Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየኢትዮጵያ ዶሮዎች የዘረመል ዱካ

የኢትዮጵያ ዶሮዎች የዘረመል ዱካ

ቀን:

ቀለል ያለ ባህሪያቸው ከማንም ጋር እንዲግባቡ አድርጓቸዋል፡፡ በተንጣለለው የምርምሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ ወጪና ወራጁ ቢበዛም ሁሉንም በስም እየጠሩ ያናግራሉ፡፡ ስለ ሥራ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ስለ ሰዎቹ የግል ሕይወት ሳይቀር ያማክራሉ፡፡ ውሏቸው በሥራ የተወጠረ ቢሆንም፣ ሻይ ቤት ውስጥ ስለተሰበረ ማንቆርቆሪያ ሳይቀር መረጃ አያመልጣቸውም፡፡ ተመራማሪ ሆነው ብዙ ዓመት ሠርተዋል፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከሠሩም ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ዶክተር መባልን አይፈልጉም፤ ራሳቸውንም ታደለ ደሴ ነኝ ብለው ማስተዋወቅ ይቀናቸዋል፡፡ ዶ/ር ታደለ በዓለም አቀፉ የእንስሳት ጥናት ተቋም የአኒማል ጀነቲክስ ብሪዲንግ ባለሙያ ናቸው፡፡

     በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና የዓለም ክፍሎች በልዩ ልዩ የምርምር ሥራዎች ተሰማርተው ወዲህና ወዲያ ሲሉ የሚኖሩት ንቁው ዶ/ር ታደለ ከሰሞኑ በሥራቸው እንዲደሰቱ ‹በሕይወቴ አንድ ቁም ነገር ሠራሁ› እንዲሉ ያደረጋቸውን መጽሐፍ አስመርቀዋል፡፡ በመጽሐፉ ያሰፈሩትን ነገር ከማብራራት ይልቅ አንብቦ ማስነበብ የሚቀናቸው ዶ/ር ታደለ ያረፈበትን ጠረጴዛ የሚያክለውን መጽሐፋቸውን ገልጠው ማንበብ ያዙ፡፡

     ከጤፍ ፍሬ የደቀቀና ጥቅጥቅ ያለውን ጽሑፍ ያለ ማጉያ ለማንበብ እንኳንስ በእሳቸው ዕድሜ ላለ ተመራማሪ ሁሉን ነገር ከርቀት አነጣጥሮ ማየት ለሚችል ጤናማ ዓይን ላለው አንድ ታዳጊም የማይታሰብ ነው፡፡ እናም ዓይናቸው ላይ የሰኩትን መነፅር ወደ ጎን ብለው ማጉሊያ መሣሪያቸውን በእጃቸው ወደ መጽሐፉ ደግነው ዓመት ቢቀመጡ የማይገፋ የሚመስለውን መጽሐፍ ያነቡ ጀመር፡፡ መጽሐፉ የተጻፈው በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቢሆንም፣ ስለምን እንደሚያወራና ምን እንደሚል ለማወቅ ቋንቋዎቹን ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ከእሳቸውና ከጥቂት መሰሎቻቸው ውጪ ከኢንሳይክሎፔዲያ የማይተናነሰውና በቀይ ቆዳ የተለበጠው መጽሐፍ የያዘውን ምስጢር ማወቅ የማይታሰብ፣ ማንበቡም ከባድ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡

- Advertisement -

     በያዙት ክብ ማጉያ መሣሪያ ቲሲ4ሲቲ21ቲቲ72ቲቲ0ጂጂ170 የሚል ምንነቱ ያልታወቀ በአንቀጽ የማይከፋፈል፣ በአራት ነጥብ የማይዘጋ ከጥግ እስከ ጥግ ግጥግጥ ብሎ የሰፈረ ጽሑፍ ይነበባል፡፡ ውሉ ያልታወቀ የሚመስለው የፊደላትና አኃዛት ጋጋታ የኢትዮጵያ አገር በቀል ዶሮዎች የዘረመል ዱካቸው የተከተበበት፣ የኢትዮጵያ ስለመሆናቸው እንደማረጋገጫ ሰነድ ሆነው የሚያገለግሉ ኅልቆ መሳፍርት የሆኑ ኮዶች ማውጫ ‹‹ቡክ ኦፍ ጄኖም›› ወይም የጅምላ ዘረመል ይባላል፡፡ ከቀናት በፊት የተመረቀው ቡክ ኦፍ ጄኖምን ለመቀመር የዘረመል ድርደራ (ጄኖም ሲኩዌንስ) ማዘጋጀት ነበረባቸው፡፡

     ጄኖም ሲኩዌንስ የአንድን ሕይወት ያለው አካል አጠቃላይ የዘረመል አደራደር  የሚያሳይ ሳይንሳዊ ዘዴ ሲሆን፣ የእንስሳትን ኃይለ ሕዋስ የዕፅዋትን አረንጓዴ ሃመልሚል እንዲሁም በዓይንማይታዩ ጥቃቅን ተዋህስያንን የጅምላ ዘረመል አደራደርን  ሙሉ ይዘትና አሠራርን አቅፎ ይይዛል፡፡ 

     ይህ ሳይንሳዊ ዘዴ ካሉት የዘረመል አደራደርና አሠራር ሁኔታ ለማጥናት ከሚውሉ ዘዴዎች የላቀ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ የዘረመልን ጅምላ አደራደርና ገፅታን በማሳየት የእንስሳትና ዕፀዋት በሽታን ለመለየት፣ ከበሽታ ጋር የተያያዙ ቅይር ተራቢዎችን ለመለየት፣ የሥነ ሕይወትን ዝግመተ ለውጥ ለማጥናትና ለእንስሳትና ዕፀዋት ምርታማነት የሚረዱ በራሂዎችን በላቀ ሁኔታ ለይቶ ማወቅ ያስችላል፡፡ ይኼ ዘዴ በተለይም ለበሽታ ተጋላጭ የሆኑ ነጥበ በራሂዎችን በመለየት ያላቸውን ጠቃሚና ጎጅ ባህሪያት በማጥናት ማግኘት የሚቻለውን ጥቅም በከፍተኛ መጠን መጨመር፣ ጉዳቱን ደግሞ መቀነስ ያስችላል፡፡ ይኼንን አሠራር በመጠቀም በዘረመላዊ ውርስ የሚከሰቱ የእንስሳት፣ የሰውና የዕፀዋት በሽታዎችን፣ ለካንስር ተጋላጭ በራሂዎችን፣ የበሽታ አምጭ የጅምላ ዘረመል ደረደርና ከእንስሳትና ዕፀዋት ጋር ያላቸውን መስተጋብር በመለየት ለሕክምናው ዘርፍና የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል እገዛ ያደርጋል፡፡

     ‹‹የየሰዉ ጀነቲክ ባህሪ በጣም የተለያየ ነው፡፡ ይኼንን ባህሪ ጀኖታይፕ እናደርገዋለን፡፡ ይህም ለምሳሌ አንድ ሰው ከቤተሰቦቹ የወሰደው በሽታ አልያም ልዩ ንቃተ ህሊና ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከቤተሰቦቹ የወረሰው በሽታ ግፊት ከሆነ ለእያንዳንዱ ነገር በሽታና ለሌሎችም ነገሮች መከሰት ምክንያት የሆነውን ዘረመል ኤዲት በማድረግ በዘር ሐረጉ የሚከተለው በሽታ በሱም ሆነ ወደ ቀጣይ ተወላጆቹ እንዳይተላለፍ ማስቆም የሚቻልበት ዘዴ ነው፡፡ ወይም የአንዱን ሰው የቆዳ ቀለም ቀይ የአንዱን ደግሞ ጠይም የሚያደርጉ የጂን ስብስቦችን ኤዲት በማድረግ የተፈለገውን ዓይነት የቆዳ ቀለም ያለው ልጅ መውለድ እንዲችሉ ማድረግ የሚቻልበት የምርምር ዘርፍ ነው፡፡ ‹‹በእኛ አገር የጂን ኤዲቲንግ ሥራ ስለማይፈቀድ ጂኖቹን የማጥናትና ባህሪያቸውን የመረዳት ሥራ ብቻ ነው የምንሠራው፤›› ብለዋል፡፡

     የአገር በቀል ዶሮዎች የጅምላ ዘረመል ጥናት የተካሄደውም ይኼንን መርህ ተከትሎ ሲሆን፣ የባህሪ ጥናቱ የትኛው ዘረመል ለእንቁላል ምርት፣ የትኛው ለክብደት ምክንያት ነው የሚሉ መረጃዎችን ያካተተ ነው፡፡ ይህም የዶሮዎቹን ምርታማነት ለመጨመር፣ በሽታ የመቋቋም አቅማቸውን ለማጎልበትና ሌሎችም ከዶሮዎች የሚገኙ ጥቅሞችን ከፍ ለማድረግ ይረዳል፡፡

     ከዚህም ውጪ የጅምላ ዘረመል ጥናቱ መካሄድ ኢትዮጵያ የእነዚህ ጂኖች ባለቤት ነች ብሎ መዝግቦ መያዙም የአገር ሀብትን ከማስጠበቅ አኳያ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡  የጂን ሀብቷ ተመዝግቦ በመረጃነት መያዙ ማንም አካል ከውጭ መጥቶ እንዳሻው ሊጠቀምበት ቢሻ መረጃ ይዞ መከልከልና ክስ መሥርቶ መከራከር ቀላል ነው፡፡ ‹‹በጤፍና በቡና ላይ ያጋጠመውን ዓይነት የባለቤትነት ውዝግብ ጉዳይ እንዳይፈጠር ያደርጋል፡፡ የተለየ ጠቃሚ ነገር ተገኝቶበት ሰዎች ሊወስዱት ከፈለጉ የሮያልቲ ክፍያ መጠየቅም ያስችለናል፤›› በማለት የባለቤትነትን መብት ከማስጠበቅ አንፃር የተመዘገበ መረጃ መኖሩ ሌላው ጥቅሙ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር መጪው ትውልድ ይኼንን መጽሐፍ እንደ ማጣቀሻ አድርጎ ሊማርበት፣ እንደ መነሻ አድርጎ ሌሎች ተጨማሪ ጥናቶችን ለማካሄድ ሊጠቀምበት የሚችልበት ዕድል መኖሩም ሌላው  የመጽሐፉ ፋይዳ እንደሆነ ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡

     ‹‹እንደ አገር ይኼ የመጀመርያው ከመሆኑ ባለፈ በአፍሪካም ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ እንደ አንድ የጥበብ ሥራ፣ እንደ ቅርስ ከእነ ሉሲ ጋር እንዲቀመጥ ለብሔራዊ ሙዚየም አስረክበናል፤›› የሚሉት ዶ/ር ታደለ መጽሐፉ በመዘጋጀቱ በምርምር እንደ ማጣቀሻ፣ ለባለሙያው መነሳሳትን እንደሚፈጥር ይናገራሉ፡፡

     በሳይንስ ሊዳብሩ ከሚችሉ ባህርያት በተጨማሪ አገር በቀል ዶሮዎች በተፈጥሮና አካባቢያዊ ተፅዕኖ ሥር ሆነው ያጎለበቷቸው ባህሪያት መካከል በሽታ የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ መሆን አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ዶሮዎቹ እርስ በርስ ያላቸው ጄኖታይፕ ከሌላው በተለየ በእጅጉ ብዝኃነት ያለው ሲሆን፣ ይህም የተሻለ ዝርያ ለማግኘት ትልቅ ግብአት እንደሆነ ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡

     ብዝኃነቱ ሊፈጠር የቻለው ከከባቢ ጋር ተስማምቶ ለመኖር (አዳፕቴሽን) በሚደረግ ጥረት ነው፡፡ የዶሮዎቹ ጀነቲክ ሜካፕ በተፈጥሮና በአካባቢ ተፅዕኖ ሥር ይወድቃል፡፡ ሰዎች ዶሮዎቹን ለማሻሻል በሚያደርጉት ጥረት ከመጀመርያው የተለየ ጀነቲክ ሜካፕ ያለው ዶሮ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ተፈጥሯዊ ሥነ ምህዳር ክልል ውስጥ ለመኖር የሚደረገውን ትግል ማሸነፍ የቻሉ መኖር በሚችሉበት የዳርዊን ቲዎሪ ተሽለው የተገኙ ጠንካራ ጂን ያላቸው በተፈጥሮ ሒደት ይመረጣሉ፡፡ እነዚህ ሒደቶች የዶሮዎቹ የጀኔቲክሜካፕ ብዝኃነት እንዲኖር ምክንያት ናቸው፡፡

     ‹‹በተፈጥሮ ከሚኖራቸው ልዩ ባህሪ ባሻገር አካባቢያቸው የሚያሳድርባቸው ተፅዕኖ የጀነቲክ ሜካፓቸው ላይ ልዩነትን ይፈጥራል፡፡ በአካባቢ ተፅዕኖ የሚፈጠር ልዩ የጀነቲክ ሜካፕ ግን ሊፈጠር የሚችለው በሚሊዮን ዓመታት ሒደት ነው፡፡ በእያንዳንዱ አካባቢ ያሉ የዶሮ ዝርያዎች በጣም የተለያዩ ናቸው፤›› በማለት በሁለቱ መንገዶች የሚከሰቱ ተለያይነቶችን አብራርተዋል፡፡

     ይህ የጀነቲክ ተለያይነት ከሌላው በተለየ ምርጥ ውጤት መስጠት የሚችሉበት ምስጢር የተለያዩ ነገሮች ሲደመሩ የሚፈጥሩት ኅብረት ጠንካራ በመሆኑ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ተመሳሳይ ዘረመል ያላቸው ነገሮች ሲደመሩ የተለየ ነገር የመፍጠር አቅማቸው እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ ‹‹ሱዳን ጠረፍ ላይ ያለን ዶሮ ሐረር ላይ ካለ ዶሮ ጋር ሲዳቀል ያላቸው የጀነቲክ ሜካፕ በጣም የተራራቀ ስለሆነ የሁለቱ ድቅል ምርጥ ሆኖ ይወጣል፤›› ብዝኃነት ያለውን ጠቀሜታ ያብራራሉ፡፡

     በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ሥነ ምህዳር ውስጥ የሚኖሩ ወደ 14 የሚሆኑ የአካባቢ የዶሮ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ሌላው በአገር በቀል ዶሮዎች ላይ የታየው መልካም አጋጣሚ በከባድ ሁኔታ ውስጥ ሳይበገሩ መኖር መቻላቸው ነው፡፡ ‹‹አንድ የፈረንጅ ዶሮ ሜዳ ላይ ብትለቂያት ምግብ እስካልተሰጣት ድረስ ጭራ አትበላም፡፡ የኛዎቹ ግን የሚበሉትን ለማግኘት ወጥተው ይጭራሉ፡፡ በዚህ መልኩ ለመቶ ሺና ሚሊዮን ዓመታት ስለኖሩ ጂናቸው ተላምዶታል፤›› ሲሉ አይበገሬነታቸው፣ አውሬ ሲመጣ ሮጠው ማምለጥ መቻላቸው ሌላው ልዩ የሚያደርጋቸው ባህሪ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

     የአገር ውስጥ ዶሮዎች እነዚህን ዓይነት ተመራጭ የሚያደርጋቸው ልዩ ባህሪያት ቢኖራቸውም ምርታማነታቸው ደካማ መሆኑ ከማንም ያልተደበቀ በምርምሩም የተረጋገጠ ነገር ነው፡፡ የፈረንጅ ዶሮዎች በዓመት ከ250 እስከ 280 እንቁላሎችን ሲጥሉ፣ የሐበሻ ዶሮዎች ደግሞ በዓመት በአማካይ 60 እንቁላሎችን ብቻ ይጥላሉ፡፡ ቡክ ኦፍ ጄኖም ታዲያ ለዚህ ቁልፍ መፍትሔ የሚሰጥ አማራጭን የፈጠረ ሲሆን፣ የተሻለ ምርታማ የሆኑ ዶሮዎችን ለማውጣት የመጨረሻው ደረጃ ላይ መደረሱን ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር የ‹‹ሆሮ›› ዶሮዎች የሚጥሉትን እንቁላልም ወደ 180 ከፍ ማድረግ እንደሚቻልም በተግባር ታይቷል፡፡

     ‹‹የሐበሻ ዶሮዎች ከፈረንጅ ዶሮዎች በተለየ እንቁላላቸው ደማቅ ቢጫ ቀለም ያለው ሥጋቸውም የሚጣፍጥ የሆነበት ምክንያት አረንጓዴ ቅጠላቅጠል ስለሚመገቡ ነው፡፡ በምርምሩ የሐበሻ ዶሮዎች ጣዕማቸውን እንደጠበቁ ምርታማነታቸውን ማስጨመር ይቻላል፡፡ ይህ የምርምር ሒደትም የሐበሻ ዶሮዎች የሚጥሉት እንቁላል በዓመት እስከ 260 እስኪደርስ እንሠራለን፤›› ይላሉ፡፡  

     በአገር በቀል ዶሮዎች ላይ ለሚሠሩ ጥናቶች፣ ዝርያና ምርታማነትን ማሻሻያ ፕሮጀክቶች ቁልፍ ግብዓት ሆኖ እንዲያገለግል የተዘጋጀው ቡክ ኦፍ ጄኖም ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን አቅም እስከ ጥግ ድረስ እንድትጠቀምበት የሚያስችላት ነው፡፡ እንግሊዝኛው 1,166፣ አማርኛው ደግሞ 1,000 ገደማ የሚሆን ገጽ ያለውን መጽሐፍ ለማዘጋጀት እሳቸውን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ተሳትፈዋል፣ ጨርሶ ለማሳተምም ሰባት ዓመታትን ፈጅተዋል፡፡ እንደ ኒኩለር ፊዚክስ የበለጠ ውስብስብ መስሎ በሚታየው መጽሐፍ የኢትዮጵያ ዶሮዎች የዘረመል ዱካ፣ ብዝኃነት አንድም ሳያስቀር ተከትቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...