Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይናው ሹራብ አምራች አሥር ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስገኝ የሚጠበቀውን ፋብሪካ ሥራ አስጀመረየቻይናው ሹራብ አምራች አሥር ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስገኝ የሚጠበቀውን ፋብሪካ ሥራ አስጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቻይናው ሻንቴክስ ሆልዲንግ ግሩፕ ሥር ከሚተዳደሩ በርካታ ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ በመሆን በኢትዮጵያ ሥራ የጀመረው ሎንቶ ጋርመት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ በዓመት አሥር ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል የሚጠበቀውን ፋብሪካ በዱከም መሥርቷል፡፡ ቅዳሜ ሚያዝያ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. የፋብሪካው የምርቃት ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡

ከፋብሪካው ጉብኝት ቀደም ብሎ ስለፋብሪካው ዝርዝር ጉዳዮች ለጋዜጠኞች መግለጫ ተሰጥቶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያውን ሎንቶ ኩባንያ የሚከታተለው የሻንጋይ ድራጎን ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንቷ ሹ ጂፌንግ በሰጡት ማብራሪያ መሠረት፣ በዱከም ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ በሰባት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተመሠረተው የሹራብ ፋብሪካ፣ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በዓመት አሥር ሚሊዮን ዶላር ገቢ የማስገኘት አቅም ይኖረዋል፡፡ ለአሁኑ ግን በሁለት ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2018 ብቻ 50 ሺሕ ሹራቦችን እንደሚያመርት የተነገረለት ሎንቶ ጋርመንት፣ ከወዲሁ ከጣልያን ገዥዎች 30 ሺሕ ሹራብ እንዲያመርትና እስከ ግንቦት ወርም ምርቱን እንዲያቀርብ መታዘዙን ጠቅሰው፣ ገዥዎቹ ምርት ከማዘዛቸው ቀደም ብሎም  ፋብሪካውን እንደጎበኙ ሚስ ጂፌንግ አስታውቀዋል፡፡ ምርቱን ከቻይና ፋብሪካዎቹ ይገዙ የነበሩ ደንበኞቹ በኢትዮጵያ ፋብሪካው የሚመረተውን እንዲገዙ የማድረግ ሥራ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡

ይሁንና ፋብሪካው ሥራ የጀመረበት የኢንቨስትመንት ካፒታል ሁለት ሚሊዮን ዶላር ብቻ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ወደ ውጭ ከሚልካቸው ልዩ ልዩ የሹራብ ምርቶችም ሁለት ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስገኝ ጂፌንግ አስታውቀዋል፡፡ የኢንቨስትመንት ካፒታሉ አነስተኛ ስለሆነበት ምክንያት ተጠይቀው ሲያብራሩም፣ ኩባንያው የገንዘብ ችግር እንደሌለበት፣ ይልቁንም በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ በቅጡ እስኪረዳና እስኪያውቀው በማለት የመደበው የካፒታል መጠን እንደሆነ ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡

ምንም እንኳ የአሁኑ ኢንቨስትመንቱ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ይሁን እንጂ ወደ ፊት የራሱን የኢንዱስትሪ ፓርክ ኢትዮጵያ ውስጥ የመገንባት ሐሳብ እንዳለው፣ ለዚሁ ይረዳው ዘንድም ከወዲሁ በሦስት ከተሞች ላይ ጥናት መጀመሩን ጂፌንግ በአስተርጓሚያቸው በኩል አስታውቀዋል፡፡

እንደ ጂፌንግ ማብራሪያ ሻንቴክስ ሆልዲንግ በዓመት ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያገኝ፣ በሥሩም ከ600 ያላነሱ ኩባንያዎች በ100 አገሮች ውስጥ የሚያንቀሳቀስ ግዙፍ ኩባንያ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሎንቶ ጋርመንት ከወዲሁ ለ400 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ቀስ በቀስም የሰው ኃይሉን ብዛት ወደ 1000 እንደሚያሳድገው አስታውቋል፡፡

ለሠራተኞች ስለሚከፈለው ደመወዝና በሥራ ቦታ ላይ ስለሚደረገው የሥራ ላይ ደኅንነት ሥርዓትም ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ የሎንቶ ጋርመንት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጇ ሃይ ሆንግ ዡ እንዳሉት፣ ለሠራተኞች የሚሰጠው ጥቅማ ጥቅምና መደበኛ ክፍያ ከሥልጠና ይጀምራል፡፡ ሠራተኞቹ ፋብሪካው ከገጠማቸው አዳዲስ የሹራብ ሥራ ማሽኖች ጋር ትውውቅ ስላልነበራቸው ቀድሞ ሥልጠና በመስጠት መጀመሩን ጠቅሰው፣ አንድ ሹራብ ለመሥራት የሚፈጅባቸው ጊዜ እየታየ ቀልጣፋ ለሆኑትና በፍጥነት ለሚያመርቱት በሠሩት መጠን ማበረታቻ እንደሚደረግላቸውና ወርኃዊ ክፍያቸውም የተሻለ የሚባል እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ሆኖ የቻይና ሠራተኞች አንድ ሹራብ ለማምረት ከሚፈጅባቸው ጊዜ አኳያ ሲታይ፣ ኢትዮጵያውያኑ ሠራተኞች ብዙ እንደሚቀራቸው ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ለውጭ ገበያ የሚያቀርባቸው ልዩ ልዩ የወንዶችና የሴቶች ሹራቦችን ሲሆን፣ የምርቶቹ መዳረሻዎችም ጣልያን፣ ቱርክ፣ ቤልጂየም፣ ብራዚል፣ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ሩስያ፣ አሜሪካና ሌሎችም አገሮች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

ሻንቴክስ ሆልዲንግስ ምንም እንኳ በአልባሳት አምራችነቱ በስፋት የሚታወቅ ቢሆንም፣ በፋይናንስ፣ በሪል ስቴት፣ በፋርማውሲቲካልና በሌሎችም በርካታ መስኮች የሚንቀሳቀስ ኩባንያ ነው፡፡ ይህንን በመንተራስም የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ቦጋለ በቀለ በመክፈቻው ዕለት ሲናገሩ፣ ‹‹[የአሁኑ ኢንቨስትመንት] ለመግቢያ ያህል እንጂ እንደ መንግሥት ሻንቴክስ ሆልዲንግ የኢንቨስትመንት መስኮች ያለውን አቅም እንገነዘባለን፤›› ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው መንግሥት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይም ለአምራቹ ዘርፍ ስለሰጠው ትኩረትና፣ በ2017 ዓ.ም. እንደሚደረስበት ስለሚታሰበው በአፍሪካ ቀዳሚውን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የመፍጠር ጉዞ ንግግር አድርገዋል፡፡ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን ከሚያመላክቱ ጉዳዮች ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንደሚገኝበት አቶ ቦጋለ ጠቅሰው፣ በጥቅምት ወር የተደረገው የምንዛሪ ለውጥ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በሚከፈተው የሌተር ኦፍ ክሬዲት ላይ ይታሰብ የነበረው የ3.5 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ ወደ 0.5 በመቶ ዝቅ መደረጉም ለዘርፉ ተዋኖች ከሚደረጉ የማበረታቻ ዕርምጃዎች ውስጥ እንደሚመደቡ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች