Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየመድኃኒት አቅርቦትን የሚያሳልጠው ስምምነት

የመድኃኒት አቅርቦትን የሚያሳልጠው ስምምነት

ቀን:

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ልዩ ልዩ መድኃኒቶችን ከመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ በቋሚነት ማግኘት የሚያስችለውን ውል ተፈራርሟል፡፡ ማኅበሩ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚያገለግሉ የስኳር፣ የካንሰር፣ የደም ብዛትና የመሳሰሉትን መድኃኒቶች እንዲሁም በኤጀንሲው መጋዘኖች በብዛት ተከማችተው የሚገኙ መድኃኒቶችን ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡

በአዋጅ የተቋቋመው የመድኃኒት አቅርቦት ፈንድ ኤጀንሲ መድኃኒቶች፣ የሕክምና መገልገያዎችና ሌሎች ግብአቶችን ለመንግሥት የጤና ተቋማት እንዲያቀርብ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ ኤጀንሲው ከመንግሥት የጤና ተቋማት ውጭ ላሉ የግል የጤና ተቋማትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች መድኃኒት እንዲያቀርብ የሚገደድበት አግባብ ያልተጠበቀ የመድኃኒት እጥረት ሲያጋጥምና ኤጀንሲው ብቻ የሚያስመጣቸው የመድኃኒት ዓይነቶችን ብቻ እንደሆነ የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወ/ሮ አድና በሬ ገልጸዋል፡፡

‹‹መድኃኒት ክምችት እኛ ጋ እያለ በጤና ተቋማት የለም ተብለው የሚንከራተቱ ሰዎችን እንድንደርስ ያደርገናል፤›› የሚሉት ወ/ሮ አድና ስምምነቱ የአቅርቦት ሰንሰለቱን የሚያሳልጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

የጣሊያን ወረራ በፊት በሐምሌ 1927 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በአሁኑ ወቅት 40 ፋርማሲዎችና የመድኃኒት መደብሮች በአገር አቀፍ ደረጃ አሉት፡፡ ከውጭ የሚያስመጣቸውንና በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ከመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ቅርንጫፎች የሚገዛቸውን መድኃኒቶች በፋርማሲዎቹ ያሰራጫል፣ መጠነኛ ትርፍ በመያዝም ለማኅበረሰቡ ይሸጣል፡፡ በየዓመቱም ከ100 ሚሊዮን እስከ 115 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሽያጭ እንደሚያከናውን የማኅበሩ ምክትል ዋና ጸሐፊና የሀብት ልማት ማሰባሰብ ዘርፍ አቶ ወንድአውክ አበዜ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ማኅበሩ በሚቀጥለው ዓመት የፋርማሲና የመድኃኒት መሸጫ መደብሮቹን ቁጥር ወደ 60 የማሳደግ ግብ ይዞ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከኤጀንሲው ጋር የተፈራረመው ውልም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የመድኃኒት የአቅርቦት ፍላጎት ለማርካት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ በ2011 ዓ.ም. የማኅበሩ የመድኃኒት ሽያጭ መጠንም 200 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ ከኤጀንሲው የሚገዛቸው መድኃኒቶች መጠንና ዓይነትም በዚሁ መጠን እየጨመሩ የሚሄዱ ይሆናል፡፡

‹‹መፈራረማችን የመድኃኒት ጥያቄ ባቀረብን ቁጥር አፋጣኝ ምላሽ እንድናገኝ ያደርገናል፤ ከዚህም ባሻገር በጠየቅነው መጠን እንድናገኝ ይረዳናል፡፡ በክምችታቸው በብዛት የሚገኙ መድኃኒቶችን ተቀብለን በፋርማሲዎቻችን ለማኅበረሰቡ እንድናደርስ ይደረጋል፡፡ እኛ ጋ በብዛት የሚገኙ መድኃኒቶችም እንደዚሁ የመጠቀሚያ ጊዜ አልፎባቸው ከመበላሸታቸው አስቀድሞ እነሱ ተቀብለውን የመድኃኒት እጥረት ወዳለበት አካባቢ ማቅረብ እንዲችሉ ያደርጋል፤›› ያሉት አቶ ወንድአውክ ናቸው፡፡ 

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በነዚህ ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለተጋለጡ 7.9 ሚሊዮን ዜጎች ልዩ ልዩ ሰብአዊ ድጋፍ ማድረጉን ከቀናት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡ በእነዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ 560 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል፡፡ ኤልኒኖን ተከትሎ በተከሰተው ድርቅና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰዎችና በእንሰሳት ላይ በደረሱ አደጋዎችም የማኅበሩ ምላሽ ቀላል አልነበረም፡፡ በመሬት መደርመስ፣ በጎርፍና በድርቅ ለተጠቁ ወገኖች የምግብና መድኃኒት፣ የአልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ከ103 ሺሕ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በመመልመል በሰብአዊና በልማት ተግባራት እንዲሳተፉ ማድረጉን፣ በአሁኑ ወቅትም ከ47 ሺሕ በላይ በጎ ፈቃደኞች እንዳሉት፣ የአባላቱ ቁጥርም ወደ 6.1 ሚሊዮን ማደጉን ማኅበሩ ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን እንደርሳለን፡፡ አቅማችን ውስን በመሆኑ እንጂ በየዓመቱ መድረስ የምንችለው የሰዎች ቁጥር እስከ 20 ሚሊዮን እንዲሆን እንፈልጋለን፤›› ሲሉም አቶ ወንድአወክ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የዓለም ቀይ መስቀል ፌዴሬሽን 48ኛ አባል ሆኖ የተመዘገበው በተቋቋመበት ዓመት ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...