Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየሙያተኞችን ህልውና መፈታተን የጀመረው የእግር ኳሱ አመራርና የአሠራር ችግር

የሙያተኞችን ህልውና መፈታተን የጀመረው የእግር ኳሱ አመራርና የአሠራር ችግር

ቀን:

  • ባላደራ ቦርድ እንዲቋቋም የሚጠይቁ አሉ

ዳር እስከ ዳር መነጋገሪያና ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የዝቅጠት ሁሉ ቁንጮ ማሳያ የሆነ የሜዳ ውስጥ ነውጥ፣ በስፖርቱ ተዋናዮች ሲፈጸም ሕዝብ ታዝቧል፡፡ የስፖርት አንደኛው ተልዕኮ ሥነ ምግባርና መከባበር፣ ብሎም ወንድማማችነትን ማሳየት ቢሆንም፣ እነዚህ ቅንጦቶች የሆኑበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ፣ እንኳን ለስፖርቱ የዲሲፕሊን ሕግጋት ሊገዛ፣ ለመደበኛ የወንጀል ሕጎችም የማይመለስ የመብት ጥሰትና ጥቃት የሚፈጸምበት የትዕይንት ሜዳ ሆኖ እየታየ ይገኛል፡፡

እንዲህ ያለው አጓጉል የሕግም፣ የስፖርታዊ ጨዋነትም ‹‹አለሌነት›› ሲበዛ ከፍቶ የታየው በጨዋታ ዳኞችና ታዛቢዎች ላይ መሆኑ ደግሞ ይብሱን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም በላይ እግር ኳሱን በበላይነት የሚመራ ተቋም አመራር የማናለብኝነትና የአሠራር ችግር መሆኑ ክስተቱን ይበልጥ እያጎላው ይገኛል፡፡

በዚሁ የአመራር ክፍተት የጨዋታ ዳኞች የጥቃቱ ዒላማ የሚሆኑበት በጨዋታ ሜዳ ውስጥ በሚፈጸም ድርጊት ብቻም አይደለም፡፡ በዓለም አቀፉም ሆነ አህጉር አቀፍ የእግር ኳስ ሕግጋት ፍፁም ተቀባይነት በሌለው፣ የዳኞቹ የብሔር ማንነት ጭምር ተገን እየተደረገ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አይተው እንዳላዩ እንዲያልፉ ጫና የሚደረግባቸው፣ በየክልሉ ለማጫወት ሲሄዱ ከፀጥታ ኃይሎች ሳይቀር ሁከትና ብጥብጥ እንዳይነሳ ተጠንቀቁ እየተባሉና በተዘዋዋሪ ለክልሉ ወይም ለባለሜዳው ቡድን ውጤት ይዞ እንዲወጣ የሚደረግባቸው ጫና ሲድበሰበስ ኖሯል፡፡

ይህንኑ ከሰሞኑ የጨዋታ ዳኞችና ታዛቢዎች ማኅበር በአዲስ አበባ በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በግልጽ አስታውቋል፡፡ በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔው፣ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ከጅምሩ በይፋ ሊወገዝ ባለመቻሉና ዳኞችም ሆኑ ታዛቢ ዳኞች በፍትሐዊነት ጨዋታዎችን ለመምራትና ለማጫወት ጥረት በሚያደርጉበት ሰዓት የገፈቱ ቀማሾች ከመሆን ግን አልታደጋቸውም፡፡ ይህንኑ በአደባባይ ሲናገሩት ተደምጠዋል፡፡ በኮብል ድንጋይ የተደበደቡ፣ ከፍተኛ የዱላና የቡጢ ውርጅብኝ አርፎባቸው ለጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ የተዳረጉ ዳኞችም በርካቶች ስለመሆናቸው ጭምር በጉባዔው ተንፀባርቋል፡፡

የዳኞችና ታዛቢዎች ማኀበር ባለፈው ረቡዕ ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በብሔራዊ ወጣቶች አካዴሚ በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ፣ በአባላቱ ላ እየደረሰ ያለው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት በፌዴሬሽኑና በሌሎችም በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አፋጣኝ መፍትሔ እስካልተበጀለት ድረስ፣ ከሚያዝያ 25 እስከ ግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ማናቸውንም ጨዋታዎች እንደማይዳኙ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ፣ ከዳኞችና ታዛቢዎች ማኀበር አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔና ውሳኔ ማግሥት፣ ከ16 የፕሪሜየር ሊግ የክለቦች ሥራ አስኪያጆች ጋር በጁፒተር ሆቴል ባደረገው ስብሰባ፣ በተለያዩ ጊዜያት በሚካሄዱ ውድድሮች በዳኞችና ታዛቢዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ችግርና የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል አሳሳቢ መሆኑን አምኖ፣ ማኅበሩ ግን ጨዋታዎችን ላለመዳኘት የተላለፈውን ውሳኔ ማጤን እንደሚገባው በማሳሰብ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡ ይሁንና በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት ለደረሰው የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበትና እንደሌለበት ምንም አለማለቱ ግን ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡

የዳኞችና ታዛቢዎች ማኅበር በቅድመ ሁኔታነት ካስቀመጣቸው ማለትም የሕይወት ኢንሹራንስና የመሳሰሉትን አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ፣ የጥያቄውን ተገቢነት ተቀብሎ፣ ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል፡፡

ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል መንስዔዎች

የዳኞችና ታዛቢዎች ማኅበር በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከአባላቱ ሲነገር የተደመጠው፣ ‹‹ለዚህ ሁሉ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል በዋናነት ተጠያቂው የኢትዮጵያ እግር ኳስ አመራሮችና በየደረጃው የተቀመጡ የፍትሕ አካላት ናቸው፤›› ብለው፣ የስፖርታዊ ጨዋነቱ መጓደል ሰለባ ከሆኑት የጨዋታ ዳኞች ፌዴራል ዳኛ ለሚ ንጉሤ፣ ‹‹እግር ኳስ ከሚያካትታቸው መሠረታዊ ግብዓቶች ዳኝነት አንዱ ነው፡፡ ዳኝነት ቅፅበታዊ ውሳኔ የሚጠይቅ እንደመሆኑ፣ ስህተት ሊኖር እንደሚችል ሊወሰድ ይገባል፡፡ ይኼ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የእግር ኳስ አንዱ አካል ነው፡፡ ይሁንና ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ግን እግር ኳሳዊ የሆነው ነገር እየተለወጠ ጉዳዩን ውስብስብ እያደረገው ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋናነት ተጠያቂው ተቋሙን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው፡፡ ውሳኔዎች በተላለፉ በማግሥቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው የፍትሕ አካል እንኳ በወጉ ሳይነገረው፣ በይግባኝ ስም ውሳኔው ይለወጣል፡፡ ለምን ብሎ የሚጠይቅ አካልም የለም፡፡ በዚህ መሀል የፊፋንና የካፍን ሕግ ለመተግበር በሚታትሩ የጨዋታ ዳኞች ላይ እያጋጠመን ያለው ሰብአዊነት የጎደለው ድርጊት እንዲፈጸም ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡ እኔን ጨምሮ የሙያው ባልደረቦች የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ዕጣ ክፍላቸው እንዲሆን አድርጓል፤›› ብሏል፡፡

ሌሎችም ፌዴራልና ኢንተርናሽናል የጨዋታ ዳኞችና ረዳቶቻቸው ለዚህ ሁሉ ችግር እንዲዳረጉ ዋናው ምክንያት ወጥነት የጎደላቸው የፌዴሬሽን ውሳኔዎች ስለመሆናቸው ይስማማሉ፡፡

የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተፈራ ደምበል በበኩላቸው፣ በእሳቸውና በባልደረቦቻቸው የሚተላለፉ ውሳኔዎች እንዴትና በምን ዓይነት የሕግ አግባብ እንደሆነ ሳይታወቅ፣ ውሳኔዎች በተላለፉ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ውሳኔዎች ሲሻሩ የሚያውቁት በተቋማዊ አሠራር ሳይሆን፣ ከመገናኛ ብዙኃን ስለመሆኑ ጭምር ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮች በበኩላቸው፣ ለዚህ በዋናነት እንደምክንያት የሚጠቅሱት፣ ‹‹በፌዴሬሽኑ አሁን በኃላፊነት ካለው አመራር ብዙዎቹ ተቋሙን እንደገና ለመምራት ለምርጫ ዕጩ ሆነው የቀረቡ ናቸው፡፡ ዛሬ የተወሰነው ውሳኔ በማግሥቱ እንዲሻር የሚደረገው ደግሞ ውሳኔው የተላለፈባቸው ክለቦችም ሆነ የሙያ ማኅበራትን ድምፅ ላለማጣት በሚል ነው፤›› በማለት ተቋሙ መያዣ መጨበጫ ወደ ሌለው ዝቅጠት የገባበትን ቁልፍ ችግር ያብራራሉ፡፡

መፍትሔውን አስመልክቶ አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ‹‹አሁን ያለነው የፌዴሬሽኑ አመራሮች የአገልግሎት ጊዜያችንም ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ በመሆኑ፣ በጉባዔ እንድንወገድ ተደርጎ፣ የፌዴሬሽኑ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ለጊዜያዊ ባለአደራ ቦርድ ኃላፊነቱን መስጠት ብቻ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ይህ ሳይሆን ባለው ይቀጥል ከተባለ ግን፣ ችግሩ የበለጠ እየተወሳሰበ ከመሄድ ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ጭምር ያስረዳሉ፡፡

ስፖርት በማኅበራዊ ዘርፍ የሰው ልጆችና አገሮች መተዋወቂያ፣ የግንኙነትና ትስስር መፍጠሪያ፣ ከዚህም ሲያልፍ በአካሉና በጤንነቱ የጎለበተ ዜጋን ለማፍራት እየተጫወተ የሚገኝ ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን የሚገልጹ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች፣ በኢኮኖሚው ረገድም ቢሆን ዓለም ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል በቢሊዮን የሚቆጠር ፋይናንስ የሚፈስበት አዋጪ የኢንቨስትመንት አማራጭ እየሆነ መምጣቱን ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በመነሳትም በኢትዮጵያ እግር ኳሱ በተለይም በአሁኑ ወቅት ውጤት ማጣቱ ሳያንስ ለሰዎች ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር ጠንቅ መሆኑ እጅግ እንደሚያሳፍርም ያስረዳሉ፡፡

የዳኞችና ታዛቢዎች ማኀበር ውሳኔን ተከትሎ በጉዳዩ ከፌዴሬሽኑ ጋር የመከሩት የክለቦች ሥራ አስኪያጆች በበኩላቸው፣ በእግር ኳሱ እየተፈጠረ ካለው ነባራዊ እውነታ በመነሳት ለችግሩ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ በዳኞች እንቢተኝነት ውድድሮች የሚቋረጡ ከሆነ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት ወራጅም ሆነ ወጪ ቡድን እንደማይኖር ሲያስጠነቅቁ ተደምጧል፡፡  

ይሁንና በኢትዮጵያ በተለይም በእግር ኳሱ አሁን አሁን የሚስተዋለው ጉዳይ ቅርፅና ይዘቱን እየቀያየረ የሚያስከትለውም የሕይወትና የንብረት ከፍተኛ ጉዳት የሚያሳስባቸው የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች፣ ‹‹ለዚህ ችግር ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች መፍትሔ ሊሆኑ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች ለስፖርቱ ዕድገትና ሰላም የሚጨነቁና የሚያስቡ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን እየታየ ያለው ይኼ ሁሉ ረብሻና ሁከት በተፈጠረበት በዚህ ወቅት፣ ስለ ወጪና ወራጅ ማሰብ አልነበረባቸውም፡፡ ተቋሙም ሕጋዊ ባለቤት ሳይኖረው በግለሰቦች የግል ፍላጎት ብቻ እንዲህ ሲሆን፣ ለምን ብለው መጠየቅ በቻሉም ነበር፤›› በማለት መንግሥት በዚህ ጉዳይ እጁን አጣጥፎ መቀመጥ እንደሌለበትም ያሳስባሉ፡፡         

በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይም በአሁኑ ወቅት በስፖርቱ ስም የሚስተዋሉ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደሎች፣ በዋናነት ተቋሙን የሚመራው አካል መፍትሔ የሚሆን አቅም ማጣቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የአገሪቱ ክለቦች አደረጃጀት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሔር ተኮር ቅርፅ እየያዘ መምጣቱ በዋናነት የሚጠቀሱ አሉ፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ ለችግሩ መፍትሔ የሚሉትን ሲጠቁሙ፣ ‹‹በጨዋታ ጊዜ አዘውትረው ወደ ሜዳ የሚገቡና በተመልካቹ ዘንድ ተሰሚነት አላቸው የሚባሉ ወጣቶችን በመመልመልና ኃላፊነትም በመስጠት ፀጥታውን እንዲያስከብሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ስታዲዮም በወልዋሎ ዓዲግራትና መከላከያ ጨዋታ ላይ በተከሰተው አለመግባባት፣ የወልዋሎ ክለብ ተጫዋቾች የጨዋታውን የመሀል ዳኛ እንደዚያ ሲያዋክቡና ሲደበድቡ የፀጥታ ኃይሎች በሥፍራው ቢገኙም፣ ሜዳ ውስጥ ለሚፈጠሩ ምክንያቶች እንዴት ማስቆም እንደሚቻል ከፊፋ መርሐ አንፃር እጃቸውን አጣጥፈው ተቀምጠው ቢታዩ አይፈረድባቸውም፡፡ ለዚህም ሲባል የፀጥታ አስከባሪ ወጣቶች ተደራጅተው የፀጥታ ማስከበር ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ቢሆን ኖሮ ግን፣ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ስታዲየም የተፈጠረውን አስነዋሪ ተግባር ሜዳ ውስጥ በመግባት ለዳኛውም ከለላ በሆኑት ነበር፡፡ በዚህ መንገድ የስታዲዮሞችን ፀጥታ የማስከበር ሥራ በብሔር ፖለቲካ የመተርጎም ዕድል በጠበበ ነበር፤›› በማለት ነው የሲቪል ፀጥታ አስከባሪዎችን አስፈላጊነት ያብራሩት፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...