Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በቤተሰብ ሐኪም ላይ ያነጣጠረው ሕክምናዊ ጉዞ

ዶ/ር ዮሐንስ ይመር ተወልደው ያደጉት፣ የመጀመርያና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በደሴ ከተማ ነው፡፡ ከዲላ ጤና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በላብራቶሪ ቴክኖሎጂና ከሐያት ሜዲካል ስኩል ደግሞ በሜዲስን ተመርቀዋል፡፡ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፋሚሊ ሜድሰን ሲኒየር ረዚደንት ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ የፋሚሊ ዶክተሮች ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የማኅበሩ መጠሪያ ኢትዮጵያን ሶሳይቲ ኦፍ ፋሚሊ ፊዚሺያንስ ይባላል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ የፋሚሊ ዶክተሮች ማኅበር ማለት ነው፡፡ ማኅበሩ የተቋቋመው ጥቅምት 2008 ዓ.ም. ሲሆን፣ ስፔሻላይዝድ በሚያደርጉና በጨረሱ ሰባት ሐኪሞች የተመሠረተ ነው፡፡ የሶሳይቲው ዋና ዓላማ ከፍ ብሎ በዝርዝር የተጠቀሱትን አገልግሎቶች ተግባራዊ እንዲሆኑና በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለውን የጤና ችግር ለመቅረፍ መሥራት ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው የአባላቱ ቁጥር 40 ደርሷል፡፡ በፋሚሊ ዶክተር፣ በሶሳይቲውና በሌሎችም ተጓደኛ ሥራዎች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም ዶክተር ዮሐንስ ይመርን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓቱ አደረጃጀት እንዴት ይገለጻል?

ዶ/ር ዮሐንስ፡- የጤና ሥርዓቱ ሦስት ደረጃዎች የያዘ መዋቅር አለው፡፡ እነርሱም የመጀመርያ ደረጃ ጤና አገልግሎት፣ ሁለተኛ ደረጃ ጤና አገልግሎትና ሦስተኛ ደረጃ ጤና አገልግሎት ናቸው፡፡ የኅብረተሰቡን ጤና እና የጤና አገልግሎት ሥርዓቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የመጀመርያ ደረጃ ጤና አገልግሎት (ፕራይሜሪ ሔልዝ ኬር) ላይ መሥራት ወሳኝ ነው፡፡ በአብዛኛው ጊዜ በየሆስፒታሉ በየጤና ተቋማቱ ለሚከሰቱ ችግሮች መንስዔ በመጀመርያ ደረጃ ጤና አገልግሎት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ፋሚሊ ሜዲሰን ስፔሻሊስት ወይም ፋሚሊ ዶክተር ክፍተቱን ይሸፍናል፡፡ የመጀመርያ ጤና አገልግሎትን ያጠናክራል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የላቀ የጤና አገልግሎት ለውጥ ይመጣል፡፡ ይህንንም መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራበት መሆኑን ሊታወቅ ይታወቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ፋሚሊ ዶክተር ማለት ምን ማለት ነው? ፋሚሊ ዶክተር ለመሆን ምን ዓይነት የትምህርት ደረጃ ይጠይቃል? ተግባርና ኃለፊነቱስ እስከ ምን ድረስ ነው?

ዶ/ር ዮሐንስ፡-  ፋሚሊ ዶክተር ማለት የቤተሰብ ሐኪም እንደማለት ነው፡፡ የቤተሰብ ሐኪም ለመሆን ደግሞ የመጀመርያውን የዶክትሬት ዲግሪ ማግኘት ይገባል፡፡ ይህን ለማግኘት ደግሞ ስድስት፣ ሰባት ዓመት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መማር ግድ ይላል፡፡ ይህም ከተጨረሰ በኋላ እንደገና ተጨማሪ ለስፔሻላይዜሽን ለሦስት ዓመት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መከታተልና ማጠናቀቅ ይገባል፡፡ ይኼንን ሒደት የጨረሰ ሰው ፋሚሊ ሜዲሰን ስፔሻሊስት ወይም ፋሚሊ ዶክተር ልንለው እንችላለን፡፡ ፋሚሊ ሜዲሰን ስፔሻሊስት ልክ እንደ ሌሎቹ ኢንተርኒስት፣ ሰርጂን፣ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት እንደምንለው ሁሉ ራሱን የቻለ አንድ ስፔሻሊቲ ነው፡፡ ስፔሻሊቲው ግን ለየት የሚያደርገው ሰርጂን ወይም ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ቀዶ ሕክምናውን ብቻ እንጂ ሌላውን አያይም፡፡ የፋሚሊ ዶክተር ወይም ሜዲሰን ስፔሻሊስት ግን ቀዶ ሕክምናውን ጨምሮ በሁሉም የሕክምና ዘርፎች ላይ አለ፡፡ በአጠቃላይ ፋሚሊ ሜዲሰን ስፔሻሊስት ሆኖ ለመውጣት የውስጥ ደዌ፣ ቀዶ ሕክምና፣ ወዘተ ስፔሻሊስት ለመሆን የሚያስፈልገውን መሥፈርት ሁሉ ማሟላት አለበት፡፡ ፋሚሊ ዶክተር ተግባሩ በሁሉም ዕድሜና ፆታ ለሚገኙ ዜጎች በሁሉም ድንገተኛ በሆኑና ባልሆኑ፣ እንዲሁም የውስጥ ደዌ ሕክምናና ለቀዶ ሕክምና አገልግሎቶች መስጠት ነው፡፡ የእናቶችና ሕፃናት ሕሙማንን በጤና ተቋም ወይም ከጤና ተቋም ውጪ ምርመራና ሕክምና በመስጠት ክትትል ያደርጋል፡፡ ጤናን በማበልፀግ፣ በሽታን መከላከል፣ ምርመራ፣ ሕክምና፣ ትምህርትና ሥልጠና መስጠት፣ ጥናትና ምርምር ማድረግና ማማከር፣ የመጀመርያ ደረጃ የጤና ሕክምና አገልግሎት መስጠትና መምራት ዋና ኃላፊነቱና ተግባሩ ነው፡፡ በሥሩ ላሉ ቤተሰቦችና ማኅበረሰቦች በቤት፣ በተዘዋዋሪ፣ በድንገተኛ በተመላላሽ ወይም በሆስፒታል በማስተኛት የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በጤና ኬላና በጤና ጣቢያ የሚሰጡ የቤተሰብ ጤና አገልግሎቶችን በበላይነት ይመራል፡፡ የአገልግሎት ትስስር ስለመፈጠሩ ያረጋግጣል፡፡      

ሪፖርተር፡- በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚታዩ ችግሮች ምን ይመስላሉ?

ዶ/ር ዮሐንስ፡- ሕመምተኞች በግልጽ ችግራቸውን ተገንዝበው መረጃ ለመስጠት አለመቻል፣ ተባባሪ አለመሆን፣ ሁሉንም የጤና ችግሮች ለይቶ ለማከም የችግሮች ስፋትና ጥልቀት መወሳሰብ፣ የጤና ችግሮች መንስዔያቸውን ለመለየት አስቸጋሪ መሆኑ፣ የተወሰኑ መድኃኒቶች ከታካሚው ችግር ጋር ያለመጣጣም ወይም ተጓዳኝ ችግሮች ማስከተል፣ ተደራራቢ የጤና ችግሮች መኖር፣ መድኃኒት የሚወስዱ ሕሙማን መድኃኒት ለመውሰድ ፈቃደኛ አለመሆን፣ የተሃድሶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ሕሙማን ለመለየት የሚረዳ በቂ መረጃ አለማግኘት፣ ሕክምናን በቤትና በሥራ ቦታ የመስጠት ልምድ አለመኖር፣ የቤተሰብ ሕክምና ቡድን የሥራውን ባህሪ አለመረዳት፣ ወረርሽኝና አደጋዎች ሲከሰቱ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችሉ ግብዓቶችና የሰው ኃይል አለመሟላት፣ ትምህርትና ሥልጠና ለመስጠት ክፍተቶችን ለይቶ አለማወቅ፣ ለጥናትና ምርምር በቂ ግብዓትና መረጃ ያለማግኘት፣ የጤና ፖሊሲ ስትራቴጂ ጉዳዮች ላይ ለማማከር የአገሪቱን ተጨባጭ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት አለማወቅና ተቀባይነትን አለማግኘትና የመሳሰሉት ችግሮች ያጋጥሙናል፡፡   

ሪፖርተር፡- የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ዶ/ር ዮሐንስ፡- እዚህንም ችግሮች ለመፍታት ሕሙማኑ በባለሙያው ላይ እምነት እንዲያሳድሩና ተገቢውን መረጃ ለመስጠት እንዲተባበሩ የኮሙዩኒኬሽን (የግንኙነትን) ክህሎትን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ተጨማሪ መረጃዎችን ከሌሎች አካላት በመሰብሰብ ለሕሙማኑ ጉዳት በማያስከትል ሁኔታ በመሣሪያ የታገዙ ምርመራዎችና ሕክምናዎች በማድረግ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል፡፡ ለዚህም የተሻሻሉ ዘዴዎችን ለማወቅና ተግባራዊ ለማድረግ የራስን ዕውቀትና ክህሎት በማዳበር፣ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅዶች ከተገቢ ግብዓት ጋር የማቀድና የማስፈቀድ አቅም ሊኖር ይገባል፡፡ ከዚህ በፊት ላጋጠሙ ችግሮች የተወሰዱ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን በመገንዘብና ተግባራዊ በማድረግ የግል ዕውቀትንና አመዛዛኝነትን በመጠቀም፣ እንዲሁም በዘርፉ የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸውን በማማከር፣ ለሕመምተኛው ተገቢውን ክትትል ማድረግ ሌላው የመፍትሔ አቅጣጫ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህም በላይ አስፈላጊውን መድኃኒት ለውጥ በማድረግ፣ የተሃድሶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ሕሙማን ለመለየት የሚረዱ በቂ መረጃዎችን በተለያዩ መንገዶች፣ በማሰባሰብ፣ ልዩ ልዩ ሳይንሳዊ የምርምር ዘዴዎች በማወቅና ተግባራዊ በማድረግ፣ የማማከርና በቡድን የመሥራት፣ እንዲሁም የመምራትና የማስተባበር ዕውቀትና ክህሎት በማዳበር፣ ነባራዊ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በሚገባ ለመገንዘብ ጥረት በማድረግ፣ በመረጃ ላይ በመመሥረት የፖሊሲ አውጪዎችን በማሳመን ችግሮቹን መፍታት ይቻላል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የፋሚሊ ዶክተር ተጠያቂነትና ሚስጥራዊ መረጃን የመጠበቅ ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?

ዶ/ር ዮሐንስ፡- ፋሚሊ ዶክተሮች የሕክምና አገልግሎት ለሚሰጧቸው ታካሚዎች ቤተሰቦች፣ ማኅበረሰብና ለሕክምናው ሙያ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ የታካሚውን ሁኔታ ለመረዳት በትጋት መሥራትን፣ ታካሚውን በጥልቀት መመርመርን፣ አግባብነት ያላቸውን ምርመራዎች ማዘዝን፣ እንዲሁም የስህተት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን የሚቻለውን ያህል በማስወገድ ወይም በመቀነስ አጠቃላይ የጤና እንክብካቤ ዕቅድ ማውጣትን ይጠይቃል፡፡ ሚስጥራዊ መረጃን አስመልክቶ ደግሞ ከጥቃቅን ግላዊ መረጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉትን ሚስጥር በጥንቃቄ የመያዝ ኃላፊነት አለበት፡፡ እነዚህ መረጃዎች በጥንቃቄና በሚስጥር ባይያዙ በፋሚሊ ዶክተር ወይም በቡድኑ ላይ አመኔታ ያሳጣል፡፡ የተቋሙ አገልግሎት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡

ሪፖርተር፡- የተሳካ የጤና አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ማቅረብ የሚቻለው እንዴት ነው?

ዶ/ር ዮሐንስ፡- ማንኛውም ሕመም የያዘው ሰው በሽታው የሚለየው በመጀመርያ ደረጃ በጤና አገልግሎት ነው፡፡ ሐኪሙ በሽታው ያለበት ደረጃ የተለየ ስፔሻሊስት የሚያስፈልገው ሆኖ ካገኘው ነጥሎ ወደ ጠቅላላ (ጄኔራል) ሆስፒታል ይልከዋል፡፡ ጄኔራል ሆስፒታሉ ደግሞ የዋና የበሽታው ደረጃ ከሐኪሙ በላይ ሆኖ ካገኘው ወደ ተርሸሪ (ስፒሻላይዝድ) ሆስፒታል ይልካል፡፡ ፕራይሜሪ ሔልዝ ኬር ወይም የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል እስከ 100 ሺሕ ሰዎችን ያስተናግዳል፡፡ ከዚህም ቀጥሎ ጤና ጣቢያና ጤና ኬላ (ሔልዝ ፖስት) የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ሥር ደግሞ በማኅበረሰቡ ደረጃ ወደ ታች ሲወርድ ሔልዝ ዴቨሎፕመንት ቲም የሚባል አለ፡፡ አንድ ቲም የጤና አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን ከ20 እስከ 30 አባወራዎችን ይይዛል፡፡ ስለሆነም የጤና አገልግሎቱ ሥርዓት እነዚህን መስመሮች ተከትሎ ነው የሚሄደው፡፡ ይኼንን ሰንሰለት ወይም መንገድ ተከትሎ መሄድ ሲቻል ነው የተሳካ የጤና አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ማቅረብ የሚቻለው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ጤና አገልግሎት ላይ በትክክል ካልተሠራ በሁሉም ተቋማት ላይ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት የተስተጓጎለ ያደርገዋል፡፡ ኅብረተሰቡ በየጊዜው የሚያቀርባቸው የተለያዩ እሮሮዎች መንስዔዎቻቸው በመጀመርያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ላይ በትክክል ባለመሠራቱ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የጤና ኢንሹራንስ ፖሊሲ እንዲተገበር የመጀመርያ ደረጃ ጤና አገልግሎት ወሳኝና ዋናው ቁልፍ ነው፡፡ የተመረጠና በከፍተኛ ደረጃ ሊታከም የሚችለው ደረጃውን ጠብቆ በሪፈራል ሲስተም ሲኬድ ነው፡፡ ይህ ሆነ ማለት በየቦታው የሚከሰተውን መጨናነቅና የቀጠሮ መብዛት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመርያ ደረጃ ጤና አገልግሎት የሚሰጠውን ጥቅም ጠቅለል ባለ መልኩ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ዮሐንስ፡- የመጀመርያ ደረጃ ጤና አገልግሎት ቅድመ በሽታ መከላከልን ያጠናክራል፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታሎች የሚመሩት በፋሚሊ ዶክተሮች መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በዚህ መልኩ የሚመራ የመጀመርያ ደረጃ ጤና አገልግሎት ደግሞ የአገሪቱን ብዙ ችግር ሊቀረፍ ይችላል፡፡ ከማኅበረሰቡም ጋር የጠበቀ ግንኙነትና ትውውቅ ይኖረዋል፡፡ ታካሚው ቀልጣፋና ጥራት ያለው ሕክምና እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡ በሆስፒታል ያለውን እንግልትና ውጣ ውረድ ይቀንሳል፡፡ አላስፈላጊ ሪፈራልን፣ ረዥም የሐኪም ቀጠሮን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ የጤና ኢንሹራንስ ተግባራዊ እንዲሆን ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል፡፡ ሥር የሰደደ ሕመም (ክሮኒክ ኢልነስ) ያላቸውን ታካሚዎች ተከታታይ የሆነ ክትትል ማድረግ ያስችላል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ክትትልም የሕመም መባባስን፣ ሞትን፣ በበሽታ ምክንያት የሚመጣን የኢኮኖሚ ጫናን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አገራዊ የሕክምና አሰጣጡ የተሻለ ጥራት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመርያ ደረጃ ሕክምና አገልግሎትን ለማጠናከር ማኅበሩ ያበረከተው አስተዋጽኦ አለ?

ዶ/ር ዮሐንስ፡- የውስጥ ደዌ፣ ቀዶ ሕክምና፣ ወዘተ በሙሉ የየራሳቸው የሥራ መግለጫ አላቸው፡፡ ፋሚሊ ዶክተር ግን እስካሁን አልነበረውም፡፡ ሚናውም አይታወቅም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሶሳይቲው ከጤና ጥበቃና ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴሮች የሰው ሀብት ልማት ጋር በመተባበርና አንድ ላይ በመሆን በአገሪቱ ተግባራዊ የሆነን የሥራ መግለጫ (ስኮፕ ኦፍ ፕራክቲስ) አዘጋጅቷል፡፡ ከዚህም ሌላ በኢትዮጵያ የመጀመርያ ደረጃ ሕክምና ሥርዓት ውስጥ ፋሚሊ ፊዚሺያን ምን ሚና ይኑረው? የአገሪቱ ዋና የጤና ችግር ምንድነው? የሚለው በዝርዝር እንዲቀርብ ለሶሳይቲው የቤት ሥራ ተሰጥቶት ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የኬንያን፣ የካናዳን፣ የአሜሪካን የእንግሊዝንና የናይጄሪያን ልምድ በመውሰድ ከአገራችን የጤና ችግሮች ጋር የተያያዘ የመነሻ ሐሳብ አዘጋጅተናል፡፡ በቅርቡ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚገባ ሲሆን፣ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡   

ሪፖርተር፡- በባሕር ማዶ ከሚገኙ መሰል ተቋማት ጋር ግንኙነት አላችሁ?

ዶ/ር ዮሐንስ፡- በደንብ አለው፡፡ ከእነዚህም መካከል ከአሜሪካ አካዴሚ ኦፍ ፋሚሊ  ፊዚሺያንና የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ተቋማቱ በተለያየ መንገድ እየረዱንና እያስተማሩንም ነው፡፡ በተለይ ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት በሥልጠና በፋይናንስ በትምህርት ረገድ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...

በርካታ ሐኪሞችን የሚፈልገው የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና

በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ባለፉት አሠርታት የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሆኖም በጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ዘርፍ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ቢሻልም፣ የጨቅላ ሕፃናት...