Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከጥያቄዎቻችን በስተጀርባ የመሸጉ እውነቶች!

ሰላም! ሰላም! በመላው ዓለም የምትገኙ ቤተሰቦች፡፡ በሥራ፣ በኑሮ፣ በችግር ከኢትዮጵያ ርቃችሁ የምትገኙ እንደምን ሰንበታችኋል? እዚህ ኢትዮጵያ ሁሉ ሰላም፣ ሁሉ ሙሉ ነው፡፡ ከዶላር እጥረት ውጪ በአሁኑ ወቅት እዚህ ግባ የሚባል ችግር የለንም፡፡ ዕድሜ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን፡፡ ባሻዬ ደግሞ ‹‹አንድ ሺሕ ዓመት ይግዙን፤›› በማለት ነው ሥራቸውን ያሞካሹላቸው፡፡ ለነገሩ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በገዛ አንደበታቸው ለሥልጣን ዘመን ገደብ ይበጃል በማለታቸው፣ የባሻዬ ምኞት እንደሚመክን መገመት አይከብደንም፡፡ እንግዲህ ምሥጋና ይግባቸውና ችግር አለበት የተባለውን ቦታ እያነፈነፉ፣ ከምንጩ በማድረቅ አገራዊ ኃላፊነት ተጠምደው ይገኛሉ፡፡

ይህ አካሄዳቸው የገረመው የባሻዬ ልጅ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹እመነኝ ሶሪያና ሊቢያ ድረስ መዝለቃቸው አይቀርም፤›› ሲለኝ ፈገግ አልኩ፡፡ እኔም ብሆን ለምንም እንደማያንሱ ሙሉ እምነቴ ነው፡፡ እንዲህ ናት ኢትዮጵያ፡፡ ከውስጥ ወደ ውጭ፡፡ ከአምቦ መቐለ፣ ከመቐለ ጎንደር፣ ከጎንደር ባህር ዳር፣ ወዘተ ወጣ ሲሉ ደግሞ ከጂቡቲ ሱዳን፣ ከሱዳን ሊቢያ፣ ከሊቢያ ሶሪያ እያደረጉ ‘ዓለም እንዴት ሰነበተች’ እያሉ ከራሳቸው አልፈው ለጎረቤት ለሩቅ አገሮች የመፍትሔ ቋት እንደሚሆኑ ማንም ሰው መጠርጠር የለበትም ብል ምናለበት? ‘ደግ ተመኝ ደግ እንድታገኝ’ እንዲሉ ማለት ነው፡፡

      ማንጠግቦሽ በበኩሏ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፈችው መልዕክት፣ ‹‹ክቡር ሆይ የኤርትራን ነገር አደራ፤›› ነበር ያለችው፡፡ ማንጠግቦሽ ተጫዋች ሆናብኛለች፡፡ ምን ብትለኝ ጥሩ ነው? ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩን አግኝቼው እንዲያው አንዳች ነገር ባስቸገርኳቸው?›› አለችኝ፡፡ እኔም ፈገግ ብዬ፣ ‹‹ምነው እኔን የፈለግሽውን ጠይቂኝ አመጣልሻለሁ…›› ብላት፣ ‹‹አንተማ ልክ ነህ፣ ምንም አጉድለህብኝ አታውቅም፡፡ አሁን ግን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ነው በሄዱበት አንዳች ነገር ይዘውልኝ እንዲመጡ የምፈልገው፤›› ነበር ያለችው፡፡ ወዳጆቼ እኔ እንግዲህ ማንጠግቦሽን ካገባሁበት ጊዜ ጀምሮ አንዲትም ቀን አንድም ነገር አጓድዬባት አላውቅም፡፡ ታዲያ አሁን ይኼው ከእኔ በላይ የሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያመጡላት የፈለገችው ምን ይሆን? መቼም እሳቸው ነጋዴዎችን ጠርተው እንዳማከሩት እንዲሁ እኛንም ደላሎችን ጠርተው እስኪያማክሩን ድረስና በዚያውም የማንጠግቦሽን ጥያቄ እስካደርስላቸው ድረስ፣ ያው ምናልባት በዚህ አጋጣሚ ካነበብኳት ብዬ መልዕክቱን እዚህ አኖራለሁ፡፡

      መቼም በታላቁ ሸራተን አዲስ ጠርተው ሲያወያዩን የሚሰማኝን ደስታ እያሰብኩ ከአሁኑ እየተብነሸነሽኩ እገኛለሁ፡፡ በግምት ወደ ሰላሳ ጥያቄ የምጠይቃቸው ይመስለኛል፡፡ ታዲያ የማንጠግቦሽን ጥያቄ አስቀድሜ እንደሆነ ልብ በሉልኝ፡፡ ዶላር አምጡ እንደማይሉን አውቃለሁ፡፡ ባይሆን የቤት ኪራይም ሆነ የመሬት ሽያጭን አታስወድዱ እንደሚሉን ገምቻለሁ፡፡ መቼም አብዛኛው ሰው ከእያንዳንዱ ጭማሪ ጀርባ የደላላ እጅ አለበት ብሎ የሚያስብ ስንት አለ መሰላችሁ? ልክ ያኔ ነዳጅ ጨመረ ብለው የቤት ኪራይ እንደጨመሩት አከራይ ማለት ነው፡፡ ኪራይ ውስጥ ለካ ደላላ አለበት? ኧረ ስንት አሉ? አንድ ኪሎ ስኳር አንድ ብር ጨመረ ብለው የአንድ ብርጭቆ የሻይ ዋጋ ላይ አምስት ብር የሚጨምሩ፡፡ ሁሉም ለመጨመር ተዘጋጅቶ ነው የሚሠራው፡፡ መቼ ይሆን የሚቀንስ ነገር የምናገኘው? አሁንስ ይመራል፡፡

      መቼ ዕለት ነው አንድ ቡቲክ ‘50 በመቶ ቅናሽ አድርጌያለሁ ኑ እና በነፃ ውሰዱ’ ያላቸውን አልባሳትና መጫሚያዎች ዋጋ እንኳን ሊቀንስ፣ ከመደበኛው ዋጋ 25 በመቶ ጨምሮ እየሸጠ እንደነበር የነገረኝ ደላላው ጓደኛዬ ነው፡፡ የእኛ ሰው ታዲያ የፈረንሣይ፣ የቱርክ፣ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ… የተባሉትን ዕቃዎች በቅናሽ ስም እየተጋፋ ሲሸምት መመልከት አዝናኝ ትርዒት ነው፡፡ ሕዝቡስ ምን ያድርግ? ቀነሰ የሚባል ነገር መስማት ከመጠማቱ የተነሳ፣ ቀነሰ የተባለውን በተጨመረበት ዋጋ ነው የሚገዛው፡፡ በዕውቀቱ ሥዩም እንዳለው፣ ያልጨመረ ነገር ቢኖር ኪሎ ሜትሩ ብቻ ነው፡፡

ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ እንመለስ፡፡ እሳቸው የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ውለዱ እንደሚሉም እጠረጥራለሁ፡፡ ባለሀብቶቹን ዶላር አምጡ እንዳሉት እኛን ደላሎች ደግሞ ኢንቨስተር አምጡ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሐሳብ እኔም እስማማለሁ፡፡ ትንሽ ቋንቋ እየቸገረኝ ነው እንጂ፣ አንዳንድ ኢንቨስተሮች እያገኘሁ ነው፡፡ ደግነቱ የባሻዬ ልጅ አለልኝ፡፡ ‹‹መቼም በዚህ ወቅት አንደ የውጭ ኢንቨስተር ላመጣ ደላላ›› ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ቀጥለዋል፣ ‹‹ለዚህ ዓይነቱ ደላላ ልዩ ሽልማት እናበረክታለን፡፡ በሚሠራው ሥራ ሁሉ ቀረጥ እንዳይከፍል እናደርገዋለን፡፡ በስሙም ቢሆን መንገድ እንሰይምለታለን፡፡ 500 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤቱ እንዳለ ሆኖ…›› እያሉ ጆሮ ገብ በሆነው ንግግራቸው ሲያብራሩ ይመስለኛል ንግግራቸውን መጨረስ አቅቶት፣ አብዛኛው ደላላ አዳራሹን ለቅቆ ሲወጣ ይታወቀኛል፡፡ ለምን? አትሉኝም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ቅር ተሰኝተው አ . . .፣ አይደለም፡፡ ዳሩ ግን ወደ ሥራ ለመግባት ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም፣ ኢንቨስተር መፈለግ አለብን በማለት ነው፡፡

      ታዲያ ይህ መልካም አጋጣሚ ለእኔ ምቹ ሁኔታን ፈጠረልኝ ማለትም አይደል? እኔም የማጠግቦሽን ጥያቄ አስቀድሜ ጥያቄዎቼን በሙሉ ያለማንም ተቃውሞ አቀርብላቸዋለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ በማለት እንድናገር ዕድል የሚሰጡኝ ይመስለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹እሺ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት መድረኩን ለአንተ እሰጣለሁ፡፡ ጥያቄዎችህን ሁሉ ማቅረብ ትችላለህ፡፡ ይህች አዲሲቷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ማንኛውም ዜጋ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ መጠየቅ የሚችልበት፡፡ እኛም ደግሞ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉ ለጥያቄዎቹ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን…›› እኔም ማይኩን እቀበልና በሕይወት ዘመኔ ያገኘሁትን ምናልባትም ብቸኛ ሊባል የሚችለውን ዕድል እንዲህ በማለት እጠቀምበታለሁ፡፡

      ‹‹ክቡር ሆይ! በእውነቱ እርስዎ መሪ በሆኑበት አገር በመፈጠሬ አምላኬን አመሠግናለሁ፡፡ ምንም እንኳን የሥልጣን ዘመንዎ አሥር ዓመት እንዲሆን እንደሚፈልጉና በሥራ ላይ እንዳሉ ባውቅም፣ እኔ በተፃራሪ 100 ዓመት እንዲነግሡ መልካም ምኞቴን ሳልገልጽ አላልፍም፤›› ስል፣ ጉባዔው በጭብጨባ ሲናጋ ይታወቀኛል፡፡ ውይ! ለካ ደላሎቹ ሁሉ ጉባዔውን ለቅቀው ሄደዋል፡፡ ብቻ ያለው ሰው በቂ ነው፡፡ ለዚህ በኩር ሐሳብ ጭብጨባ ለማምጣት ንግግሬን ቀጥያለሁ፡፡

‹‹እነሆ በርካታ ጥያቄዎችን አንስቼ የኢትዮጵያ ደላሎችን ሁሉ በገጠር በከተማ ያሉትን ወክዬ በፊትዎ እንደ መቆሜ መጠን፣ የኢትዮጵያ ደላሎችን የሚመለከቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ሁሉ ወደ እርስዎ አቀርባለሁ፡፡ ከዚህ ሁሉ በፊት ግን እርስዎም መጀመርያ በተመረጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የቤተሰብን ታላቅ ሚና ከእናትዎ እስከ ባለቤትዎና ልጆችዎ ድረስ ገልጸው ነበር፡፡ በዚህም ለአገር ግንባታ ዋነኛ ምስሶው ቤተሰብ እንደሆነ ዕሙን ነው፡፡ ስለሆነም ለቤተሰብዎ ያለዎት አክብሮትና ፍቅር ሳላደንቅ አላልፍም፡፡

‹‹እኔም ታዲያ የእርስዎን ፈለግ በመከተል በመጀመርያ የውዷ ባለቤቴን የማንጠግቦሽን ሰላምታና ጥያቄ ወደ እርስዎ በማድረስ ጥያቄዬን እጀምራለሁ፡፡ ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ በግል የምታውቅዎት እስኪመስል ስለእርስዎ አውርታ አትጠግብም፡፡ በኢቢኤስ ላይ ያየችውን ያንኑ የእርስዎን ንግግር በኢቢሲ ትደግመዋለች፡፡ እሱ ሲገርመኝ በፋና እንደገና ደግማ ታዳምጣለች፡፡ በዚህ ሊገረሙ ይችላሉ፡፡ እሷ ግን በዚህ አታበቃም እንደገና ሬዲዮኑን ጠምዝዛ የእርስዎ ንግግር በሚተላለፍበት ጣቢያ ሁሉ ደግማ ደጋግማ ታደምጥዎታለች፡፡ ይህቺ እኔን የምትወድ እርስዎንም የምትወድ ባለቤቴ እኮ አንድ ጥያቄ አዘውትራ ብትጠይቀኝ እርስዎ ዘንድ ይደርስላት ብዬ ነው፡፡ አሁን ያው በሥራ ምክንያት ወደ ውጭ እየወጡ ስለሆነ አንድ ነገር እንዲያመጡላት ትፈልጋለች፡፡ ይህንን ስል መቼም ምንድነው እንዳመጣላት የምትፈልገው? እንደገና ደግሞ አንተ ለምንድነው የማታመጣላት? በሚል ስሜት እንደሚያዩኝ አምናለሁ፡፡ እኔም እንደ እርስዎ ነበር ያስብኩት፡፡ ምንድነው የምትፈልጊው? የፈጀውን ይፍጅ እንጂ አመጣልሻለሁ ብላትም፣ ያው ከእኔ አቅምና ችሎታ በላይ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡

      ስለሆነም ክቡር ሆይ የውዷ ባለቤት ጥያቄ ወዲህ ነው፡፡ ጂቡቲ ሄደዋል፣ ሱዳንም ሄደዋል የሚባል ነገር ሰምቻለሁ፡፡ እኔ ነዳጅም፣ ስኳርም፣ ዶላርም አምጡልኝ ብዬ አላስቸግርዎትም፡፡ ነገር ግን በሚቆዩበት አሥር ዓመት ውስጥ በሚያደርጉት የውጭ ጉዞ አስደንጋጭና ያልተጠበቀም ቢሆን ኤርትራን ይዘውልኝ ኑ  በማለት ውዷ ባለቤቴ አደራዋን አሸክማዎታለች፤›› ስል፣ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለመልስ ሳይቸኩሉ ትንሽ ጎንበስ ብለው ማሰላሰል ይጀምራሉ፡፡ የማንጠግቦሽን ጥያቄ አቅርቤያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ የወከለኝን የደላላውን ማኅበረሰብ ጥያቄ አቀርባለሁ፡፡ የሆነስ ሆነና ዋናው ጉዳይ ግን መዘንጋት የለበትም፡፡ ወገኖቼ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ማቅረባችን ጥሩ ነው፡፡ ግን ጥያቄያችን ምላሽ ለማግኘት ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ አካል እንዲያደርጉን ምን ትላላችሁ? መልሶቻችን ያሉት ጥያቄዎቻችን ውስጥ እኮ ነው፡፡ ከጥያቄዎቻችን በስተጀርባ ያሉትን እውነቶች አንርሳ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት