Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርሕግን ያልተከተለ አሠራር ያማረው ጉባዔው ወይስ ቅሬታ አቅራቢዎቹ?

ሕግን ያልተከተለ አሠራር ያማረው ጉባዔው ወይስ ቅሬታ አቅራቢዎቹ?

ቀን:

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነን ሪፖርተር ጋዜጣ ሚያዝያ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. የረቡዕ ዕትሙ ገጽ 3 ያሠፈረው ‹‹የፌዴራል ዳኞች ምልመላ ቅሬታ አስነሳ›› የሚለው የተሳሳተ ዘገባ ነው፡፡ ጋዜጣው ቅሬታ አቀረቡልኝ ያላቸውን አቤቱታ አቅራቢዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ለሦስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዕጩ ዳኞችን ለመመልመል በቅርቡ ያካሄደው የማጣሪያ ምልመላ ‹‹ሕግን ያልተከተለ፣ አድልኦና መገለል ያለበት አሠራር ነው›› በማለት ያትታል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይህንን ቅሬታቸውን ለኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማቅረባቸውንም ይገልጻል፡፡ ወደ ጉዳዩ ከመግባታችን በፊት አንድ ቅሬታ የቀረበበት ጉዳይ፣ ቅሬታውን መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ አቤቱታው የቀረበበት ‹‹ቅሬታ ሰሚ አካል›› በኩል በቀረበለት ጉዳይ ላይ ውሳኔውን ከማሳወቁ በፊት (ጉዳዩ የቀረበለት አካል ቅሬታውን በይግባኝ የማየት፣ በሕግ የተሰጠው ግልጽ ሥልጣን አለው የሚለውን ግምት ወስደን) ቅሬታ አቅራቢውም ሆነ አንድ የፕሬስ ውጤት በእንጥልጥል ላይ ያለን ጉዳይ በሚዲያ ማሠራጨት ተገቢ ነው ወይ? በቅሬታ ሰሚው ላይ ከወዲሁ ተፅዕኖ ለማሳደር ወይም የምልመላ ሒደቱን ለማደናቀፍና ብዥታ ለመፍጠር ታስቦ የተወጠነ አይመስልም ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለጊዜው ገታ አድርግን በቀጥታ ወደ ጉዳዩ እንግባ፡፡ ከሁሉም በፊት አንባቢ በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተገቢ ግንዛቤ እንዲኖረው በማሰብ ስለፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሥልጣንና ተግባር፣ እንዲሁም የዕጩ ዳኞች የምልመላ ሥርዓት ትንሽ ማለቱ ተገቢ ይሆናል፡፡  

በኢትዮጵያ ታሪክ ትኩረት ተነፍጓቸው፣ ተዳክመውና ተልፈስፍሰው ከቆዩት መንግሥታዊ ተቋማት መካከል ፍርድ ቤቶች በመጀመርያው ረድፍ ይሠለፋሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ዘመናዊ ዳኝነት በኢትዮጵያ ከተዘረጋ ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁሉም ዜጎች ክፍት የሆነ፣ አሳታፊ፣ ግልጽነት የተላበሰና በብቃት ላይ የተመሠረተ የአሿሿም ሥርዓትና በሚታወቅ ዝርዝር መሥፈርት የተመሠረተ የዳኝነት የምልመላ ሥርዓት እንዳልነበረ ለማንም የተወሰረ አይደለም፡፡ ለዳኛ የሚያበቁ ግልጽ መሥፈርቶች ወጥተው፣ መሥፈርቱን እናሟላለን የሚሉ ዜጎች እንዲወዳደሩ የተሰጠ ዕድል አልነበረም፡፡ ዳኛ የመመልመልና የመሾም ወይም የማሾም ሙሉ ሥልጣኑ የአስፈጻሚው ከመሆኑም በላይ አንድ ሰው በየደረጃው ላሉ ፍርድ ቤቶች እንዴት በዳኝነት እንደሚሾም፣ ከተሾመ በኋላ ያለውን ነፃነትና የተጠያቂነት ሥርዓት በዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ የተደገፈ ሥርዓትም ሆነ የዳኝነት አካሉን ከምልመላው ጀምሮ የሥራ አፈጻጸሙን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን ያለው ገለልተኛ አካል አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ በዳኞች ምልመላና በአሿሿም ላይ መሠረታዊ ለውጥ የመጣው የፌዴራል የዳኝነቱ አካሉን በገለልተኛ አካል ማስተዳደር ከተጀመረ በኋላ ነው፡፡ የተሻሻለው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አዋጅ ቁጥር 684/20002 ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ የዳኝነት ነፃነትንና ገለልተኛነትን ለመጠበቅ ሲባል የጉባዔው አባላት ስብጥር ከአስፈጻሚው ውጪ ተደርጓል፡፡ ጉባዔው ከፌዴራል የዳኝነት አካል አምስት፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስት፣ ከአስፈጻሚ አንድ፣ ከጠበቆች ማኅበር አንድ፣ ከዩኒቨርሲቲ የሕግ ተቋም አንድ፣ ከታዋቂ ሰው አንድ ያቀፈ ሆኖ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የጉባዔው ሰብሳቢ ናቸው፡፡ አዋጁ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችን የመመልመል ሥልጣን ለጉባዔው ይሰጣል፡፡ ጉባዔው አዋጁን ለማስፈጸም ደንብ ወይም መመርያ ሊያወጣ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 14 በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በ2003 ዓ.ም. የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዕጩ ዳኞች ምልመላ ሥርዓት አፈጻጸም መመርያ አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡

- Advertisement -

ይኼው አሳታፊ ግልጽነት የተላበሰና በኢትዮጵያ የዳኝነት ታሪክ እንደ አንድ እመርታዊ ለውጥ የሚታየው የምልመላ ሥርዓት የተወዳዳሪዎች የምዝገባ ሒደት፣ የማስታወቂያ አገላለጽና የማጣሪያ ሥርዓቶች፣ እንዲሁም የውጤት አገላለጽ ግልጽነት ባለው መንገድ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እኩል ዕድል በሚሰጥ አቅጣጫ እየተመራ ይገኛል፡፡ የምልመላ ሥርዓቱ ግልጽነት ለተወዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆን ሒደቱን መከታተል ለሚፈለግ ሦስተኛ ወገንም ሆነ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን በማሰብ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ጭምር በመጠቀም ሒደቱን አሳታፊና ግልጽነት የተላበሰ ለማድረግ የተጓዘው ርቀት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ስለሆነም የጉባዔው የዳኞች የምልመላው የአሿሿም ሥርዓቱ ለሌሎች ተቋማት እንደ አንድ የጥሩ ተሞክሮ ማዕከል ሆኖ ያገለገለ እንደሆነ እንጂ፣ የሚያስወቅሰው አይሆንም፡፡ እያንዳንዱ የምልመላ ሒደት ከተወዳዳሪዎች ጥሪ ማስታወቂያ ጀምሮ የምዝገባ፣ የቅድመ ማጣሪያ፣ የጽሑፍ ፈተናና የቃለ መጠይቅ ሒደቱንም ሆነ በመጨረሻም በዚህ መንገድ የተመለመሉትን ዕጩ ዳኞች ለሹመት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመቅረባቸው በፊት በሥነ ምግባራቸው ለሕግና ለሕገ መንግሥቱ ያላቸው ተገዥነትና እምነት በተመለከተ በሕዝብ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ይደረጋል፡፡ ስለሆነም በጉባዔው የሚመራው የፌዴራል ዳኞች የምልመላ ሥርዓት ከማንም ተቋም በላይ በግልጽ መሥፈርት ተመሥርቶ የሚከናወን አሳታፊና በግልጽነት የተሞላ ብቻ ሳይሆን፣ በሒደቱ ቅሬታ ያለው አካል ቅሬታውን የሚያቀርብበትና ምላሽ የሚያገኝበት ሥርዓት ዘርግቶ የሚካሄድ መሆኑ ሒደቱን ሙሉዕ ያደርገዋል፡፡ 

በዚሁ መሠረት ባለፉት ሰባት ዓመታት ለሦስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተደረገው ዕጩ ዳኞች ምልመላ ሥርዓት (በ2004፣ 2006 እና 2008) ለተወዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዜጋ ግልጽ፣ አሳታፊ፣ ተደራሽ፣ ተዓማኒና ብቃት ላይ በተመሠረተ መንገድ መፈጸም ተችሏል፡፡

በ2010 ዓ.ም. እየተካሄደ ያለው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዕጩ የምልመላ ሒደትም ከላይ የተጠቀሱትን የሕግ ማዕቀፎችና መሥፈርቶች ተከትሎ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ጉባዔው ለሦስቱ ፍርድ ቤቶች ዳኞችን መመልመል እንደሚፈልግ፣ ተደራሽ በሆኑ የኅትመትና የኤሌክትሪክ ሚዲያዎች፣ በፍርድ ቤቱ ማኅበራዊ ሚዲያ፣ እንዲሁም በክልልና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በመለጠፍ ለሁሉም ጥሪ አድርጓል፡፡ በዚህ መንገድ በወጣው የቅድመ ዕጩ ዳኝነት ምዝገባ ማስታወቂያ መሠረት ለሦስቱም ፍርድ ቤቶች 3,330 አመልካቾች ተመዝግበዋል፡፡ ይህ ቁጥር ጉባዔው ከዚህ በፊት በስድስት ዓመታት ካካሄዳቸው ሦስት የፌዴራል ዳኞች የምልመላ ሒደቶች በተመዝጋቢ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ጉባዔው በአዋጁና በመመርያው በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ከአመልካቾቹ መካከል የተሻለ ብቃትና የሥራ ልምድ ያላቸውን በጥንቃቄ በመለየትና በማጣራት ለጽሑፍ ፈተና ያለፉ አመልካቾች ስም ዝርዝር በፍርድ ቤቱ ማኅበራዊ ሚዲያ ጭምር ይፋ ሆኗል፡፡ ይህንን ተከትሎም ሚያዝያ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የጽሑፍ ፈተናው እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ 

በጽሑፍ ፈተና ያለፉትን በፍርድ ቤት ድረ ገጽ ይፋ ከተደረገ በኋላ ለሦስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ለዕጩ ዳኝነት ካመለከቱት መካከል ጥቂቶቹ የተዘረጋውን የአቤቱታ አቀራረብ ሥርዓት በመጠቀም ቅሬታቸውን ለጉባዔው ጽሕፈት ቤት በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ የጉባዔው ጽሕፈት ቤት አቤቱታቸውን መርምሮ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በጽሕፈት ቤቱ ምላሽ ያልረኩ ወገኖች ቅሬታቸውን በይግባኝ መልክ ለጉባዔው ሰብሳቢ አቅርበዋል፡፡ ጉዳዮቻቸውና ማስረጃዎቻቸው በመመርመር ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ጉባዔው የዘረጋው ይህ ዓይነቱ ግልጽነት የተላበሰ ሥርዓት በመታገዝ በጽሑፍ፣ በአካል ጭምር ግልጽና አሳማኝ ምላሽ ከተሰጣቸው ከእነዚህ አካላት መካከል ጥቂት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች አመልካቾች (በ2006 ዳኛ የሆኑ ናቸው) በሪፖርተር ጋዜጣ ቀርበው ሕግን ባልተከተለና አድልኦ በተሞላበት ሁኔታ ከሒደቱ ተገልለናል በማለት ቅሬታ ያቀረቡት፡፡ እነዚህ አቤቱታ አለን የሚሉት ዳኞች ጉባዔው በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ያቀረቡትን የዳኝነት የሥራ ልምድ ከሌሎች ተወዳዳሪዎቻቸው ያነሰ በመሆኑ ማጣሪያውን ማለፍ እንዳልቻሉ ያቀረቡትን ማስረጃ በማገናዘብ ምላሽ የተሰጣቸው መሆናቸውን አንባቢው ሊገነዘብልን ይገባል፡፡

በጋዜጣው ላይ ቅሬታቸውን ያቀረቡት እነዚህ ወገኖች ለአቤቱታው መነሻ ሆነን ያሉትን የሕግና የአሠራር ጥሰት እያነሳን እውነታውን ወደ መመልከት እንግባ፡፡ እንደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ አገላለጽ ጉባዔው ባደረገልን የማስታወቂያ ጥሪ መሠረት ከተመዘገብን በኋላ ወደ ቀጣዩ የጽሑፍ ፈተና የሚያቀርቡት ለመለየት ያካሄደው የማጣራት ሥራ በአዋጅ 684/2002 አንቀጽ 11 ስለፌዴራል ዳኞች አሿሿም የተዘረጋው ሥርዓት የጣሰና ሕግን ያልተከተለ ነው ይላል፡፡ ቀጠል በማድረግም ‹‹ዕውቅና ካለው ትምህርት ተቋም በሕግ ትምህርት ቢያንስ የመጀመርያ ዲግሪ በከፍተኛ መሥፈርት አውጥቷል፤›› በማለት ጉባዔውን ወንጅለውታል፡፡ እዚህ ላይ አንባቢ እንዲገነዘብልን የምንፈልገው በጋዜጣው የተገለጸው መሥፈርት ዝቅተኛ ተፈላጊ ችሎታ እንጂ ከዚህ በላይ ብቃትና ልምድ ያላቸውን እንዳይመረጡ የሚከለክል ሕጋዊ መሠረት የለም ብቻ ሳይሆን፣ የተሻለ የዳኝነት ልምድ ያላቸው ከማንም ተወዳዳሪ በላይ የተሻለ የመመረጥ ዕድል አላቸው፡፡

ዳኛ ሆኖ ለመሾም ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንዳሉት በአዋጁ አንቀጽ 11/1/ ከሀ እስከ ረ የተዘረዘሩት ዝቅተኛ ተፈላጊ መሥፈርቶች ማሟላት እንዳለበት ይዘረዝራል፡፡ ይህ አንቀጽ አንድ ለቅድመ ዕጩነት የሚቀርብ አመልካች ወይም ተወዳዳሪ ዝቅተኛ የተፈላጊ ችሎታ መሥፈርት እንጂ ወደ ማጣሪያ ለማለፍ ከተጠቀሰው በላይ የካበተ የሥራ ልምድ ያላቸው ተወዳዳሪዎች እንዳይመረጡ የሚከለክል ሕግም ሆነ በሕግ የተደገፈ ምክንያት የለም፡፡ በአዋጁ መንፈስ መሠረት ማድረግ የማይቻለው የተጠቀሱት አስገዳጅ ዝቅተኛ መሥፈርቶችን የማያሟላ አመልካች ለጽሑፍ ፈተና ማቅረብ የማይቻል መሆኑ ነው፡፡ በማጣሪያ ሒደት አስገዳጅ የሆነውን ዝቅተኛ ተፈላጊ መሥፈርቱን በማያሟሉ መካከል በማበላለጥ መምረጥ የተለመደ አሠራርና የሕግ ድጋፍ ያለው ነው፡፡ የሚፈለገው የዕጩ ዳኞች ብዛት ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች ብዛት እያመዛዘነ መመርያውን ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት ለጉባዔው የተሰጠ ሥልጣን መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

አዋጁን ተንተርሶ በ2003 ዓ.ም. የወጣው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዕጩ ዳኞች ምልመላ ሥርዓት አፈጻጸም መመርያ አንቀጽ 15/2/ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡፡ ‹‹እንደሚፈለገው የተወዳዳሪዎች ብዛት እየታየም የተሻለ የሥራ ልምድ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ቅድሚያ እንዲያገኙ ሊደረግ ይችላል፤›› ይላል፡፡ ጉባዔው የሚቀርቡትን ለማጣራት ለሥራ ልምድ በተለይ ለዳኝነት የሥራ ልምድ ትኩረት እንዲሰጥ ጉባዔው ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የተፈጸመ ሕጋዊ አሠራር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ጉባዔው ያሻሻለው አዲስ መመርያ የለም፡፡ ሥራ ላይ ያለውን መመርያ የአዋጁን መንፈስና ዓላማ በተከለተ መንገድ ለማስፈጸም የተሰጠውን ሥልጣን መሠረት ተደርጎ የተከናወነ ተግባር  ነው፡፡ ጉባዔው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ‹‹መሥፈርቱን ባናሟላም ቅድሚያ ልትሰጡን ይገባል፤›› በማለት ሕግን ያልተከተለና ሚዛናዊነት የጎደለው ጥያቄያቸውን ባለማስተናገዱ የጉባዔውን ሥርዓት የተከተለ አሠራር ማጥላላት ተገቢም አይደለም በሕግም ያስጠይቃል፡፡

ጋዜጣው ቅሬታ አቅራቢዎቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ጉባዔው የማጣራት ሒደት ለዳኝነት የሥራ ልምድ ልዩ ትኩረት መስጠቱ ተገቢ አይደለም የሚል አስገራሚ ትችትም አስደምጦናል፡፡ ዳኝነትን ለመሰለ በሰው ሕይወት፣ ነፃነትና ንብረት ላይ አስገዳጅ ውሳኔ የሚወሰን ሙያዊ፣ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ሹመትን ጣመረ ከባድ ኃላፊነት የተሸከመ ሥራ ይቅርና ለማንኛውም የአገልግሎት ሰጪ ተቋም የወጣ የተፈላጊ የሥራ መደብ ማስታወቂያ ለሚፈለገው የሥራ ኃላፊነት የተሻለ ቅርበት ያለው ባለሙያ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሕግ ባለሙያዎች ስለሆኑ ለቀባሪ ማርዳት ሊሆን ይችላል፡፡ በዳኝነት ለሚሠራ ዕጩ ዳኛን ለመመልከት በዳኝነት የተሻለ አገልግሎት ላለው ተወዳዳሪ ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ብቻ ሳይሆን ቅቡልነት ያለው ሕጋዊ አሠራር ነው፡፡ መምህር ለመቅጠር የፈለገ አንድ ዩኒቨርሲቲ ተቋም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማስተማር ልምድ ያለውን መምህር ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚቀጥር ሁሉ፣ ዓቃቤ ሕግ ለመሾም የፈለገ የፍትሕ ተቋም የዓቃቤ ሕግነት የሥራ ልምድ ያለውን ቅድሚያ ሰጥቶ ማጣሪያውን እንዲያልፍ እንደሚመርጠው ሁሉ፣ ዳኛ ለመመልመል በዳኝነት በርከት ላሉ ዓመታት ለሠሩት ቅድሚያ መስጠቱ ኃጢያቱ የቱ ላይ ነው? ለነገሩ ቅሬታ አቅራቢዎቹ መምህራን፣ ዓቃቢያን ሕግና ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች ከምልመላው ተገልለዋ የሚል ስሞታ ያቀረቡት ለተነሱበት ሕገወጥ ዓላማ ከጎናቸው ለማሠለፍ ታስቦ እንጂ፣ ስለሌሎች ተወዳዳሪዎች አስጨንቋቸው እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ይመስለናል፡፡ ጉባዔው ቀደም ሲል ያወጣው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዕጩ ዳኞች የምልመላ ሥርዓት አፈጻጸም መመርያ በሕግ ዕውቀታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በዳኝነት ልምዳቸው የተሻለ አገልግሎት ያላቸውን ቅድሚያ እንደሚሰጥ ከማንም በላይ እነሱ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡

ሌሎች ተገልጋዮች ከሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች መካከል ዋነኛው በየደረጃው ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች የምትሾሟቸው ዳኞች መካከል ቀላል የማይባል ቁጥር በቂ የዳኝነት የሥራ ልምድ ስለሌላቸው በችሎት አመራርና በፍርድ ጥራት ላይ ሰፊ ክፍተት እየተፈጠረ መሆኑን ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ ዛሬ ዛሬ ዳኛ ለመሆን የሚያበቁ መሥፈርቶች ጠበቅ ያሉና ብቃትን፣ የሥራ ልምድን፣ ሥነ ምግባርንና ሕዝባዊ አመለካከትን መነሻ ያደረጉ መሆን አለባቸው የሚለው ሐሳብ ሚዛን እየደፋ የመጣውም ዳኞች ከተሸከሙት ወገብ የሚያጎብጥ ኃላፊነትና ከባድ ሸክም ጋር ለማጣጣም እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ ስለዚህ በተለይ ከባድና ውስብስብ የፍትሐ ብሔር የወንጀል ጉዳዮች ለሚመለከቱ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች የካበተ የዳኝነት ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች መሾም ሕጋዊም ተገቢም መሆኑን ለመረዳት ምርምር የሚያስፈልግ ጉዳይም አይደለም፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹም ብለውታል እንደተባለውም ጉባዔው በምን መልኩ ከሕግ አግባብ ውጪ እንደተጓዘና አድልኦ እንደፈጸመ ፍንጭ የሚሰጥ አንዳችም በሕግና በማስረጃ የተደረገፈ የቀረበ ነገር የለም፡፡ ሒደቱም የምልመላው ግልጽነትና አሳታፊነት ያጎላው እንደሆነ እንጂ ለትችት የሚረዳው ነገር አለ ብለን አናምንም፡፡

አቤቱታ አቅራቢዎች አንባቢውን ለማደናገርና ጉባዔው እያካሄደ ያለውን የዕጩ ዳኞች የምልመላ ሒደት ለማደናቀፍ ቆርጠው መነሳታቸውን የሚያመላክት ሌላው ጉዳይ ቅሬታ አቅርበው የጉባዔው ጽሕፈት ቤትና የጉባዔው ሰብሳቢ ለቅሬታቸው ምላሽ እንደሰጧቸው እንኳ ለመግለጽ ድፍረት አላገኙም፡፡ አንባቢንና የመንግሥት አካላትን ለማደናገር እነሱ ከሕግ ውጪ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ብቻ በሕግ ማዕቀፍ እየተመራ ያለውን የምልመላ ሒደት ማጠልሸት ተገቢ አይሆንም፡፡ እኔ ካልተመለመልኩ ሁሉም ነገር ገደል ይገባል በሚል መፈክር ያነገቡ እነዚህ ወገኖች፣ እነሱ የማይካተቱ ከሆነ እየተካሄደ ያለው የዳኞች የምልመላ ሒደቱ እንዲሰረዝ ድፍረት የታከለበት ጥያቄ ማቅረባቸውም ተሰምቷል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? በሕግና በሥርዓት በሚመራ አገር እንዲህ ዓይነት አጉራ ዘለል ጥያቄ ማቅረብ ያውም የሕግ ዕውቀት ካለው ሰው ተገቢነት አለውን? ዓላማው ግልጽ ነው፡፡ ሒደቱን ሆን ብሎ ለመረበሽና ለማደናቀፍ የታሰበ ከመሆኑም በተጨማሪ በሒደት ላይ ያለን የምልመላ ሥርዓት ተዓማኒን እንዲያጣ፣ ተወዳዳሪዎች ተስፋ እንዲቆርጡ፣ በውጤቱ የምልመላ ሥርዓቱ ዋጋ ለማሳጣት የሚደረግ ሴራ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል፡፡

‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› መፈክር ያነገቡ እነዚህ ቅሬታ አቅራቢዎች መሥፈርቱን ባለማሟላታቸው ምክንያት ከማጣሪያው እንደቀሩ እያወቁና ጉባዔው በዘረጋው የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓት መሠረት ቅሬታቸውን አቅርበው በቂ ምላሽ ተሰጥቷቸው እያለ፣ ጉባዔው የጀመረውን ግልጽነት የተላበሰ አሳታፊና ብቃት ላይ የተመሠረተ የምልመላ ሒደት እንዲሰረዝ በድፍረት ጠይቀዋል፡፡ ቅሬታ ማቅረብ መብት ቢሆንም፣ ማንኛውም የሚቀርብ ጥያቄ ሕግንና አሠራርን የተከተለና እውነት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ይቅርና የሕግን ሀ፣ ሁ፣ . . .  የሰነቁ ሰዎች ሌላው ዜጋም ይዘነጋዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ እውነታው ይህ ከሆነ ሕግን ያልተከተለ አሠራር ያማረረው ታዲያ ማነው? ጉባዔው ወይስ ቅሬታ አቅራቢዎቹ?

ዘገባውን ይዞ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ የጉባዔው ጽሕፈት ቤት ኃላፊን ለማነጋገር ስልክ ደውለን ልናገኛቸው አልቻልንም በሚል ምክንያት ብቻ እንዲህ ዓይነት የዕጩ ዳኞች የምልመላ ሒደቱን ለማደናቀፍ የተሰጠን የአንድ ወገን አስተያየት ይዞ መውጣት ከሁሉም በፊት የጋዜጠኝነት ሙያ የሚዛናዊነት መርህ እንደሚጥስ ለጋዜጣው አዘጋጅ ይጠፋዋል የሚል እምነት የለንም፡፡ እንዲህ ዓይነት የተቀነባበረ ወሬ የሚያስከትለውን ውጤት ተገንዝቦ ጉዳዩን ሚዛን ለመጠበቅ አዘጋጁን ከዚህ በላይ ጥረትና ትጋት ማድረግ አይጠበቅበትም ነበርን? ሌላው ቢቀር ቢሯችን ብቅ ብሎ መጠየቅና እውነታውን ለመረዳት ይቻል እንደነበር የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡

ስለሆነም ግልጽነት በተላበሰ አሳታፊና ብቃትን ማዕከል ባደረገ፣ መልኩ እየተከናወነ ያለውን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዕጩ ዳኞች ምልመላ ለማደናቀፍ፣ ሒደቱን ከእውነታው በራቀና በተወናበደ መንገድ ተዓማኒነት ለማሳጣትና ተወዳዳሪዎችን ተስፋ ለማስቆረጥ የተጀመረው ዘመቻ መቆም እንዳለበት ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

(ሰለሞን በላይ፣ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...