በደመወዝ ማነስ ምክንያት ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚፈልሱ ሠራተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ያሳሰበው የፌዴራል መንግሥት፣ የክፍያ ማስተካከያ ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑ ታወቀ፡፡
የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትር አቶ ታገሰ ጫፎ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ለሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ለማድረግ ጥናቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ የግብርና እና የእንስሳት ሀብት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከሠራተኞች ጋር ባካሄዱት የትውውቅ ስብሰባ፣ የደመወዝ ጭማሪን በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡
ሠራተኞቹ ለአቶ ሽፈራው ባደረጉት ገለጻ በደመወዝ ማነስ ሳቢያ በርካታ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች፣ የተሻለ ደመወዝ ወደሚያገኙባቸው ተቋማት እየፈለሱ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ሽፈራው ከሠራተኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ የሚገኘውን የባለሙያ ፍልሰት ለመቀነስ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የመንግሥት ሠራተኞችን ፍልሰት ለማስቀረት የደመወዝ ማስተካከያ ለማድረግ እየተጠና ነው፡፡ ከዚሁ ጋርም የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ምዘና እና ደረጃ አወሳሰን በአፋጣኝ እንደሚካሄድ፣ ይህም የመካከለኛ አመራርና የሰው ኃይልን ጨምሮ አንኳር የሆኑ ችግሮችን ይፈታል፤›› በማለት አቶ ሽፈራው ለሠራተኞች ገልጸዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመንግሥት ሠራተኞች በደመወዝ ማነስ ምክንያት፣ የሥራ ምዘና እና የደረጃ አወሳሰን ላይ በርካታ ቅሬታዎች በማንሳት ላይ ናቸው፡፡ በተለይ ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ ከተመደቡበት ሥራ ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ፣ እንዲሁም የዋጋ ግሽበቱ ኑሮአቸውን እያከበደባቸው ስለሆነ ባገኙት አጋጣሚ አቤቱታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡
የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ሚኒስቴር ይህንን ጉዳይ ለማስተካከል ጥናት እያካሄደ መሆኑን ቢገልጽም፣ ጥናቱ ረዥም ጊዜ በመውሰዱ የሠራተኞች ቅሬታ እየተስፋፋ መምጣቱ ይነገራል፡፡
የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ታገሰ በአሁኑ ወቅት ጥናቱ እየተጠናቀቀ በመሆኑ፣ የደመወዝ ስኬልም ሆነ የሥራ ምዘና እና ደረጃ መወሰን ሥራዎች በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
በርካታ የመንግሥት ተቋማት የሠራተኛ ቅጥር ለመፈጸም ተደጋጋሚ ማስታወቂያ ቢያወጡም የሚፈልጉትን ያህል ሠራተኛ የማያገኙ ከመሆኑም በላይ፣ ነባሮቹም ሠራተኞች የተሻለ ደመወዝ ወደሚያገኙበት እየፈለሱ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንቅፋት እየሆነ በመምጣቱ፣ መንግሥት በአፋጣኝ ወደ መፍትሔ ዕርምጃ ይገባል ተብሏል፡፡