Monday, July 22, 2024

ዴሞክራቲክ ተቋማት በነፃነትና በገለልተኝነት እንዲደራጁ ግፊት ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ላጋጠሙ ሥር የሰደዱ ችግሮች እንደ መነሻ ተደርጎ የሚወሰደው፣ የዴሞክራቲክ ተቋማት በነፃነትና በገለልተኝነት አለመደራጀትና ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አለመደረጉ ነው፡፡ ዴሞክራቲክ ተቋማት የሚባሉት ምርጫ ቦርድ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ዕንባ ጠባቂ ተቋምና ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ተጠሪነታቸው ለፓርላማው እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን  በአስፈጻሚው አካል በሚደረግባቸው ተፅዕኖ ምክንያት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ባለመቻላቸው ለበርካታ ችግሮች ምክንያት ሆነዋል፡፡ የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነትና ነፃነት ጉዳይ ለዓመታት እያከራከረና እያጨቃጨቀ አምስት ምርጫዎች ተካሂደው ምን እንደተፈጠረ ከአገር አልፎ ዓለም የሚያውቀው ነው፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሙስናን መከላከል አቅቶት ተሽመድምዶ ተቀምጧል፡፡ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ዕንባ ጠባቂ ተቋም አለን ቢሉም፣ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ በተነፃፃሪ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶችን የኦዲትና የክዋኔ አፈጻጸም በሚገባ መርምሮ ሙያዊ ሪፖርት የማቅረብ ብቃቱ የሚደነቅ ሲሆን፣ ነገር ግን በሕግ አውጪው ፓርላማም ሆነ በአስፈጻሚው አካል በሚገባ ባለመደገፉ ልፋቱ ከንቱ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህ ተቋም ነፃነቱ ተጠብቆ በሙሉ ኃይል መሥራት ቢችል ኖሮ የት መድረስ ይቻል እንደነበር ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ዴሞክራቲክ ተቋማቱ በነፃነት ተደራጅተው በገለልተኝነት መመራት ባለመቻላቸው ለሕገወጥነት የተመቻቸ መደላድል ተፈጥሯል፡፡ ይኼ በፍጥነት እንዲስተካከል ቅድሚያ መስጠት ይገባል፡፡

የአሁኗን ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከፊቷ ይጠብቋታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ አዲሱ አስተዳደራቸው መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚጀምሩት፣ ተቋማዊ ነፃነት በማስፈን በጠንካራ አደረጃጀት ሥራ ሲጀምሩ ነው፡፡ በተለይ የሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ሙሉ ትኩረት ተቋማትን ከብልሹ አሠራሮች የሚያላቅቁ ወሳኝ ዕርምጃዎች ላይ መሆን አለበት፡፡ ይኼ ይሆን ዘንድ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠንካራ ሆኖ ተጠሪው የሆኑ ዴሞክራቲክ ተቋማት በነፃነት እንዲደራጁ፣ ከአስፈጻሚው አካል አላስፈላጊ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው በገለልተኝነት እንዲሠሩ የማድረግ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ተቋማቱ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በሥነ ምግባራቸውና በትጋታቸው አንቱ የተባሉ አመራሮችንና ባለሙያዎችን በመያዝ ለመሠረታዊ ለውጥ እንዲዘጋጁ መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ የተቋማቱ አመራሮች ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት፣ ወገንተኝነትና ጥቅም ፈላጊነት የፀዱ ገለልተኛ መሆናቸው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ዛሬ ወገንተኛ ሆኖ ተቋማቱን የሚመራ ተሿሚ ነገ ለሚሰጠው ድርጎና ተጨማሪ ሹመት እያሰፈሰፈ፣ በነፃነትና በገለልተኝነት እንደማይሠራ የነበሩት ልምዶች ከመጠን በላይ ይናገራሉ፡፡ ይኼ ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን እንደ ምሳሌ ብንወስድ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ተቋማት በጣም አወዛጋቢው ነው፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር ሁሌም ነፃነቱና ገለልተኝነቱ ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ይኼንን ተቋም የሚመራ አካል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር የማያገናኘው ድር ካልተበጣጠሰ በስተቀር ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዴት ይኖራል? ይህ የገለልተኝነት ጉዳይ ከኢሕአዴግ በተጨማሪ ሌሎች ፓርቲዎችንም ይመለከታል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ሌሎቹ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርድን ነፃነትና ገለልተኝነት ካላከበሩ ውጤቱ ጉም መጨበጥ ነው፡፡ እስካሁን በነበረው ልምድ ግን ኢሕአዴግ በብርቱ መወቀስ ይኖርበታል፡፡ ሌሎቹን አዳክሞ ራሱን ከማፈርጠሙም በላይ ምርጫ ቦርድን በራሱ አምሳል ጠፍጥፎ ሠርቶታል ተብሎ ሲወገዝ፣ የፓርላማ መቀመጫዎችን ከእነ አጋሮቹ መቶ በመቶ መቆጣጠሩ እንደ ማስረጃ ይቀርብበታል፡፡ በዚህም ምክንያት ለዓመታት ብሶቶች ሲሰሙ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ምርጫ 2007 በዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ ከተደመደመ በኋላ፣ በጥቂት ወራት ውስጥ ሕዝባዊ አመፅ ፈንድቷል፡፡ አገሪቱም ላለፉት ሦስት ዓመታት ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ ለበርካታ ዜጎች ሕይወት ሕልፈት፣ አካል ጉዳት፣ እስር፣ እንግልትና መጠኑ ለማይታወቅ የአገር ሀብት ውድመት ምክንያት ሆኗል፡፡ ይኼንን ቀውስ ላለመድገምና ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለመሸጋገር፣ የምርጫ ቦርድ ነፃነትና ገለልተኝነት ጉዳይ የሞት የሽረት ጥያቄ መሆን አለበት፡፡

ገለልተኝነትና ነፃነት በሌለበት ዴሞክራቲክ ተቋማት አሉ ከማለት ይልቅ ዝምታ ይመረጣል፡፡ አንድ ችግር ያጋጠመውን ዜጋ ዕንባውን ማበስ የሚገባው ተቋም በአግባቡ መሥራት ካልቻለ መኖሩ ምን ይጠቅማል? ይኼንን ያህል አቤቱታዎች ተቀብዬ ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቄያለሁ ብሎ ሪፖርት የሚያቀርብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አለ ከማለት ይልቅ የለም ብሎ መደምደም ይቀላል፡፡ በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ተከሳሾችም ሆኑ ታራሚዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲደርስባቸውና ስቃይ ሲፈጸምባቸው ማስቆም የማይችልና የተሟላ ሪፖርት አቅርቦ የማያጋልጥ ተቋም ስለነፃነቱ እንዴት መናገር ይችላል? እያድበሰበሰና እያለባበሰ የሚያቀርበውን ሪፖርትስ ማን ይቀበለዋል? የባለሥልጣናትን ሀብት መዝግቦ በአደባባይ በማቅረብ እስቲ ፍረዱ ማለት ያልቻለ ፀረ ሙስና ተቋምስ መኖሩ ፋይዳው ምንድነው? ይህም አልበቃ ብሎ ያለውን ሥልጣን ተቀምቶ የሥነ ምግባር መምህር ነኝ ብሎ ሲቀርብስ ማን ይሰማዋል? በአስፈጻሚው አካል ሳንባ እንዲተነፍሱ የሚደረጉ ተቋማት የተሽመደመዱት እኮ አደረጃጀታቸው ነፃ ባለመሆኑና አይሆንም በማለት ገትረው ለመከራከር የሚደፍሩ ተሿሚዎች ባለመኖራቸው ነው፡፡ በአንፃራዊነት ምሥጉን ሥራ የሚያከናውነው ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የበለጠ አደረጃጀቱንና ነፃነቱን አስጠብቆ መሥራት ካልቻለ፣ አመራሩን ጨምሮ ሠራተኞችን ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ከላይ የተነሱትን መጠነኛ ማሳያዎች ለግንዛቤ ያህል በመውሰድ ጊዜ የማይሰጠው ሥራ መጀመር አለበት፡፡ በነበረው ሁኔታ መቀጠል አይቻልም፡፡

ሕዝብ መሠረታዊ ለውጦችን እየጠበቀ ነው፡፡ ለውጦቹ ዕውን ይሆኑ ዘንድ ዕገዛ ለማድረግም ቃል እየገባ ነው፡፡ ፓርላማው ይኼንን የሕዝብ ስሜት ከመቼውም ጊዜ በላይ በተባበረ ድምፅ ማገዝ ይኖርበታል፡፡ የምክር ቤት አባላትም ተጠሪነታቸው ለወከላቸው ሕዝብ፣ ለህሊናቸውና ለሕገ መንግሥት እንደ መሆኑ መጠን አስፈጻሚውን አካል ሰንገው መያዝ አለባቸው፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ ቀልዶች ቆመው ሥር የሰደዱ ችግሮች እንዲፈቱ ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል፡፡ አስፈጻሚው አካልም ለሕዝብ እየገባ ባለው ቃል መሠረት እጅና እግራቸው የታሰረውን ዴሞክራቲክ ተቋማት ነፃ ማውጣት አለበት፡፡ እነዚህ ተቋማት ማንም ተመረጠ ማን በሕግ የበላይነት ሥር በገለልተኝነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ነፃነት ይፈልጋሉ፡፡ ለአንድ ጎራ የሚደረግ ወገንተኝነት አገሪቱንና ሕዝቧን ምን ዓይነት ማጥ ውስጥ እንደከተተ ከበቂ በላይ ታይቷል፡፡

ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው በነፃነት የሚኖሩባት አገር መገንባት የሚቻለው ተቋማት ጠንካራ፣ ነፃና ገለልተኛ ሆነው ሲደራጁ ነው፡፡ ይህ አደረጃጀት አቶ እከሌን ወይም ወ/ሮ እከሊትን ለማስደሰት ወይም ለማስከፋት ሳይሆን፣ አገር በሕግ የበላይነት ሥር በሰላም መተዳደር ስላለባት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት ሕገወጥነት ይስፋፋል፡፡ ሥርዓት አልበኝነት ይሰፍናል፡፡ የአገር ሀብት የጥቂቶች መጫወቻ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያዊያን መብትና ነፃነት ይደፈጠጣል፡፡ በገዛ አገር ባይተዋር መሆን ይለመዳል፡፡ እነዚህ ሁሉ ለዓመታት የታለፈባቸው አሳዛኝ ክስተቶች ናቸው፡፡ አሁን በአገሪቱ የለውጥ ነፋስ ሽው እያለ በመሆኑ፣ ይህ ለውጥ መሠረታዊ ሆኖ የእኩልነት ሥርዓት እንዲያመጣ ሰላማዊውና ዴሞክራሲያዊው ትግል ይቀጥል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ይህ ለውጥ በስሜታዊነትና በግብታዊነት ሳይሆን፣ በምክንያታዊነት ዕውን እንዲሆን በአንድነት ይሠለፉ፡፡ አላስፈላጊ ቁርሾዎችንና ፍትጊያዎችን በመተው ለአገር ህልውና ሲባል የለውጡን ጀልባ መቅዘፍ፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት ይሁን፡፡ ዴሞክራቲክ ተቋማት በነፃነትና በገለልተኝነት እንዲደራጁ ግፊት ይደረግ!  

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...