Friday, December 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ያላሳከከን ቦታ ማከክ ትርፉ ቁስለት ነው

በሮባ ገዳ

ይኼንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ያነሳሳኝ ዋናው ጉዳይ፣ ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን የሥራ አፈጻጸም ሲሰጡ የነበሩ መግለጫዎችን አስመልክቶ መሥሪያ ቤቱ ከምሥረታው ጀምሮ እየተንከባለሉ የመጡት ችግሮች ለዚህ አፈጻጸም ድክመት እንደዋና መንስኤ መወሰድ እንደሚገባቸው እነዚህን መግለጫዎች ለሚዲያ ለሰጡ፣ ለጻፉና ላነበቡ አካላት እውነታውን ለማሳወቅ፣ እንዲሁም ቀደም ሲል ስለመሥሪያ ቤቱ ግልጽ ግንዛቤ ላልነበራቸው የመንግሥት አካላት ደግሞ የነበሩትንና አሁንም ያልተፈቱትን ችግሮች በግልጽ ማሳወቁ በቀጣይ መወሰድ ለሚገባቸው የመፍትሔ እርምጃዎች አቅጣጫ ጠቋሚ ይሆናል ብዬ በማመን ነው፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው ለእነዚህ መግለጫዎች ቀጥታ ምላሽ መስጠቱ አስፈላጊ ነው የሚል እምነት ባይኖረኝም፣ ባለሥልጣኑ ተጠሪ ሆኖ በቆየባቸው ሚኒስቴሮች የበላይ ኃላፊዎች የባለሥልጣኑን ችግሮች ለመንግሥት አቅርበው መፍትሔ ከማሰጠት ይልቅ የባለሥልጣኑን ኃላፊዎች በማሸማቀቅና ለሚነሱት ጥያቄዎች ራሳቸው ያልተጋ ምላሽ በመስጠት አንዳንዴም ችላ ብለው ወደ ጎን በመተው፣ ይልቁንም በመብራት ኃይል የሚሠሩ የኃይል ማዳረስ ሥራዎች እጅግ አስፈላጊ ስለሆኑ ቁጥጥር እንደማያስፈልግ በግልጽ በመናገር፣ አንዳንዴም የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን ሪፖርቶች ችላ በማለትና ተቆጣጣሪ አስፈላጊ አይደለም በማለት ባለሥልጣኑን ከመደገፍና ኃላፊነቱን እንዲወጣ ከማገዝ ይልቅ ተቃራኒውን አማራጭ ይዘው ቆይተዋል፡፡ ይልቁንም ባለሥልጣኑ ሰሞኑን ከሁለት የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴዎች (የተፈጥሮ ሀብትና አከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ) ጋር ባደረጋቸው ሁለት ግምገማዎች ላይ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርን ወክሎ ተገኙ የተባሉት ሚኒስትር ዴኤታና ሌሎች የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ምናልባትም እነዚህ ሰዎች ባለባቸው ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን በባለሙያነታቸውም ጭምር ለዘርፉ የሚበጀውን አሠራር ጠንቅቀው ተረድተዋል የሚል ግምት እንዲኖረኝ አድርጎኛል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመውና የዚህን ባለሥልጣን ሥራ የሚከታተለው ቋሚ ኮሚቴም መሥሪያ ቤቱ ያሉበትን እጥረቶች ለዓመታት ተከታትሎ የተረዳ ቢሆንም፣ የዋናው ሚኒስቴር ሪፖርቶች በዋናው የፓርላማ ጉባኤ ላይ በሚቀርቡበት ወቅት ጉዳዩን በማንሳትና የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ ባለሥልጣኑ በየሦስት ወሩ ቋሚ ኮሚቴው ላይ ሪፖርት በሚያቀርብበት መድረክ ላይ በተደጋጋሚ ወደላይ ገፍታችሁ መሄድ አልቻላችሁም በማለት የባላሥልጣኑን የሥራ ኃላፊዎች መውቀስ የሚጠበቅ አባባል ሆኗል፡፡ እስኪ አሁን እውነት ሰዎች በእርስ በርስ ትውውቅ ወይም በተለያዩ መንገዶች በመቀራረብ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጉዳዮች እንደ ግል ጉዳይ ሲፈጸሙና ሲያስፈጽሙ በቆዩበት ሥርዓት ውስጥ በበላይ ኃላፊዎች ዘንድ ተሰሚነት ያለው ማነው? የኢነርጂ ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊዎች ወይስ የፓርላማ አባላት?

በተለይ ከ2006 እስከ 2008 ዓ.ም. የባለሥልጣኑን የሥራ አፈጻጸም የገመገሙት የዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎችም በግምገማቸው ወቅትና ባዘጋጁት ሪፖርት የባለሥልጣኑን ችግሮች የተረዱና ለችግሮቹም ዋና መንስኤ ያልተሟላለት የሕግ ማዕቀፍ መሆኑን፤ ይህም በአፋጣኝ መጽደቅ እንደሚገባው ለዚህ ደግሞ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት አባል በሆነው ሚኒስቴሩ በኩል ክትትል ሊደረግ እንደሚገባው በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡

መንግሥት በፈጠረው አደረጃጀት አብዛኞቹ መሥሪያ ቤቶች ተጠሪ በሆኑባቸው ሚኒስቴሮች በኩል ነው ጉዳዮቻቸውን ለመንግሥት ማቅረብ የሚችሉት፡፡ በመሆኑም የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኤጀንሲ የአሁኑ የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን በዚህ አደረጃጀት መሠረት ችግሮቹን አሳውቆ መፍትሔ ለማግኘት ዕድለኛ አልነበረም፣ መንገዱም ከሰማይ እርቆት ላለፉት 20 ዓመታት ተጉዟል፡፡ ይህ ሳያንስ እንዲያውም ሰሞኑን አፈጻጸሙ ደካማ ነው ተብሎ የሚዲያዎች መዘባበቻ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በመሆኑም የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ለረጅም ጊዜ የባለሥልጣኑን ሥራዎች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ስሠራ የቆየሁ በመሆኔ ያሉትንና እስካሁን ድረስ ታፍነው የቆዩትን ጉዳዮች በይፋ አውጥቶ መነጋገርና በዘርፉ ለሚታዩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማስገኘት አስፈላጊ መሆኑን ስለማምን ይኼንን ጽሑፍ አቅርቤያለሁ፡፡

ለመሆኑ መሠረታዊ ችግሮች ምንድናቸው?                                                                                               

ከላይ በተቀመጠው መሠረት በመጀመርያ የመሥሪያ ቤቱን አመሠራረት ብንመለከት መንግሥት መሥሪያ ቤቱን በአዋጅ ሲያቋቁም እውነት አምኖበት ነው ወይስ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ዕርዳታና ብድር ለማግኘት ፈጻሚና ተቆጣጣሪ አካላትን በመለየት እነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በወቅቱ ይጠይቁ የነበረውን መስፈርት ማሟላት አስፈላጊ ስለነበር ነው?

ከላይ እንደተጠቀሰው መንግሥት የዚህን ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት አስፈላጊነት አምኖ ካቋቋመ ለሰፊ ኅብረተሰብ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ከተደራጀና ቁጥጥር ከሚደረበት ፈጻሚ መሥሪያ ቤት ከሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጋር ለምን በአንድ ሚኒስቴር ሥር ጨፍልቆ ማቆየት አስፈለገ? በሌሎች አገሮች ያሉ የዘርፉ ተቆጣጣሪ አካላት ለዘርፉ ጤናማ ዕድገት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነና ሥራው በጊዜ ልጓም ያልተበጀለትን የኃይል አቅርቦት በኋላ ለመቆጣጠር መሞከር ሰዶ ማሳደድ እንደሚሆን እየታወቀ ለቁጥጥር ሥርዓቱ ማደግ ትኩረት ተሰጥቶት አልተደራጀም፡፡

አገሪቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት በኃይል መቆራረጥና አልፎ አልፎ ሙሉ ለሙሉ በጭለማ ስትዋጥ፣ ኅብረተሰቡ አቤት የሚልበት ቦታ እንኳን አጥቶ በየሬዲዮ ጣቢያዎች ስልኮችን ሲያጨናንቅ ጉዳዩ የማይመለከታቸው የበላይ ኃላፊዎች ጣልቃ ገብተው ችግሮችን በመሸፋፈን ምላሽ ሲሰጡ ለመሆኑ ተቆጣጣሪው መሥሪያ ቤት የት ደረሰ እንዴት አልተባለም?

አገሪቷ በኢነርጂ ዘርፍ ከራስ ተርፎ  ለጎረቤት አገሮች የሚበቃ ኃይል ለማምረት በራሷ ግዙፍ መዋለ ንዋይ እያፈሰሰች እያለች፣ እንዲሁም ባለሀብቶች ደግሞ በግሪድና ከግሪድ ውጭ ከተለያዩ ምንጮች ኃይል አመንጭተው ለኃይል ተጠቃሚው ኅብረተሰብ እንዲሸጡ የተለያዩ ሥራዎች በስፋት ሲሠሩ ተቆጣጣሪው ሙሉ ቁመና ኖሮት እንዲሠራ እንዴት አልታሰበም፡፡ ምክንያቱም በተለይ ባለሃብቶች ገንዘባቸውን አፍስሰው ያመረቱትን ኃይል ለገበያ ማቅረብ ከጀመሩ በኋላ ብዙ ሕግ ነክ ጥያቄዎች እንደሚያነሱ የተለያዩ አገሮች ተሞክሮዎች ያሳያሉ፡፡

ኃይል አቅራቢው የመንግሥት ልማት ድርጅት መሆኑና ብዙ የማትረፍ ጉጉት ባይኖረውም አሁንም ያለው ትልቅ የአስተሳሰብ እጥረት የኤሌክትሪክ መስመር ሲዘረጋ አሠራሩና የሚሠራባቸው ቁሳቁሶች ጥራትና ደረጃቸውን ካልጠበቁ በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሰው አደጋ የከፋ መሆኑ እየታወቀ የቁጥጥር ሥራው እንዲጠናከር ትኩረት አለመስጠቱና ሌሎችንም በርካታ የአመለካከት አጥሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ ዋናዎቹ የችግሮቹ መነሻዎች ከላይ የተጠቀሱት ይሁኑ እንጂ በባለሥልጣኑም አመራር በኩል እንደማንኛውም የዚህ አገር አመራር የማስፈጸም ክፍተት መኖሩ የማይካድ እውነታ ቢሆንም በርካታ ጠንካራ ጎኖች ነበሩት፣ አሁንም አሉት ማለት ይቻላል፡፡

መሥሪያ ቤቱን ላለፉት 20 ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት የመሩት ኃላፊ መሥሪያ ቤቱን ከውልደቱ ጀምረው ሲደርስባቸው የነበረውን ጫና ተቋቁመው እንደምንም ጠጋግነውና ደጋግፈው ለማቆምና ደረጃውን የጠበቀ ተቆጣጣሪ (ሪጉሌተር) ለማድረግ ስመጥር የዘርፉን ባለሙያዎች ከውጭ አገሮች ድረስ በማስመጣት ሰፊ ልምድ እንዲገኝ ለፍተዋል፡፡ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ጥናቶችን አዘጋጅተው በማቅረብ ከዘርፉ አጋሮች ባገኙዋቸው የገንዘብና የቴክኒክ እገዛዎች አፈጻጸማቸው በውጭ ኦዲተሮች ጭምር የተመሰከረላቸው በርካታ ፕሮጀክቶችን ከፍጻሜ በማድረስ ለቁጥጥር ሥርዓቱ መዳበር ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አሁንም ራሱን ችሎ መቆም የተሳነው ከ20 ዓመታት ያላነሰ ዕድሜ ያለው መሥሪያ ቤት ይዘው ተስፋ ሳይቆርጡ እየሠሩ ናቸው፡፡ መሥሪያ ቤት መያዝ ካለበት ባለሙያ 15 በመቶ ብቻ ይዘው ራሳቸው በምሽትና በዕረፍት ቀናት ጭምር በመሥራት ባለሙያዎችንም አልፎ አልፎ ከአቅማቸው በላይ ተደራራቢ ሥራዎችን በማሠራት፣ ከሙያቸው ውጪ አዋጅና ደንቦችን በማዘጋጀት ጭምር ሠርተዋል፡፡ እንዲህም ሆኖ ሰሞኑን ሲዘገቡ ለከረሙት ወሬዎች እንኳን ምላሽ መስጠት የፈለጉ አይመስሉም፡፡ እኔ ደግሞ ቀደም ሲል ከመሥሪያ ቤቱ የእንጀራ መሶብ ቆርሼ የበላሁት፣ አሁንም በቅርብ ርቀት ችግሩን የሚገነዘብ ዜጋ እንደመሆኔ የማውቀውንና የተገነዘብኩትን እውነታ ተናግሬ በመሸበት…መርጫለሁ፡፡

በርካታ የምሕንድስና፣ የሕግ፣ የምጣኔ ሀብትና ሌሎችም ባለሙያዎች ለቁጥጥር ሥርዓቱ አስፈላጊ የሆኑ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን በውጭ አገራት ጭምር ወስደው በማገልገል ላይ እያሉ በተለያዩ ምክንያቶች (በአብዛኛው በክፍያ ምክንያት) ብን ብለው ሲጠፉ የተቀመጡትን መዋቅሮች እንኳን ጥሰው ቢሆን ወደ መንግሥት ጠጋ ብለው  ጉዳዩን ለማስረዳት የደፈሩ አይመስለኝም፡፡ በዚህም ምክንያት መገኘት የነበረበት ውጤት ሳይገኝ ቀርቷል፡፡

ሰሞኑን በተደረጉት ሁለት የተለያዩ የቋሚ ኮሚቴዎች ግምገማዎች ላይ ጉዳዩ ያጠነጠነው አንድ ነገር ላይ ብቻ ነበር፤ የኢነርጂ ደንብ ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ግፊት አላደረጋችሁም ተብሎ የባለሥልጣኑ ማኔጅመንት ተተችቷል፡፡ እስኪ ይታያችሁ ይህ መሥሪያ ቤት አዘጋጅቶ ከማቅረብ ውጭ ሌላ ግፊት ማድረግ ያስፈልግ ነበር ወይ? ውኃ ወደ ላይ አያፈስም እንደሚባለው መግፋትስ ይቻል ነበር ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ወደ ላይ የገፉት ሁሉ ከመጣል ይልቅ ተገፍትሮ ሲወድቁ አይተናልና፡፡ ካስፈለገስ በየትኛው መድረክ? መሥሪያ ቤቱ የሚኒስትሮች ምክርቤት አባል አይደለም፡፡ አስተያየቶች እንኳን ቢኖሩ የባለሙያ እገዛ በማድረግ ጭምር ቶሎ ጠርቶ እንዲጸድቅ ማድረግ እየተቻለ በመመላለስ ብቻ ዓመታትን በማስቆጠር መጨረሻ አፈጻጸሙ ደካማ ነው ተባለ፡፡ ሚዲያዎችም መሠረታዊ ችግሮችን ሳያጠሩ ይህንኑ ሲያራግቡ ሰነበቱ፡፡

ሌላው የራሱ ቢሮ እንኳን ሳይኖረው በግለሰቦች ሕንጻ ላይ ሠራተኛው እንደ ግል ቤት ተከራይ ተሳቆ እየሠራ የፍተሻ ላቦራቶሪ አላቋቋማችሁም ተብሎ የግምገማ ውርጅብኝ እንደዘነበበት ሰምቻለሁ፡፡ ለአንባቢያን እንድ ቁምነግር ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ባለሥልጣኑ ያኔ ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ብድር ለማግኘት ሲባል በሩጫ ያህል ሲቋቋም ከዛሬ 20 ዓመት በፊት መሆኑ ነው፤ ይበዛም ይነስም የራሱ የሆነ ሕንጻ የነበረውና በሞራልም በተስፋም ከዛሬ በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የሚገርመው ባለሥልጣኑ ይዞት የነበረው ቦታና ቢሮ ለልማት ይፈለጋል ተብሎ ለቆ እንዲወጣ ከተገደደ በኋላም ላለፉት ከ4 ዓመታት ያላነሰ ጊዜ በቦታው ላይ ምንም ዓይነት የልማት አለመሠራቱ ነው፡፡ አሁንም ከላይ እንደተጠቀሰው ለፍተሻ የሚያገለግሉ በርካታ መሣሪያዎች ከለጋሾች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍና ከመንግሥት በተመደበ በጀት ተገዝተው ስቶር ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ እነዚህን መሣሪያዎች ዘርግቶና ፈትሾ በአግባቡ ሥራ ለማስጀመር በቂ የሆነ ላቦራቶሪ ያስፈልጋል፡፡ ላብራቶሪ ማቋቋም ብቻ ሳይሆን ፍተሻዎቹ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ኢንቨስትመንቱም ብዙ ስለሆነ ዘላቂ ባልሆነ የግለሰብ ሕንጻ ውስጥ ገንዘብ ማፍሰስ እንደባለሙያ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለመሥሪያቤቱ ቢሮ፣ ላቦራቶሪ፣ የማሳያና የሥልጠና ማዕከል የሚያገለግል ቦታ ሳይኖር መሥሪያ ቤቱን ሲገመግሙት ውለው ቢያድሩ ውኃ ቢወቅጡት…. እንደሚባለው ነው፡፡

ሰሞኑን ከተነሱት አስተያየቶችና አስተያቱን ተከትሎ ብቻ ተቋሙንና ሁኔታውን በቅጡ ያልተረዱ የሚዲያ ባለሙያዎች አገሪቱ ደረጃቸውን ባልጠበቁ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች እንድትጥለቀለቅ ባለሥልጣኑ ምክንያት ሆኗል የሚሉ ዘገባዎችን ሲያስተጋቡ ተመለከትኩ፡፡ እንደኔ ዓይነቱ በተቋሙ ውስጥ ላገለገለ ሰው ዘገባው ያሳዝናል፡፡ በእርግጥ አገሪቷ ደረጃቸውን ባልጠበቁ ከቀላል አስከ ከባድ የኤሌክትሪክ መገልገያ መሣሪያዎች መጥለቅለቋ የማይካድ ሃቅ ይመስላል፡፡ ቅዝምዝም ወዲህ ፍየል ወዲያ ይላሉ አበው ሲተርቱ፤ ችግሩ ወዲህ ነው፤ እንደነዚህ ያሉ ከባባድ ችግሮች ለመጋፈጥ በማያስችል ብቻም ሳይሆን ቀደም ሲል ባስቀመጥኩት ‘ሲሮጡ የታጠቁት…’ በሆነ ሁኔታ የተቋቋመ መሥሪያ ቤት፣ ለዚህም በቂ የሆነ የአደረጃጀትና ተቋማዊ ሥነልቦና ሳይታጠቅ ብዙም ውጤት መጠበቅ ያላበደሩትን ክፈል እንደ ማለት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ እኔ እስከማውቀው ድረስ የባለሥልጣኑ ኃላፊነት፣ የኢትዮጵያ ደረጃ የሌላቸው የኤሌክትሪክ ምርቶች የኢትዮጵያ ደረጃ እንዲዘጋጅላቸው ለኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ጥያቄ በማቅረብ ምርቱ የኢትዮጵያ ደረጃ እንዲወጣለት ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ በቂ ምስክር ነው፡፡ አንድ ምርት አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ እንዲኖረው ካስፈለገና በሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ከታመነበት በመጀመሪያ በአገር ውስጥ ያንን ምርት ለመፈተሽ የሚቻል መሆኑ ሲረጋገጥ ደረጃው አስገዳጅ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ከዚህ አሠራር ውጭ ደረጃዎች አስገዳጅ እንዲሆኑ ማድረግ ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ምርት ገበያ ላይ እንዳያገኝ ማድረግ ነውና አንዳንዴም ዓለም አቀፍ አሠራሮችን በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ችግር ደረጃ በማውጣት ብቻ የሚፈታ ሳይሆን በአገር ውስጥ በቂ የፍተሻ አቅም በመገንባት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡  

በመጨረሻም የባለሥልጣኑ ማነቆ ብቻም ሳይሆን የኛን አገር የተቋም አደረጃጃትና አመራር ብልሹነት ለማመላከት ልሞክር፡፡ ይህ መሥሪያ ቤት በምንም ምክንያት ይሁን በምን ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ‘እንዲደራጅ’ ተደርጓል:: በወቅቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኤጀንሲ በሚል የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንና ሌሎች በኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ላይ የሚሰማሩ ተቋማትን ፈቃድ የሚሰጥና የሚቆጣጠር በሚል ዓላማ የተቋቋመ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈ፣ በየጊዜው የሚጠራበት ሚኒስቴር ሲቀያየርበት የኖረ ተቋም ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ሲቋቋም የተሰየመለት ዋና ዳይሬክተር ዛሬም በትግል ላይ ናቸው፡፡ የሚገርመው ነገር  መሥሪያ ቤቱ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን ሲያሳልፍ እኚህ አመራር አጥፍተሃልም አልምታሃልም ተብለው አያውቁም፡፡ ጥሩ ሠርተሃል ዕድገት ይገባሃል አልያም መምራት አልቻልክም ተብሎ በሌሎቹ ላይ እንደሚደረገው እንኳን መሥሪያ ቤት አልተቀየረላቸውም፡፡ የመጣው ሁሉ ‘ባለህበት እርገጥ’ ብሎት የሚያልፍ ይመስላል፡፡ በመሥሪያቤቱ በቆየሁበትና እስከማውቀው ድረስ እኚህ አመራር ለውጥ መጣም አልመጣም ከላይ እንደጠቀስኩት ሌት ቀን የሚለፉ መሆናቸውን ለህሊናዬ መንገር ለአንባቢ ደግሞ ማሳወቅ ሰብአዊ ግዴታ እንዳለብኝ እየተሰማኝ ነው፡፡

የተቋሙ ችግር ዘርፈ ብዙ ነው፤ አደረጃጀቱን እንኳን ብንመለከት በዚህ አገር ከተደራጁት ከ170 በላይ (ሚኒስቴሮችን ጨምሮ) የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ በአንድ ኃላፊ የሚመራ ብቸኛ ተቋም ነው ብል የምሳሳት አይመስለኝም፡፡ ሁሉም ተቋማት ሚኒስትር ዴኤታ፣ ምክትል ዋና ኮሚሽነር፣ ምክትል ዋና ዳይሬከተር ወዘተ. እንደየአደረጃጀታቸው ሁለትና ከዚያ በላይ የተቋም የበላይ ኃላፊ ያላቸው ናቸው፡፡ ከሚኒስቴር ደረጃ በታች ያሉት አንዳንድ ተቋማት እንኳን ከዚህም ባለፈ፣ የበላይ አመራሮች አማካሪ፣ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወዘተ አደረጃጀት እንዳለቸው እንሰማለን፡፡ ግዙፉን ካፒታል የሚያንቀሳቅሰውን የኃይል ዘርፍ ይመራል፣ ይቆጣጠራል ተብሎ ወደ ተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን ስትሄዱ ግን ‘ጽድቁ ቀርቶብኝ በወጉ በኮነነኝ’ ዓይነት ነው፡፡ አደረጃጀት ያስፈለገበት ያለምክንያት አይደለም፤ ሥራውን በተሻለ አቅም ለመምራት የታሰበ እንደሆነ ይገለጻል፡፡  እናም ይህ መሥሪያ ቤት ተፈልጎ ነው የተቋቋመው ወይስ በሆነ ወቅት አስገዳጅ ሁኔታ ስለተፈጠረ እንዳይሞት እንዳይሽር ተደርጎ የተፈጠረ ነው ብሎ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል:: ከአራት ዓመታት በፊት እንዲሁ ከብዙ ጩኸትና ውትወታ በኋላ የመሥሪያቤቱ አደረጃጃት፣ ሥልጣንና ተግባር እንዲፈተሽ ተደርጎ የኢነርጂ አዋጅ እንዲታወጅና ተቋሙም ተሻሽሎ እንዲደራጅ መደረጉን አስታውሳለሁ፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኤጀንሲ ይባል የነበረው የኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ሥራዎች በኃላፊነቱ ላይ ተደምሮ የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን ተብሎ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንዲሻሻል ተደርጎ ተቋቋመ፡፡ በማቋቋሚያ ደንቡ ላይ ባለሥልጣኑ የሥራ አመራር ቦርድ እንደሚኖረው ቢነገርም አሁንም ከ4 ዓመታት በኋላም ይህ አልተፈጸመም፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የተቋሙ መዋቅር ታስቦ ጥናት ተደርጎ የሠራተኛ ብዛት ከ120 ወደ 260 እንዲሰፋ የወረቀት ጥናት ቢደረግም በአሁኑ ጊዜ በሥራ ገበታ ላይ የሚገኘው ሠራተኛ መጠን ከ30 በመቶ እንደማይበልጥ ወስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡

እንግዲህ ይህንን የመሰለውን ጉዳይ ነው ሚዲያዎች ጫፍ ይዘው ትልቅ አጀንዳ ያገኙ በማስመሰል ባለሥልጣኑ ላይ ሲረባረቡ የከረሙት፡፡ ከዚህ ይልቅ የታዩት ጉድለቶች መንስኤዎች ምን ምን እንደሆኑ ወደ ባለሥልጣኑ በመቅረብ የሥራ ኃላፊዎችን በማነጋገር ጉዳዩን አውጥተው ቢሆን ኖሮ ባለሥልጣኑ ጉዳዩን ለመንግሥት ለማሳወቅ ሌላ አማላጅ ባላስፈለገው ነበር፡፡ አበቃሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን ባልደረባ የነበሩ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles