Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየድል ደወል

የድል ደወል

ቀን:

ፋሺስት ጣሊያን አዲስ አበባን በያዘበት ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን (1928 ዓ.ም.) በሕዝቡና በአርበኞች ተጋድሎ የኢትዮጵያ የድልን ቀን ሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን (1933 ዓ.ም.) ተበሰረ፡፡ 77ኛ ዓመቱንም ቅዳሜ ሚያዝያ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ተዘከረ፡፡ ዘውዴ ረታ ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት›› በሚለው መጽሐፋቸው ስለ ታሪካዊቷ ሚያዝያ 27 እንዲህ ጽፈዋል፡፡

‹‹ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ በከፍተኛ አጀብ እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ላይ ከታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት አደባባይ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ዓላማችንን መልሰው ሰቀሉት፡፡ የክብር ዘብ ተሰልፎ፣ በራስ አበበ አረጋይ የሚመራው አሥር ሺህ አርበኞች ያሉት ጦር ዙሪያውን በሀገር ፍቅርና በብሔራዊ ስሜት እንደቆፈጠነ፣ በሱዳን በኩል የመጣውና በሻለቃ ዊንጌት የሚመራው የጌዲዮን ጦርም ተሰልፎ፣ መድፍ ተደጋግሞ እየተተኮሰ ሰንደቃችን በክብር ከፍ አለ፡፡›

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስደት መልስ መናገሻ ከተማቸው ሚያዝያ 27 ቀን ገብተው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከማውለብለባቸው አራት ወር ግድም በፊት ጥር 12 ቀን ሱዳን ድንበርን ተሻገረው ኢትዮጵያ ገብተው ያውለበለቡት ኦሜድላ ላይ ነበር፡፡

ከሰባ ሰባት ዓመታት በፊት የድሉን ብሥራት አስመልክተው ባለቅኔው የእንጦጦ ራጉኤሉ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ፡- ‹‹ኢትዮጵያ ከማር ለሚጣፍጥ ለስምሽ አጠራር ሰላም ይገባል፡፡ ባምላክ እጅ ለተሠራ ለራስ ፀጉርሽም ሰላምታ ይገባል፡፡ ምሳሌ የሌለሽ መቅደስ ኢትዮጵያ ጠላት ጣሊያን ስላረከሰሽና መሠዊያሽን ስላጠፋ ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ ተቀደሽ፣ ኃይልንም ገንዘብ አድርጊ›› ብለው ተቀኝተውላት ነበር፡፡ ‹‹እናታችን ኢትዮጵያ ሆይ ለታረዙ ልብስ ነሽና በባንዲራሽ ጥላ ሰብስቢ ልጆችሽን›› እያሉም ዘመሩላት፡፡

የመከራው አንድ ጥግ

ከሰማንያ ሁለት ዓመታት በፊት የተፈጸመው የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ በኢትዮጵያ ላይ ብዙ መከራዎችን ትቶ ማለፉ አይዘነጋም፡፡ እርመኛ አርበኞች አገራዊ ነፃነት ለማስከበር የሕዝቡን ልዕልና ለማስጠበቅ ያደረጉት ተጋድሎ የትየለሌ ነው፡፡ ጣሊያን በዓድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ከ40 ዓመት ቆይታ በኋላ በፋሺስታዊ መንግሥቷ አማካይነት በአምስቱ ዘመን የሠራችው ግፍ ተነግሮ አያልቅም፡፡ ወረራውን በፈጸመች ባመቱ በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በአካባቢው ከፈጸመችው ግፍ አንስቶ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢው ብዙ ጥፋትን አድርሳለች፡፡ ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያው የፋሺስት ወንጀለኞች የኢትዮጵያን ሠራዊት የፈቱበት በተምቤንና በሐሸንጌ በመርዝ ጋዘ ያደረሱት እልቂት ይጠቀሳል፡፡

አቶ ጥላሁን ጣሰው ‹‹Trying Times›› (ትራዪንግ ታይምስ) በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደጻፉት፣ ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 .. ኢትዮጵያን የወረረችው፣ በቅኝ በያዘቻቸው በሰሜን በኤርትራ በኩልና በደቡብ ምሥራቅ በኢጣሊያን ሶማሊላንድ በኩል 400 ሺሕ  ወታደሮች፣ 300 የጦር አውሮፕላኖች፣ 30 ሺሕ ተሽከርካሪዎችና 400 ታንኮች አማካይነት ነበር፡፡ ሙሶሎኒ በወቅቱ የደረሰበትን ሽንፈት ለመቋቋምና ለመቀልበስ የወሰደው እርምጃ ሠራዊቱ በመርዝ ጋዝ እንዲጠቀም ማዘዙ ነው፡፡

 የታኅሣሥ 18 ቀን 1928 .. የሙሶሎኒ ትዕዛዝ በተምቤንና በሐሸንጌ ሐይቅ ለሺዎቹ እልቂት ሰበብ ሆኗል፡፡ ‹‹በተምቤን ጦርነት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ ባልሆኑ መሣርያዎች ድል አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ድል በማድረጉ ፋሺስት የኬሚካል ጥቃቱን ፈጸመ፡፡ በዚያን ጊዜ ያለቁት 700 ሺሕ የሚደርሱ ናቸው፡፡››

አቶ ጥላሁን፣ በተምቤን ጦር ግንባር አዛዥ የነበሩት ራስ ካሳ በመጽሐፋቸው የገለጹትን፣ ከፈረንሣይኛ ተተርጉሞ ያገኙትን አውስተዋል፡፡ ‹‹የተምቤን ጦርነት ጊዜ አሸነፍን፤ ዋናው ነገር [ኢጣሊያ] ሩቅ የሚመታ መሣርያ አላቸው፤ እኛ በቅርብ ሆነን ማጥቃት እንችላለን፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ተዝናንተን ሳለን አንድ ቀን የእነርሱ አውሮፕላኖች ቢመጡ እንፈትሻቸዋለን ስንል በጣም ከርቀት ሆነው አውሮፕላኖቹ ለእርሻ አረም ማጥፊያ በሚሆን መርጪያ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ ጥይት የሚደርስበት አይደለም፡፡ ዝም ብሎ ይወርዳል ኬሚካል ሰልፈር (ድኝ) አለው፡፡ መስተርድ ጋዝና ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ጣሉ፡፡ ሰውም መቃጠል አገርም በሙሉ መቃጠል ጀመረ፡፡ ዋሻው ውስጥም ሆኖ መቋቋም አይቻልም ሰው ሁሉ አለቀ፡፡ አንድም ጣሊያን ከዚያ በኋላ አልሞተም፡፡››

የውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች በተለይ የፋሺስት ደጋፊ የሆኑት፣ በተምቤን ስለተካሔደው ጦርነት ‹‹የመጀመርያው የተምቤን ጦርነት›› ‹‹ሁለተኛው የተምቤን ጦርነት›› በማለት ታሪኩን ያዛባሉ፡፡ ‹‹የመጀመርያው የተምቤን ጦርነት የሚሉት ኢትዮጵያውያኑ የተወሰነ ድል አገኙ፡፡ ሁለተኛው የተምቤን ጦርነት ላይ ግን በራስ ካሳና ራስ እምሩ  ራስ ሥዩም መንገሻ የሚመራውን ጦር አሸነፉት ይላሉ፡፡›› አቶ ጥላሁን እነዚያን ጸሐፍት ከመሞገት አልተመለሱም፡፡

‹‹ሁለተኛ የተምቤን ጦርነት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ሒሮሺማና ናጋሳኪ ላይ የአቶሚክ ቦንብ በመውደቁ የሒሮሺማና የናጋሳኪ ጦርነት የሚባል ነገር እንደሌለ ሁሉ አንድም ሰው በውጊያ ባልሞተበት በአውሮፕላን በተረጨ መርዝና ከሰልፈር (ድኝ) እና በተቀጣጣይ ፈንጂ በተደበላለቀ ሁሉ ማለቁን ያወጉናል፡፡ በሐሸንጌ ሐይቅ ስለደረሰው እልቂት የራስ ካሳ እይታንም ደራሲው አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ሁሉም የቀይ መስቀል ፈረንጆች ሠራተኞች ከተመለሱ በኋላ በሐሸንጌ ሐይቅ ሜዳ ላይ የሔዱት ሰዎች ሐይቁ ከተመረዘ በኋላ በሙሉ ያልቃሉ፡፡››

ይህ ዘግናኝ ክሥተት በውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች ሲቀርብ የተገለጸው ‹‹የንጉሠ ነገሥቱ ጦር መሸነፉን በሐሸንጌ ሐይቅ ውስጥ በሞላው ሬሳ አወቅነው፤›› ተብሎ ነው፡፡

የዚያን ጊዜ ያለቁት ከወንድሞቻቸው ጋር ወደ ጦር ሜዳ የሔዱ በአብዛኛው ሴቶች፣ ሲቪልና ጥቂት ቁስለኞች መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ጥላሁን፣ አጽንዖት የሰጡበት ነገርም አለ፡፡ ‹‹እኛ አዲስ አበባ ውስጥ ስለተደረገውና ጥቂት ሺሕ ሰዎች ስላለቁበት እናስባለን፡፡ ያኛው በገጠር የተከናወነው ግን እየተረሳ ይሔዳል፡፡ ከተሞች ውስጥ የሚሞተው ሁልጊዜ ይታወሳል፡፡ ገጠሮች ላይ የሚሞተው ይጠፋል፡፡››

አንድ ደራሲ እንደከተበው፣

‹‹…ቢነገር ቢወራ ቢተረክ ቢጻፍ

      ፍጻሜ የለውም የፋሺስቶች ግፍ››፡፡

እንስት ጀግኖቹ

‹‹ሰንበሌጥ [ለቤት ክዳን የሚሆን ሳር] ውስጥ ሆኖ ሲተኩስ አየው ነበር፡፡ ድንገት ፊቱን ወደኔ መለስ አደረገ፣ ወደቀም፡፡ እኔም የያዝኩትን ቦታ ለቅቄ ወደ እሱ ሄድኩኝ፤ ሞቶ ነበር፡፡ በወንዙ ሌላኛው አቅጣጫ በጎን በኩል የጠላት ወታደሮች ተጠግተው ነበር፡፡ ከነበርኩበት ቦታ ከማፈግፈጌ በፊት ወደ ወንዙ አቅጣጫ ተኩስ ከፈትኩ፣ ሦስት ሰዎችንም ገደልኩ፡፡ ከዚያም የባሌን አስከሬኑንና መሣሪያውን እየተጎተትኩ ወደ ኋላ አፈገፈኩ፤ የተቀሩትና ከኔ ጎን ተሠልፈው የነበሩት ሁሉ ግን ደህና ነበሩ፡፡ ወደ ጦር ሠፈሩ ተመለስኩ፡፡ በማግሥቱም አስከሬኑን በዲርማ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስቀበርኩ፡፡››

እናት አርበኛዋ እመት ልኬለሽ በያን በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ ባለቤታቸው ሰማዕትነትን ሲቀበሉ ያዩትንና እሳቸው የፈጸሙትን ጀብዱ ያመለከቱበት ነበር፡፡ ፀሐይ ብርሃነ ሥላሴ ‹‹Women guerrilla fighters›› በሚለው ድርሳናቸው እንደገለጹት፡፡

የፋሺስት ወረራና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ

‹‹… ከእግዚአብሔር መንግሥት በቀር የፍጡር መንግሥት ሁሉ አንዱ ከአንዱ የማይበልጥ ሥራ የለውም፡፡ ነገር ግን በምድር ላይ ኃይለኛ የሆነው መንግሥት ምንም በደል የሌለበትን የሌላውን መንግሥት ሕዝብ ለማጥፋት የሚገባው መስሎት በተነሳበት ጊዜ ተጠቂው ወገን ለመንግሥታት ማኅበር የተበደለውን የሚያቀርብበት ሰዓት ነው፡፡ እግዚአብሔር ታሪክ ለምትሰጡት ፍርድ ለመንግሥት ማኅበርም ምስክር ሆነው ይመለከታሉ…›› 

82 ዓመታት በፊት ሰኔ 23 ቀን 1928 .. የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት (1923–1967 ..) ርዕስ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የፋሺስት ጣሊያን ወረራ አስመልክቶ በጄኔቭ የመንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ሸንጎ ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ኃይለ ቃል ነው፡፡ 

በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን (1888 ..) ዓድዋ ላይ ድል የተመታው የጣሊያን ወራሪ ሠራዊት 40 ዓመት ቆይታ በኋላ በፋሺስቱ ቤኔቶ ሙሶሎኒ አማካይነት ኢትዮጵያን መውረሩና በተለይ በዓለም የተከለከለው የመርዝ ጋዝ በመጠቀም የኢትዮጵያን ሠራዊት 1928 .. መፈታቱ ይታወሳል፡፡ 

እርመኛ አርበኞች የአገሪቱን ነፃነት ለማስከበር የሕዝቡን ልዕልና ለማስጠበቅ መራር ተጋድሎ ማድረጋቸውም ባይዘነጋም የፋሺስት ወንጀለኞች በታኅሣሥ 1928 .. የኢትዮጵያን ሠራዊት የፈቱበት፣ በተምቤንና በሐሸንጌ በመርዝ ጋዝ ያደረሱት እልቂት ይጠቀሳል፡፡ 

በስደት ወደ አውሮፓ የዘለቁት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከክብር ተከታዮቻቸው ጋር ሆነው ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ ማድረጋቸው በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ አንዱና ቀዳሚዋ ኢትዮጵያ አባል ለሆነችበትና መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ጄኔቭ ላደረገው የመንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) የግፍ ወረራውን በመቃወም ለሥዩማኑ አቤት ማለት ነበር፡፡ 

በአንድ በኩል የጣሊያኑ አምባገነን ቤኒቶ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን በመጠቅለል በአፍሪካ የጣሊያን ግዛት መመሥረቱንና አገሪቱንም መያዙን ሲያውጅ፣ አዲስ አበባንም ፋሺስቶች ሚያዝያ 27 ቀን 1928 .. ከመያዛቸው አስቀድሞ የተሰደዱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሙሶሎኒን መግለጫ በመቃወም ለመንግሥታቱ ማኅበር አቤት ቢሉም ድጋፍ አላገኙም፡፡ አብዛኛዎቹ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል አገሮች ለጣሊያን ወረራ እውቅና ሰጥተው ነበርና፡፡  የአርነት ተጋድሎው ግን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ቀጥሏል፡፡

ሴቶችና ተጋድሏቸው

በሰሜን የማይጨው ግንባር ከዘመቱት ሴቶች መካከል ከአርሶ አደር ቤተሰብ እስከ ልዕልታቱ ይገኙባቸዋል፡፡ / ኃይሉ ሀብቱ፣ ‹‹Fighting Fascism Ethiopian Women Pafriots 1935 – 1941›› በሚለው ጥናታቸው እንደጠቀሱት፣ እመት ዘነበች ወልደየስ ባለቤታቸውን ተከትለው የዘመቱት አርበኛ ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኙ ሲሆኑ፣ ሌላዋ ዘማች ልዕልት ሮማነወርቅ ኃይለ ሥላሴ ከባለቤታቸው ከባሌው ገዢ ጋር አብረው ከትተዋል፡፡ በተመሳሳይም የሸዋው ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ የልጅ ልጅ ልጅ / ላቀች ደምሰው ከባለቤታቸው ደጃች መንገሻ አቦዬ ጋር የወንድ ልብስ ለብሰው ሽጉጣቸውን ታጥቀው ዘምተዋል፡፡ / ዘነበች ወልደየስ ከባለቤታቸው ከራስ አበበ አረጋይ፣ / ሸዋነሽ አብርሃም ከባለቤታቸው ከደጃች ኃይሉ ከበደ (ሌተናል ጄኔራል) ጋር እንዲሁ ከትተዋል፡፡ አንዳንድ ሴቶች አባቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውንም ተከትለዋል፡፡ ሴቶች ከባለቤታቸው ጋር ቢዘምቱም የግድ በነሱ እዝ ውስጥ መዋሉን አይመርጡም ነበር፡፡ አንዱ ማሳያ የደጃች ሀብተሚካኤል ባለቤት የወሰዱት ቆራጥ ዕርምጃ ነው፡፡

ሰው ተጎድቶባቸው ነበርና በዶሎ ግንባር የመጣውን የጣሊያን ጦር ለመግጠም ያመነቱትን ባለቤታቸው ደጃች ሀብተሚካኤል አቋም ባለመቀበል 150 ወታደሮች ይዘው ክተት ያሉት በቅሎ ላይ ፊጥ ብለው ነበር፡፡ የጣሊያንን ሠራዊት ገጥመው ሠራዊታቸው በርካታ የፋሺስት ወታደሮችን ገድሏል፡፡ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ማርኳል፡፡ ስማቸው በውል ባለመገለጹ አንዳንድ ጸሐፍት ‹‹ስሟ ያልታወቀው›› እያሉ ይጠቅሷታል፡፡

የልዕልቲቱ እመቤት ሆይ ከበደች ሥዩም መንገሻ ባለቤት ደጃች አበራ ካሳ፣ ለፋሺስቶች እጅ መስጠትና መገደል፤ እመቤት ሆይ ከበደችን ከተዋጊነት አልመለሳቸውም፡፡ አርባ ወታደሮችን ይዘው ከሌሎች ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር ፍልሚያውን ተቀላቅለውታል፡፡ / ቀለመወርቅ ጥሩነህ ተመሳሳይ ርምጃ ወስደዋል፡፡ ባላቸው 1929 .. ወደ ጣሊያኖች ቢገቡም በርሳቸው ሥር የነበሩትን አርበኞች ይዘው ወደ ኬንያ ማፈግፈጋቸው ተጽፏል፡፡

የጠላትን ሁኔታ ለመሰለል፣ ምስጢራዊ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ፤ ሴቶች ከወንዶች የተሻለ ችሎታ ለማሳየታቸው አንዷ ተጠቃሽ የውስጥ አርበኛዋ / ሸዋረገድ ገድሌ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ተድላ ዘገየ እንደጻፉት፣ አርበኞች የአዲስ ዓለምን ምሽግ ደጋግመው ለማጥቃትና ለመጨረሻም ለማስለቀቅ የቻሉት በቆፍጣናይቷ / ሸዋረገድ ገድሌ ድጋፍ ጭምር ነው፡፡

በሕክምና ሥራም የረዱ ብዙ ናቸው፡፡ ሰው በቆሰለ ጊዜ ደሙን አጥበው፣ መግሉን አጥበው፣ የተገኘውን የአገር ባህል መድኃኒት አድርገው፣ መግበውና ውኃ አጠጥተው ያድናሉ፡፡ የሞተባቸውም እንደሆነ ለማያውቁት ሰው ጭምር እርር ብለው አልቅሰው ቀባሪ ለምነው ያስቀብራሉ፡፡

ሕክምናን በተመለከተ / ስንዱ ገብሩና / ጽጌ መንገሻ ተጠቃሽ ናቸው፡፡  ‹‹ኢጣልያ በኢትዮጵያከወልወል እስከ ጎንደር›› በተሰኘው የአቶ ተድላ ዘገየ መጽሐፍ እንደሚያብራራው፣ ወይዘሪት ስንዱ በአዲስ አበባ ከአባታቸው ከከንቲባ ገብሩ ጋራ ጎሬ ከተማ ገቡ፡፡ ወይዘሪት ጽጌ መንገሻ ደግሞ ከወንድማቸው ከአቶ ይልማ መንገሻ ጋር አምቦ ከተማ፣ ከጥቁር አንበሳ ጦር ጋር ተቀላቀሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ወጣቶች ጎሬ ካለው ሐኪም ቤት ያገኙትን ያህል መድኃኒት ወስደው ጦሩ በየሄደበት ቦታ ሁሉ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት እስከ መጨረሻው አገልግለዋል፡፡ ደንበኛውን የቀይ መስቀል መለዮ አድርገው፣ እንደ ወንድ ኮትና ሱሪ ለብሰው፣ ቡሽ ባርኔጣ አድርገው በጦርነት ጊዜ የቆሰለውንና የታመመውን በማከም ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በአምስቱ ዘመን በተለያዩ ግንባሮች በውጊያው አውድማ ውስጥ ከዘመቱት በሺዎች ከሚቆጠሩት ሴቶች መካከል ፊታውራሪ በላይነሽ ገብረ አምላክ አንዷ ናቸው፡፡ 14 ዓመት በፊት 90 ዓመት አረጋዊት ሳሉ ያነጋገራቸው ሺበሺ ለማ እንደጻፈው 1928 .. ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ሲወር ባለቤታቸው በጅጅጋ በኩል ወደ ጂቡቲ ለስድስት እንዲሄዱ ቢገፋፏቸው አገራቸውን ትተው እንደማይሄዱ ተጋድሏቸውን እንደሚቀጥሉ ነግረዋቸው ተለያይተዋል፡፡ በምሥራቅ ግንባር ሰርጎ የገባው የፋሺስት ወራሪን ሱሪ ታጥቀው፣ ዝናር ታጥቀው ብረት አንግተው ተፋልመዋል፡፡ ከወረራው 10 ዓመት በፊት ያረፉትን የአባታቸውን ፊታውራሪ ገብረአምላክ ውብነህ ማዕረግን የያዙት ፊታውራሪ በላይነሽ፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ለኢትዮጵያ ድል 75 ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ መታሰቢያ ያሳተመው ‹‹እኔ ለአገሬ›› መጽሔት የፊታውራሪ በላይነሽን ገድል ዘርዝሮታል፡፡

‹‹ጣሊያን አሁንም ዋጩ በሚባል አገር ለአሰሳ መጣ፡፡ ኃይለ ማርያም መብረቁ ለሚባሉ አርበኛ ወረቀት ጻፍኩና፣ ‹‹ ዕርዱኝ›› አልኩ፡፡ እኔን ለመርዳት ብዙዎች ብረት ይዘው መጡልኝ፡፡ ለጋራሙለታው ሰው ለፊታውራሪ ሺመልስ ሀብቴም ወረቀት ጽፌ መሣሪያ ይርዱኝ ብዬ ላኩባቸው፡፡ እሳቸውም አንድ መትረየስና 15 ጠመንጃ ላኩልኝ፡፡ ከዚህ በኋላ አርበረከቴ የነበረውን ጣሊያንን እንዲህ እያልን እያቅራራን እንወጋው ጀመር፡፡

እናንተም ወዲህ እኛም

እንመጣለን

አረበረከቴ ላይ እንገናኝ፡፡

ተጋዳይ፣ ተጋዳይ፣ ተጋዳይ አርበኛ

ገዳይ እቁኒ ላይ ሾላ መገናኛ፡፡

ምናባቱ ፋሽስት፣ ምናባቱ

በረዢም ቁመቱ፣

በደንዳና ባቱ፣

እንወጋዋለን በገዛ ብረቱ፡፡

‹‹ጣሊያን መልሶ ማጥቃት ሲያረግብን ቦረዳ የሚባል አካባቢ ሄደን ተዋጋን፡፡ ከዚያም ከሺመልስ ሀብቴ ጋር ሆነን ወደ ሸዋ አቅጣጫ ውጊያ ጀመርን፡፡ እስከ አርባጉጉ ድረስ እየተዋጋን ቀጠልን፡፡ ነገር ግን በዚያ መቆየት ስላልቻልን ወደ ባሌ ተጓዝን፡፡ ጣሊያንም እዚያ ድረስ ተከታትሎን መጣ፡፡ እኛም መልሰን ወጋነው፤ ፊታውራሪ ሺመልስ ሲዋጉ፣ ሲዋጉ ቆይተው ሲዳሞና ባሌ ጠረፍ ላይ ሞቱ፡፡ የጣሊያን ኃይል እያየለ በመምጣቱና በሌሎቹም ችግሮች ምክንያት አቅማችን ስለተዳከመ መበታተን የግድ ሆነብን፡፡ እኔም ወደ ሸዋ መጣሁ፡፡

‹‹ሸንኮራ፣ ደጃዝማች ፍቅረማርያም የሞቱበት አገር እንዳለሁ፣ አሁንም ጣሊያን ተከትሎኝ መጣ፡፡ እጄን ሳልሰጥ ስዋጋ ቆይቼ ወደ አድአ አፈገፈግሁ፡፡ ጣሊያንም እንደገና ዱካዬን አፈንፍኖ መጣ፣ ቢሾፍቱ ቡርቃ የሚባል፣ ምንጃር ቡልጋ የሚገኝበት ቦታ ጦርነት ገጠምነው፡፡

‹‹እዚያ በጥይት ተመትቼ ቆሰልኩ፡፡ ከዚያም ብረቴን ቀብሬ ቁጭ አልኩ፡፡ እዚያ እየበላሁ፣ እየጠጣሁ፣ ባንዳው እንዳያሳብቅብኝ፣ ጣሊያንም እንዳያገኘኝ ጎፈሬዬንም ተቆርጬ  እያለሁ የጃንሆይን ወደ አገር መግባት ሰማሁ፡፡ የእሳቸውን መምጣት ስንሰማ አዲስ አበባ ለመቀበል መጣን፡፡ ግን አልመጡም አሉን፡፡ ገሚሱ እሳቸውን ለመቀበል ጎጃም ሄደ፣ እኔ ተመለስኩ፡፡

‹‹ጃንሆይ ከገቡ በኋላ እንደገና መጣሁና እየፎከርን ገብተን ጃንሆይን አገኘናቸው፡፡ እኔ ቀሚስ ለብሼ ከአርበኞቹ ተለይቼ ጃንሆይን እጅ ነሳሁ፡፡ የእኔ ዝና ቀድሞውንም ተሰምቶ ነበርና፣ ደጃዝማች ይገዙ ሀብቴ እጄን ይዘው ለጃንሆይ ጉድ ላሳይዎትብለው አቀረቡኝ፡፡ እኔም ቆንጆ ሆኜ የከተማ ሰው መስዬ ነበር የቀረብኩት፡፡

‹‹ጄኔቭ በነበርንበት ጊዜ፣ በላይነሽ የምትባለው ሴት ትዋጋለች እየተባለ የምንሰማው እሷን ነው?› ብለው ጠየቁ፡፡ ደጃዝማች ይገዙምአዎብለው አቀረቡኝ፡፡ ጃንሆይም በፈገግታ ተቀበሉኝ፡፡አለሽ እንዴ! ማን ትባያለሽ?› አሉኝ፡፡ እኔም፣ፊታውራሪ በላይነሽ ነኝአልኳቸው፡፡በስምሽ ተጠሪበትብለው ሹመቱን አፀደቁልኝ፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...