Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሚድሮክ ወርቅና ሶዳ አሽ ፋብሪካ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በፓርላማ ጥያቄ ተነሳባቸው

ሚድሮክ ወርቅና ሶዳ አሽ ፋብሪካ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በፓርላማ ጥያቄ ተነሳባቸው

ቀን:

በለገደንቢ የሚገኘውን ሚድሮክ ወርቅ ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ፋብሪካዎች፣ በአካባቢና በኅብረተሰቡ ላይ በሚያደርሱት ብክለትና ጉዳት መንግሥት ዕርምጃ ባለመውሰዱ በፓርላማ ጥያቄ ተነሳበት፡፡

ሐሙስ ሚያዝያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. የአካባቢ፣ ደንና የአየር ለውጥ ሚኒስቴር የስምንት ወራት ሪፖርት ለምክር ቤቱ ሲያቀርብ የምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡ ጥያቄዎቹም በዋናነት በሚድሮክ ወርቅና በአብያታ ሶዳ አሽ ፋብሪካ ላይ የተሰነዘሩ ናቸው፡፡

በቅርቡ ኮንትራቱ በታደሰለት ለገደንቢ በሚገኘው የሚድሮክ ወርቅ ማምረቻና የአቢያታ ሐይቅን ሊያጠፋው ተቃርቧል በተባለው የሶዳ ማምረቻ ላይ፣ መንግሥት ለምን ዕርምጃ አይወስድም ሲሉ የምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹በኦሮሚያ ክልል በሻኪሶ አካባቢ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ሲቆፈር የቆየ ማዕድን አለ፡፡ ይኼ ቦታ ለዘመናት ሲቆፈር ይቆይ እንጂ ጥገና አይደረግለትም፡፡ በዚህ አካባቢ ማዕድኑን ለማጣራት የሚጠቀሙት ኬሚካል ችግር እንዳለው አርሶ አደሮችም አርብቶ አደሮችም ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ ይኼንን ችግር ለመፍታት ለምን እንዳልተቻለ፣ አሁንም ችግሩን ለመፍታት ምን እየተሠራ እንደሆነ ሊጣራ ይገባል፤›› ሲሉ አንድ የምክር ቤት አባል ጠይቀዋል፡፡

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ ገመዶ ዳሌ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሕግ እየተከበረ ማኅበራዊ ቀውሶችን አግባብ ባለው መንገድ ለመፍታት እየሠራን ነው፡፡ ውል ከመፈራረም ጀምሮ መካተት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሐሳብ እየሰጠን ነው የሄድነው፡፡ ውሉን ያደሰው አካልና ጉዳዩን የሚከታተለው አካል ምላሽ መስጠት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን የትኛውም ልማት በአካባቢ ላይ የጎላ ተፅዕኖ ማድረስ የለበትም፡፡ ቢያደርስ ደግሞ የሚያስተካክልበት አሠራር ሊኖር ይገባል የሚል አቋም አለን፤›› ብለዋል፡፡

የለገደንቢ የሚድሮክ ወርቅ ፋብሪካ ከ20 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን ይዞታ ሥር ነበር፡፡ የዛሬ 20 ዓመት በ170 ሚሊዮን ዶላር ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ነበር የተዘዋወረው፡፡ ሚድሮክ በመጀመርያ ለ20 ዓመታት ነበር ከመንግሥት ጋር የተዋዋለው፡፡ በቅርቡ የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ፈቃዱን ለተጨማሪ አሥር ዓመታት አድሶለታል፡፡

ፈቃዱ መታደሱ ከተሰማ በኋላ በአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ የተነሳበት ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ ጉዳዩን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለማጥናት የጥናት ቡድን ማቋቋሙን ሰሞኑን አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ የአቢያታ ሐይቅን ‹‹እየገደለ ነው›› የሚባለውን የሶዳ አሽ ፋብሪካ በተመለከተ ለሚኒስትሩ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ሚኒስትሩ ፋብሪካው ወደ ሐይቁ እየለቀቀው ነው በተባለው ሶዳ አሽ ምክንያት በሐይቁ ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ  ሚኒስቴሩና አጋር ድርጅቶች በጋራ ያደረጉት ጥናትና ውጤት ለመንግሥት ቀርቦ ውሳኔ እየተጠበቀ እንደሆነ በመግለጻቸው ነው ጥያቄው የቀረበው፡፡

‹‹ሶዳ አሽ ወይም ሶዲየም የተፈጥሮ ይዞታችንን እያጠፋ ነው ያለው፡፡ ይህ ለድርድር መቅረብ የለበትም፡፡ መዘግየትም የለበትም፡፡ ይኼ ውሳኔ አብያታ ሐይቅ ከጠፋ በኋላ ዘግይቶ የሚወሰን ከሆነ ለእኛ ጥቅም የለውም፡፡ ነገ የታሪክ ተወቃሽ ነው የሚያደርገን፤›› ሲሉ አንድ የምክር ቤት አባል ጠይቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ፋብሪካው በደርግ ጊዜ መቋቋሙን ገልጸው፣ ከመሠረቱ ሳይጠና የተገነባና መገንባትም ያልነበረበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ሲቋቋም ያለ በቂ ጥናት ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ችግሩ ሲታወቅ ማስቆም ያልተቻለው በመንግሥት ተቋማትና ሕግን በሚያስከብረው አካል ተቀናጅቶ አለመሥራት ምክንያት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ በሚኒስትሩ ሪፖርት እንደቀረበው፣ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ በተደረገ ክትትልና ቁጥጥር ሕግን አላከበሩም በተባሉ ከ1,000 በላይ የተለያዩ ድርጅቶች ላይ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ 155 የሚደርሱ ፋብሪካዎች በኦሮሚያ ክልል የመጀመርያ፣ እንዲሁም 45 ፋብሪካዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡ ስድስት ፋብሪካዎች ደግሞ እንዲዘጉ መደረጋቸውንም ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባ፣ በደቡብና በትግራይ ክልሎችም ተመሳሳይ ዕርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል፡፡                                                                                                                      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...