Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የስንዴ እጥረትን ለመቅረፍ ከመጠባበቂያ ክምችት 70 በመቶው መሠራጨቱ ተገለጸ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት 800 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከውጭ ለማስገባት ጨረታ ቢያወጣም፣ በተደጋጋሚ የጨረታው ውጤት በመሰረዙ ምክንያት በአገሪቱ የስንዴ አቅርቦት እጥረት ተከስቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህ ቀደም ከመጠባበቂያ ክምችቱ 200 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ሲሰራጭ ቢቆይም፣ መንግሥት በቅርቡ የ300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ተጨማሪ ስንዴ ከመጠባበቂያ በማውጣት ለማሰራጨት ተገዷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ በመሆን ባለፈው ሳምንት የተሾሙት አቶ መስፍን አሰፋ ዓርብ ሚያዝያ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ወቅት እንዳሉት፣ መንግሥት ከሚያከፋፍለው የ300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ውስጥ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮታው መሠረት የሚደርሰውን መጠን እያሰራጨ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

የተፈጠረው እጥረት ለሁለት ሳምንት ያህል የስንዴ ዱቄት የአቅርቦት መቋረጥ ማስከተሉንም አቶ መስፍን አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና በተፈጠረው እጥረት ሳቢያ በዳቦ መሸጫዎች የመጠን መቀነስና የዋጋ መጨመር ድርጊቶች ተስተውለዋል፡፡ እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀናት በነበረው ዋጋ መሠረት አንድ ኩንታል ስንዴ እስከ 1,500 ብር ሲሸጥ ታይቷል፡፡ አቶ መስፍን ግን መንግሥት ማሰራጨት በመጀመሩ ሳቢያ በኩንታል እስከ 50 ብር የሚደርስ የዋጋ ቅናሽ መታየቱን የንግድ ቢሮው ኃላፊ ጠቅሰዋል፡፡     

ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረው የ1,200 ብር በኩንታል ዋጋ አኳያ ጭማሪው ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ የሞኮሮኒና የፓስታ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል፡፡ ይህንን ተከትሎም ‹‹ከመጠን በላይ ዋጋ የጨመሩት ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው፤›› በማለት አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃዎች በድፍኑ እየተወሰዱ እንደሚገኙ ከመግለጽ በቀር ምን ያህሉ አምራቾች ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው አልተጠቀሰም፡፡

የዋጋ ንረቱ ያስከተለውን የምርት አቅርቦት ለመቅረፍ መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚያሰራጨው ስንዴ ውስጥ የአዲስ አበባ ወርኃዊ ኮታ 165 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ እስከ 50 በመቶ የሚደርሰውን የስንዴ አቅርቦት ለዱቄት ፋብሪካዎችና ዳቦ ቤቶች ማሰራጨት እንዳስቻለ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ሥር የግብይት ተሳታፊዎች ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን በቀለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከተመደበው የ165 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ውስጥ የ70 በመቶ ሥርጭት ላይ መድረስ እንደተቻለም አቶ ሰሎሞን አስታውቀዋል፡፡

የንግድ ሚኒስቴር፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና ሌሎችም የመንግሥት አካላት በየሳምንቱ እየተሰበሰቡ በምርት አቅርቦትና ሥርጭት እንዲሁም በዋጋ ሁኔታ ላይ የሚመክሩበት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የስንዴን ወቅታዊ ሁኔታ ጨምሮ በሌሎችም ምርቶች ላይ ግምገማ እንደሚያደርግ አቶ መስፍን አስታውሰዋል፡፡

ከውጭ የሚገዛው ስንዴ በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚገባ ቢታሰብም፣ ባለፈው ሳምንት በድጋሚ የግዥ ጨረታው በመሰረዙ ሳቢያ የስንዴ አቅርቦቱን ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መስከረም ላይ ተገዝቶ መግባት የነበረበት ስንዴ እስካሁን በመጓተቱ እንዳለ ሆኖ፣ አሁን በደጋሚ በወጣው ጨረታ መሠረት ያለ ምንም ሌላ ችግር ስንዴው ተገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ለመግባት ቢያንስ አምስት ወራት እንደሚፈጅበት ይገመታል፡፡ ይህም ሆኖ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከ1.4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ጥሬ ስንዴ መሰራጨቱን የንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡ የስንዴ ዱቄትም ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ እንደተሰራጨ ሲጠቀስ፣ ስኳር ከ861 ሺሕ ኩንታል በላይ መሰራጨቱን ንግድ ቢሮ ይፋ አድርጓል፡፡

ከዚህ ባሻገር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በንግድ ቢሮው በኩል የተከናወኑ ተግባራት በማስመልከት አቶ መስፍን ባቀረቡት ሪፖርት በርካታ ክንውኖችን ዳሰዋል፡፡ በሪፖርታቸውም የዳቦ ግራም በማሳነስ ሲሸጡ የነበሩ 626 ነጋዴዎች መገኘታቸው ተጠቅሷል፡፡

የብረት ምርት እጥረት ያጋጠመበትን ክስተት የተመለከተው ሲሆን፣ እጥረቱን መነሻ በማድረግ የማይገባ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል የተባሉ 22 የችርቻሮ መደብሮች ላይ የማሸግ ዕርምጃ ተወስዶባቸው እንደነበር አስታውዋል፡፡

ንግድ ቢሮው በሕገወጥ የንግድ ተግባር ውስጥ ተገኝተዋል ያላቸው 14,684 ነጋዴዎችን እንደለየ በሪፖርቱ አመላክቶ፣ ልዩ ልዩ ጉድለት በታየባቸው 29,908 ነጋዴዎች ላይ ከቃልና ጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ማሸግና ንግድ ፈቃድ መሰርዝ ብሎም ማገድ ድረስ ባለው ደረጃ ዕርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች