በአያሌው አስረስ
የማይጨው ጦርነት የተካሄደው ከ82 ዓመታት በፊት መጋቢት 22 ቀን 1928 ዓ.ም. ነው፡፡ ማይጨው በስተስሜን በተያያዘ የተራራ ሰንሰለቶች የተከበበ ሲሆን፣ ሌላው አካባቢ ወጣ ገባና ሜዳማ ነው፡፡ አሁን የማይጨው ከተማና የማይጨው ዩኒቨርሲቲ አርፈውበት ይገኛል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ‹‹ሕይወቴና የኢትዮጵያ ዕርምጃ›› በተባለው አንደኛ መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ጦሩ ወደ ውጊያ የገባው በአራት ክፍል ተመድቦ ነው፡፡ የመጀመርያው ምድብ መሪ ራሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ ሲሆኑ፣ በእሳቸው ሥር ቀኛዝማች መኩሪያ ባንት ይርጉ፣ ግራዝማች (ኮሎኔል) ክፍሌ እርገቱ፣ ግራዝማች አበራ ግዛውና ሌሎችም የሚገኙ ሲሆን፣ ደጃዝማች አደፍርሰው (በኋላ ራስ) በደጀንነት ተሠለፉ፡፡
በግራ ክንፍ የዘመተው ጦር መሪ ራስ ጌታቸው ሆነው በእሳቸው ሥር ደግሞ የከምባታ፣ የዕቃ ቤትና የገንዘብ ሚኒስቴር ጦር የተሠለፈ ሲሆን፣ በቀኛዝማች ተክለ ማርቆስ ወልደ ገብርኤል የሚታዘዘው ጦር በዚሁ ምድብ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ጦሩ የሚንቀሳቀስባቸውን መስመሮች የሚያመለክቱና የሚመሩት ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ሆኑ፡፡
በቀኝ የጦሩ መሪ ራስ ሥዩም መንገሻ ሲሆኑ፣ በእሳቸው ዕዝ ውስጥም ሰናድር ያዥ፣ የወለጋ ጦር፣ የሊቀ መኳስ ወልደ ገብርኤል ጭፍራና በቀኛዝማች ወልደ ዮሐንስ የሚመራ የመድፈኛ ጦር ተመድቦለታል፡፡ ለዚሁ ጦር መንገድ መሪነት ፊታውራሪ ተድላ አበራ ተሰጥተዋል፡፡
ራስ ካሳ ኃይሉ (በዚህ ጊዜ የጦር ሚኒስትር ሆነዋል) የመሀሉ የጦር መሪ የተደረጉ ሲሆን፣ በእሳቸው ሥርም ራስ ከበደ መንገሻ፣ በሊጋባ ዋለሉ የሚመራው የመሀል ሰፋሪ ጦርና ሌሎችም የተመደቡ ሲሆን፣ የጦሩ መንገድ መሪ የማይጨው አገረ ገዥ ደጃዝማች አበራ ተድላ ነበሩ፡፡
‹‹ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ከወለወል እስከ ጎንደር›› የተባለው መጽሐፍ ደራሲ ተድላ ዘዮሐንስ ሠራዊቱ በዚህ መልክ ከተደለደለ በኋላ ጦርነቱን መቼ እንግጠም የሚለው ጥያቄ ማስቸገሩን፣ የጦር መሪዎቹ ሠራዊታችን አልተከተለንም በሚል ምክንያት ማብዛታቸውን አስመልክቶ አታዮ ላይ መጋቢት 19 ቀን በተደረገ ስብሰባ ጦርነቱን ከሁለት ቀን በኋላ በ21 ለማድረግ ተወስኖ እንደነበር ያስረዳል፡፡
ንጉሡ ከመጋቢት 16 እስከ 19 ቀን በቆዩበት ጊዜ ሠራዊቱ በውጊያ ጊዜ መከተል ያለበትን ሥነ ሥርዓት በዝርዝር መስጠታቸው ሲታወስ፣ አደጋ የሚያስከትል ሆኖ እስካልተገኘ ድረስ ምርኮኛን አለመግደል፣ ቁስለኛ አነሳለሁ ወይም ግዳይ እጥላለሁ ብሎ ወደ ኋላ መመለስ ውጊያ ላይ ያለውን የወገን ጦር ለጥቃት የሚዳርግ በመሆኑ ፊትን አለማዞር፣ በጦርነቱ ላይ የተገኘን ንብረት ለመዝረፍ አለመጣደፍ፣ ጠላት የሸሸ መስሎ ሲያፈገፍግ፣ ግራና ቀኝ በተጠመደ መትረየስ ውስጥ ሊያስገባ ስለሚችል መጠንቀቅ ከተሰጡት መመርያዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ሆኖም በጦርነቱ ወቅት ወታደሩ ፉከራውን እየሰማ ምርኮውን ለማሳየትና በንጉሡ ፊት ለመፎከር ወደ ኋላ ይመለስ እንደነበር በወቅቱ ተዘግቧል፡፡
ለመጋቢት 21 ቀን ታስቦ የነበረው ውጊያ መሰረዙ ሌሊት 11 ሰዓት ላይ ተነገረ፡፡ የንጉሡን የስልክ ግንኙነቶች እየጠለፉ መረጃ የሚያገኙት ጣሊያኖች ይህን ቀን የኢትዮጵያ ጦር በሰፈረበት ቦታ ላይ በቦምብ ለመደብደብ ተጠቀሙበት፡፡ እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ጣሊያኖች ለረዥም ጊዜ ባካሄዱት የስለላ ሥራ እጅግ ብዙ መረጃ አቀባዮች አደራጅተው እነሱም በከፍተኛ ደረጃ መጠቀማቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ወገን የጦርነቱ መዘግየት ያማረረው አንድ ወታደር ወደ ጣሊያኖች ሄዶ ‹‹ሐበሾች ሊወጉዋችሁ ተዘጋጅተዋል›› ብሎ እንደ ነገራቸው ሁሉ፣ ለንጉሡ የጦር መሪዎችም ተመሳሳይ መረጃ በመስጠት ለሁለቱም የሰጠውን ምልክት የጥይት ድምፅ በማሰማት ጦርነቱን እንዳይጀመር እንዳደረገው ታሪክ ይናገራል፡፡
ጦርነቱ ከመጀመሩ ከሁለት ቀናት በፊት ‹‹ድል እናደርጋለን ካልሆነም እንሞታለን›› ብለው የተማማሉት ‹‹የአርበኞች ጀብዱ›› በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ የተተረጎመው መጽሐፍ ጸሐፊ ጆሴፍ ፐርስ፣ ‹‹በመትረየስ ጥይት መሀል የሚርመሰመሱ›› ሲሉ የገለጣቸው ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን ምሽግ ለመወርወር ተሯሯጡ፡፡ ከጠዋት ሁለት ሰዓት ጀምረው ጣሊያኖች ከሰማይ በሚያወርዱባቸው ቦምብና የመርዝ ጋዝ፣ በምድር ላያቸው ላይ በሚፈሰው የመትረየስና የመድፍ ጥቃት ሳይበገሩ የሞተና የቆሰለ ወገናቸውን እየተራመዱ፣ የጠላታቸውን አንገት በሰይፍ እየቀሉ እጁን እየጎመዱ ወደ ፊት ገሰገሱ፡፡
ያላቸውን የናስ ማስርና የውጅግራ ጥይት እየቆጠቡ የሚተኩሱት ኢትዮጵያውያን ታንኩን ተጠግተው በመስኮት እያስገቡ እየተኮሱ፣ ብዙውን ባለበት እንዲቆም ከማድረጋቸው በላይ በማቃጠልም ከጥቅም ውጪ አደረጉ፡፡
የጥቁር ወታደሮች ብርጌድ አዛዥ ፔርዚዮ በሮሌ ‹‹ሐበሾች ይህን የሽቦ አጥር አልፈው ያጠቁናል ብላችሁ አታስቡ›› ሲል የተመካበት ምሽግ ተሰበረ፣ የሰባተኛው ብርጌድ አዛዥ ተገደለ፡፡ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥም የ24ኛው ብርጌድ አዛዥ ተገደለ፡፡
ከሐረር ጦር ትምህርት ቤት የወጡ መድፈኞች የጣሊያንን ስምንተኛ መድፈኛ ባታሊየን ጨረሱት፡፡ የክብር ዘበኛ ወታደሮች በሽፋን ተኩስ ተከልለው በመጠጋት አሥረኛውን ባታሊዮን በመግደልና በማቁሰል ከጥቅም ውጪ አደረጉት፡፡ የባታሊዮኑን አዛዥ ዘረቲኒና ኮሎኔል ሩጂሮ ገደሉ፡፡ የማዘዣ ቦታውን የተረከበው ለጄኔራል ዳልሜዝ ‹‹አሁን እዚህ ቦታ የሚታኮሰው የቆሰለ ሠራዊት ብቻ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ሁላችንም እንሞታለን፡፡፡ እስክንሞት መታኮሳችንን እንቀጥላለን፤›› በማለት ማስተላለፉን ጳውሎስ ኞኞ ‹‹የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት›› በተባለው መጽሐፉ ምንጭ ጠቅሶ ያስረዳል፡፡
ጣሊያኖች በግንዲላና በድንጋይ ካብ የገነቡትና እንዳይደረስበት በሽቦ አጥር መከላከል የፈለጉት ምሽግ ተጣሰ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ወደ ስድስት ምሽጎች አስለቀቁ፡፡ ድል የኢትዮጵያውያን ለመሆን ተቃረበች፡፡ ዓድዋ የሚደገም ቢመስልም ግን አልሆነም፡፡
‹‹የሐበሻ ጀብዱ›› ጸሐፊ አዶልፍ ፓርላስካ ሁኔታውን፣ ‹‹የሦስቱ ራሶች ጦር የጦሊያንን ምሽግ ሰብሮ ገባ፡፡ ድል በኢትዮጵያውያን እጅ የገባች መሰለች፡፡ በዚህ ቅፅበት ደግሞ ዓድዋ ሊደገም የሰዓታት ልዩነት ሲቀረው፣ እነዚያ ከሃዲዎች ራያና አዘቦዎች ድል በእጅ ሊያስገባ የተቃረበውን ወንድማቸውን ከጀርባ ገብተው ጨፈጨፉት፡፡ ድልን በእጅ ሊጨብጥ ወደፊት የገሰገሰውን የእናታቸውን ልጅ ድል ነሱት፤›› በማለት ገልጦታል፡፡ ይኼንኑ ሁኔታ ‹‹የአርበኞች ጀብዱ›› የተባለው መጽሐፍ ጸሐፊ ጆሴፍ ፐርስ ‹‹የውርደት ትርዒት ታየ›› ብሎታል፡፡
ንጉሡ በዚህ ጦርነት አንደ አንድ ወታደር የተዋጉ መሆናቸውን ዛሬም የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ ጦርነቱ እስከ ሌሊቱ አምስት ሰዓት ቢቀጥልም አሸናፊነቱ አልተገኘም፡፡ ኢትዮጵያ ድል ሆነች፡፡ ከዚህ በኋላ የተያዙት ዕቅዶች እየከሸፉ፣ ምንም ዓይነት ሙከራ ሳይደረግ ንጉሡ በጭንቅ በመከራ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ በኋላም ተሰደዱ፡፡ ጣሊያን በወር ውስጥ አዲስ አበባን ይዞ በኢትዮጵያ ለአምስት ዓመት የቅኝ ግዛት አስተዳደር መሠረተ፡፡
ከነፃነት በኋላ በ1942 ዓ.ም. አፄ ኃይለ ሥላሴ በማይጨው ከተማ በጦርነቱ የወደቁ ወገኖች አፅም እንዲሰባሰብ አድርገው የመታሰቢያ ሐውልት አቆሙላቸው፡፡ አሁን አጥሩ ተነቃንቋል፡፡ ለምልክት የተረፈች አንድ የዕብነ በረድ ድንጋይ ትገኛለች፡፡ ሐውልቱ ላይ የነበረው የዙፋን ቅርፅ በግማሽ ከመቦደሱም በላይ ሐውልቱም በጣም ተጎድቷል፡፡ በአጠገቡ የሚታየው ቋጥኝ ለልማት ተብሎ ተቆፍሮ የወጣ ነው፡፡ ከእነ አካቴው ከመፍረስ ያዳነው የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጩኸት መሆኑን ኃላፊዋ ወ/ሮ ፀሐይነሽ ንጉሤ ባለፈው ወር አካባቢውን በጎበኘሁበት ጊዜ ገልጸውልኛል፡፡ የሰማዕታት አፅም የበሚገኘው ማይጨው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ለመጎብኘት ያለው ፍዳ ግን አይጣል፡፡
ድሮ አፅሙ መሀል ከተማ ውስጥ እያለ በየዓመቱ ቤተ ክርስቲያኗ ፀሎተ ፍትሐት ታደርስ ነበር፡፡ ሕዝብ ተሰብሶቦ ዕለቱን ያስብ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ አሁን አሁን እየቀነሰ መጥቷል፣ ተረስቷል ተብሏል፡፡
የማይጨው ከተማ ነዋሪዎች ይህን ቀን የሐዘን ቀን አድርገው ለማሰብ አንድ መርሐ ግብር ቢያዘጋጁ ለከተማዋ ውሎ ሲያድር መታወቂያ ሊሆናት ይችላል፡፡ አፄ ምንሊክ ዓድዋ ጦር ሜዳ ላይ ለብሰውት የዋሉትን የክብር ልብስ ለማይጨው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ሰጥተውት የሚገኘውም እዚያ ነው፡፡ እኔ ግን ለማየት ጊዜ አላገኘሁም፡፡
ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች በአካባቢያቸው ታሪክና የተፈጥሮ ሀብት፣ ማኅበራዊ ሁኔታ ላይ በርካታ ሥራዎች እያከናወኑ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የማይጨው ዩኒቨርሲቲ፣ የማይጨውን ጦርነትና የጦር ሜዳ አንድ ሥራ አድርጎ ቢይዘው መልካም ነው፡፡ ስለነፃነት የወደቁ ወገኖችንም ከመረሳት ይታደጋቸዋል፡፡ በንጉሡ ላይ የተዘራውና ቀንድ ያወጣው ጥላቻ ዓይኑን እስካልጋረደው ድረስ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡