Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትኢወገናዊ በሆኑ ተቋማት ላይ ዴሞክራሲን መገንባት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ግዳጅ ነው

ኢወገናዊ በሆኑ ተቋማት ላይ ዴሞክራሲን መገንባት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ግዳጅ ነው

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የኢሕአዴግ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› መከራውን ሲያይ፣ ሲታሽ፣ ሲተሻሽ፣ ብቅ ጥልቅ፣ ብልጭ ድርግም፣ ሲል ቆይቶ ባልተለመደና ከራሱ ከድርጅቱ ፈቃድና ዕቅድ ውጪ የዶ/ር ዓብይን የአመራር ዘመን አስጀምሯል፡፡ ገና አንድ ወሩን ሚያዝያ መጨረሻ ላይ የሞላው የዓብይ ዘመን የአገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ችግር የሆኑትን መሟላት የሚገባቸውን፣ ብዙዎችም የሚፈልጓቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ይፋ አድርጓል፡፡ ዶ/ር ዓብይ ከተናገሯቸውና ከጠቋቆሟቸው የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ቆልፈው ከያዙት ችግሮች መካከል አንዱ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆኑ ተቋማት አለመኖር ነው፡፡ የአቶ ዓብይ ዘመን ተስፋና ትርጉም ባለው ንግግርና ዕይታ ቢጀምርም፣ በብዙ የሕዝብ ድጋፍ ቢታጀብም፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እወስደዋለሁ ያሉትና የወሰዱት ኃላፊነት በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥ ጭምር አኩራፊዎች፣ ተጠራጣሪዎች፣ ተቀናቃኞች ያሉበት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ዴሞክራሲን የማጥለቅ የችግሩ ስፋትና ክፋት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ሥር መሠረት የለውና አንዳንዱም ዕድሜ ለዶ/ር ዓብይ እንጂ አደባባይ የማይነገር ጭምር ነበር፡፡

የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በገዥው ክፍልና በሥልጣን ማስከበሪያው የታጠቀ ኃይል ትስስር ላይ የቆመ ነው፡፡ የመንግሥትም የደፋ ቀና ጉዞ ከታጠቀ ኃይልና ከተመላኪነት ጋር የተያያዘ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የታጠቀውን ኃይል መቆጣጠር ሲሳነውና የንጉሡ ተመላኪነት ሲቦተረፍ በወታደራዊ ግልበጣ ተወገደ፡፡ ወታደሩንና ሕዝቡን በዚህም በዚያም አፍዝዞ የአንድ ሰው ተመላኪነትና አምባገነንነት እንዲሆን ያደረገው ደርግ ብሎ ብሎ የወደቀው፣ በአመለካከቱ የቀረፀውን የወታደርና የደኅንነት ኃይል ታማኙ አድርጎ ማንቀሳቀስ ሲሳነው ነው፡፡ ደርግን የተካው ኢሕአዴግም ለወግና ለወሬ ያህል ብቻ ሳይሆን በሕገ መንግሥቱም ስለ ሲቪል መከላከያ ግንኙነት ቢናገርም (አንቀጽ 87)፣ የሥልጣኑን መሠረት የጣለው የደርግን ሠራዊትና የደኅንነት መረብ አፍርሶ በራሱ ሠራዊት ላይ የተማከለ የሥልጣን ማስከበሪያ አውታር በማቋቋም ነው፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለማይከሰስና ከሰማይ ለተሰጠ ፍፁማዊ ገዥነት መሣሪያ የሆነ አውታረ መንግሥት እንደገነቡ ሁሉ፣ የደርጉ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም የራሱን ተመላኪነትና ተቆጣጣሪነት በኢሠፓ መረቡ አማካይነት በኅብረተሰቡ ላይ እንዳዋቀረው ዓይነት ኢሕአዴግ መጥቶም በግል፣ በቡድን፣ በፓርቲ አምሳል የመቅረፅ ታሪክንና ተግባርን አላስቆመም፡፡ ገና ወደ ሥልጣን እንደመጣ የነበረውን የአገዛዝ (የደኅንነትና የጦር አውታር) ፍርሶ የራሱን ታጋዮች አከርካሪው ያደረገ ግንባታ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያካሄደው ለውጥ፣ ከፓርቲ ነፃ የሆነ መንግሥታዊ የአገዛዝ አውታርን ዕውንና ተጨባጭ እንዳያደርግ ሰንክሎ ይዞናል፡፡ የአገሪቱ ደኅንነትና መከላከያ ዛሬም ከኢሕአዴግ ጋር ከተሳሰረ አመጣጡ አልተላቀቀም፡፡ አልተላቀቀም ብቻ ሳይሆን የአገር ደኅንነት ጉዳይ ሆኖ በቋሚነትና በዘላቂነት የሚሠራበት ሥራ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ያን ያህል ደግሞ በይፋ የማይነገር ከንግግር በላይ፣ ንግግር የማይደፍረው ጉዳይ ሆኖም ኖሯል፡፡

የዴሞክራሲ ሥርዓተ መንግሥት ህልውና የግድ የየትኛውም ፓርቲ ይዞታ ያልሆነ ዓምደ መንግሥት ማደራጀትን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ በጭራሽ ተነጥሎ አይታይም፡፡ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተስፋ ከደርግ ውድቀት በኋላም መውጫ የሌለው ጎሬ ውስጥ የተቀረቀረው፣ ምርጫን የባለ ብዙ ፓርቲ ሥርዓትን ቢያንስ ቢያንስ በሕግ ያስተዋወቀው ፓርቲ የራሱን ሠራዊት የሽግግሩ መንግሥት የመከላከያ ኃይል አድርጎ ባቋቋመበት ጊዜና ከዚያ ጀምሮ ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ በመከላከያው ውስጥ ብዙ ለውጥ የተደረገ፣ በተለይም የፖሊስና የመመከላከያ ሠራዊቱ ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጣ ገጽታ ያለው መሆኑ ቢያጠራጥርም ዛሬም የተቋማቱ ኅብለ ሰረሰር ኢሕአዴግ ነው፡፡

ለመከላከያና ለፀጥታ ኃይል የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆንና የፓርቲ ሥራ ማካሄድ በሕግ የተከለከለ ይሁን እንጂ፣ አውታሩ እንዳለ ቢያንስ በገዥው ፓርቲ አመለካከት የተጠረዘ መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ እርግጥ ነው እውነቱን በሙሉና የውስጥ ዝርዝሩን በሙሉ መናገር አይችልም፡፡ ነገር ግን ጠቅላላ ኅብረተሰቡን በሙሉ በአንድ የኢሕአዴግ አመለካከት ለመጠረዝ የሚለፋ ገዥ ቡድን ዋናው የሥልጣን መሣሪያው ላይ የበለጠ ትኩረት ከማድረግ እንደማይመለስ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ከሎጂካዊ ግምት ያለፉ ነፀብራቆችን ማስቀመጥም ይቻላል፡፡ ‹‹ሥርዓቱን/ሕገ መንግሥቱን የመጠበቅ ኃላፊነት››፣ ‹‹የአገሪቱን ሰላም ከውጭ ጠላት ከፀረ ሰላሞችና ከአሸባሪዎች መጠበቅ››፣ ለዚህም በየጊዜው የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታዎች ማስገንዘብ የኢሕአዴጋዊ አጠባ ግልጽ መንገዶች ናቸው፡፡ በሠራዊቱ ውስጥ የኢንዶክትሪኔሽን መምርያ/ዳይሬክቶሬት አለ ማለት ብዙ ይናገራል፡፡

ከመከላከያና ከፀጥታ ውጪ ያሉት መንግሥታዊ አውታራትም በጠቅላላ በኢሕአዴግና በአጋር ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች የተዋጡ ናቸው፡፡ የአገሪቷን መንግሥታዊ አውታራት ከገዥው ፓርቲ መለየት እስኪያቅት ድረስ የተንሠራፋው የኢሕአዴግ የአንድ ብቻ ፓርቲ የ27 ዓመታት አገዛዝ፣ የመንግሥና የፓርቲ ተግባራትና እንቅስቃሴዎችን መቀላቀል እንዲሁ ‹‹ለአዋጁ ያህል››፣ ለይስሙላ ሲል እንኳን አላውቅበት ብሏል፡፡ ማስመሰል እንኳን አቅቶታል፡፡ በአንድ ወቅት ማለትም በሪፐብሊኩ መመሥረት ሰሞን እነ ጄኔራል ፃድቃንን የመሳሰሉ ጄኔራል መኮንኖች ከፓርቲው/ከኢሕአዴግ አባልነት በክብርና በይፋ ሲሰናበቱ ታዝበናል፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ጄኔራል ፃድቃን ራሳቸው ጋዜጠኛ የሆነ ጥያቄ ሲያነሳላቸው ‹ይህን ጥያቄ መመለስ የሚችሉት ፖለቲከኞች ናቸው፣ እኔ ወታደር ነኝ የእኔ ድርሻ የሲቪል ፖለቲከኞችን ውሳኔ ማስፈጸም ነው› ሲሉም ሰምተናል፡፡ ዛሬ ከ27 ዓመት ‹‹ምራቁን የዋጠ›› ፖለቲካና ዴሞክራሲ በኋላ እነ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊነታቸው የመንግሥት ‹‹ዕውቅ›› ቃል አቀባይ ሆነውም መልስ ሲሰጡ እናያለን፡፡ የተመሠረተው ሥርዓት በሲቪል ሰርቪሱና በፖለቲካ ተሿሚዎች መካከል ልዩነት አያውቅም፡፡ በድርጅታዊ ሰንሰለቱ በየማኅበራቱ፣ በየተቋማቱ የተሠረጫጨው የአንድ ለአምስት አደረጃጀትን ከሠፈር እስከ ሲቪል ሰርቪስ ድረስ የዘረጋው የቤተሰብ ፖሊስ ተጠሪ እስከ ማቋቋም ድረስ ማን ከልካይ አለብን ያለው ኢሕአዴግ፣ በስብሰባና በሕዝብ መገናኛ ዘዴዎች የሚናኝ የ‹‹አብዮታዊ  ዴሞክራሲ››ን (የኢሕአዴግን ገዥነት) መተኪያ የለሽ የሚያደርግ፣ ተቃዋሚዎችን ‹‹ቀልባሽ፣ ሕገ መንግሥት አፍራሽ፣ የሰላምና የሕዝብ ፀር›› አድርጎ የሳለ አመለካከትና ፕሮፓጋንዳ ‹‹የመንግሥት ፖሊሲ›› አድርጎ አውጇል፡፡ ዛሬ ‹‹ልማታዊ ዴሞክራሲ››፣ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የሚባሉ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የማይታወቁ ሐሳቦች የሁሉም፣ የፓርቲም፣ የመንግሥትም ባለሥልጣናት አፍ ማሟሻ ሆነው የምንሰማው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

እናም ዶ/ር ዓብይ አህመድ ‹‹የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚያስጠብቁ የአገር ኩራትና መመኪያ . . . ›› እንዲሆኑ እንሠራለን፣ ‹‹የዴሞክራሲ ተቋማት ተጠናክረው ከወገንተኝነት ፀድተው ሕዝባዊ ተዓማኒነታቸው እንዲጎለብት መወሰድ ያለባቸው ቁልፍ ዕርምጃዎች በጥናት ላይ ተመሥርተን፤›› እንወስዳለን ሲሉ አዲስ ነገር የሆነብን በዚህ ምክንያት ነው፡፡ አዲስ ነገር ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት የማይደፈር፣ እንደ ክህደት የሚቆጠር አደገኛም የሚያስጠቃም ነበር፡፡ ይህንን በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ‹‹ክፉ ዓይን›› ውስጥ ያስገባ የነበረ ጉዳይ የመንግሥትና የሕዝብ አጀንዳ ማድረግና በተለይም ከፖለቲካ ወገንተኛነት እናፀዳለን ማለት የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ሕመም ማወቅ ያህል ወሳኝና ከፍተኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕመም ዴሞክራሲን ኢወገናዊ በሆኑ ተቋማት ላይ ማቋቋም አለመቻላችን ነውና፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሐዋሳ ጉብኝታቸው እግረ መንገዳቸውንና በአጋጣሚ ስለ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ‹‹የምሥጋና ፕሮግራም›› በሰጡት ማብራሪያ ውስጥ ያነሱት አንድ ጉዳይ፣ የአገራችንን የሥር የመሠረት ችግር የሚያመለክትና እሱም ላይ እንድንረባረብ የሚያስገድድ ነው፡፡ ‹‹ያ ፕሮግራም . . . ›› አሉ ዶ/ር ዓብይ በአቶ ኃይለ ማርያም ሽኝትና ሽልማት ላይ ጥያቄ ላነሱትና ተቃውሞ ላሰሙት ወገኖች መልስ ሲሰጡ፣ ‹‹ያ ፕሮግራም የኃይለ ማርያም ፕሮግራም አልነበረም፡፡ ያ ፕሮግራም አሁን ሥልጣን ላይ ተቀምጠን ሥልጣን መልቀቀ የሞት የሽረት ነው ብለን ለምንቸገር ሰዎች አትቸገሩ፣ በሰላም ከለቀቃችሁ መንግሥትም ሕዝብም ያከብራችኋል የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ፈልገን ነው፡፡››

ዝርዝሩ ውስጥ አልገባም እንጂ ጥያቄውም፣ ተቃውሞውም፣ መልሱም አገራችን ‹‹የቸገረ ነገር የጠፋ ለመላ!›› የሚባል ቁጭ ብሎ መምከርን፣ በአንድ ወይም በሌላ ፓርቲ ብቻ መፈታት የማይፈቅድ ውስብስብ ችግር ያለባት መሆኑን ያመላክታል፡፡ የኢፌዴሪ ሁለተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹በገዛ ፈቃዳቸው››፣ ‹‹የመፍትሔው አካል ለመሆን›› ሥልጣን መልቀቃቸው ሚስጥር ሆኖ መቅረቱ ራሱ ገና ያልተነካው የሥር የመሠረት ችግራችን ማሳያ ነው፡፡ በአንድ የፓርቲ አገዛዝ ውስጥ፣ በአንድ የምርጫ ዘመን ውስጥ፣ የአንድ ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆነ የሌላ ባለሥልጣን ከሥልጣን የመልቀቅ ጉዳይ እንዲህ እንደ ውጭ ኢንቨስትመንት ‹ማበረታቻ› የሚጠይቅ፣ ዋስትናም የሚፈልግ መሆኑ ትልቁንና ዋናውን ችግር እንዳያዘናጋን፣ ዶ/ር ዓብይ ያነሱትን ችግርም ጥልቀት እንዳይሸፍንብን ልብ መባል ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡   

በኢሕአዴግ ውስጥ ከኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ዓብይ አህመድ የተላለፈው የሥልጣን ሽግግር የምናውቀውን ያህል ይህን ያህል ካስቸገረ፣ ከአንድ ፓርቲ ወደ ሌላ ፓርቲ ስለሚደረግ የሥልጣን ሽግግር ለማውራት ኢትዮጵያ እጅግ በጣም ገና ገና ወደ ኋላ ነች፡፡ ችግሩ ብዙ ነው፡፡ በምዕራብ አገሮች እንደሚታየው፣ እዚህ አፍሪካ አኅጉር ውስጥም በናይጄሪያ፣ በጋና እንደታየው የትኛውም ፓርቲ ሥልጣን ላይ ወጣ ትርምስ ሳይፈጠር፣ መናጋት ሳይኖር የአገርና የሕዝብ የተረጋጋ ጉዞ የሚቀጥልበት ሁኔታ ለእኛ አገር በጣም ሩቅ ነው፡፡ የዶ/ር ዓብይ ዘመን ይህንን መንገድ ስለመጀመሩም የሚወስነው አሁንም በሕዝቡ ግፊትና በኢሕአዴግ ውስጥ ባለው የአዝማሚያ ኃይል አሠላለፍ ላይ ነው፡፡

እስካሁን ለ27 ዓመት እንዳየነው የኢሕአዴግ ገዥ ፓርቲነት በምርጫና በአማራጭ ፓርቲ የሚቀየር ስለመሆኑ እምነት የሚያሳድር ነገር በጭራሽ አልነበረም፡፡ የ2008 ዓ.ም. ወዲህ አመፅና የለውጥ አንቅስቃሴም ያመጣው (ለዚያውም ከ2007ቱ ‹ባለ አምስት ዘጠኝ ውጤት› ማለትም 99.999 በመቶ ማግሥት) ይኼው ችግር ነው፡፡ ብዙ ምክንያቶችና ዝርዝሮች አሉት፡፡ የመጀመርያው በአማራጭነት ኢሕአዴግን በምርጫ የሚፈታተን ብርቱ ፓርቲ አለመኖሩ ነው፡፡ ለዚህ ስላበቁን ኢሕአዴግም ተቃዋሚዎቹም ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ አሉ የሚባሉት ተቃዋሚዎች ተባብረው ቢመጡ እንኳ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወገናዊነት ነፃ የሆነ የምርጫ ውድድር ሜዳ የማግኘት ጉዳይ ሌላ ፈተና ነው፡፡ እዚህ የምርጫ ውድድሩ ሜዳና ምርጫ አስፈጻሚው ላይ ትንሽ ዘርዘር አድርገን ጉዳዩን እናንሳ፡፡ የመንግሥት አውታሮች ለኢሕአዴግ አዘንባይ ሆነው በመቀረፃቸውና በእንደዚያ ዓይነት ‹‹ሠራዊት›› የተሞሉ በመሆናቸው፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ ተቋም የማነፅና የመገንባት የዶ/ር ዓብይ አዲሱ ትልም ይህንን መሥሪያ ቤት ከዚህኛው የሚል ልዩነት የማያመጣ ነው፡፡ ብዙ ፓርቲዎች ኖረውም (ኑሮ ካሉት) ምርጫ እየተደረገም፣ በግል ጋዜጣም አሁን ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያውም ስንቱ ነገር እየተባለም ቢሆን የቀጠለው የኢሕአዴግ አገዛዝ በተፈጥሮው ለአንድ ፓርቲ አገዛዝ የታነፀ ነው፡፡

ሌላው ሌላው የመንግሥት ዘርፍ ሁሉ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ዘመም እንዲሆን፣ ይኼው ተዛነፍ እንዲጠናወተው አድርጎ ያነፀ ሥርዓት የምርጫ አስፈጻሚ አካላቱን ግን አይነካካቸውም ብለን እንድናምን የሚያደርግን ምንም ምክንያት የለም፡፡ እስከ ዛሬ በተካሄዱት ምርጫዎች ኢሕአዴግና አጋሮቹ አሸናፊ እየሆኑ የመጡት በፖለቲካ ተቀባይነት የሚተካከላቸው ተቃዋሚ በጭራሽ ጠፍቶና ከእንከን በፀዳ የምርጫ ሒደት ነው ወይ የሚል ጥያቄ ቢነሳ፣ እንኳን ሌላው ኢሕአዴግ ራሱ ያለ ጥርጥር አዎ ብሎ መመለስ አይችልም፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች የገዥ ፓርቲ አባል ወይም ደጋፊ ላለመሆናቸው መታወቂያ አለመያዛቸው መተማመኛ የማይሆንበት ፖለቲካ ነው  ኢሕአዴግ የፈጠረው፡፡ የለየለት ደጋፊ ወይም ባለመታወቂያ አባል መሆን ሳያስፈልግ የገዥው ፓርቲ መንሰራፋት በገዛ ራሱ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለው መካረር፣ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎቻቸው ላይ ከዚህ ቀደም የደረሰውና ደረሰብን የሚሉት ጥቃትና እንግልት የሚያስፈራራና የሚያስገድድ ነው፡፡ በአንፃሩ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል የቆየው በጠላትነት መጠማመድ ባይኖር ወይም ቢፈርስ፣ የውገናው ክረት ይረግባል፡፡ ወይም ከእነ ጭራሹ አይኖርም፡፡ በፍርኃት የድምፅ ማጭበርበር አባሪ ተባባሪ የመሆንን ዕድል/ዕዳ ይቀንሳል፡፡ ያለ አድልኦ አደራን የሚወጡ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ለማግኘትና ለመምረጥ፣ እንዲያም ሲል ብልሽትና ሐሜት ያነሰበት ምርጫ ለማካሄድ (ለዚያውም ፓርቲዎች ለመሸፈጥ እየሞከሩም ቢሆን) ያመቻል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ያለው አተካከል በፓርቲው ፈቃድ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ቢፋጅ በማንኪያ ቢበርድ በእጅ ለመግዛት የሚያስችል ሆኖ በመቅረፁ ያየናቸውን ዓይነት የምርጫ ውጤቶችና የድኅረ 2007 ምርጫን፣ የማግሥቱን ዓይነት ተቃውሞ ቀስቅሷል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲ በምርጫ ያሸነፈበት ዕድል አገኘ እንበል፡፡ እንዲያም ቢሆንም ትርምስና አፍርሶ መገንባት ሳይኖር ሕይወትና ጉዞ ስለመቀጠሉ መተማመኛ የለም፡፡ የገዥው ፓርቲ እኔ ነን አሸናፊው ብሎ በጉልበት የማይቆይበትና የማይቀማበት ወይም አሸናፊ ነኝ ባለ ወገንና አልለቅም ባለው ወገን መካከል ሕዝብ ተከፋፍሎ ቀውስ ውስጥ የማይገባበት፣ የተለፋበት የልማት ሥራና የኢንቨስትመንት ሥራ ለውድመት የማይጋለጥበት ሁኔታ አለመደላደሉን ይኼው ያለፉት ሦስት ዓመታት አሳይተውናል፡፡ በምርጫ ተሸንፎ ከሥልጣን መውረድን የመሰለ የከፋ የሞት ሽረት የድመት አፍንጫ የማሽተት ነገር የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ድንገት ነባሩ ገዥ ፓርቲ እንደ ምንም ወርዶ ተቃዋሚዎች ሥልጣን መጨበጥ ቢችሉ እንኳን፣ የነባሩን ገዥ ቡድናዊ አሻራና ቁጥርጥር ለማፅዳት ሲል መንግሥታዊ አውታራቱን ማበራየት ይመጣል፡፡፡ ይህን ግትልትል ችግር አይቀሬ የሚያደርገው ከቡድናዊ ወገናዊነት ነፃ የሆኑ አውታራትን የመገንባት ተግባር አለመከናወኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያም የዴሞክራሲ ችግር ይኼው ነው፡፡

ሥልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲና ተቃዋሚዎች በጠላትነት የፖለቲካ ወጥመድ ውስጥ ተለያይተውና ተሰነካክለው ከቀጠሉ፣ አሁን እንደሚታው አዲስ ሁኔታ ደግሞ ኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት የለውጥ ኃይሉን የማያግዝ ከሆነና ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲን ማዳን ማለት ኢትዮጵያን ማዳን ማለት ነው›› እንቅፋት ከሆነ፣ ኢወገናዊ በሆኑ ተቋማት ላይ ዴሞክራሲን ማቋቋም ለኢትዮጵያ በዓብይ ዘመንም የማይሳካ ሥራ፣ የሚያመልጥ ዕድል ይሆናል፡፡

በድምፅ ካርድ የተመረጠ መሪ፣ ዓብይ አህመድ ሆነ ሽፈራው ሽጉጤ ወይም ሌላ ሰው፣ ወታደሩንና ደኅንነቱን ለመያዝ ሳይሠጋና ሳይጨነቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ውስጥ ሲገባ ሥልጣኑንም መቀዳጀት የሚችልበት፣ የሥልጣኑም ዘላቂነት በሕገ መንግሥትና በተግባሩ ብቻ የሚወሰንበት ሥርዓት አንድ ብሎ የሚጀመረው ወታደሩ፣ ፖሊስና ደኅንነቱ፣ የምርጫ አስፈጻሚውና ሌሎችም የሥልጣን አካላት ከግለሰብና ከፓርቲ ታማነኝነት ጋር ሳይጠብቁ በሕጋዊ መንገድ በኩል ማንም መጣ ማን፣ እንደ ተቋም በገለልተኛነት የሚቀበሉና አገራዊ ሙያዊ ተልዕኳቸው ላይ የሚያተኩሩ አድርጎ በማደራጀት ነው፡፡ የፖለቲካ ትርምስ ሳይፈጠር፣ የመፈናቀልና የሙያ ብክነት እገጭ እገው ሳይኖር ከሕዝብ ጋር በእርጋታ እዚህ ሒደት ውስጥ ለመግባት፣ አሁን ያለንበት ዓብይ አህመድ መርቀው የከፈቱት ምዕራፍ ጥሩ አጋጣሚና ሊያመልጥ የማይገባው ምናልባትም ተመልሶ የማይገኝ ዕድል ነው፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...