Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ሰፋፊ የማዕድን ቦታዎችን ከባለሀብቶች ሊነጥቅ ነው

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ሰፋፊ የማዕድን ቦታዎችን ከባለሀብቶች ሊነጥቅ ነው

ቀን:

  • የመሬት ኪራይ ከሁለት እጥፍ በላይ ጨምሯል

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግሥት ከ20 ሔክታር በላይ የማዕድን ቦታዎችን የያዙ ባለሀብቶች ለክልሉ እንዲመልሱ አዘዘ፡፡

ቤንሻንጉል በወርቅና በዕምነበረድ ሀብት የሚታወቅ ክልል ነው፡፡ በተለይ በዳለቲ፣ በፀዳልና በመተከል አካባቢ የሚገኘው ነጭ ዕምነበረድ ከፍተኛ ተፈላጊነት አለው፡፡ በቅርቡ በክልሉ የወጣው መመርያ የዕምነበረድ አምራቾችን የሚመለከት እንደሆነ ታውቋል፡፡

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት ሰፋፊ የዕምነበረድ ቦታዎችን የያዙ ባለሀብቶች 20 ሔክታር ብቻ አስቀርተው፣ የተቀረውን ለክልሉ እንዲመልሱ በቅርቡ እንደወሰነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ቦርድ ውሳኔውን በዕምነበረድ ፍለጋና ልማት ሥራ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ውሳኔውን አሳውቋል፡፡

በክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አሻድሊ ሐሰን ሰብሳቢነት የሚመራው የማዕድን ሀብት ልማት ቦርድ ለባለሀብቶቹ ሚያዝያ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ ከ20 ሔክታር (0.2 ካሬ ኪሎ ሜትር) በላይ ይዞታ የያዘ ባለፈቃድ መሬቱን እስከ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ለክልሉ እንዲመልስ ጠይቋል፡፡

በዳለቲ፣ በፀዳልና በመተከል አካባቢዎች ከ160 በላይ የዕምነበረድ ፍለጋና ልማት ፈቃድ ያላቸው ባለሀብቶች እንዳሉ ይገመታል፡፡ አንዳንድ ነባር ባለይዞታዎች ከ500 እስከ 600 ሔክታር መሬት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ በርካቶች ከ100 ሔክታር በላይ ይዞታ እንዳላቸው ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ተገቢውን ሳይንሳዊ የፍለጋ ጥናት ሠርተው ወደ ምርት የተሸጋገሩት ጥቂት እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

በክልሉ በቅርቡ የማዕድን መሬት ኪራይ ከሁለት እጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡ ቀደም ሲል የምርመራና የምርት ፈቃድ ያላቸው ባለሀብቶች ለአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ 300 ብር ይከፍሉ ነበር፡፡ አሁን ግን የምርመራ ፈቃድ ባለይዞታ በካሬ ኪሎ ሜትር 1000 ብር፣ የምርት ፈቃድ ባለይዞታ በካሬ ኪሎ ሜትር 5,000 ብር እንዲከፍል ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ የባለቤትነት ክፍያ (ሮያሊቲ) ከሦስት በመቶ ወደ ስምንት በመቶ አድጓል፡፡

በዕምነበረድ ፍለጋና ምርት የተሰማሩ ኩባንያዎች የክልሉ መንግሥት የወሰደውን ዕርምጃ አምርረው ተቃውመዋል፡፡ በክልሉ በዕምነበረድ ፍለጋና ምርት የተሰማሩ ባለሀብቶች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በርካታ ግለሰቦች ዕምነበረድ የሚገኝባቸውን ሰፋፊ መሬቶች ይዘው ሳይሠሩ የተቀመጡ አሉ፡፡ የዚያኑ ያህል ደግሞ ተገቢውን የምርመራ ሥራ አከናውነው ወደ ምርት የተሸጋገሩ በርካታ ባለሀብቶች እንዳሉ የሚናገሩት ባለሀብቶቹ፣ በጅምላ ሁሉም ላይ አንድ ዓይነት ዕርምጃ መወሰዱ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹ቤንሻንጉል ርቀት ያለው ቦታ ነው፡፡ መሠረተ ልማትም የለም፡፡ መንገድ በሌለበት ጫካ መንጥረን፣ መንገድ ጠርገን ነው የገባነው፡፡ የኤሌክትሪክ መስመርም ስለሌለ በጄኔሬተር ነው የምንጠቀመው፡፡ ማሽኖች ገዝተን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሰንና ጥናት አሠርተን ያለማነውን ቦታ ምንም ካልሠሩት እኩል እንዴት መልሱ እንባላለን?›› ያሉ አንድ ባለሀብት፣ ክልሉ ውሳኔውን ከማሳለፉ በፊት የምክክር መድረክ እንዳላዘጋጀ ተናግረዋል፡፡

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ አሻድሊ ሐሰን ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ ክልሉ መሬት ለባለሀብቶች ሲሰጥ የኖረው በልማዳዊ አሠራር እንደበር ገልጸዋል፡፡ ባለሀብቶች ሰፋፊ መሬቶችን ቢይዙም የሚያለሙት ጥቂቱን እንደሆነ የገለጹት አቶ አሻድሊ፣ የልማት ሥራ መካሄድ ስላለበት ያላግባብ የተሰጡ ሰፋፊ መሬቶች ተቀንሰው ማልማት ለሚችሉ ለሌሎች ባለሀብቶች ለመስጠት ታስቦ የተላለፈ ውሳኔ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሁለት መቶ ሔክታር መሬት ወስዶ ጥሩ ሠራ የሚባለው ስምንት ሔክታር ያለማ ነው፡፡ ከ500 ሔክታር በላይ የወሰዱ ባለሀብቶች አሉ፡፡ ማዕድን በተፈጥሮ ከመሬት ሥር የሚገኝ ሀብት በመሆኑ፣ ወደ ጎን ያለው ስፋት ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ባለ ሀብቶቹ በበኩላቸው ሰፊ መሬት ይዘው ያላለሙ በርካታ ባለሀብቶች እንዳሉ ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ ዕርምጃው በጥናት ላይ የተመረኮዘ መሆን እንደነበረበት ይገልጻሉ፡፡ የክልሉ የማዕድንና ኢነርጂ ቢሮና የማዕድን ሀብት ልማት ቦርድ ባለሙያዎች፣ በክልሉ በማዕድን ምርመራና ምርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችንና ግለሰቦችን የሥራ አፈጻጸም ገምግመው ዕርምጃ መውሰድ ነበረባቸው እንጂ፣ ሁሉንም በአንድ ላይ ፈርጆ መሬት መልሱ ማለት ፍትሐዊ ውሳኔ አይደለም ሲሉ ባለሀብቶች ይከራከራሉ፡፡

አቶ አሻድሊ በበኩላቸው፣ መሬት ወስደው ምንም ዓይነት ልማት ያላከናወኑ ባለሀብቶች ጉዳይ በተለየ ሁኔታ ታይቶ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በዕምነበረድ ፍለጋና ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶች ለክልሉ አስተዳደር አቤቱታ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...