የተሳፈርንባት በጥሩ ሁኔታ የተያዘች ናት፡፡ በዚያ ላይ በማስታወቂያዎች ደምቃለች፡፡ ከአሮጌ ዕቃዎች እስከ ኮምፒዩተር የምንፈልጋቸውን ነገሮች የሚጠቁሙ ማስታወቂያዎች ተገጥግጠውባታል፡፡ ሃይማኖታዊና ዓለማዊ ጥቅሶችም በየፈርጃቸው ተሰድረዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ የቦብ ማርሌና የቴዲ አፍሮ ፎቶግራፎችም ሥፍራቸውን ይዘዋል፡፡ የታክሲዋ ሾፌር ፀጉሩ የተቆጣጠረ ቀላ ያለ ለግላጋ ወጣት ነው፡፡ በእንክብካቤ የተያዙት ታክሲዋና ሾፌሯ ብቻ ሳይሆኑ ወያላውም ጭምር ነው፡፡ ፅድት ያለና የዘናነጠ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ታክሲዋን በፈረቃ እየተቀያየሩ ሳይሾፍሯት አይቀርም፡፡ ሲነጋገሩም በጣም ተከባብረው ነው፡፡ በሥርዓት ያደጉ ይመስላሉ፡፡
ከሜክሲኮ ቦሌ የምትሠራው ታክሲ መቀመጫዋ ይደላል፡፡ ውስጧም ፀዳ ያለ ሆኖ ዘና በሚያደርጉ ለስላሳ ሙዚቃዎቿ ተሳፋሪዎቿን ታዝናናለች፡፡ ጉዞ ተጀምሯል፡፡ አሪፉ ወያላ ሒሳብ መቀበል እንደ ጀመረ አንዲት ኮረዳ ሳቋን ለቀቀችው፡፡ ከዚያ ዝግ ተደርጎ ከተለቀቀው ለስላሳ ሙዚቃ ውጪ ፀጥታ በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ፣ የእዚች ቆንጂዬ ልጅ ሳቅ ምን ይሉታል? አልኩኝ ለራሴ፡፡ ወያላው ፈገግ እያለ፣ ‹‹በሰላም ነው? ምን ገጠመሽ?›› አላት፡፡ በዓይኑም ጠቀስ አደረጋት፡፡ በሾፌሩ ትይዩ ባለው ጥቅስ ላይ እንዳፈጠጠች፣ ‹‹ያንን ጥቅስ አላነበብከውም?›› አለችው፡፡ ሁላችንም ወደ ሾፌሩ አቅጣጫ አንጋጠጥን፡፡ ‹‹በርትተህ ከተማርክ የአለቆችህን ቁጥር ትቀንሳለህ›› ይላል የዚያ የጉደኛ የታክሲ ጥቅሶች ጸሐፊ ጥቅስ መሆኑ ነው፡፡
ሁላችንም ማለት ይቻላል ሳቅ በሳቅ ሆንን፡፡ አንዲት በመካከለኛ ዕድሜ ያሉ ወይዘሮ፣ ‹‹እጅግ በጣም የሚደንቅ ጸሐፊ ነው፡፡ ካሁን ቀደም ‘መብታችሁ ትዝ የሚላችሁ ታክሲ ውስጥ ነው? መጨቃጨቅ ከአሸባሪነት አይተናነስም፤‘ አሁን ደግሞ ይኼንን በመጻፉ አደንቀዋለሁ፤›› አሉ፡፡ ወይዘሮዋ ወቅታዊ ጉዳዮችን እየተከተለ የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች የባለ ጥቅሱን የግንዛቤ ምጥቀት የሚያሳይ ነው ሲሉ አከሉበት፡፡ እንዲህ ዓይነት በሳል አስተያየት የሚሰጡ እንስቶችን ሳይ እጅግ በጣም ደስ ስለሚለኝ እኔም ለእሳቸው አድናቆቴን ገለጽኩላቸው፡፡ ‹‹እንደ እርስዎ ዓይነት አርቆ ተመልካች ባይኖር ኖሮ የሰው ልፋት ሁሉ ገደል ይገባ ነበር፡፡ እርስዎ ለእንዲህ ዓይነቱ የፈጠራ ችሎታ ትኩረት ሰጥተው በአደባባይ የተሰማዎትን መናገር በመቻልዎ ሊመሠገኑ ይገባል፤›› በማለት አወደስኳቸው፡፡ እሳቸው የእኔን ምሥጋና ተቀብለው ፍላሚንጎ ወረዱ፡፡
ያቺ የመወያያ አጀንዳችንን የቆሰቆሰች ልጅ ወያላውን በፍቅር እያየችው ጎሸም አደረገችው፡፡ እየሳቀ እያያት፣ ‹‹ምነው እቱ?›› አላት፡፡ ‹‹ሰዎች እንዲህ ሲመሠጋገኑ ደስ አይልም?›› ስትለው፣ እሱም የዋዛ አልነበረምና፣ ‹‹እኔም አንቺን በጣም ነው ያደነቅኩሽ፣ ስሜትሽን ሳትቆጣጠሪ በመሳቅሽ የመወያያ ርዕስ ከፈትሽልን፣ አድናቂዎችሽ ነን፤›› አላት፡፡ ልጅቷ በወያላው ምሥጋና ፍንድቅድቅ ብላለች፡፡ አጠገቤ ያለው ሰውዬ ግን ልጅቷን ደስ በማይል ስሜት ይመለከታታል፡፡ የእኔ እሱን አትኩሮ ማየት የገባው ሰውዬ፣ ‹‹ይህች ልጅ ሞልቀቅ ያለች አትመስልም?›› አለኝ፡፡ በጣም ገርሞኝ፣ ‹‹መብቷ መሰለኝ?›› አልኩት፡፡ ‹‹መብቷ ሊሆን ይችላል፣ ሴት ልጅ እንዲህ ስትሆን ማየት ያስጠላል፡፡ ይች አገር ለምን እንደማታድግ የሚገባህ ሞልቃቆች በዝተው ለአገር የምንቆረቆር ሰዎች አንጀታችን ድብን ስለሚል ነው፤›› ሲለኝ የጠነዛ ፖለቲከኛ መስሎኝ ደብሮኝ ዘጋሁት፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ በጥራዝ ነጠቅ እውቀት ሁሉንም ነገር ማጨለም ስለሚወዱ ያንገሸግሹኛል፡፡ ዕይታቸው ደግሞ አንድ ዓይነት ነው፡፡ ሁልጊዜ ማላዘን ይወዳሉ፡፡
ወያላውና ልጅቷ በመግባባት ጨዋታቸውን ቀጠሉ፡፡ ሾፌሩ አልፎ አልፎ ሳቅ እያለ ያያቸዋል፡፡ ኦሎምፒያን አልፈን የጎደለ ወንበር ሞልተው ጉዞ ወደ ቦሌ ቀጠለ፡፡ የአዳዲስ ገቢዎችን ሒሳብ ከተቀበለ በኋላ ልጅቷና ወያላው እንደገና ወሬያቸውን ጀመሩ፡፡ ወዲያው፣ ‹‹ፈተና ስለደረሰ የጥናት ፕሮግራም ይውጣና እንዘጋጅ እንጂ?›› አለች ልጅቷ፡፡ ሾፌሩ ፕሮግራም መውጣቱን ነግሯት ማታ የተዘጋጀውን ፕሮግራም እንደሚወያዩበት ሲነግራት ተሳፋሪዎች ጆሮዎቻችን ቀጥ አሉ፡፡ ልጅት ወሎ ሠፈር ተሰናብታቸው ሄደች፡፡ ወያላውና ሾፌሩ በኋላ የጥናት ፕሮግራሙን ፎቶ ኮፒ አስደርገው ለጓደኞቻቸው ይዘው እንደሚሄዱ ተነጋግረው ተስማሙ፡፡ ወያላውን ጠጋ ብዬ ‹‹ትማራላችሁ እንዴ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ወንድማማቾች ነን፡፡ አባትና እናታችን በሞት ተለይተውናል፡፡ ታናናሾቻችንን እያሳደግን እኛ ደግሞ ማታ ዩኒቨርሲቲ እንማራለን፤›› ሲለኝ፣ ‹‹እግዚአብሔር ያሰባችሁትን ይሙላላችሁ፤›› ብያቸው ስወርድ፣ ያ ጨለምተኛ ደግሞ “እነዚህ ተምረው የት ሊደርሱ ነው?” እያለ ያጉረመርም ነበር፡፡ ምን ዓይነቱ ደባሪ ነው እባካችሁ?
በሕይወት መንገድ ላይ የሚገጥሙን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ አክብደን ያየናቸው ቀለው፣ በተቃራኒው እንደ ገለባ ያቀለልናቸው ደግሞ ከብደውና ገዝፈው ሲገኙ እንደመማለን፡፡ ‹‹መማር ያስከብራል አገርን ያኮራል›› የሚለውን ኅብረ ዜማ ከልብ የምወደው፣ እንዲህ ዓይነቶቹን ታታሪ የነገ ፍሬዎች ስለሚያስታውሰኝ ጭምር ነው፡፡ የአደባባይ ሰዎች የሚኖሩንና እስኪደንቀን ድረስ ከአንደበታቸው ማር ማር የሚል መልዕክት የሚንቆረቆረው ከእውቀት ማዕድ በተገኘ አንደበተ ርቱዕነት መሆኑን ዋቢ መጥቀስ ካስፈለገ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን እማኝ ማድረግ ይቻላል፡፡ እሳቸውም እኮ ተማሩ ብለው ነው የመከሩን፡፡ ትንሽ እውቀት አደጋ ስለሆነ ተምረን በምክንያታዊ አስተሳሰብ ብንመራ ተመራጭ ነው፡፡ ቀን ቢያቅት ማታ መማር ይቻላል፡፡ የመለኪያ አንገት ጨብጦ የማያውቁትን ፖለቲካ ከመፈትፈት ወደ ትምህርት ቤት ማምራት ይቅደም እላለሁ፡፡
(ኪሩቤል መሳይ፣ ከገርጂ)