Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የብር ምንዛሪ መውደቅ ያስከተለው የዋጋ ዕድገትና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የገባበት ፈተና

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ጥቅምት 2010 ዓ.ም. የብር ምንዛሪ በ15 በመቶ መውረዱ ይፋ እንደተደረገ ወዲያው በከፍተኛ ሁኔታ የዋጋ ጭማሪ ከታየባቸው ምርቶች ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችና የግንባታ መሳሪያዎች በዋናነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

  ይህ የዋጋ ለውጥ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አደገኛ ሊሆን እንደሚችል የተገለጸውም ወዲያው ነበር፡፡ የምንዛሪ ለውጡ በተደረገ በቀናት ልዩነት ገበያ ላይ የነበሩ የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ ባልተጠበቀ ሁኔታ በመጨመሩ ምክንያት የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ማኅበር የታየው ጭማሪ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በማመን በጉዳዩ ላይ ጥናት እንዲደረግ እስከመወሰን ደርሷል፡፡ ለዚህም ጥናት ሃብኮም ኮንሰልቲንግ የተባለ አማካሪ ድርጅት ቀጥሮ ያስጠናው ጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው፣ ዋና ዋና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ ከምንዛሪ ለውጡ በኋላ በአማካይ 51 በመቶ ጨምሯል፡፡

  የብር የምንዛሪ ለውጡ ከተነገረበት የመጀመርያ ሳምንት ጀምሮ የታየው የዋጋ ለውጥ፣ በፊት በአማካይ ይታይ ከነበረው የዋጋ ዕድገት አንፃር ሲታይም ከፍተኛ የሚባል ጭማሪ መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡

  የዋጋ ለውጡን በተጨባጭ ያሳየው ይህ ጥናት፣ በምሳሌነት ካቀረባው የግንባታ ግብዓቶች ውስጥ አንዱ ብረት ነው፡፡ ከምንዛሪ ለውጡ በፊት ከ6 እስከ 20 ሚሊ ሜትር መጠን ያላቸው ከውጭ የሚገቡ ብረቶች (አርማታ ብረት) በወር በአማካይ ይታይባቸው የነበረው የዋጋ ዕድገት 1.3 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ በተመሳሳይ መጠን ያለው የአገር ውስጥ ብረትም በአማካይ ዕድገቱ 1.68 በመቶ እንደነበር ጥናቱ ያሳያል፡፡

  የብር የምንዛሪ ለውጡ በተደረገ በመጀመርያው ሳምንት ግን ከውጭ የሚገቡት የብረት ምርቶች በአንድ ጊዜ 49.17 በመቶ፣ የአገር ውስጥ ብረት ደግሞ 46.76 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡

  ይህ የዋጋ ለውጥ ከሐምሌ 2009 ዓ.ም. አንፃር ሲታይ የአገር ውስጡ 57 በመቶ ከውጭ የሚገባው ደግሞ 58 በመቶ ጭማሪ ታይቶበታል፡፡ ከሐምሌ 2009 ዓ.ም. ቀደም ብሎ ባሉት ስድስት ወራት ከውጭ የሚገቡ ብረቶች በአንድ ኪሎ ግራም 23.57 ብር ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ብረት ደግሞ በኪሎ ግራም 20.29 ብር ይሸጥ ነበር፡፡

  ይህ ዋጋ ከጥቅምት 2010 ዓ.ም. በኋላ በተለይም የብር ምንዛሪ ለውጡ በተደረገ የመጀመርያው ሳምንት ላይ በኪሎ ግራም 23.57 ይሸጥ የነበረው የውጭ ብረት 37.23 ብር የገባ ሲሆን፣ 20.29 ብር ይሸጥ የነበረው የአገር ውስጥ ብረት ደግሞ ወደ 37.84 ብር አድጓል፡፡

  ሆኖም በመንግሥት ተቆጣጣሪነት 37.23 ብር የሚሸጠው የውጭ ብረት ወደ 33.91 ብር ዝቅ ማለት ቢችልም፣ ከብር ምንዛሪ ለውጡ በኋላ የብረት ዋጋ 42 እና 41 በመቶ እንደጨመረ ያሳያል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ደግሞ በቂ ምርት ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ በማድረግና ገበያ ውስጥ የበለጠ እጥረት በመፈጠሩ ዋጋውን እንደገና ከፍ አድርጎታል፡፡ ይህም የምንዛሪ ለውጡ ከተደረገ ከአሥር ሳምንታት በኋላ የአገር ውስጡ 71 በመቶ የውጭው ብረት ደግሞ 62 በመቶ መጨመሩን ያሳያል፡፡

  ሌላው የዋጋ ጭማሪ የታየበትት የግንባታ ግብዓት አሸዋ ነው፡፡ ከሐምሌ 2009 ዓ.ም. 462 ብር ይሸጥ የነበረው ሦስት ሜትር ኪውብ አሸዋ፣ ከምንዛሪ ለውጡ በኋላ 500 ብር ገብቷል፡፡ በመሆኑም 21.21 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

  የተለያየ ይዘት ያላቸው የብረት በሮች ሐምሌ 2009 ዓ.ም. ድረስ ከ800 እስከ 1,530 ብር ይሸጡ እንደነበር የሚያመላክተው ይኸው ጥናት፣ ጥር 2010 ዓ.ም. ላይ ከ19 እስከ 37 በመቶ ጭማሪ ታይቶባቸዋል፡፡ ይህ አጠቃላይ የብረት በሮችን ለማሠራት የሚያስፈልገው ወጪ በአማካይ 30 በመቶ ጭማሪ እንዲታይበት አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ ጋልቫናይዝድ ብረቶች ላይ የ22 በመቶ ጭማሪ እንደታየም ጥናቱ አመላክቷል፡፡

  ከብር ምንዛሪ ለውጡ በፊት 450 ብር ይሸጥ የነበረው ኳርቲዝ ቀለም ጥር 2010 ዓ.ም. 515.5 ብር የገባ ሲሆን፣ 160 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ጋሎን የፕላስቲክ ቀለም ደግሞ ወደ 184 ብር ደርሷል፡፡ በአጠቃላይ የቀለም ዋጋ በ15 በመቶ ጭማሪ የታየበት መሆኑ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ፈታኝ ሆኗል፡፡

  ከብር ምንዛሪ ለውጡ ወዲህ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቶበታል ተብሎ ከተጠቀሱት የግንባታ ምርቶች መካከል ሴራሚክም ይገኝበታል፡፡ ከምንዛሪ ለውጡ በፊት በካሬ ሜትር 350 ብር ይሸጥ የነበረው የሴራሚክ ዓይነት፣ ጥር 2010 ዓ.ም. ላይ ዋጋው 570 ብር ደርሷል፡፡ ሌሎች የሴራሚክ ዓይነቶችም በተመሳሳይ ከ63 እስከ 73 በመቶ ጭማሪ የታየባቸው ሲሆን፣ በጥቅል ደግሞ በአማካይ 66 በመቶ ጭማሪ እንደታየ ተመልክቷል፡፡ በአጠቃላይ በጥናቱ የተካተቱ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችና መሳሪያዎች በድምር ያሳዩት አማካይ የዋጋ ዕድገት 51 በመቶ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡

  በዚህን ያህል ደረጃ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከምንዛሪ ለውጡ በፊት በተሰላ ዋጋ የተጀመሩ ግንባታዎች ቀጣይነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ መንግሥትም ይህንን ክፍተት ማየት እንዳለበት ያስረዳል፡፡

  ማካካሻ ሊኖራቸው ይችላል የተባሉትም ሆነ ማካካሻ ላይኖራቸው ይችላል የተባሉ የግንባታ ግብዓቶችን አሁን ባለው ዋጋ ገዝቶ ግንባታዎቹን ማስጨረስ እጅግ ከባድ እንደሚሆን ያነጋገርናቸው ኮንትራክተሮች ያመለክታሉ፡፡

  አንዳንድ ፕሮጀክቶችም በዚሁ የግንባታ ግብዓት ዋጋ መናር ምክንያት ግንባታቸውን ማስቀጠል ከባድ መሆኑንም የጠቀሱ አሉ፡፡ ይህ ሥጋት የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ሕልውና ጭምር እየተፈታተነ ነው፡፡

  እንዲያውም ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ሁነኛ ሚና ያላቸው አንዳንድ ግንባታዎች፣ በግንባታ ግብዓቶች ዋጋ መናር አደጋ ላይ መሆናቸውን የጠቆሙ አሉ፡፡ እንዲህ ያለ የዋጋ ውድነት ሲከሰት መንግሥት ሁኔታውን በአግባቡ ተረድቶ ፈጣን ምላሽ ካልሰጠ ደግሞ ጉዳቱ ሰፊ መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡

  በተለይ ከብር ምንዛሪ ለውጡ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የዋጋ ለውጥ የሚያስተካክልበት መንገድ ካልተፈለገ፣ በርካታ ፕሮጀክቶች ሊቆሙ ይችላሉ የሚል ሥጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ ችግሩ በዚህ ብቻ የሚያቆም ሳይሆን በአገሪቱ በርካታ ዜጐችን ቀጣሪ ነው በሚባለው የግንባታ ዘርፉ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች የሥራ ዋስትናም አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ በጥናቱም እንዲህ ያሉ ሥጋቶች የተንፀባረቁ ሲሆን፣ እንደመፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውንም አንዳንድ ነጥቦች አስቀምጧል፡፡ እንደመፍትሔ ካስቀመጠው ውስጥ አንዱ የዋጋ ዕድገቱን የሚመጣጠን ማካካሻ መደረግ ያለበት መሆኑን ነው፡፡ ከማኅበሩም ሆነ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ከሰጡ ኮንትራክተሮች መገንዘብ እንደሚቻለው፣ በምንዛሪ ለውጡ ሳቢያ የተፈጠረው ችግር መፍትሔ አልተበጀለትም፡፡ በመሆኑም የሚቆሙ ፕሮጀክቶች ካሉ መልሶ ወደ ሥራ ማስገባት ከባድ መሆኑን ነው፡፡ በተለይ ከቆሙ በኋላ ደግሞ በድጋሚ በጨረታ ማስተላለፍ ቢፈለግ አደጋው የበለጠ ይሆናል፡፡ ይህም ተቋርጠው በድጋሚ ጨረታ የተላለፉ ፕሮጀክቶች ዋጋ መጀመሪያ ከነበረው የግንባታ ዋጋ በ200 በመቶና ከዚያም በላይ በሆነ ዋጋ ሊጠየቅባቸው ስለሚችል፣ አሁን ያለውን ክፍተት አይቶ የማስተካከያ ዕርምጃ ቀድሞ መውሰድ ጠቀሜታ አለው ይላሉ፡፡

  በዘርፉ የተሰማሩ ኮንትራክተሮች እንደሚጠቁሙት፣ በተለይ የዋጋ ጭማሪው የተደረገው የብር የምንዛሪ ለውጡ መደረጉ በተሰማ ማግስት በመሆኑ የግንባታ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፡፡

  አንዳንድ ምርቶችንም ከዓለም አቀፍ ዋጋው በላይ በአገር ውስጥ እንዲሸጡ መደረጉና ይህም ቁጥጥር የማይደረግበት መሆኑ ችግሩን አባብሷል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ተጠይቆባቸው የሚገቡ ምርቶች ዋጋቸው በግልጽ እየታወቀ፣ እዚህ ሲደርሱ የሚሸጡበት ዋጋ የተለየ ሆኖ ሲገኝ ለምን ይህ ሆነ የሚል ጥያቄ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ያለመደረጉ ሌላው ችግር ሆኖ ተጠቅሷል፡፡

  ማኅበሩ ያስጠናው ጥናት ባለፈው ሳምንት ይፋ ሲደረግ እስከ ጥር ድረስ ያለውን ገበያ መሠረት በማድረግ ሲሆን፣ ከዚህ ጥናት በኋላ ያለው የገበያ ሁኔታም የበለጠ ውድነት የሚታይበት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ አሁንም ችግሩ ለማሳየት ተጨማሪ ጥናት እየተደገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

       ከዚህ ጋር ተያይዞ በአገር ውስጥ ያለው የግብይት ሥርዓትም ቢሆን አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህ ሳምንት ለሚሠሩት ሥራ ብረት የገዙ አንድ ኮንትራክተር፣ መንግሥት የብረት ገበያን በአግባቡ መቆጣጠር እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አሁን አሁን በኮንስትራክሽን ግብዓት አምራች ፋብሪካዎች እየታየ ያለው የብረትና መሰል ምርቶች የሽያጭ ሒደት፣ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የተመቸ አይመስልም፡፡

  ይህም የሆነበት ምክንያት መንግሥት በተለይ ለብረትና ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ ባዘዘበት ወቅት፣ ፋብሪካዎቹ የሚሸጡበትን ዋጋ ጨምረው ደረሰኝ የሚቆርጡት ግን ባነሰ ዋጋ መሆኑ ነው፡፡

  ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሁለት ጉዳት በኮንትራክተሩ ይፈጠራል፡፡ አንደኛ የገዛውን ትክክለኛ ደረሰኝ የማያገኝ በመሆኑ ለኪሳራ ሊዳርገው ይችላል፡፡ ሁለተኛው ሥጋት ደግሞ በኮንትራት ሕግ መሠረት ማካካሻ የሚገባው ቢሆን እንኳን ይህንን ዕድል እንዳያገኝ ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ከፋብሪካዎቹ ማግኘት ያለበት ታክስ እንዳያገኝ የሚያደርግ በመሆኑ፣ እንዲህ ያለው ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት እኚሁ ኮንትራክተር ይገልጻሉ፡፡

  የኢትዮጵያ የደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ያስጠኑትን ጥናትና አሁንም እያስጠኑ ያሉትን ጥናት በማያያዝ መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ለሚመለከታቸው አካላት ያቀርባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች