ምርቱም ገለባውም ተደባልቋልና፥
የምታበጥረው ጐራው ና ጐራው ና።
ዐርበኞች ሲመጡ እየተኳኰሱ
ያንበጣ ጕዞኛ ይመስላል ርሳሱ።
እኛው መጡ እኛም አየናችው፤
መድኀኒት የጠጡ ይመስላል ፊታቸው።
እኛው መጡ እንደ ባርማሽላ እየተመረጡ፤
በመጡበት መንገድ መመለሻ ሊያጡ።
ራሰ ዘናኑ እግረ ውትርትሩ፥
እጁ መርዘኛ ነው አይኖርም አገሩ።
ምናባቱ ንብረት ምናባቱ፤
ንብረት ባይኖረው ነው ነብር መፈራቱ።
ድዋሮ ከጉሙ ጣርማ በር የዋሉ፥
ይማግዱት ቢያጡ ነዶ ሣር ቅጠሉ፥
በመትረየስ ጥይት ባረር እየቈሉ፥
ያርባ ዓመት ጭንኵሮ ባርማሽላ በሉ።
እገጭ እጓ ሲል ነው የወንድ አብነቱ፤
ሴትም ትዋጋለች ተረጋ መሬቱ።
ጦር መጣ ጦር መጣ ጫፉን ነቀነቀው፤
ጐበዝን ደስ አለው ፈሪን ጨነቀው።
የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፤
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ።
- ስብስብ በእ.ነ.ሥ. ‹‹ዝክረ አርበኞች››