Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየእግር ኳሱ ጉባዔ ስያሜውን የሚመጥን ውሳኔ እንዲያሳልፍ ተጠየቀ

የእግር ኳሱ ጉባዔ ስያሜውን የሚመጥን ውሳኔ እንዲያሳልፍ ተጠየቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዓለም አቀፍ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (ፊፋ) የተላከውን የምርጫ ሕግ ለማፅደቅ ለቅዳሜ ሚያዝያ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ጠቅላላ ጉባዔውን ጠርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላላ ጉባዔው ፊፋ ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት ቀጣዩን የፌዴሬሽኑን ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለመምረጥ የሚያስችለውን አዲስ አስመራጭ ኮሚቴ እንደሚሰየም ይጠበቃል፡፡

ሂደቱን በተመለከተ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር፣ ፊፋ ቀደም ሲል የነበረው አስመራጭ ኮሚቴ እንዲበተን ማዘዙ የሚታወስ መሆኑ ነው፡፡ ፊፋ ቀደም ሲል የነበረውን አስመራጭ ኮሚቴ እንዲበተን ትዕዛዝ ያስተላለፈው ደግሞ በዋነኝነት አስመራጭ ኮሚቴው የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚገኝበት አቋም ገለልተኛና ነፃ አይደለም በሚል ምክንያት በመሆኑ ነው፡፡

እነሱም ገለልተኛነታቸው ብቻ ሳይሆን፣ የኮታ አሠራርን በተከተለ አግባብ የመጡ፣ ከሁለት ጊዜ በላይ በአስመራጭነት ያገለገሉና የመንግሥት ተሿሚዎች ጭምር የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር፣ ቀደም ሲል ‹‹ነፃና ገለልተኛ አይደለም›› በሚል ምክንያት ነው እንዲበተኑ የተደረገው፡፡

አሁን ደግሞ ፊፋ አዲስ በላከው የምርጫ ሕግ ውስጥ አዲስ የሚመረጠው አስመራጭ ኮሚቴ፣ ለምርጫ እንዲቀርብ የሚደረገው ባለው የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መሆኑ፣ ከነባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደግሞ ሰባ በመቶ ያህሉ እንደገና ለምርጫ የሚቀርቡ ከመሆናቸው አንፃር የዚህኛውስ ነፃነትና ገለልተኛነት ማረጋገጫው ምንድነው? የሚል ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል፡፡

ይህን ጥያቄ በሚገባ ማጤን ደግሞ መቋጫ ላጣው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የተሳካ የፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለመምረጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እልባት ለመስጠት የሚያስችል ከመሆኑ አንፃር፣ የአስመራጭ ኮሚቴ ምርጫው ከአቀራረቡ ጀምሮ ስብጥሩ ጥንቃቄ የሚሻ፣ ለሌላ ውዝግብ በር የማይከፍት መሆን እንዳለበት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ግለሰቦች ማሳሰቢያ አዘል ጥቆማዎቻቸውን ይሰጣሉ፡፡

ከእነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል በክለብ ሥራ አስኪያጅነት ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ቡና፣ አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅነት የሚታወቁት አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ አቶ ገዛኸኝ ከሆነ፣ ፊፋ ምንም እንኳን አዲሱን የአስመራጭ ኮሚቴ ዝርዝር ለጉባዔው የሚያቀርበው አሁን በኃላፊነት ባለው የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቢሆንም፣ ያንን ተቀብሎ የማፅደቅም ሆነ ያለማፅደቅ ሙሉ ሥልጣን ያለው ደግሞ ጉባዔው በመሆኑ ይህ አካል አርቆ ማስተዋል ይጠበቅበታል፡፡

‹‹ምክንያቱም ጉባዔው የእግር ኳሱ ትልቁ የሥልጣን አካል እሱና እሱ ብቻ ነው፡፡ ያለፈው ውዝግብና ንትርክ እንዳይደገም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የመፍትሔው አካል መሆን ይኖርበታል፤›› የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ ‹‹ያለፈው ዓይነት ማለትም ከእግር ኳሳዊው ምልከታ ይልቅ እርስ በራሱ በሚጣረስ ከአካባቢያዊ ስሜት ተላቆ፣ የስፖርቱን ቀጣይ አቅጣጫና ዕድገቱን ለሚያፈጥኑ አስተያየቶች ቅድሚያ ሰጥቶ መወያየትና መከራከር ይኖርበታል፤›› ይላሉ፡፡

እንደ አቶ ገዛኸኝ ሁሉ ሌሎችም የስፖርቱ ባለሙያተኞች፣ ‹‹የፊፋን ሕግ ግለሰቦቹ ለሚፈልጉት ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዲሆን፣ በዋናነት የጠቅላላ ጉባዔው ክፍተትና ደካማነት መሆኑን ይስማማሉ፡፡ እንደ አንድ የእግር ኳስ ትልቅ የሥልጣን አካል የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ስያሜውን የሚመጥን ቢሆን ኖሮ፣ የእግር ኳሱ የውስጥ ገመና ሰው የሌለው እስኪመስል አደባባይ ባልወጣ ሲሉ የሚከራከሩት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ አሁንም ለሌላ ውዝግብና ንትርክ ላለመዳረግ ጉባዔው ሰከን ብሎ በማሰብ የመፍትሔውን አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅበት ያሳስባሉ፡፡

ፊፋ በቅርቡ የላከው የምርጫ ሕግ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የደረሰው ከ10 ዓመት በፊት ታውቋል፡፡ የምርጫ ሕጉ ከመጣ በኋላ ሁለት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫዎች ተከናውነዋል፡፡ ይሁንና የዚህ የምርጫ ሕግ ጉዳይ ግን ተነስቶ መሆን ስለሚገባው ውይይትም ሆነ ክርክር አስነስቶ እንደማያውቅ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ጉባዔው አሁንም በተቋሙ ሊኖር ስለሚገባው ተጠያቂነትና ግልፀኝነት ትኩረት ሰጥቶና ተነጋግሮ ውሳኔ መስጠት እንደሚጠበቅበት ፅኑ እምነት አላቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...