የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር ቅድመ ሁኔታ የሌለበት ዋስትና ከመስጠት ጋር ተያይዞ፣ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ቅሬታ አስነሳ፡፡
ባለሥልጣኑ ከአራት ዓመታት በፊት የዋስትና ሰጪ (ኢንሹራንስ) ኩባንያዎች፣ መስጠት ያቆሙትን ቅድመ ሁኔታ የሌለው ዋስትና እንዳይሰጡ መከልከሉ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከቀረጥ ነፃ የገቡ በተለይም የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም አገልግሎቶቻቸውን ሲጨርሱ ከአገር እንዲወጡ የሚጠበቅባቸው ተመሳሳይ ዕቃዎች ላይ ያልተሰበሰቡ ግብርና ቀረጥ ለመሰብሰበ ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
በዚህም ዕርምጃ የቃሊቲ ቅርንጫፍ ብቻ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ከአገር ውስጥ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መሰብሰብ ችሏል፡፡ ይህንን ዕርምጃ ለመውሰድም በሚል ባለሥልጣኑ በጊዜያዊነት የአንዳንድ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የባንክ አካውንት እንዳይንቀሳቀስ አግዶ ነበር፡፡
በዕርምጃው ምክንያት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በማኅበራቸው አማካይነት ቅሬታቸውን ለባለሥልጣኑ አስገብተው ነበር፡፡ በቅሬታቸውም መሠረት አንዳንድ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባልሰጡት የዋስትና ሰነድ ሌላ ድርጅት ዋስትና የሰጠበትን ዕዳ እንዲከፍሉ የሚጠየቁበት አሠራር መኖሩን፣ ዋስትና የተሰጠበት ዕዳ አልተከፈለም በሚልም የድርጅቶቹ የባንክ ሒሳብ ሲታገድ ከዕዳው ጋር ተመጣጣኝ ገንዘብ ሲገባው የድርጅቶቹ ገንዘብ በሙሉ የሚታገድበት ሁኔታ መኖሩን፣ እንዲሁም የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የተጠየቀውን ዕዳ ከፍለው ገንዘባቸውን ከአስመጪው ለማስመለስ በሚያደርጉት ጥረት፣ ባለሥልጣኑ ትብብር እንደማያደርግላቸው የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለሥልጣኑ በወሰደው ዕርምጃ አብዛኛዎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ክፍያ እንዲፈጸሙ ተጠይቀው እንደነበር ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል፡፡
ለአብነት አፍሪካ ኢንሹራንስ ኩባንያ 13.6 ሚሊዮን ብር ያህል ተጠይቆ ነበር፡፡ ለዚህም ሲባል ባለሥልጣኑ በጊዜያዊነት የድርጅቱን የባንክ አካውንት እንዳይንቀሳቀስ አግዶ ነበር፡፡
‹‹ይህ ተቀባይነት የሌለው ዕርምጃ ነው፤›› ሲሉ ለሪፖርተር የተናገሩት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኪሮስ ጅራኔ፣ የተጠቀሰው ገንዘብ የተጠየቀው በአግባቡ ሳይጣራና ሰነዶች በአግባቡ ሳይፈተሹ ነው ብለዋል፡፡
‹‹በኋላ ድርጅቱ የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል የማይገባው መሆኑንና ከዚህ ቀደም የተፈታ መሆኑ ተረጋግጧል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ በቀረበው ቅሬታ መሠረት ባለሥልጣኑ በሰጠው ምላሽ፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚጠየቁት የዕዳ ክፍያ ጥያቄ በአግባቡ ተጣርቶ ዕዳው ድርጅቱን የሚመለከት መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበት፣ የባንክ ሒሳብ በሚታገድበት ጊዜ ከዕዳው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ ወይም ንብረት ብቻ መሆኑ እንዲረጋገጥ፣ እንዲሁም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተጠየቁትን ዕዳ ለባለሥልጣኑ ከፍለው ገንዘባቸውን ከአስመጪው ለማስመለስ ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ፣ ከባሥልጣኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ትብብር ይደረግላቸው ብሏል፡፡