Monday, February 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የስንዴ እጥረቱ የፈጠረው የገበያ አለመረጋጋት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከስድስት ወራት በፊት ከሸማቾች ማኅበራት መደብሮች አንደኛ ደረጃ የሚባለውን የስንዴ ዱቄት  ከአሥር እስከ አሥራ ሁለት ብር፣ ሁለተኛ ደረጃ የሚባለውን ደግሞ በስምንት ብር መግዛት ይቻል ነበር፡፡ ከሦስት ወራት ወዲህ ግን በሸማቾች ማኅበራት መደብሮች ዱቄት እንደልብ ማግኘት ከባድ በመሆኑ፣ ሸማቾች የግድ ወደ ችርቻሮ መደብሮች መሄድ ግድ እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ አምባሻ በመጋገር ለምትሠራበት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የምትሸጠዋ ወ/ሮ የሺ (ስሟ ተቀይሯል) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሸማቾች ማኅበር ዱቄት ማግኘት ባለመቻልዋ ስምንት ብር ትገዛ የነበረውን አንድ ኪሎ ዱቄት፣ ከችርቻሮ መደብሮች በ12 ብር ለመግዛት መገደድዋን ትገልጻለች፡፡ ከሦስት ሳምንታት ወዲህ ደግሞ አንዱ ኪሎ ዱቄት 18 ብር መድረሱ ሥራዋ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉንና ታገኝ የነበረው ትርፍ በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀነሰባት ታስረዳለች፡፡ የዚህ ሳምንት የአንድ ኪሎ ዱቄት ዋጋ ደግሞ 23 ብር በመድረሱ በዚህ ዋጋ ዱቄት ገዝቶ መሸጥ የሚያዋጣ እንዳልሆነለት ትገልጻለች፡፡

ተጠቃሚዎቹ እንደሚሉት የአንድ ኪሎ የዱቄት ዋጋ የዚን ያህል የደረሰበት ጊዜ አልነበረም፡፡ የዱቄት ዋጋ በአንድ ጊዜ የዚህን ያህል ደረጃ መድረሱ እንደ የሺ ያሉትን ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ዳቦ ቤቶችንም እየፈተነ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ሦስት ሳምንታት የዱቄት ዋጋ መወደድ ብቻ ሳይሆን በቂ ዱቄት እየቀረበላቸው ባለመሆኑ ሸማቹ በሚፈልገው ልክ ዳቦ ጋግረው ማቅረብ እንዳላስቻላቸው ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በጣም ተወደደ ቢባል 1100 ብር የሚገዙት ዱቄት፣ አሁን ከሁለት ሺሕ ብር በላይ መሆኑ በሥራቸው ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡

በተለይ ድጎማ የተደረገበትን ስንዴ ፈጭተው ለዳቦ ቤቶቹ የሚያቀርቡ የዱቄት ፋብሪካዎች የሚሰጣቸው ስንዴ በመቀነሱ እንደ ልብ ለዳቦ ቤት ማቅረብ አልቻሉም፡፡ በርካታ ዳቦ ቤቶች ድጎማው ከማይመለከታቸው የዱቄት አምራቾች፣ ኩንታሉን እስከ 1,800 ብር እየገዙ እየተጠቀሙ ነው፡፡ በዚህ ዋጋ ገዝተው ባመጡት ዱቄት የሚሸጡት ዳቦ፣ በቀደመው ዋጋ ሳይሆን ዋጋ ጨምረውና መጠን ቀንሰው እስከመሸጥ አስገድዷቸዋል፡፡  

ከዱቄት አምራቾች መረዳት እንደምንችለው ለዱቄት ዋጋ መወደድ ዋናው ምክንያት የስንዴ መወደድና መንግሥት በድጎማ ስንዴ ሲያቀርብላቸው ለነበሩ ዱቄት አምራቾቸ ይሰጣቸው የነበረው ስንዴ በመቀነሱ ነው፡፡

አንድ ኩንታል ስንዴ ከ1200 እስከ 1500 ብር እየተገዛ ነው፡፡ ከእህል በረንዳ በተገኘ መረጃ መሠረት በዚህ ሳምንት አንድ ኩንታል ስንዴ ከ1,400 እስከ 1,500 ብር እንደተሸጠ ያሳያል፡፡ የስንዴ ዋጋ የዚህን ያህል ዋጋ ያወጣበት ጊዜ እንዳልነበረም ሸማቾች ያስታውሳሉ፡፡ በቂ ስንዴ ገበያ ላይ እንደሌለም ያመለክታሉ፡፡

የስንዴ ዋጋ መወደድ መዘዝ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ እንደ ሞኮሮኒ ፓስታ ያሉ ምርቶችም በቂ የምርት ግብዓት ባለማግኘታቸው ምክንያት ዋጋ መጨመራቸው እየተገለጸ ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ የፓስታና የሞኮሮኒ መሸጫ ዋጋ አራት ጊዜ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገበት የችርቻሮ መደብር ባለቤት የሆነችው ትግስት ትገልጻለች፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት አምስት ጊዜ በጅምላ በምትረከበው ፖስታና ሞኮረኒ ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረጓን ታስረዳለች፡፡

 ከሁለት ወራት በፊት አንድ የአገር ውስጥ ፓስታ 12 ብር ተረክባ፣ 13 ብር ትሸጥ ነበር፡፡ በዚህ ሁለት ወራት ውስጥ ሃምሳና አንድ ብር እየጨመረች አሁን የችርቻሮ ዋጋው 16 ብር ገብቷል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጭማሪ በረዥም ጊዜ የሚከሰት ቢሆንም፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ የታየው ተደጋጋሚ ጭማሪ ግን ከዚህ በፊት በተለየ በአጭር ጊዜ ልዩነት በተደጋጋሚ የተከሰተ እንደሆነም ትገልጻለች፡፡ ‹‹ለእኔ ለደንበኞች በሳምንትና በሁለት ሳምንት ልዩነት የሞኮሮኒና የፓስታ ዋጋ ጨምሯል ማለት እያሳቀቀኝ ነው፤›› የምትለው ትዕግስት፣ የአንዱ ኪሎ ሞኮሮኒ መሸጫ ዋጋ በአሁኑ ሳምንት 28 ብር መድረሱን ትገልጻለች፡፡ ከአንድ ወር በፊት ግን አንዱን ኪሎ መኮሮኒ ከ18 እስከ 20 ብር ትሸጥ እንደበር አስታውሳለች፡፡ ከአንድ ወር ወዲህ ግን በተደጋጋሚ ከማከፋፈያ የተደረገው ጭማሪ ዋጋውን 28 ብር አድርሶታል፡፡

የስንዴ ዋጋ መውረድ ዋናው ችግር በቂ ምርት በአገር ውስጥ አለመኖሩ ሲሆን፣ የስንዴ ፍላጎትን ለመሙላት ሲባል ከውጭ የሚገባው ስንዴ ጨረታ በተደጋጋሚ መሰረዝም ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡     

ከኢትዮጵያ ዱቄት አምራቾች ማኅበር የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በተለይ ባለፉት ሁለት ወራት ዱቄት አምራቾች እጥረት ያጋጠማቸው መንግሥት በድጎማ የሚሰጠው ስንዴ በመቀነሱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዱቄት አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉነህ ለማ፣ የዱቄት እጥረቱ የተፈጠረው መንግሥት በድጎማ ለዱቄት ፋብሪካዎች ይሰጥ የነበረው ስንዴ ኮታ ከመቀነሱ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ያረጋግጣሉ፡፡ መንግሥት ኅብረተሰቡን ለመጥቀም ሲል በኢትዮጵያ ንግድ ኮርፖሬሽን በኩል በወር 600 ሺሕ ኩንታል ስንዴ በድጎማ ዋጋ ለዱቄት ፋብሪካዎች ያከፋፍላል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት ግን የሚሰጠው ስንዴ በግማሽ በመቀነሱ፣ በዚህ ድጎማ የሚጠቀሙ የዱቄት ፋብሪካዎች ለዳቦ ቤቶችና ለሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚሰጡትን ዱቄት እንዲቀንሱ አድርጓቸዋል፡፡

በተከሰተው እጥረት አዲስ አበባ ላይ በየወሩ የሚከፋፈለው 165,657 ኩንታል ስንዴ በግማሽ እንዲቀነስ መደረጉን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የግብይት ተሳትፎ ቢሮ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ቢሯቸው የተከሰተውን እጥረት ለመቅረፍ በጊዜያዊነት ከሌሎች ተቋማት በብድር የተገኘን ስንዴ እያከፋፈለ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ያለውን የዳቦ አቅርቦት ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንደፈጠረ ያመለክታሉ፡፡ አንዳንድ ወገኖች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ደግሞ፣ አሁን ላለው የስንዴ እጥረትና የዋጋ መወደድ ከወራት በፊት በአገር ውስጥ ያለውን የስንዴ መጠን በትክክል ከማሳወቅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በገበሬ እጅ አለ ተብሎ የተገመተውና በተግባር ወደ ግዥ ሲገባ የተገኘው የስንዴ ምርት መጠን አለመመጣጠን እንዲሁም ያለውን የስንዴ ክምችት አይቶ ከውጭ ስንዴን ካለማስገባት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

አቶ ሙሉነህ ይህ ሐሳብ ትክክል ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ ሌላው ችግር ግን በዚህ ክፍተት መሀል የስንዴ እጥረት አለ ሲባል ሁሉም ገዝቶ ማስቀመጡም በአንድ ኩንታል ስንዴ ዋጋ ላይ እስከ 200 ብር ጭማሪ ሊያሳይ ችሏል፡፡ ይህም ለችግሩ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

ዋናው ጉዳይ ግን ላለፉት ሁለት ወራት የተፈጠረው እጥረት መንግሥት በድጎማ የሚሰጠው ስንዴ በግማሽ መቀነስና ይህንን ተረድቶ በወቅቱ ማቅረብ ባለመቻሉ ነው፡፡ በአዲስ አበባ 40 በመቶ የሚሆኑ ዳቦ ቤቶች በድጎማ ከመንግሥት በሚሰጠው ስንዴ ዱቄት የሚጠቀሙ መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ሙሉነህ፣ ለእነዚህ የሚቀርበው ዱቄት መቀነስ በድጎማ የሚቀርበውን ዱቄት የማይቀበሉ ዳቦ ጋጋሪዎች ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረ ነው፡፡

በተለይ የስንዴ ዋጋ በአንድ ጊዜ እስከ 1,400 ብር መድረሱ የዱቄት የችርቻሮ ዋጋ ከ2,000 ብር ሊደርስ ችሏል፡፡ በዚህ ዋጋ ገዝቶ 100 ግራም ዳቦ በአንድ ብር ከ30 ሳንቲም መሸጥ ከባድ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት በድጎማ ስንዴ የሚቀርብላቸው አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ፋብሪካዎች 39 ናቸው፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች የሚያመርቱትን ዱቄት በየክፍለ ከተማው ላሉ ከ1,200 በላይ ዳቦ ቤቶች እያቀረቡ ነው፡፡ ቀሪዎቹ 60 በመቶ የሚሆኑ ዳቦ ቤቶች ደግሞ የዱቄት ግዥውን የሚፈጽሙት ከድጎማ ውጭ በሚገባው ስንዴ በተዘጋጀው ዱቄት በመሆኑ ሥራቸው ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ አንዱን ኩንታል ስንዴ በ1,400 ብር ገዝተው አበጥረው፣ ፈጭተውና አሽገው ሲያቀርቡ ዋጋው እስከ ሁለት ሺሕ ብር ሊደርስ ስለሚችል መንግሥት በድጎማ የሚያቀርበው ስንዴ መቀነስ አጠቃላይ ገበያውን እንደበረዘው ያስረዳሉ፡፡

እንደ አቶ ሙሉነህ ገለጻ መንግሥት በድጎማ አንዱን ኩንታል ስንዴ ለዱቄት ፋብሪካዎች የሚሸጠው 550 ብር ነው፡፡ ዳቦ ቤቶች ደግሞ ከዱቄት አምራቾቹ ዱቄቱን የሚረከቡት በ796 ብር መሆኑም ተገልጿል፡፡ በመላ አገሪቱ በድጎማ የሚከፋፈለው ስንዴ በወር 600 ሺሕ ኩንታል ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ለአዲስ አበባ ዱቄት ፋብሪካዎች የሚሰጠው ወደ 160 ሺሕ ኩንታል እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት በድጎማ የሚሰጠውን ስንዴ ማቋረጥ የሌለበት መሆኑ ነው፡፡ አቶ ሙሉነህም እንደሚሉት፣ እንደ አሁን ያለው ችግር እንዳይከሰት መንግሥት በድጎማ የሚያቀርበውን ስንዴ በትክክል መስጠትና አሠራሩንም መቆጣጠር ያስፈልገዋል፡፡

ሌላው መንግሥት ይህንን አለማድረጉ አጠቃላይ ገበያውን የሚበርዝ በመሆኑ የስንዴ ግዥውን ክምችቱ ከማለቁ በፊት ማድረግ እንደሚገባው ነው፡፡ የስንዴ ግዥ ጨረታ በተደጋጋሚ መሰረዙ ግን ችግሩን እንዲባባስ ሊያደርገው እንደሚችል ተሠግቷል፡፡

መንግሥት ግን አሁን ከመጠባበቂያ ክምችት በማውጣት የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ እየሞከርኩ ነው ቢልም፣ አሁንም እጥረቱ እንዳለ ነው፡፡ አቶ ሙሉነህ ደግሞ ከመጠባበቂያ ሰሞኑን የተሰጠው ስንዴ በተወሰነ ደረጃ ያለውን ችግር እየቀነሰ ቢሆንም፣ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ የቀረፈ ያለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች