- ሉሲዎቹ ወደ ሥፍራው ያቀናሉ
የአፍሪካ እግር ኳስ ውድድሮች በአምስት ዞኖች ተከፋፍሎ መከናወን ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከሁሉም ዞኖች በደካማ የእግር ኳስ እንቅስቃሴው ብቻ ሳይሆን፣ ቋሚና ወጥ የሆነ የውድድር መርሐ ግብር እንደሌለው የሚታወቀው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) ነው፡፡
በአብዛኛው በኪስዋህሊ ተናጋሪዎች የሚታወቀው ይህ ዞን፣ ወጥ ባልሆነ መርሐ ግብሩ ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙዎቹ አገሮች በመደበኛው የውስጥ ፕሮግራሞቻቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ ስለመሆኑ ጭምር ይነገራል፡፡ በዚህም በተለይ ኢትዮጵያ የደቡቡን ዞን ብትቀላቀል ለውስጥ የውድድር መርሐ ግብሯ ብቻ ሳይሆን ለእግር ኳሱ ዕድገት የተሻለ እንደሚሆንም የሚያምኑ አሉ፡፡
ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ከግንቦት 3 እስከ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ላይ እንደሚሳተፍ ታውቋል፡፡ ቡድኑ ከሚያዝያ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ መደበኛ ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡
በዚሁ መሠረት ለብሔራዊ ቡድኑ 24 ተጫዋቾች ተመርጠዋል፡፡ እነርሱም ቀጥለው የተመለከቱት ናቸው፡፡ ከመከላከያ ማርታ በቀለ፣ ከሐዋሳ ከተማ ዓባይነሽ ኤርቂሎና ምርቃት ፈለቀ፣ ከደደቢት መስከረም ኮንካ፣ ሰናይት ቦጋለ፣ ሎዛ አበራና ትዕግሥት ዘውዱ፤ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትዕግሥት መዓዛ፣ ፅዮን እስጢፋኖስ፣ ታሪኳ ዴብኮ፣ ዙሌይካ ጁሃድ፣ ሕይወት ዳንጊሶና ረሒማ ዘርጋው፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ መሰሉ አበራ፣ ብዙአየሁ ታደሰ፣ ቤዛዊት ተስፋዬና ቤተልሔም ሰማን፤ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ቤተልሔም ከፍያለውና ዓለምነሽ ደመቀ፣ ከዲላ ከተማ ገነማ ወርቁ፣ ከኢትዮጵያ ወጣቶች አካዴሚ አረጋሽ ካልሳ፣ ከጥረት ኮርፖሬሽን ታሪኳ በርገና፣ ከአዳማ ከተማ ሴናፍ ዋቁማና ከድሬዳዋ ከተማ ፀጋነሽ ተሾመ መሆናቸው ታውቋል፡፡