Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየሥራ ማቆም መብትና እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎት በኢትዮጵያ ሕግ

የሥራ ማቆም መብትና እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎት በኢትዮጵያ ሕግ

ቀን:

(ክፍል ሁለት)

በውብሸት ሙላት

በሚያዝያ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ በዚሁ ‹‹በሕግ አምላክ›› ዓምድ ከላይ በተገለጸው ርዕስ ክፍል አንድ ሆኖ የቀረበ ጽሑፍ ነበር፡፡ በዚህ ደግሞ ሁለተኛውን ክፍል እንቀጥላለን፡፡ የሚያተኩረው አስፈላጊ አገልግሎት የሚባሉት የሥራ ዘርፎች ውስጥ የተሠማሩ ሠራተኞች የሥራ ማቆም መብት ላይ ያለው ገደብ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ‹‹እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎቶች››  (ከዚህ በኋላ አስፈላጊ አገልግሎቶች በሚል የሚጠቀሱ) ተብለው የተለዩ ተቋማት ወይም የሥራ ዘርፎች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የሥራ ማቆም መብት የላቸውም፡፡ አሠሪዎችም ቢሆኑ እነዚህን ድርጅቶች መዝጋትም አይችሉም፡፡

ከአሁኑ አዋጅ በፊት በነበረው የአገራችን የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ አስፈላጊ አገልግሎቶች ተብለው ተዘርዝረው የነበሩና በአሁኑ አዋጅ ላይ ካልተካተቱ ወይም ከተሠረዙ ውስጥ ባንክ፣ ፖስታ፣ አገር አቋራጭ አውቶብስና የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቶች ይገኙባቸዋል፡፡

በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎቶች ተብለው የተለዩት የአየር መንገድ አገልግሎት፣ የኤሌክትሪክ መብራት ኃይል፣ የውኃ አገልግሎት የሚሰጡና የከተማ ፅዳት የሚጠብቁ ድርጅቶች፣ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት፣ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች፣ የመድኃኒት ማከፋፈያ ድርጅቶችና የመድኃኒት መሸጫ ቤቶች፣ የእሳት አደጋ አገልግሎትና የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ናቸው፡፡

እነዚህን አስፈላጊ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ድርጅቶችን በመዝጋት ከሠራተኛው ጋር መደራደር አይቻልም፡፡ ሠራተኞችም የተለያዩ መብቶቻቸውን ለማስከበር በማሰብ ሥራ ማቆም አይችሉም፡፡

የሥራ ማቆም መብት ላይ ገደብ የተጣለባቸውን የሥራ ዘርፎች ሕገ መንግሥቱን፣ ዓለም አቀፋዊ ልማድና አሠራሩን፣ እንዲሁም የተለያዩ አገሮችን ተሞክሮ ላይ በመመርኮዝ ፍተሻ ይደረጋል፡፡ ፍተሻው ከእነዚህ ሕግጋት፣ ተሞክሮና ልማዶች አንፃር መስማማት ወይም አለመስማማታቸውን ማሳየት ነው፡፡ ከዚያም ሊሻል የሚችለውን መንገድ ማመላከት ነው፡፡

የአስፈላጊ አገልግሎቶች ትርጉም

ሥራ የማቆም መብትን የዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ ስምንት ላይ ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡ ይሁንና መብቱ ተግባራዊ የሚደረገው ከየአገሮቹ ሕግጋት ጋር በተጣጣመ መልኩ ወይም በሚፈቅዱት ሁኔታ መሆን እንዳለበት ይኼው አንቀጽ ይናገራል፡፡ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅትም የሥራ ማቆም መሠረታዊ የሠራተኞች መብት በመሆኑ ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ በማቋቋሚያ ሕጉና በሌሎች ስምምነቶችና አስተያየቶች ላይ አካትቶታል፡፡

ይሁንና አንዳንድ የሥራ ዘርፎችና አገልግሎቶች ለኅብረተሰቡ በጣም አስፈላጊ  በመሆናቸው ሠራተኞች የሥራ ማቆም መብታቸውን ዕውቅናና ጥበቃን በሚመለከት መንግሥታት ባይፈቅዱ የማያስወቅስ መሆኑን አምኖበታል፡፡ አሠሪዎችም፣ ሠራተኞችም፣ መንግሥትም አንዳንድ የሥራ ዘርፎች ወይም የአገልግሎት ዓይነቶች ለኅብረተሰቡ በጣም አስፈላጊ ስለመሆናቸው መካካድ የለም፡፡ አለመስማማት የሚፈጠረው ምን ምን ዓይነት አገልግሎቶች በጣም አስፈላጊ ናቸው የሚለው ላይ ነው፡፡ አገሮችም መንግሥታዊ ፖሊሲያቸው ላይ በመመሥረት የትኞቹ በጣም አስፈላጊ እንደሆኑ ይለያሉ፡፡

የየአገሮቹ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፖሊሲዎች የመለያየት ዕድሉ ከፍ ያለ በመሆኑ አስፈላጊ የሚባሉትም አገልግሎቶች ተመሳሳይ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በምሳሌነት የኢትዮጵያን ፖሊሲ እንመልከት፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲነቱ እየተከተለ ያለው ርዕዮተ ዓለም ልማታዊ መንግሥት የሚባለውን ነው፡፡

እንደዚህ ዓይነት ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ አገሮች ከሠራተኛ ይልቅ ወደ አሠሪዎች ማጋደልን ለምደዋል፡፡ ለፋብሪካ ባለቤቶች፣ ለአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማበረታቻ ማድረግ፣ የተለያዩ ማትጊያዎችን መስጠት፣ ከልማታዊ መንግሥት ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም አስፈላጊ አገልግሎቶች በማለት የሚለዩዋቸው ብሎም የሥራ ማቆም መብትን የሚገድቡባቸዋው የሥራ መስኮች ሊበዙ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓታቸው የዳበረ፣ ሊበራል ዴሞክራሲና ገበያ መር ኢኮኖሚ የሚከተሉ አገሮች ደግሞ አስፈላጊ አገልግሎት የሚሏቸው በቁጥር ያንሳሉ፡፡ የሥራ ማቆም መብት ላይ የሚጥሉትም ገደብ ከይዘት አንፃር በጣም ጠባብ ነው፡፡    

አገሮች ሊኖራቸው የሚችለውን የፖሊሲ ልዩነት ከግንዛቤ በማስገባት ይመስላል አስፈላጊ አገልግሎት ለመባል መለኪያ ይሆን ዘንድ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ዝቅተኛ መሥፈርት አውጥቷል፡፡ በመሆኑም አስፈላጊ አገልግሎቶች የሚባሉት የትኞቹ እንደሆኑ በቅድሚያ እንመልከት፡፡ ለዚህም ይረዳን ዘንድ የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ሰነዶች የመጀመርያ እናድርጋቸው፡፡

ዓለም አቀፉ ድርጅት በመሥፈርትነት ያስቀመጠው ጠቅለል አድርጎ ነው፡፡ በመሆኑም በሕዝብ ላይ የሚከሰቱት አደጋዎች በሕይወት በጤንነትና በግላዊ ደኅንነት ጉዳት የሚያደርሱ ከሆነ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅትም ሠራተኞች የሥራ ማቆም መብታቸውን መንግሥት ሊከለክል እንደሚችል ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ይህ ነው እንደ መሥፈርት የተወሰደው፡፡

የአገልግሎቶቹ መቋረጥ ሕዝብን በጠቅላላው ወይም የተወሰነውን የሕዝብ ክፍል ሕይወት፣ ደኅንነት ወይም ጤና ለአደጋ የሚያጋልጥ ከሆነ አስፈላጊ አገልግሎት ሊባል እንደሚችል ስለመደራጃት ነፃነት ለዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት አስተያየታቸውን የሰጡት የባለሙያ ኮሚቴዎች ገልጸዋል፡፡

ኮሚቴው ስምንት ዘርፎችን ለይቶ አስቀምጧል፡፡ ይህ ማለት ግን በእነዚህ ብቻ የታጠረና ምንም ሌላ አገልግሎት አይጨመርም ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ ስምንት የሥራ/የአገልግሎት ዓይነቶችም የሆስፒታል፣ የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ የስልክ፣ ፖሊስና መከላከያ ሠራዊት፣ የእሳት አደጋ፣ የማረሚያ ቤትና የአየር ትራፊክ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች አስፈላጊ አገልግሎት እንደሆኑና እነዚህን አገልግሎቶች በሚሰጡ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችም የሥራ ማቆም መብታቸውን መንግሥት ሊገድብ እንደሚችል ይኼው የባለሙያዎች ኮሚቴ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ኮሚቴው አስፈላጊ አገልግሎቶችን ከመዘርዘር አልፎም አስፈላጊ ሊባሉ የማይችሉትንም ጨምሯል፡፡ አገሮች አስፈላጊ ያልሆኑትን እንደ አስፈላጊ የመውሰድ ልማድና አዝማሚያቸው ስላየለ ይመስላል ኮሚቴው አስፈላጊ ሊባሉ የማይችሉትንም በማሳያነት ያስቀመጠው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ፣ የባንክ፣ የትምህርትና ቆሻሻ አስወጋጅ (የከተማ ፅዳት)፣ የወደብ አገልግሎት ይገኙበታል፡፡

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይኼውም አንዳንዴ አስፈላጊ አገልግሎት አይደሉም የተባሉት አንዳንዴ አስፈላጊ የሚሆኑባቸው ጊዜያት ሊኖር መቻሉን ነው፡፡ ለምሳሌ የከተማ ፅዳት ረዘም ያለ ጊዜ ከተቋረጠ የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ መጣሉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለሆነም አገልግሎት መስጠቱ ሲቋረጥ የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ የማይጥል መሆን አለበት የሚለውን መለኪያ አያሟላም፡፡ ሙሉ በሙሉ የሥራ ማቆም መብትን ከመገደብ የቆይታ ጊዜንና ዝቅተኛውን አገልግሎት በሕግ ማስቀመጥ ይገባል ማለት እነዚህን ሁኔታዎች ለማጣጣም ነው፡፡

እንግዲህ እነዚህ ጉዳቶች የማይቀርና ከፍ ያለ ጉዳት (Imminent And Substantial Harm) ኅብረተሰቡ ላይ የሚያሳድሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው፡፡ ክልከላው ተገቢ እንዲሆን እስኪ በተለያዩ አገሮች የተደረጉ የሥራ ማቆሞችንና ያስከተሉትን ጉዳት በምሳሌ እንመልከታቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 አርጀንቲና ላይ ፖሊሶች ለሁለት ቀናት ደመወዝ እንዲጨመርላቸው ሥራ በማቆማቸው የንግድ ተቋማት በወሮበሎች ተመዘበሩ፡፡ ባለቤቶቹም ለመከላከል ሲሞክሩ የሞቱና የቆሰሉት በርካቶች ነበሩ፡፡ በዚሁ ዓመት አዲስ የወጣውን የትምህርት ፖሊሲ በመቃወም በሜክሲኮ ሲቲ ከአሥር ሺሕ በላይ የአንደኛ ደረጃ መምህራን ከሁለት ወራት በላይ ሥራ በማቆማቸው ተማሪዎች ከትምህርታቸው ተስተጓጎሉ፡፡

እንግሊዝና ዌልስም በዚሁ ዓመት የእሳት አደጋ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድርገው ነበር፡፡ ሥራ ሲቆም የሚከሰቱና የማይቀሩ አደጋዎች ካሉ፣ እንዲሁም የአደጋዎቹ መጠን ከፍ ያለ ሆኖ ኅብረተሰቡን ለአደጋ የሚዳርግ ከሆነ አስፈላጊ አገልግሎቶች ይባላሉ፡፡

እንግዲህ ማንኛውም አገር (መንግሥት ያለው) ቢያንስ የሕዝቡን ደኅንነትና ፀጥታ የመጠበቅ ዝቅተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ በአንፃሩ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ደግሞ መብቶቹ ላይ የሚኖሩት ገደቦች አነስተኛ ሆነው ጥቅሞቹን ለማስጠበቅ የተለያዩ ሰላማዊ ትግሎችንና ድርድሮችን ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ሁለቱን ለማመጣጠን የሚደረገው ጥረት በመካከሉ ሕዝብ ስለሚገኝ እንዳይጎዳ ለማድረግ ነው፡፡

አስፈላጊ አገልግሎቶችና ሕገ መንግሥቱ

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 42 ስለሠራተኞች መብት ዕውቅና ለመስጠትና ጥበቃ ለማድረግ የተደነገገ ነው፡፡ የመንግሥት ሠራተኞችንም ይሁን ሌሎችን ምን ዓይነት መብቶች ሊኖሯቸው እንደሚችሉ ጠቅለል በማድረግ አስቀምጧል፡፡ በፋብሪካም ሆነ በአገልግሎት ዘርፍ በተሠማሩ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች፣ የእርሻና የገጠር ሠራተኞች፣ እንዲሁም ከተወሰነ ኃላፊነት በታች የሚገኙና የሥራ ጠባያቸው የሚፈቅድላቸው የመንግሥት ሠራተኞችም ጭምር የሥራና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች እንዲሻሻልላቸው የመደራጀትና የመደራደር መብት አላቸው፡፡

እነዚህ ሠራተኞች ከመደራጀትና ከመደራደር ባለፈም ሥራ የማቆምም መብትም ጭምር ያካትታል፡፡ በእርግጥ የትኞቹ የመንግሥት የመደራጀት፣ የመደራደርና ሥራ ማቆም መብት እንደሚኖራቸው በሕግ እንደሚወሰን ተገልጿል፡፡ ከመንግሥት ሠራተኞች ውጪ የመደራጀት፣ የመደራደርና ሥራ የማቆም መብት ላይኖራቸው የሚችል ሠራተኞች ስለመኖሩ ሕገ መንግሥቱ ምንም ክፍተት አልተወም፡፡ አስፈላጊ አገልግሎቶች የሚባሉትም ከመንግሥት ሠራተኞች እንጂ፣ ከዚያ ውጭ የሆኑ የግል፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አይመለከትም፡፡

የሥራ ፀባያቸው የሚፈቅድላቸው የመንግሥት ሠራተኞች በማለት ነው፡፡ እነዚህን የሚገልጻቸው የሥራ ፀባያቸው በእነዚህን መብቶች ለመገልገል የማያስችላቸው ወይም መብቶቹና ሥራዎቹ አብረው የማይሄዱት የትኞቹ እንደሆኑ መለየት የሕግ አውጪው ተግባር ነው፡፡ በተጨማሪም የመንግሥት ሠራተኛ ሆነው እነዚህን መብቶች መጠቀም የማይችሉት ከየትኛው ዕርከን በታች (ለምሳሌ ከሚኒስትር ዴኤታ በታች፣ ከመሥሪያ ቤት ዋና ኃላፊና ምክትሎች፣ ወይም ማናጀሮች/ሥራ አስኪያጆች) የሚገኙት እንደሆኑ በሕግ የሚወሰን ነው፡፡ የሥራ ጠባይና ከተወሰነ ዕርከን በታች ተብለው የተገለጹት ለመንግሥት ሠራተኞች እንጂ ለሌላ አይመስልም፡፡

 ይሁን እንጂ በአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ደግሞ የሥራ መሪዎች እንደ አሠሪው ወኪሎች ስለሚወሰዱ እንዲህ ዓይነት ሠራተኞችም በሥራ ማቆም ውስጥም መሳተፍ የሚፈቀድላቸው ስለመሆኑ አጠራጣሪ ነው፡፡ የአሠሪው ወኪል ወይም እንደራሴ እንደሆኑ ስለሚቆጠሩ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁም ጭምር አይገዙም፡፡ ይልቁንም በፍትሐ ብሔር ሕጉ እንጂ!

 በሕገ መንግሥቱ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ላይ እንደተገለጸው ሌሎች ሕጎች በሚወጡበት ጊዜ እነዚህ መብቶች ሳይቀናነሱ ለመስከበር ሥርዓት የሚያሰፍኑ መሆን እንዳለባቸው ሠፍሯል፡፡ ስለሆነም በአዋጁ ላይ የተዘረዘሩት አስፈላጊ አገልግሎቶች ተብለው የተዘረዘሩትና በመንግሥት  የማይተዳደሩ ለሆኑት እነዚህን መብቶች ለመገደብ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የለም፡፡

አስፈላጊ አገልግሎቶች በአዋጁ

አሠሪዎቹም መዝጋት የማይችሉባቸው ሠራተኞቹም ሥራ ማቆምን የማይፈጽሙባቸው የሥራ ዘርፎች አዋጁ ላይ ተዘርዝረዋል፡፡ እንደውም አስፈላጊ አገልግሎት በማለት ብቻ ሳይቆጠብ እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎት ድርጅቶች የሚል ሐረግ ተጠቅሟል፡፡ በእነዚህ የሥራ መስኮች ላይ የተሠማሩ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የሥራና የኢኮኖሚ ሁኔታቸውን አሠሪው እንዲያሻሽልላቸው ሥራ በማቆም ወይም በማቀዝቀዝ ማስገደድ አይችሉም፡፡

እነዚህ ሥራ ማቆም የማይችሉት የመንግሥት ብቻ ሳይሆኑ የግልም ጭምር ናቸው፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች የሚለው በሲቪል ሰርቪስ ሕጉ የሚተዳደሩትን ብቻ ወይስ ደግሞ የመንግሥት ሠራተኛ ሆነው ነገር ግን በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁም የሚተዳደሩትን ይጨምራል የሚለው በራሱ ግርታ የሚፈጥር ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ የመንግሥትም ሆነው የሥራ ፀባያቸው መደራጀት፣ መደራደርና/ወይም ሥራ ማቆም የማይችሉትን በሕግ አስቀድሞ መለየት እንደሚያስፈልግ ከሕገ መንግሥቱ መረዳት ይቻላል፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ግን በዚህ መልኩ አልተለዩም፡፡

እስኪ እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎት ተብለው የተዘረዘሩትን እያንዳንዳቸውን እንመለከታቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንግሥት ቢሆንም እንኳን በተመሳሳይ በአገር ውስጥ በረራ አገልግሎት የሚሰጡ የግል ድርጅቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ መብቱ የተከለከለው ለመንግሥትም ለግልም ሳይል ሁሉንም ነው፡፡ የኤሌክትሪክ መብራት ኃይል ከማመንጨት ባለፈ ማሠራጨት የሚችለው መንግሥት ብቻ በመሆኑ ይኼንን በሚመለከት ያው የሥራ ፀባያቸው የማይፈቅድላቸው የመንግሥት ሠራተኞች በሚለው ሥር ሊካተቱ ይችላሉ፡፡

የውኃ አገልግሎትም እንደዚሁ ነው፡፡ የከተማ ፅዳት አገልግሎት የሚሰጡ የግልም የመንግሥትም ድርጅቶችም ቢኖሩም ክልከላው ሁሉንም ነው፡፡ አስፈላጊ ስለመሆኑ ብሎም የፅዳት አገልግሎቱ አለመሰጠቱ የሕዝብ ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

የከተማ አውቶብስ አገልግሎትም ቢሆን የግልም የመንግሥትም መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ከታክሲ ነጥሎ መከልከል ብዙም አሳማኝ አይደለም፡፡ አንደኛ ነገር ከአዲስ አበባ ከተማ በስተቀር የከተማ አውቶብስ የሚጠቀሙ ከተሞች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ አውቶብሶቹ ራሳቸው በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እስከመኖራቸውም የሚረሳበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ አዲስ አበባም ጭምር ከአውቶብስ ያልተናነሰ እንዲያውም በላቀ ሁኔታ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት ታክሲዎች ናቸው፡፡ በየክልሎቹ ደግሞ ታክሲና ባጃጅ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ መብት የተነፈጋቸው የከተማ አውቶብስ ብቻ ናቸው፡፡ የአገር አቋራጮችንም አይመለከትም፡፡ ከአስፈላጊነት አንፃር ቢለካ የአዲስ አበባ አውቶብሶች አገልግሎት ከሚያቆሙ በመላው ኢትዮጵያ የአገር አቋራጭና የጭነት አገልግሎት መስጠታቸውን ቢያቆሙ ጫናውና ጉዳቱ ከፍ ያለ እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው፡፡

የሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች፣ የመድኃኒት ማከፋፈያ ድርጅቶችና መሸጫ ቤቶችም እንዲሁ የመንግሥትም የግልም ናቸው፡፡ እነዚህም ተቋማት የሥራ ማቆም ማድረግ አይችሉም፡፡ በእርግጥ በተለይ በተናጠል የመድኃኒት መሸጫዎች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ይህ መብታቸው ላይ ገደብ መደረጉ ብዙም አሳማኝ ላይሆን ይቻላል፡፡ የእሳት አደጋ መከላከያ የመንግሥትም እጅግ በጣም አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎትም በመሆኑ ብዙም አከራካሪ ላይሆን ይችላል፡፡

ይሁን እንጂ ግራ የሚያጋባ ነገር የሚፈጠረው በግል ድርጅቶች/ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሠሩ የእሳት አደጋ መከላከል ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች ተነጥለው ይህ መብታቸው ይታገዳል ወይ የሚለው ነው፡፡ በአገራችን የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በብቸኝነት የሚሰጠው መንግሥት በመሆኑ አንደኛውን መሥፈርት ያሟላል፡፡

ከሙሉ ሥራ መዝጋት ባሻገር

ሦስት የሚያሳስቡ ነገሮችን እንጥቀስ፡፡ የመጀመርያው የሕገ መንግሥታዊነት ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎቶች ያልሆኑ ወይም ከአንዳንዶቹ በላቀ መልኩ አስፈላጊ የሆኑ እያሉ የተመረጡበት ሁኔታ ዘፈቀዳዊነት ይንፀባረቅበታል፡፡ ሦስተኛው ሙሉ በሙሉ ከሥራ መዝጋት ባለፈ ሌሎች አማራጮችን በሕጉ ውስጥ አለማካተትን ነው፡፡ እዚህ ላይ የምንመለከተው ሦስተኛውን ነው፡፡

ስለሥራ ማቆም ሲነሳ በአዋጁ ላይ የተሰጠው ትርጓሜ ሥራ ማቀዝቀዝንም ይጨምራል፡፡ ሙሉ በሙሉ ሥራ ሳያቆሙ ነገር ግን መቀነስን ይመለከታል፡፡ በመሆኑም አስፈላጊ የሚባሉት ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ከማቆም በመለስ ማቀዝቀዝን መፍቀድ ይቻላል፡፡ ማቀዝቀዝ ደግሞ ዝቅተኛውን አገልግሎት እየሰጡ መሆን አለበት፡፡ ዝቅተኛውን አገልግሎት በመስጠት የሥራ መቆም አድማ ማድረግ ይቻላል፡፡

ሥራ ማቆም ድንገተኛ ካልሆነ

አዋጁ ላይ እንደተገለጸው ሠራተኞች ሥራ ከማቆማቸው በፊት ሊፈጽሟቸው የሚገባቸው ሒደቶች አሉ፡፡ ማስጠንቀቂያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች በስምምነት ለመጨረስ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከሠራተኛው ማኅበር አባላት ውስጥ ቢያንስ ከሦስት እጁ ሁለቱ በስብሳባ ተገኝተው ከእነዚህ ውስጥ አብላጫው የሥራ ማቆሙን ሊደግፈው ይገባል፡፡

ለሥራ ክርክር ቦርድ ወይም ለፍርድ ቤት ጉዳዩ ከቀረበ ደግሞ ውሳኔ ከመሰጠቱ ከ30 ቀናት በፊት የሥራ ማቆም ዕርምጃ መውሰድ አይቻልም፡፡ እነዚህ ሒደቶች ሳያሟጥጡ ሥራ ማቆም ስለማይቻልና ለድርድርም ጊዜ ስለሚሰጥ ድንገተኛ ስለማይሆን አገልግሎቶቹን እንዳይቋረጡ አስቀድሞ መፍትሔ ለመዘየድ ያስችላል፡፡ ስለሆነም በተለይ አንዳንዶቹ አስፈላጊ አገልግሎቶች የተባሉት በእነዚህ ሒደቶች ውስጥ ስለሚያልፉ በድንገት ሕዝቡን አደጋ ላይ አይጥሉም፡፡

ዝቅተኛ አገልግሎቶችን በመግለጽ የሥራ ማቆምን ማስከበር ይቻላል፡፡ ሙሉ በሙሉ ሳያስቀሩም ሳይፈቅዱም ይህንን መብት ለሠራተኞች እንዲከበርላቸው ማድረግ ይቻላል፡፡ የበርካታ አገሮች ልምድም ይኼንኑ ነው የሚያሳየው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...