Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሰሜናዊው የጉዞ ማስታወሻ

በሳራ ሞገስ ገብረዮሐንስ

ከእያንዳንዱ ዕድሜ ጠገብ ታሪክ አጠገብ፣ ትንፋሽን ነጥቆ ከሚያስቀር ውብ፣ አስደናቂ፣ ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ሥፍራዎችን ከቦ የሚገኝ ማኅበረሰብ፣ እያንዳንዱ እንቅስቃሴው የማንነቱን ቅኝት ለዛ የሚመሰክር፡፡ ይህ ሰው ለማተቡ ሟች ነው፣ ይህ ሰው ጨዋታ አዋቂ ነው፣ ይህ ሰው ቀልዱ ጊዜና ቦታ አለው፣ ይህ ሰው እንግዳ አክባሪ ነው፣ ይህ ሰው ከሰሜን ብቻም አይደለም፣ ከደቡብ ብቻም አይደለም፣ ከምሥራቅ ከምዕራብ ከመሀል ብቻም አይደል ከመላው ኢትዮጵያ እንጂ፡፡

መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጀርመን የመጡ ዘጠኝ ጎብኚዎችን ይዘን የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች ለማስጎብኘት እኔና የሥራ ባልደረቦቼ ሌሊት 11 ሰዓት ላይ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተገናኝተን ወደ ጎንደር ለማቅናት ቀጠሮ ይዘናል፡፡ በተባለው ጊዜና ቦታ ተገኝተን እንግዶቻችንን ይዘን ጉዞ ጀመርን፡፡ አውሮፕላኑ ከተነሳ ከ50 ደቂቃ በኋላ ራሳችንን የአፍሪካ መናገሻ ከሆነችው ጎንደር አገኘን፡፡ ምንም እንኳን እያንዳንዱ ዕርምጃችን የታሪክ አሻራ ያረፈባቸው የጎብኚን ቀልብ ጠልፈው በሚያስቀሩ መስህቦች አጠገብ ቢሆንም የእኔ ስሜት ግን ከዚያ ሰው (አሰግድ ተስፋዬ) ላይ ነው፡፡ አገሩን ስንጎበኝ በፈገግታ ከተቀበለን አብያተ ክርስቲያናትን ስንጎበኝ የእማሆይ ቂጣ ቅመሱ እያሉ ከሚጋብዙን የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እናት (ደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም)፣ ውኃ ጥማችን ለማስታጋስ ጎራ ስንል ገንቦዋን አዘንብላ ጠላና ፍሩንዱስ ከምትጋብዝ ባለሙያ ሴት (እሌኒ) ልማድ ይዞኝ ያልተመጠነ ሳቄን ሳስጮህ ኧረ ወሽከት ብለሽ ሳቂ ብሎ ከሚገስፅ አምሳለ ታላቅ ወንድም (አቤ) ላይ አርፏል፡፡ በቀጣዩ ቀን ማለዳ ተነስተን የዕለቱ የጉብኝት መርሐ ግብር ወደ ሆነው ወደ ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እያቀናን ነው፡፡ ደባርቅ ከሚገኘው የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ወደ ፓርኩ የመግቢያ ክፍያን ፈጽመን በሚኖረን ቆይታ ከአውሬውም ከምኑም ሥጋት ነ እንሆን ዘንድ ስካውት እየተባሉ የሚጠሩትን ታጣቂዎች ከመኪናችን ጫንን፡፡ ሁሉም ጎብኚ የቦታው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ጫካው፣ ዱሩ፣ በውስጡ ያቀፋቸው ብርቅዬ የዱር እንስሳት ውህደት ከመማረክም አልፎ ስስት ያሳደረበት ይመስል እያንዳንዱን ነገር በቃኝ ወደ ማያውቀው የካሜራቸው ሆድ ይጠቀጥቁታል፡፡ ከዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ አጠገብ እኔና ስካውቶቹ ወግ ይዘናል፡፡ ለዛ ባለው አነጋገር ነብሴ ውስጥ ተስንቅሮ የሚቀር ጨዋታ፣ አገራችሁ የት ነው? ጠየቅኩ ስሜን ጃን አሞራ በኩራት መለሱ፡፡ ታዲያ ከዚያ ደባርቅ ድረስ እየተመላለሳችሁ ነው የምትሠሩት? ሌላ ጥያቄ፡፡ አይ በሳምንትም በአስራ አምስት ቀንም እየተመላለስን እንጂ፡፡ እንዴ ባለቤትዎስ? እሷ አንበሳ ናት ማንም አይደፍራትም፣ ኧረ እንደው ትንሽ አይጠራጠሩም? ማን እሱዋን? ባይሆን እኔ እደነቃቀፍ እንደሁ እንጂ … ለዚህ የአገሬ ሰው ሚስቱ ከራሱ እምነት በላይ የሚያውለበልባት ሰንደቁ ነች፡፡

      ለጉብኘት የያዝነው አጭር ጊዜ ሁሉንም የአገራችንን መስህቦች በወፍ በረር ለመቃኘት የሚያስችል በመሆኑ ከጊዜ ጋር እየተሽቀዳደምን ወደ አውሮፕላኑ ገባን፡፡ አውሮፕላኑ ሲነሳ የተሰማን ስሜት ሳይጠፋ ጥንታዊቷ ሮሀ ላይ አረፍን፡፡ ከዚህች የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መገኛ፣ የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት መናገሻ፣ የዓለም ሕዝብን አጃኢብ ያሰኘ የሥነ ሕንፃ ጥበብ ከሰፈረባት ከተማ ታሪክ እንደ ወንዝ ጅረት ከአንደበቱ ኩልል እያለ ሲወርድ ቢውል የማይደክመው ፈገግታ ለሰከንዶች ክፍልፋይ እንኳን ከገፅታው የማይታጣ ሌላው የአገሬ ሰው ጠበቀን (አዲስ)፡፡ ጭሱ የአካባቢውን አየር በመልካም መዓዛ ከአወደው ጊርጊራ ጀርባ አንዲት የደም ገንቦ የመሰለች ውብ ሴት አርሂቡ አለችን፡፡ እኛም ሳናንገራግር ከቡናዋ ታድመን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጎብኘት ተነሳን፡፡ አዲስም ከጊዜ እየተሻማ ሁሉን አስዳሰሰን፡፡ ወቅቱ ዐቢይ ጾም ነበርና ሁሉም ቤተ መቅደሶች ለማስቀደስ በመጡ ምዕመናን ተሞልተዋል፡፡ በመስቀል ቅርፅ እየተንቦለቦለ ከሚወጣው ጭስ ስር ቆሞ በምዕመኑ መሀል ጎብኚ ይዞ መንቀሳቀስ ለጥሞና የመጡ ምዕመናንን ይረብሻል፡፡ በሌላ በኩል እዚህ ድረስ የአገሬን ታሪክ አይተው ለዓለም ሊመሰክሩ የመጡ ሰዎች ይዘው መሄድ አለባቸው በሚሉ መንታ ሐሳቦች ወደ መሀል ሆኖ ላፍታ ካሰበ በኋላ ከጭንቅላቱ ጀምሮ እስከ ታች ካጣፋው ነጠላ ሥር አንድ እጁን ጭሱ ወደሚወጣበት ግድግዳ እየጠቆመ ይህ ሥጋ ወደሙ የሚጋገርበት ሥፍራ ነው አለ፤ ጎብኚዎቹ በሚረዱበት ቋንቋ፡፡ በዚህ መልኩ ያስጀመረን የጉብኝት ጉዞ አፍን አስከፍተው ልብን ይዘው በሚጓዙ ትረካዎች ቀጥለው ዋሉ፡፡

ጀምበር ወደ ማደሪያዋ ስትገባ እኛም ለዕለቱ ወደተያዘልን ማደሪያ ሄደን በቀጣዩ ቀን ማለዳ ተነሳን፤ ዛሬም ሌላ የጉዞ መዳረሻ አለን ወደ ኢትዮጵያ የሥልጣኔ እምብርት አክሱም፡፡ ታዲያ ጉዞአችን ያለሸኚ አልነበረም፤ ትናንት ከተማው ከተማችን እስኪመስለን ሁሉን ያስጎበኘን ሰው ዛሬ ጓዛችን ተሸክሞ ሰላም ግቡ ሊለን አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ሸኘን፡፡ የሌላውን ባላውቅም ለእኔ አንድ አብሮ አደጌን ለረዥም ጊዜ ተለይቼው የሄድኩ ያህል ተሰማኝ፡፡ አክሱም የደረስነው ረፋዱ ላይ ነበር፡፡ ከተማዋ ላይ በርካታ ጎብኚዎች ይስተዋላሉ፤ በየሆቴሉና በአገልግሎት መስጫ ሥፍራዎች፣ በሙዚየምና በአክሱም ሐውልቶች አካባቢ እንዲሁም የቅዱሱ ታቦት ማደሪያ በሆነችው አክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከምሳ በኋላ ለምናደርገው ጉብኝት በጉዞ ለደከመው ጉልበታችን ኃይል መሙላት አስፈላጊ ነውና እጅ የሚያስቆረጥም ስልስ በህልበት በላሁ፡፡ አይ ባልትና! ከአንዱ ጥግ በወርቀዘቦ ጥለት የተዋበ የባህል ቀሚስ ለብሳ በረዶ የመሰሉ ነጫጭ ሲኒዎችን ረከቦቷ ላይ ደርድራ አንገተ ረጅም አፍንጫ አልባ ጀበና የተጎለተበትን ምድጃ በመሽረፊት ታራግባለች፡፡ ጠጋ ብለን አጠገቧ ከተደረደሩት ዱካዎች ላይ አረፍ አልን፡፡ አንገቷን ሰበር አድርጋ ታዘዘችን፣ ስሟን ጠየቅናት አልማዝ አለችን፡፡ ከንፈሩዋን ላመል አላቃ ድርድር ብሎ የበቀሉ ጥርሷን እያሳየች፡፡ አቤት የጎንደሩ አቤ ይህን ሳቅ ቢያይ ወሽከተ ማለት እንደዚህ ነው ይለኝ ነበር፡፡ አልማዝ መልክ ብቻ አልነበረችም፤ የዶሮ ዓይን የመሰለ ቡናዋ፣ ከተማዋን አስመልክቶ ለምንጠይቃት ጥያቄ በመረጃ አስደግፋ የምትሰጠን መልስ ቀልቤን ያዘው፤ በነገራችን ላይ አክሱም ልብ ያልኩት ሌላም ነገር ነበር የባጃጅ ነጂው፣ ታክሲ ሾፌሩ፣ ተማሪው፣ መንገደኛው ከተማው ላይ ስላሉ የቱሪስት መስህቦች ሲጠየቅ አላውቅም የሚለው ነገር የለም፡፡ ይልቁኑም ከታሪክ ድርሳናት ጋር ቢመሳከር ዝንፍ የማይል ምላሽ ይሰጣሉ እንጂ፡፡ በየመዳረሻው ያለው ጊዜ አጭር ስለሆነ የአልሚን ቡናና ወግ ለመሰናበትና ቀጣዩን ረጅም ጉዞ በንቃት ለመጓዝ እንዲረዳን ማልደን ቡናዋን ከበብን፡፡

      ቅዳሜ መጋቢት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ሰባት ጉልበታቸው ለማንኛውም መልክዓ ምድር አስተማማኝ የሆነ ላንድክሩዘር መኪናዎች ከ1-7 ቁጥር ከጀርባቸው ለጥፈው ከአክሱም ከተማ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ጉዞ ጀመርን፡፡ አንዱን ተራራ ሲጨርሱ ሌላ ተራራ እየተተካ የሙቀቱም መጠን ከለመድነው እየጨመረ 1 ቁጥር በተለጠፈበት መኪና እየተመራን ጉዞአችንን ተያያዝነው፡፡ የዓድዋ ተራሮችንና የገርዓልታ ተራሮችን በካሜራ ለመያዝ ከተደረገው የአፍታ ዕረፍት በስተቀር መኪናዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ አፍዴራ ለመድረስ መገስገሱን ተያይዘውታል፡፡ ቀጠሮአቸው ከሰው ጋር አልነበረም፣ ከተፈጥሮ ጋር እንጂ፡፡ እዚያ ጋ ፀሐይ ወደ ማደሪያዋ ስትገባ ለማየት በርካታ ጎብኚዎች አድማስ አቋርጠው ይመጣሉ፡፡ ምክንያቱም ከቦታው ያለው ተፈጥሮ ልዩ ውበታማ ነው፡፡ የክልሉ መግቢያ ላይ የምትገኘው በርሃሌ ላይ ለቀጣይ ጉዟችን የሚያስፈልጉንን መንገድ መሪዎችና ፖሊሶች (ስካውቶች) ጭነን መንገዳችንን ጀመርን፡፡ የእኔ ወግ መውደድ ላይ የተፈጠሩ መልካም ዕድሎች ይመስሉኛል፡፡ አንደኛው መንገድ መሪ (ሐጂ ሁሴን) እኔ የተሳፈርኩትን መኪና ጋቢና በር ከፍተው እንደገቡ በሾፌራችን (ብሩክ) የሙዚቃ ምርጫ ብቻ ደምቆ የቆየው የመኪናችን ድባብ ወደሌላ ምዕራፍ ተሻገረ፡፡ የ70 ዓመቱ አዛውንት ሐጂ ሁሴን መንገዱን ከታሪክ ጋር እያቆራኙ ለአንድ ዓረፍተ ነገር የሦስት ቋንቋዎች ቃላት ያስረዱን ጀመር (አማርኛ፣ አፋርኛና ትግርኛ)፤ ልክ Despicable Me በተሰኘው ፊልም ላይ እንዳሉት የሚኒየንስ ገፀ ባህሪያት፡፡ እንዲህ እያልን ደረቱን ለሰማይ ገልጦ ወደ ተዘረጋው ነጭ የበረዶ ምንጣፍ ከመሰለ የጨው ባህር ደረስን፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲፈነቅሉና ቅርፅ ሲያወጡለት የዋሉትን አሞሌ ጨው በግመሎቻቸው ጀርባ ላይ ጭነው፣ ግመሎቻቸው እንዳይለያዩ በገመድ አቀጣጥለው ወደምትጠልቀው ጀንበር አቅጣጫ የሚጓዙትን የሲራራ ነጋዴዎች መመልከት፣ የሆነ ዓይነት ስሜት ይፈጥራል፡፡ ልክ በሰፊው በተወጠረ ሸራ ላይ የእጅ ሥራ የተቀላቀለበት ፎቶን እንደመመልከት ዓይነት ነጋዴው ጨው ከላቡ ጋር ተቀላቅሎ ሲወርድ የዋለበት ግንባሩ ድካሙን ቢያሳብቁበትም፣ በድካም የዛሉ እጆቹን ለሰላምታ ከፍ ከማድረግ ግን አላገደውም፡፡ ይህን ቅፅበታዊ ነገር አይተን ሳንጨርስ ልክ እንደተወረወረ ሁሉ ጀንበሯ ከተራሮቹ ጀርባ  ወደቀች፡፡ እኛም በሙቀትና በድካም የዛለ ሰውነታችንንና በውኃ ጥም የተጣበቀ ላንቃችንን ይዘን ከዚያ እንደ ጥጥ ከነጣ የጨው መሬት ላይ ወዲህ ወዲያ እንላለን፡፡ እንግዶቹ አሁንም ካሜራዎቻቸውን ከተዘረጋላቸው የተፈጥሮ ማዕድ እያጎረሱ ቢሆንም፣ የሁሉንም ቀልብ የሚስብ ማዕድን ዘርግቶ የሚጠብቀን ሌላ ባላገር ከዚያ ከጨው ሜዳ መሀል አገኘን፡፡ የደረቀ ጉሮሮአችንን በቀረበልን እህል ውኃ አርሰን ስለዕለቱ ማደሪያችን ምንም ሐሳብ አላደረብንም ነበር፤ ሰው በልቶ የሚጠግብ የማይመስለው ባላገሩ እራታችንን አጥግቦ ላዳር አዘጋጀን፡፡ ሰፊ ሜዳ ላይ በጣም ብዙ ባለ  አራት እግር የአልጋ ዓይነት ርብራቦች ላይ የተዘረጉ ፍራሾች መደዳውን ተድርድረዋል፤ ከላይ የአልማዝ ፍንጥቅጣቂ እንደተለጠፈበት ጥቁር ጨርቅ ሰማዩ ከዳር እዳር ተወጥሯል፣ ከስር የቀኑን ሙቀት ለማሳበቅ ግለቱን ያለቀቀ አሸዋው ከመሀል እስኪጠፋቸው ድብን ያለ እንቅልፍ የወሰዳቸውን ሰዎች እያየሁ ቤቴን አሰብኩ፤ ልተኛ ስል በሰረገላ ቁልፍ ቆልፌ ትሪና ሌሎች ተንኳኪ ነገሮችን የማስደግፍበት በር ላይ ጎኔን ፍራሹ ላይ አድርጌ ቤቴ እቆጥረው የነበረውን ጣሪያ በኮከብ ተክቼ እንቅልፌን መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡ ወይ እንቅልፍ ድሮም እሹሩሩ በሉኝ የሚለው የኔ እንቅልፍ ደብዛው ጠፋ፡፡ ሲነጋ ገና ሰማይና ምድሩ ከመላቀቃቸው የምሥራቋ ፀሐይ ምድሪቱን ተረክባ ያገኘችውን ታነድ ጀመር፡፡ እኛም ከዚህ ሳትብስ መሬት ላይ የፈሰሰው የቀለም ውህደት የሠዓሊ ሸራ እንጂ ተፈጥሮአዊ መልክዓ ምድር ወደማትመስለው ወደ ዳሎል አመራን፡፡ ሲረግጡት እግር ሥር ፍርክስ እያለ ጉዞ በሚገታው የተቃጠለ ድንጋይ ላይ በሐጂ መሪነት የጉንዳን ዓይነት ሠልፍ ይዘን ተጓዝን፡፡ ወደ ስፍራው የሚጓዙ ሁሉም ሰዎች አወቁንም አላወቁንም የራሳቸውን ድካም ሸሽገው የእኛን ሞራል እየገነቡ ወደ ሥፍራው የምናደርገውን ጉዞ አጓጊ አደረጉልን፡፡

እንቅልፍ ባይኔ ሳይዞር ያደርኩት እኔ ያን ቀለም የተረጨበትን መሬት ለማየት በማደርገው ጉዞ የረገጥኩት ድንጋይ ተፈርክሶ ልወድቅ ስል በእጄ የተደገፍኩት ድንጋይ የቀኝ እጄን ፍቆ ቢያልፍም የተንከባካቢዎቼን ቁጥር ግን ጨምሮታል፡፡ ግማሹ ከሥፍራው ከሚገኝ ማዕድን መድኃኒት ሲቀምምልኝ፣ ግማሹ እጆቼን ይዞ ወደ መኪናዬ መለሰኝ፡፡ ሰባቱ መኪናዎች የበፊት ቅደም ተከተላቸውን ሳይለቁ ሌላ ረጅምና ፈታኝ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ወደ ጭሳማው ተራራ ኤርታሌ፡፡ አባላን ረብቲንና ሌሎችም ሰፋፊ በግራር የተሸፈኑ ቦታዎችን አልፈን ከአሸዋ ሜዳ ላይ ገባን፡፡ እዚህ ለምልክት የሚያዝ ምንም ዓይነት ነገር በሌለበትና ነፋሱ አሸዋውን እያነሳ ሲበትን እንኳን ሌላውን እርስ በርስ መተያየት በሚያቅትበት ቦታ፣ ሐጂ ብቻ እጃቸውን ወደ ግራ ወደ ቀኝ እያደረጉ አቅጣጫ ይጠቁማሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ለሁሉም ሾፌር ፈታኝ በሆነ መንገድ ላይ የሐጂ ጥቆማ ብቻ በቂ አልነበረም፡፡ የሆነ ምትሀታዊ ኃይል ካልተጨመረ  በስተቀር፡፡ እዚህ ምንም ዓይነት የመገናኛ መረብ ከማይሠራበት ሥፍራ ከመኪናዎቻችን መካከል አንዱ ድንገት ከአሸዋው ውስጥ ገብቶ ለመንቀሳቀስ አዳጋች ሁኔታ ውስጥ ሲገባ የእያንዳንዳችን ልብ ይህ ነው በማይባል ፍርሃት ተያዘ፡፡ ነገር ግን መቼም እንኳን በዚህ ጭንቅ ሰዓት ወትሮም መተባበር ባህላቸው ነው ያገሬ ልጆች፣ ብዙ ደክመው ደግሞ ብዙ ስልት ፈጥረውና ታግለው ታደጉት፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ጉልበት በሙቀትና በጉዞ ቢደክምም መኪናውን ከአሸዋው ለማስወጣት በሚደረገው ጥረት ያደረጉት ርብርብ ሲታይ አጃኢብ ያሰኝ ነበር፡፡

እንዲህ እንዲህ እያልን በሐጂ የምናብ ካርታና ኮምፓስ ታግዘን ከጭለማው ተራራ እግርጌ ከተምን፡፡ ወደ ተራራው ጫፍ የሚደረገው ጉዞ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ስለሚጀመር ተጓዦች ኃይል ለማሰባሰብ የሚረዳቸውን ነገር ለመሙላት አሁንም ከጉዟችን ስንቅ አቀባይ ከባላገሩ ማዕድ ላይ አሉ የሚባሉ ኃይል ሰጪ ምግቦች ታደምን፡፡ አሁን በአቅሙ የሚተማመን ብቻ ለጉዞው ሲሰናዳ እኔ ግን አንድም በእንቅልፍ እጦትና በድካም መዛሌ በሌላ ጠዋት ዳሎል ያጋጠመኝ ነገር የማስጠንቀቂያ ደወል ስለመሰለኝ ከተራራው ግርጌ የሚቀረውን ቡድን ተቀላቀልኩ፡፡ አሁንም የትናንትናው ዓይነት ሰማይ፣ ከባድ ነፋስ፣ አሸዋ ላይ መደዳውን የተደረደሩ በርካታ ፍራሾች ስመለከት በመንገዳችን ላይ ስለሥፍራው ስጠይቅ በሙቀት ምክንያት የሚመጡ ትናንሽ ቀያይ እባቦች እንዳሉ ሐጂ የነገሩኝ ነገርን አስታወስኩ፡፡ እንዲህ አየር ላይ ባለ ካርታ መርተው ከዚህ ሥፍራ ያደረሱኝን ሰው እንዴት አልመን? ድካምና ፍርሃቴ የገባውና ጉዞውን በሳቅ በጨዋታ እያደመቀ መኪናችንን ሲያሽከረክር የነበረው ብሩክ በምን ዓይነት ጥበብ እንደሆነ ባላውቅም የመኪናውን የኋላ ክፍል እጅግ ምቹ ወደ ሆነ መኝታ ቀይሮ ጠበቀኝ፡፡ እንዲያ ሰማዩን ካጥለቀለቁት እልፍ ኮከቦች ዘግኜ ለመስተንግዶው ደረጃ ብሰጠው ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ትንኝ እንኳን ወደ እኔ ዝር ሳይል ነጋ፡፡ ታዲያ ካገር ሰው እጅ ምን አጣሁ? ምቾቱን ሳይል አልጋውን ለቆ ከሚያስተናግድ፣ በጉዞ የተቃጠለ እግርን ሊጎነጭ ከያዘው ውኃ ቀንሶ ከሚያጥብ ሰው ጋር ተጉዞ ምን ሊጎድል? ኤርታሌን ለማየት ወደ ተራራው ጫፍ የተጓዙት የቻሉት በእግራቸው፣ ያልቻሉት በግመል ጀርባ ላይ ተጭነው ተመለሱ፡፡ እኛም በሥፍራው የነበረን የቆይታ ጊዜ በማብቃቱ ፀሐይዋ ሳትገር ጉዞ ጀመርን፡፡ አሁን ጆሮዬ ላይ የሚያስተጋባው ሙዚቃ ተቀይሯል ‹‹ምድሬ ጋሞ ጎፋ ዎይታ አርባ ምንጬ›› ቀጣዩ መዳረሻችን ደቡብ ነውና በውብ ተፈጥሮ ታጅቦ ወደ ሚጠብቀን የደቡብ ሰው አቀናን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles