Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበድንበር አካባቢ የጠረፍ ንግድ ቢፈቀድም ቤንሻንጉል ጉምዝና ጋምቤላ ተጠቃሚ አይደለንም አሉ

  በድንበር አካባቢ የጠረፍ ንግድ ቢፈቀድም ቤንሻንጉል ጉምዝና ጋምቤላ ተጠቃሚ አይደለንም አሉ

  ቀን:

  ክልሎች ኢትዮጵያን ከሚያዋስኑ ጎረቤት አገሮች ጋር በ90 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የጠረፍ ንግድ እንዲያካሂዱ የፌዴራል መንግሥት ቢፈቅድም፣ በተለይ የቤንሻንጉል ጉምዝና የጋምቤላ ክልሎች ተጠቃሚዎች አይደለንም አሉ፡፡

  የፌዴራል መንግሥት በጠረፍ አካባቢ የሚገኙ ክልሎች አገሪቱን ከሚያዋስኑ ክልሎች ጋር እንዲነግዱ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን በአንፃራዊነት ሶማሌ፣ አፋርና ቦረና አካባቢ የሚገኙ ሕዝቦች ከሶማሊያና ከሶማሌላንድ፣ ከጂቡቲና ከኬንያ ጋር በተሻለ ደረጃ እየተገበያዩ ነው፡፡

  ከእነዚህ በተለየ የቤንሻንጉል ጉምዝና የጋምቤላ ክልሎች በፀጥታና በተለያዩ ገደቦች ምክንያት መነገድ ባለመቻላቸው ብዙ ርቀት ተጉዘው መሀል አገር ከሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ለመሸመት በመገደዳቸው፣ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች እንደተዳረጉ እየገለጹ ነው፡፡

  የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አልማሂ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በጠረፍ ንግድ ተጠቃሚ አይደለም፡፡

  ‹‹የቤንሻንጉል ጉምዝ ሕዝብ ከሰሜን ሱዳን ጋር በባህል፣ በሃይማኖትና በቋንቋ የተቆራኘ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ፍራንኮ ቫሉታና ከቀረጥ ነፃ መብት ቢፈቀድ መልካም ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የሁለቱ አጎራባች አካባቢዎች እንዲገበያዩ የተፈቀደው ከፍተኛው ገንዘብ ሁለት ሺሕ ብር ብቻ ነው፡፡ ሁለት ሺሕ ብር ደግሞ አሁን ባለው የብር የመግዛት አቅም ደካማ በመሆኑ ግብይት እየተካሄደ አይደለም ማለት ይቻላል፤›› በማለት፣ መንግሥት የጠረፍ ንግድ ቢፈቅድም ተግባራዊ መሆን እንዳልቻለ አቶ መሐመድ ገልጸዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም የተፈቀዱት የሸቀጥ ዓይነቶችም አናሳ መሆናቸውን፣ ከተፈቀዱት ውስጥም ስኳርና ዘይት የሌሉ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ ረዥም ርቀት ተጉዞ እንዲገበያይ በመገደዱ ለአላስፈላጊ ወጪና የጊዜ ብክነት እየተዳረገ መሆኑን አቶ መሐመድ ጠቁመዋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ነዋሪዎች ጋር ባካሄዱት ውይይት ይህ የጠረፍ ንግድ አካሄድ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚቆጣጠራቸው ኬላዎች ላይ የሚመድባቸው ባለሙያዎች በቋንቋ መግባባት ባለመቻላቸው ችግር እየተፈጠረ በመሆኑ፣ ክልሉ የጉምሩክ ሥራዎችን የሚያካሂድበት አሠራር እንዲቀየስ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ጥያቄ በመያዝ ሱዳን በሄዱበት ወቅት ከፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር ጋር መወያየታቸው ተገልጿል፡፡

  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የሁለቱን ፕሬዚዳንቶች ውይይት አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያና የሱዳን ሕዝቦች ትስስር እንዲጠናከርና የድንበር አካባቢ ነፃ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር መሪዎቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

  በጋምቤላ ክልል የጠረፍ ንግድ መቆሙ ይነገራል፡፡ የጋምቤላ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰናይ አኮሪ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር የጠረፍ ንግድ ሲያካሄድ ቆይቷል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት የደቡብ ሱዳን ፀጥታ በመደፍረሱ የጠረፍ ንግዱ ቆሟል፤›› ሲሉ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸው፣ ‹‹የባሮ ወንዝ የጀልባ ጉዞ እስከ ሰሜን ሱዳን የሚዘልቅ ቢሆንም፣ በድንበር አካባቢ የመሸገ ኃይል በመኖሩ ግብይቱን ማካሄድ አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡

  ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በተለይ ከጂቡቲ ዘይት፣ ዱቄት፣ ስኳር፣ ብርጭቆ፣ የፕላስቲክ ዕቃዎች፣ ደብተር፣ ሻይ ቅጠልና ክብሪት ይገባሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ ደግሞ የቁም እንስሳት፣ ወተትና የወተት ተዋፅዖ፣ ማር፣ ማሽላ፣ በቆሎና የሽሮ እህሎች ይላካሉ፡፡

  ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ደግሞ ባትሪ፣ ሽቶና ወረቀት የመሳሰሉ ምርቶች የሚገቡ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ደግሞ የጥራጥሬ እህሎች፣ ድንች፣ አትክልት፣ ሻይ ቅጠል፣ ሲጋራና የመዋቢያ ዕቃዎች ይላካሉ፡፡

  በእነዚህ የጠረፍ አካባቢዎች ከተፈቀደው በተጨማሪ ከፍተኛ መጠን ያለው የኮንትሮባንድ ንግድ፣ በጠረፍ ንግድ ሽፋን ሲካሄድ እንደቆየ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...