የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና የእንስሳት ሀብት ልማት ሚኒስቴር በድጋሚ ተዋህደው አንድ ሚኒስቴር በመሆናቸው፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው የሁለቱ የቀድሞ ሚኒስትሮች ዕጣ ፋንታ እስካሁን አለየም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሚያዚያ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሁለት ዓመታት አጭር ቆይታ በኋላ፣ ሁለቱ ግዙፍ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በድጋሚ እንዲወሀዱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ ተዋህደው ‹‹የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር›› ተብለው በድጋሚ ሲቋቋሙ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክርክር ተነስቶ ነበር፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አዲስ ካቢኔ ባቋቋሙበት መስከረም 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ከብዙ ተደጋጋሚ ውይይት በኋላ ሁለቱ መሥሪያ ቤቶች በተናጠል ተቋቁመው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርን እያሱ አብርሃም (ዶ/ር)፣ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስቴርን ደግሞ ፍቃዱ በየነ (ፕሮፌሰር) ሚኒስትር ተደርገው ተሹመው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እነዚህ ሚኒስቴሮች እንዲዋሀዱ በማድረጋቸው ሁለቱ ሚኒስትሮች ቦታቸውን ለአቶ ሽፈራው የለቀቁ ሲሆን፣ እስካሁንም ዕጣ ፈንታቸው በይፋ አልተገለጸም፡፡ ሁለቱ ምሁራን መሥሪያ ቤቶቻቸውን በብቃት እየመሩ እንደነበር የሥራ ባልደረቦቻቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለማሻሻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 1084/2010 በቀረበበት ወቅት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹን የመዋሀድ አስፈላጊነቱን ጥያቄ ውስጥ በማስገባት ተችተዋል፡፡
የሕዝብ ተቀካዮች ምክር ቤት አባላት ሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከተዋሀዱ ገና ሁለት ዓመታቸው መሆኑን፣ ውጤታማነታቸው ወይም የሥራ አፈጻጸማቸው በአግባቡ ሳይመረመር መዋሀዳቸው አግባብ አለመሆኑን ተችተው ነበር፡፡ በተመሳሳይ በግብርና እና በእንስሳት ሀብት ላይ የተስማሩ ኢንቨስተሮች ሁለቱም ሚኒስቴሮች ሥራቸውን መልካም በሚባል ደረጃ እያካሄዱ እንደነበር፣ እንደገና አዲስ አደረጃጀት ተፈጥሮ መዋቅር እስኪሻሻል ተጨማሪ ጊዜ መፍጀት ነው በማለት ተቃውሟቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከዚህ በፊት በነበረው አደረጃጀት በሁለቱ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሲታይ የነበረውን የሰው ኃይል ሽሚያ ለማስቀረት፣ የሁለቱም መሥሪያ ቤቶች የመጨረሻ ዓላማ አንድ በመሆኑ ውህደቱ አስፈላጊ ነው በማለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
የቀድሞዎቹ ሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አንድ አንድ ሚኒስትርና ሦስት ሦስት ሚኒስትር ዴኤታዎች ነበሯቸው፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ በመዋሀዳቸው የሁለቱ ሚኒስትሮች ብቻ ሳይሆን የሚኒስትር ዴኤታዎቹም ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን አይታወቅም፡፡