እናት ባንክ አክሲዮን ማኅበር ሳትኮን ኮንስትራክሽን ለተባለ የሥራ ተቋራጭ የገባውን ዋስትና በተደጋጋሚ እንዲከፍል ሲጠየቅ ሊከፍል ባለመቻሉ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የስድስት ሚሊዮን ብር የፍትሐ ብሔር ክስ መሠረተበት፡፡
ባለሥልጣኑ በእናት ባንክ አክሲዮን ማኅበር ላይ ክሱን ሊመሠርት የቻለው፣ ከሰመራ-ዲዲግሳ ከሚያሠራው የመንገድ ግንባታ ጋር በተገናኘ በገባው ዋስትና ምክንያት ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ግንባታውን ከሳትኮን ኮንስትራክሽን ጋር ጥር 29 ቀን 2000 ዓ.ም. ውል ሲፈራረም ግንባታውን ሲያጠናቅቅ የሚመልሳቸው አሥር ተሽከርካሪዎች ለሥራ ተቋራጩ ያስረከበ ቢሆንም፣ የሥራ ተቋራጩ ግንባታውን ካጠናቀቀበት ከግንቦት 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ተሽከርካሪዎቹን በተረከበበት አግባብ ጠግኖ ሊመልስለት እንዳልቻለ በክሱ ገልጿል፡፡
ባለሥልጣኑ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም የሥራ ተቋራጩ ተሽከርካሪዎቹን ሊመልስለት ባለመቻሉ፣ የ6,043,889 ብር የዋስትና ሰነድ ዋስትና የሰጠውን እናት ባንክ እንዲከፍለው ክሱን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት አቅርቧል፡፡
በመሆኑም ባንኩ የሰጠው የዋስትና ሰነድ ያለ ቅድመ ሁኔታና ያለ ምንም ተቃውሞ፣ ባለሥልጣኑ የክፍያ ጥያቄውን ካቀረበበት ከታኅሳስ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍለው ውሳኔ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን ዳኝነት ጠይቋል፡፡