምባሲዎች ከልብ ሠርተዋል ብለን ከጠየቅን መልስ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ ካልን የኤምባሲዎቻችን ተግባር በአግባቡ ከመቃኘት ጋር የተያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ የአምባሳደሮች ሹመት ራሱ ተፅዕኖ እንዳለው መገመት አያዳግትም፡፡

  ዶ/ር ዓብይም ኤምባሲዎቻችን ወይም ዲፕሎማቶቻችን እየሠሩ አይደለም የሚል አመለካከት ካላቸው፣ ይህ አመለካከታቸው ትክክል ነው ብለን የምንወስደው ኢትዮጵያን ከመሸጥ አኳያ ይለካ ከተባለ ነው፡፡

  ይህ ከሆነ ደግሞ ችግሩ ያለው ከመጀመሪያው የኤምባሲዎችን አደረጃጀት ላይ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የዲፕሎማቶች አመዳደብና ሹመት የአገሪቱን የወጪ ንግድ ሊያሳድግ በሚችል ደረጃ ጭምር እንዲቀኝ ባለመደረጉ ነው የሚለውም ሊያስማማን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ አገሮች ያሉን አምባሳደሮች የተመደቡበት መስፈርት ብቃት ላይ የተመሠረተ ለመሆኑም ያጠራጥራል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቷ ፖለቲካ በአቅም ማነስም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ተገምግመው ከኃላፊነታቸው የሚነሱ ባለሥልጣናት የሚጦሩበት ሹመት እየሆነ መጥቷል፡፡ በአገር ውስጥ አቅም ያነሰው ባለሥልጣን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ ይሆናል ብሎም መጠበቅ ላም አለኝ በሰማይ ዓይነት ነው፡፡

  አሁን አገሪቱ ለውጥ ላይ ነች ከተባለ ደግሞ ለውጡ እነዚህ ኤምባሲዎችና ሠራተኞቻቸውን ሊመለከት ይገባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት በተሻለ ጐዳና ለመራመድ እንዲሁም ዛሬ የአገሪቱ ዋነኛ ችግር እየሆነ የመጣውን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍ፣ አንዱ መፍትሔ ኤምባሲዎቻችን ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ተግተው መሥራት ከቻሉ ነው፡፡

  ለዚህ ደግሞ ይህንን ወሳኝ ተልዕኮ የሚያሳካ ዲፕሎማቶች ያስፈልጋሉ ማለት ነው፡፡ በየኤምባሲው ካሉ ሠራተኞች የበዙቱ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅና ምርቶቿን በመሸጥ ላይ ያነጣጠሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡

  ስለዚህ እስከ ዛሬ ከዚህ ቅኝት ውጭ የሚሠራ ከሆነ ይህንን አሠራር መለወጥ ያሻል፡፡ ሌላው ቀርቶ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት የሚልኩትን ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ እንዲልኩ ለማድረግ ያለመሠልቸት ሠርቶ የአገር ‹‹ሬሚታንስ›› ከፍ እንዲል የማድረጉ ሥራ እኮ የእነርሱ መሆን ይገባው እንደነበር ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

  እንዲህ ማድረጉ የቱንም ያህል ፈታኝ ቢሆን እንኳን ምን ያህል ተሞክሮ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ በመያዝ ፍተሻ ቢደረግ፣ ለኤምባሲዎቻችንና ለሠራተኞቹ በየዓመቱ በውጭ ምንዛሪ የሚመደበው በጀት ሊያስቆጭ ይችላል፡፡

  ስለዚህ ኢትዮጵያ ለውጥ ላይ ነች ከተባለ ኤምባሲዎቻችን የእስከ ዛሬ ጉዞ ተፈትሾ አገር በሚጠቅም ደረጃ ሊደራጁ ይገባል፡፡ የሚመደቡ ሠራተኞችም ቢሆኑ በውለታ ሳይሆን በተግባራቸው ተለክተው መሆን ይኖርበታል፡፡

  አሁን ከየአቅጣጫው እንደሚሰማው ከፍተኛ ዲፕሎማት ተብሎ የሚሾም ሰው ባለቤቱን ወይም ባለቤቷን ወይም የቅርብ ዘመዱን የዲፕሎማት ማዕረግ አሰጥቶ ኤምባሲ ውስጥ እስከማስቀጠር እየተደረሰ ነው መባሉ ራሱ፣ የሹመት አሰጣጡ መፈተሽ እንዳለበት የሚጠቁም ነው፡፡ ኤምባሲዎች በዘመድ አዝማድ የሚሞላ ከሆነ የኤምባሲዎቻችን ተልዕኮ ትርጉም እንዲያጣ ከማድረጉም ባሻገር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለብን እያልን ምንም የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ያልተሳተፉ የኤምባሲ ሠራተኞች በውጭ ምንዛሪ መክፈሉ እንደ ኪሳራ አይታይ ይሆን?

  የአገራችንን ሬሚታንስ በተመለከተ የተጠናከረ መረጃን መሠረት በማድረግ ዶ/ር ዓብይ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በዓመት ከሬሚታንስ የምትገኘው ገቢ ከናይጄሪያ በ500 በመቶ ከግብፅ ከ300 በመቶ ያነሰ ነው፡፡ ነገር ግን በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን የእነዚህን አገሮች ያህል ሬሚታንስ ሊያስገቡ የሚችል አቅም እንዳላቸው ይገመታል፡፡

  ይህንን አጋጣሚ ደግሞ ኤምባሲዎቻችን ተጠቅመውበት ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመቀስቀስ ለአገር ጠቃሚ ሥራ መሥራት አለባቸው፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት አጋጣሚው መልካም ነው ተብሎ ስለሚታመን አገር መጥቀም ማለት በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ መላክ ነው ብሎ ማሳመን ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል፡፡

  ከሬሚታንስ ይገኝ የነበረውን ግማሽ ያህል እንኳ እንዲገኝ ለማድረግ የማግባባትና የማሳመን ሥራ ብንሠራ ኖሮ፣ ዛሬ በዶላር እጥረት ምክንያት መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን ለማስገባት ወረፋ ባልተጠበቀ ነበር፡፡ ዜጐችም የሚፈልጉትን ምርት በውድ ዋጋ ባልሸመቱ ነበር ብሎ ማሳበብም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ አሁን ኤምባሲዎቻችን ለአገር ገበያ ከመፍጠር ባሻገር ውጭ ያለው ዜጋ ገንዘቡን በሕጋዊ መንገድ እንዲልክ የማሳመን ሥራ ያለማቋረጥ ሊሠሩ ይገባል፡፡ በሕጋዊ መንገድ መላክ አገር መጥቀም መሆኑን በትክክል ማስረዳት ይገባል፡፡

  ይገባል ሲባል ደግሞ እነርሱንም ይመለከታል፡፡ እውነት ከእነዚህ በውጭ ከሚገኙ የኤምባሲ ሠራተኞቻችን ምን ያህሉ አገር ቤት ላሉት ወዳጅ ዘመዶቻቸው በባንክ ቤት ገንዘብ ይልካሉ? እነርሱም እከሌ ይመጣልና ይህንን ያህል ዶላር ልኬያለሁ ካሉ፣ ነገር ተበላሸ ማለት ነውና ምሳሌ በመሆንም እንዲሠሩ ይጠበቃል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው በየአገሩ ያሉ አምባሳደሮችም ሆኑ የኢምባሲ ሠራተኞቻችን በብቃት የተመረጡ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሳይሆን የአምባሳደርነት ሹመት እንደ መጦሪያ ከታየ፣ አገሪቷ ከኢምባሲዎቻችን ውጭ ምንዛሪ ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ልትሆን አትችልም፡፡ ስለዚህ በአገሪቷ ውስጥ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሪነት እየነፈሰ ያለው ንፋስ፣ በኢምባሲዎቻችንም ያለውን ብልሹ አሠራር ጠራርጎ ሊወስደው ይገባል፡፡

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት