Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በነፃነት የመደራጀትና የመደራደር መብት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይከበር ነው የምንለው››

አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት

አቶ ካሳሁን ፎሎ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ኢሠማኮ የሠራተኞች መብት ለማስከበር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ይታወቃል፡፡ በተለይ የመደራጀት መብትን ለማስከበር በብርቱ እየታገለ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ነገር ግን በተለይ በውጭ ኩባንያዎች ውስጥ ሠራተኞችን የማደራጀት እንቅስቃሴው፣ በአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጭምር እየተደነቃቀፈበት ስለመሆኑ በይፋ እየተናገረ ነው፡፡ በአዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ የተካተቱ የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ይነካሉ ያላቸው አንቀጾች ካልተሻሻሉ፣ እስከ ሥራ ማቆም አድማ ድረስ እንደሚደርስ ማሳወቁም አይዘነጋም፡፡ አገር አቀፍ የደመወዝ መነሻ ወለል እንዲኖር መንግሥትን እየሞገተ ሲሆን፣ ሌሎች የሠራተኞች ጥያቄ መልስ እንደሚያሻቸው እየተናገረም ነው፡፡ ሲንከባለሉ የነበሩ ጥያቄዎችንም ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚያቀርብም የተገለጸ ሲሆን፣ በኢሠማኮ ጥያቄዎችና እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም በአገሪቱ አጋጥሞ የነበረው ያለመረጋጋት በሠራተኞች ላይ ጥሎት ያለፈው ተፅዕኖ፣ በቅርቡ በተደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥና ሠራተኞች ምን እንደሚጠብቁ፣ ከሜይ ዴይ በዓል ጋር በማያያዝ ኢሠማኮ ስላነሳቸው ጥያቄዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ዳዊት ታዬ አቶ ካሳሁንን አነጋግሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት አገሪቱ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ነበረች፡፡ አለመረጋጋቱ ጥሎት ያለፈው ጠባሳ ቀላል እንዳልነበር ይታመናል፡፡ እንደ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ያለመረጋጋቱ በሠራተኞች የሥራ ዋስትና ላይ አደጋ ነበረው፡፡ በርካታ ሠራተኞችን የያዙ ኩባንያዎች የሥራ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል፡፡ አጋጥሞ የነበረው ችግር እንዴት ይገለጻል? የተፈጠረውን ችግር ለማርገብና ለማስተካከል የእናንተ ሚና ምን ነበር?

አቶ ካሣሁን፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት በአገራችን ውስጥ እየተባባሰ ሄዶ የነበረው አለመረጋጋት፣ በሠራተኞችም ሆነ በምርትና በምርታማነት ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ ያለፈ ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ከሥራ መፈናቀል ተፈጥሯል፡፡ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑ የአካባቢ ነዋሪዎች ተቀጥረው ይሠሩባቸው የነበሩ ድርጅቶች ሠራተኞች ሳይቀሩ ከሥራ የተፈናቀሉበት ሁኔታ ጭምር ነበር፡፡ በኋላ ግን መፈናቀል የተከሰተባቸው ድርጅቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ከአካባቢው ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጋር ተመካክረን እንደ ገና ወደ ሥራ እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ ነው የሠራነው እንጂ፣ ሁኔታው በጣም ከባድ ነበር፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደታየው የትራንስፖርት ያለመኖር ሠራተኛው ወደ ሥራ እንዳይገባ አድርጓል፡፡ ሠራተኛው በወቅቱ የቱንም ያህል ወደ ሥራ መግባት ፍላጎት ቢኖረውም ሄዶ ለመሥራት የትራንስፖርት ችግር ነበር፡፡ በዚያ አለመረጋጋት ውስጥ የትራንስፖርት ተሽከርካሪ የሚያንቀሳቅስ ከተገኘ ዕርምጃ ስለሚወሰድበት ሄዶ መሥራት አልተቻለም፡፡ በአብዛኛው ግን ኢንዱስትሪዎች ባሉበት በተለይ በእኛ ሥር የተደራጁት እንዲህ ዓይነት ነገር እንደማይጠቅማቸውና ሲሠሩ ብቻ የሚያገኙ መሆኑን፣ ሰላም ሲፈጠር ብቻ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ያለመረጋጋቱ ከመፈጠሩ በፊት ቀደም ብለን ግንዛቤ በማስጨበጣችን እነሱ ተሳታፊ አልነበሩም፡፡ የግርግሩ ተሳታፊ ባይሆኑም ወጥተው መሥራት አልቻሉም፡፡ ካልሠሩ ደግሞ ምርት የለም፡፡ በግርግሩ ወቅት ባለመሥራታቸው ሊከፈላቸውም አልቻለም፡፡ ስለዚህ ብዙ ችግር ተፈጥሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሠማኮ ከሚያነሳቸው ሮሮዎች ውስጥ በተደጋጋሚ የሚሰማው ከሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ውጪ መብት በመጋፋት መደራጀት መነፈግ ነው፡፡ መደራጀት መብት መሆኑ የታወቀ ቢሆንምና መደራጀት ለአሠሪዎቹም የሚጠቅም መሆኑ ከታወቀ፣ ሠራተኞች እንዳይደራጁ የሚደረግበት ምክንያት ምንድነው? እናንተስ ይህንን በማሳመን ረገድ ምን ሠርታችኋል?

አቶ ካሣሁን፡- መፍትሔ ያልተገኘበት ምክንያት አንደኛ አሠሪዎችን ሰብስቦ መደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን፣ መደራጀት ለአሠሪው ጭምር የሚጠቅም መሆኑን ግንዛቤ የሰጠ ሰው ያለመኖሩ ነው፡፡ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሠራተኛው እንዳይደራጅ ይከለክላሉ፡፡ ይህንን ግንዛቤ መፍጠር ያለበት የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ አስፈጻሚ አካል ነው፡፡ የአዋጁ አስፈጻሚ አካል በዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት ነገር አይሠራም፡፡ እነሱ ሠራተኞች ተደራጅተው ሲመጡ መመዝገብ ብቻ እንጂ፣ ሄደን አናደራጅም የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ እኛ ሄዳችሁ አደራጁ አላልንም፡፡ እነሱ ሁልጊዜ ይህንን ያነሳሉ፡፡ በተለይ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎች የሚሰጠን መልስ እኛ አናደራጅም ነው፡፡ እኛ ደግሞ የፈለግነው በአዋጁ መሠረት ሠራተኛውም አሠሪውም መብትና ግዴታውን እንዲያውቅ፣ መደራጀት ለአሠሪውም የሚጠቅም መሆኑን አስረዱ የሚል ነው፡፡ ይህ እስካሁን በእነሱ በኩል አልተሠራም፡፡ ይህ ባለመሠራቱ ምክንያት መደራጀት አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ እኛ በተቻለ መጠን ከአሠሪዎች ጋር እየተነጋገርን ለማደራጀት እንሞክራለን፡፡ እንቢ ቢሉንም ማደራጀታችን አይቀርም፡፡ ግን የተደራጁት ሠራተኞች ሕጋዊ ምዝገባ አድርገው ሲገቡ ከአሠሪው ጋር ተስማምተው ሊሠሩ አይችሉም፡፡ አሠሪዎች የማኅበር መሪዎችን ያባርራሉ፡፡ ስለዚህ በስምምነት የማደራጀቱ ሥራ መኖሩ ይጠቅማል ከሚል ነው፡፡ ለምሳሌ የውጭ ኩባንያዎች እየመጡ ነው፡፡ ነገር ግን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ለማደራጀት ስንሄድ አሠሪዎቹ እሺ አይሉም፡፡ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች የአሠሪዎች ማኅበር አላቸው፡፡ በዚህ ማኅበር አማካይነት ማንኛውም በፓርኩ ውስጥ ያለ ኩባንያ ለሠራተኞች ከ650 ብር በላይ ደመወዝ እንዳይከፈል ወስነዋል፡፡ እንዲህ በመወሰናቸውም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ በአንደኛው የተቀጠረ ሠራተኛ ወደ ሌላኛው ኩባንያ መሄድ አይችልም፡፡ ይህንን በውይይት ለመፍታት ሞክረናል፣ ግን አልተቻለም፡፡ የሚገርመው ደግሞ 42 የሚሆኑ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች የራሳቸውን የአሠሪዎች ማኅበር ሲፈጥሩ፣ ሠራተኞች ይደራጁ ሲባል ግን አይፈቅዱም፡፡ ሠራተኞች እንዲደራጁ ብዙ ጊዜ ሙከራ አድርገናል፡፡ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ሳይቀር ውይይት አድርገናል፡፡ ቆዩ ገና ነው ይሉናል፡፡ ትንሽ ከቆየ በኋላ አደረጃጀቱ እንዴት እንደሚሆን እንነጋገር የሚል ምላሽ ነው የሚሰጠው፡፡ በአገራችን ሕግ አደረጃጀቱ የታወቀ ነው፡፡ እነሱ የሚያስቡት ሠራተኛው በማኅበር ቢደራጅ የሥራ ማቆም አድማ ሊያደርግ ይችላል፣ ወይም የመብት ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል የሚል ነው፡፡ አሁን እንዲያውም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሠራተኞች እንዳይደራጁ የአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት ነው የሚያስቸግረን፡፡

ሪፖርተር፡- የደመወዝ ነገር ከተነሳ የእነዚህ ኩባንያዎች ክፍያ አነስተኛ ነው፡፡ እነዚህ ሠራተኞች በዚህ ደመወዝ እየሠራችሁ መስዋዕትነት ክፈሉ እየተባሉ ነው የሚል አስተያየት ሲሰጡ ሰምቻለሁ፡፡ ምን ማለት ተፈልጎ ነው?

አቶ ካሣሁን፡- ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያን በተመለከተ አንዳንዶቹ የሚሉት ይህንኑ የሚሰጡዋችሁን ደመወዝ ተቀብላችሁ ሥሩ ነው፡፡ በዚህ ደመወዝ ካልሠራችሁ ኩባንያዎቹ ስለማይመጡ ይህንኑ እየተቀበላችሁ ሥሩ ነው፡፡ ለሚቀጥለው ትውልድ እንዲተላለፍ እናንተ መስዋዕትነት ክፈሉና ሥሩ የሚል ነው፡፡ ይህ አጉል መስዋዕትነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት መስዋዕትነት የለም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ኩባንያ ወደዚህ አገር የመጣው ለትርፍ ነው፡፡ አትርፎ ትርፉን ይዞ ለመሄድ ነው የመጣው፡፡ ይኼ የታወቀ ነው፡፡ መቼም ለዕርዳታ የመጣ የለም፡፡ ለዕርዳታ የመጣ ቢሆን ኖሮ በራሱ ተነሳሽነት ስለሰጠኝ ይችን ታህል ክፍያ ካገኘሁ ይበቃኛል ይባል ነበር፡፡ ይህ ገንዘብ ለአገራችን የሚቀር ቢሆን ኖሮ ሠራተኛው አነስተኛ ክፍያ ተከፍሎት ቢሠራ ችግር የለም ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን ገንዘቡ የሚገባው ለባለሀብቱ ነው፡፡ ትርፍ የሚያገኝበት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ትርፉ ላይ ፍትሐዊ የሆነ ደመወዝ ይከፈል ነው፡፡ ሌላ የተጠየቀ ነገር የለም፡፡ ሠራተኛው ቢያንስ በልቶ ለመዋል የሚሆን ደመወዝ ይኑረው ነው፡፡ ለቤት ኪራይ የሚሆነው ደመወዝ ይሁን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ከመስዋዕትነት ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ባይሆን የሥራ ባህላችሁን አሻሽላችሁ ጥሩ ይሥሩ ብለው ቢጠይቁ መልካም ነበር፡፡ እሱ ላይ አብረን እንሠራለን፡፡ ምክንያቱም በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በሌሎች ኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ የሚሠሩት በብዛት ከገጠር ነው የሚመጡት፡፡ የኢንዱስትሪ ባህል የላቸውም፡፡ ከዚህ አንፃር ለማስተማርና የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ ለማድረግ ሠራተኞቹ ተደራጅተው በጋራ ብንሠራ ነው የሚሻለው፡፡ ከዚህ ውጪ የሚከፈል መስዋዕትነት የለም፡፡ መስዋዕትነትማ ለምሳሌ ለህዳሴ ግድብ ሠራተኛው ከደመወዙ ያዋጣል፡፡ ለአገር ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ገንዘብ ተርፎት አይደለም የሚያዋጣው፡፡ እንደ ባድመ ላሉ ጦርነቶች ገንዘብ አዋጥቷል፡፡ ይህም ለአገር ስለሆነ ነው የምንቀበለው እንጂ፣ ይኼ ከሠርቶ መኖር ጋር የተገናኘ ጉዳይ ግን የአገር ቋት ውስጥ የማይገባ ገንዘብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚሁ ጋር እናያይዘውና የዘንድሮውን ሜይ ዴይ ስታከብሩ እንደ ጥያቄ ያነሳችሁት፣ ከዚህም ቀደም ከ1990ዎቹ ጀምሮ በየጊዜው የምታነሱት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ የሠራተኞች መነሻ የደመወዝ ወለል ሊኖር ይገባል የሚል ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄያችሁ መነሻ ያደረጋችሁት ምንድነው? መነሻ የደመወዝ ወለልን በተመለከተ የሌሎች አገሮችስ ልምድ ምን ያሳያል?

አቶ ካሳሁን፡- በዚህ ረገድ የሌሎች አገሮችን ልምድ ስናይ ያደጉትን አገሮች ትተን፣ በአፍሪካ ብቻ በ35 አገሮች የመነሻ ደመወዝ ወለል አለ፡፡ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና የመሳሰሉት አገሮች ሁሉ መነሻ የደመወዝ ወለል አላቸው፡፡ ሥራ ኖሮት ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ሰው አለ፡፡ ሥራ ኖሮት የደሃ ደሃ ሆኖ ይኖራል፡፡ መቼ ነው መካከለኛ ገቢ የሚኖረን? መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንደርሳለን ተብሎ የሚጠበቀው ጊዜ የቀረው ወደ ሰባት ስምንት ዓመት ነው፡፡ አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር መካከለኛ ገቢ ላይ የሚደርሱት ባለሀብቶች ናቸው ወይ? ከባለሀብቶቹ የሚገኝ ትርፍ ተሰልቶ ነው እዚህ ደረጃ የሚደረሰው? ሁለተኛ አንድ ሰው ሥራ ለመሥራት በልቶ ማደር አለበት፡፡ ይኼ መርህ ነው፡፡ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ ትርፍ እንዲያገኝ ወይም ለቅንጦት አይደለም መነሻ የደመወዝ ወለል የሚያስፈልገው፡፡ ሰው በወር ውስጥ ለምግብ ፍጆታ ምን ያህል ያወጣል? ተብሎ ለዚያ የሚያበቃ ነገር ይኑር ነው፡፡ ይኼ ከሌለ ሥራው ዋጋ የለውም፡፡ የሌላ ሰው ጥገኛ ሆኖ ይኖራል እንጂ ሥራ ኖሮት ራሱን የማያስተዳድር ሰው በራሱ ሊኖር አይችልም፡፡ ይኼ ደግሞ አለመረጋጋትን ይፈጥራል፡፡ ሰው ተስፋ ይቆርጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ አንዳንድ ድርጅቶች ላይ የተከሰቱ ነገሮች ነበሩ፡፡ የሥራ ማቆም ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡ ሲፈልጉ ከሥራ ይቀራሉ፡፡ ለምንድነው ቀሪ የምትሆኑት ሲባሉ ሠራሁ፣ አልሠራሁ ያው ነው፡፡ አይኖረኝም፡፡ በተመቸኝ ጊዜ ሄጄ እሠራለሁ ይባላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ለመንግሥትም ጥሩ አይደለም፡፡ ሥራ አስዣለሁ ይባል እንጂ ሥራ ያለውም ሰው ቅሬታ አለው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሠራተኞች በልተው ማደር አልቻሉም ማለት ነው፡፡ ለምን ይቀጠራሉ ከተባለም ዝም ብዬ ቤት ከምቀመጥ ልቀጠር ይባላል ማለት ነው፡፡

አንድ ምሳሌ ላንሳ፡፡ ከዚህ ወደ ዓረብ አገር የሚሄዱ ሠራተኞች አሉ፡፡ እነዚህ ሠራተኞች ከገጠር የሚመጡ፣ ምንም ዓይነት ትምህርት የሌላቸው፣ ስለሥራውም ቢሆን ግንዛቤ የሌላቸው ናቸው፡፡ ዓረብ አገር ሄደው ግን የሁለት፣ የሦስት ሰው ቤትና ልብስ እያጠቡ ይኖራሉ፡፡ ከ16 ሰዓታት በላይ ነው የሚሠሩት፡፡ እንዲህ የሚሠሩት ስለሚከፈላቸው ነው፡፡ እዚያም ቢሆን በቂ ክፍያ ነው ብለን ባናስብም፣ ሌት ተቀን ሠርተው ለቤተሰቦቻቸው የሚሆን ገንዘብ ይልካሉ፡፡ ለራሳቸውም ገንዘብ ያጠራቅማሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ነው መነሻ ደመወዝ ወለል ይኑር የምንለው፡፡ ይህ ማንንም አይጎዳም፡፡

ሪፖርተር፡- መነሻ የደመወዝ ወለል ይኑር የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ከጀመራችሁ ዓመታት የተቆጠረ ቢሆንም፣ ለዚህ ጥያቄ መንግሥት አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ያልፈለገው ለምን ይመስልዎታል? መንግሥት መነሻ የደመወዝ ወለል እንዲኖር ያልፈለገበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ካሳሁን፡- መንግሥት ለዚህ ጉዳይ የሚሰጠው ምላሽ ገበያ ይወስን እንጂ፣ ብዙ ሥራ አጥ ባለበት አገር ላይ ይህንን ወለል ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው የሚል ነው፡፡ የደመወዝ መነሻ ወለሉን ብናስቀምጥ ኩባንያዎቹ ብዙ ሠራተኛ አይቀጥሩም የሚል ምላሽም ይሰጣል፡፡ እንዲህ ያሉት ምላሾች ያስገርማሉ፡፡ እነዚህ የመጡት ኩባንያዎች ናቸው? ወይስ የተራድኦ ድርጅቶች? ብለን እንድንጠይቅ ያደርጋል፡፡ በግልጽ መነጋገር አለብን፡፡ አንድ ሰው ቢዝነስ ሲያቋቁም በመጀመርያ በባለሙያ አስጠንቶ ስንት ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉት አውቆ ነው፡፡ ያስፈልጋል ከተባለው በላይ ሠራተኛ አይቀጠርም፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ሥራ አጥ ስለበዛባት ድርጅቶች ከሚሸከሙት በላይ ሰው አይቀጥሩም፡፡ እንዲህ ካልሆነ ቢዝነስ ሳይሆን የዕርዳታ ድርጅት ነው የሚሆኑት፡፡ ስለዚህ ትንሽም ሆነ ከፍተኛ የሚባል ደመወዝ ካለ በጥናታቸው መሠረት ያስፈልገናል ብለው ያስቀመጡትን ያህል ሠራተኞች ነው የሚይዙት፡፡ አንድ ሰው በስምንት ሰዓታት ምን ያህል እንደሚሠራ ያውቃሉ፡፡ ምናልባት የምርታማነት መጠን ሊለያይ ይችላል፡፡ የቀጠሩት ሰው ምርታማ እስኪሆን ድረስ የተወሰነ ትርፍ ሰው ሊቀጥሩ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ሌላውን ለማካካስ ነው፡፡ ይኼ ማለት ግን ከሚፈልጉት በላይ ትርፍ ሠራተኞች ይቀጥራሉ ማለት አይደለም፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ለሥራ አጡ አስበው ሳይሆን ለሥራቸው አስበው ነው፡፡ ሁለተኛ ሥራ ያለውም የሌለውም ደሃ ሆኖ ማን ማንን ይረዳል? ማን ማን ላይ ጥገኛ ይሆናል? ስለዚህ መንግሥት የሚሰጠው መልስ ከዚህ አንፃር መታየት አለበት፡፡ ሌላው ገበያው ይወስን የሚለው ነገር አይሠራም፡፡ እንዴት ነው ገበያው የሚወስነው? የመደራደር አቅምና ኃይል ያለው አሠሪው ነው፡፡ ቀጣሪውም አሠሪው ነው፡፡ ትልቁ ጉልበት ያለው እዚያ ነው፡፡ ይኼ ሰው በዚህ መነሻ ላይ ሊደራደር አይችልም፡፡ የመነሻ የደመወዝ ወለልን በተመለከተ ከዚህ በፊት ያሠራነው ጥናት አለ፡፡ አሁን ደግሞ እንደገና አዲስ እያስጠናን ነው፡፡ ከዓለም ሥራ ድርጅት ጋር አሠሪው፣ ሠራተኛውና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተስማምተን በመነሻ ደመወዝ ወለል ላይ ጥናት ያካሂድ ተብሎ አሁን ጥናቱን ጨርሷል፡፡

ሪፖርተር፡- ጥናቱ ካለቀ በቀጣይ የሚደረገው ነገር ምንድነው? እናንተስ የደመወዝ መነሻ ወለሉ እንዴት እንዲቀረፅ ነው የምትፈልጉት?

አቶ ካሳሁን፡- የዓለም የሥራ ድርጅት ጥናቱን ያስጠናው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ አሁን ጨርሰዋል፡፡ አሁን ተሰብስበን ማየትና ለእኛ ማብራሪያ መስጠት ብቻ ነው የቀረው፡፡ ስለዚህ የደመወዝ ወለሉ በጥናት ላይ የተመሠረተ ይሁን ነው ያልነው፡፡ ዝም ብሎ ዝቅተኛው የደመወዝ ወለል ከዚህ በላይ ወይም ከዚህ በታች ይሁን ብለን አልወሰንም፡፡ ይህ በጥናት ይወሰን፡፡ አሠሪ፣ ሠራተኛና መንግሥት የሚሳተፉበት መድረክ አለ፡፡ በዚህ መድረክ እየታየ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ይወሰናል፡፡ ይህ አሠራር በየትኛውም አገር የሚሠራበት ነው፡፡ በየዓመቱ ይከለሳል፡፡ መነሻ ደመወዝ አንድ ቦታ ላይ የሚቆም አይደለም፡፡ ከገበያና ከኑሮ ሁኔታ ጋር እየታየ ማስተካከያ እየተደረገለት የሚሄድ ነው፡፡ መነሻ ደመወዝ ይኑር ስንል እኛ ያልነው ብቻ ይሁን አላልንም፡፡ መጠን አላስቀመጥንም፡፡ በጥናት ይመለስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከወራት በፊት ኢሠማኮ ብዙዎችን ያነጋገረ አንድ ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ ረቂቅ ደረጃ ላይ ያለው አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ የሠራተኞችን መብትና ጥቅም የሚነኩ አንቀጾችን ያካተተ በመሆኑ፣ እነዚህ አንቀጾች ካልተሻሻሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ ወስኖ ነበር፡፡ ይህ ውሳኔያችሁ ከምን ደረሰ? ሊፀድቅ ጫፍ ላይ ደርሷል ተብሎ የነበረው ረቂቅ አዋጅ አሁን ምን ላይ ነው?

አቶ ካሳሁን፡- ይህ ጉዳይ አሁንም ውይይት ላይ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ውይይቱ እንዴት ገባችሁ?

አቶ ካሳሁን፡- ውይይቱ የመጣው በመጀመርያ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መሠረታዊ ማኅበራት አመራሮችን በአሥራ አንድ ቦታዎች አወያይተን በረቂቅ አዋጁ ላይ የጋራ አቋም ያዙ፡፡ ይህ ባርነት ስለሆነ ልንሸከመውም አንችልም  ተባለ፡፡ ምክንያቱም የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የኢኮኖሚ ይዞታ ግምት ውስጥ ያላስገባ ስለሆነ ጉዳዩ በኢሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤት ሪፖርት ቀርቦ ከተወያየን በኋላ፣ ጉዳዩን ለመንግሥት አቅርቡልን በመባሉ ነው፡፡ ከዚያም በውይይት እንደፈታ አድርጉ፣ በዚህ ውይይት በአዋጁ የተጠቀሱት አንዳንድ አንቀጾች ጉዳይ በውይይት የማይፈታና መንግሥት በሩን የሚዘጋ ከሆነ አንደኛ አገራዊ ሰላማዊ ሠልፍ እንዲደረግ፣ በዚህም ውጤት ካልተገኘ አገር አቀፍ የሥራ ማቆም አድማ እንዲካሄድ ተወስኖ ይህንን ለመንግሥት እንድናሳውቅ ጠቅላይ ምክር ቤቱ በመወሰኑ፣ በዚህ መሠረት ይሁንኑ ለመንግሥት አሳወቅን፡፡ ለመንግሥት ካሳወቅን በኋላ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሦስት ሚኒስትሮች ያሉበት ኮሚቴ አዋቅረው፣ ሠራተኛው እስከ ሥራ ማቆም አድማ አደርግበታለሁ ባለው አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደገና ውይይት እንዲደረግ በማዘዛቸው ውይይት ጀምረናል፡፡ በዚህም መድረክ ኢሠማኮ ባቀረባቸው ጥያቄዎችና ተቋውሞች ላይ እንደገና ውይይት እንዲደረግበት ተወስኖ፣ ከሦስቱ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት እየተደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ጉዳይ ላይ በድጋሚ እንዲመከርበት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የተሰየሙት ሚኒስትሮች እነማን ናቸው?

አቶ ካሳሁን፡- ክቡር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ ክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ክቡር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ናቸው፡፡ ሚኒስትሮቹ አሠሪውን፣ ሠራተኛውንና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠርተው በጋራ ውይይት ተደርጓል፡፡ ከዚህ ውይይት በኋላ በአማካሪ ቦርድ እንደገና አይታችሁ አምጡና በዚያ ላይ ውይይት ካላችሁ እንደገና እናወያያችኋለን ብለው እየተወያየን ነው፡፡ ወደዚህ ስንገባ አማካሪ ቦርድ ከመቅረቡ በፊት የኢሠማኮ ሁሉም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የአሠሪዎች ፌዴሬሽን ሁሉም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የአሠሪዎች ፌዴሬሽን ሁሉም የቦርድ አባላት፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርና ባለሙያዎች ባሉበት እንድናይ ተደርጎ አሁን እየተወያየን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ እስከ ሥራ ማቆም አድማ ተቃውሞ ያሰማችሁባቸው የረቂቅ አዋጁ አንቀጾች ምን ያህል ናቸው? ለአብነት ዋና ዋና የሚሉትን በአጭሩ ያስታውሱኝ፡፡ የእነዚህ አንቀጾች መካተት የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ካሳሁን፡- ካለው አዋጅና አዲስ ከቀረበው ረቂቅ ውስጥ የተቃወምነው 18 አንቀጾችን ነው፡፡ 16 አንቀጾች ደግሞ በረቂቁ መካተት አለባቸው ብለን እንደ አዲስ አቅርበናል፡፡ በአጠቃላይ 34 አንቀጾች ማለት ነው፡፡ በዚህ በተጀመረው ውይይት ላይ 16 አንቀጾችን  ያቀረብነው መንግሥት አዳዲስ አንቀጾችን አካቶ በመላኩ፣ እኛም የምንፈልጋቸውን መጨመር ስላለብን ነው፡፡ ሁላችንም እኩል መብት ስላለን ያደረግነው ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  በረቂቁ ውስጥ ብዙ ተቃውሞ ያሰማችሁት ሠራተኞች ሲያረፍዱ ወይም ሲቀሩ ይወሰድባቸዋል በተባለ ዕርምጃ ላይ ነው፡፡ እስቲ ስለዚህ አንቀጽ ይንገሩኝ?

አቶ ካሳሁን፡- አንድ ሰው በወር ውስጥ ሁለት ቀን ካረፈደ ከሥራ ይባረራል የሚለው ነው፡፡ እኛ ሠራተኛው ያለ በቂ ምክንያት እንዲያረፍድ አንፈልግም፡፡ ነገር ግን አሁን በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ችግርና የመንገድ መጨናነቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አንድ ሠራተኛ በወር ውስጥ ሁለት ቀን አምስት ደቂቃ ቢያረፍድ ሊባረር ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ የአገሪቱን ሁኔታ ያላገናዘበ ሕግ ነው፡፡ በማርፈድ ጉዳይ ቀደም ብሎ በኅብረት ስምምነት ይወሰን ነበር፡፡ ስለዚህ መኪና ለእያንዳንዱ ቢታደል እንኳን አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በሰዓቱ መግባት እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ድንጋጌ ለማስቀመጥ መነሳት ተገቢ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለሥልጣናትም እኮ ኮብራ ይዘው ያረፍዳሉ፡፡ በቅልጥፍና የሚወስዳቸው መንገድ የለም፡፡ ስለዚህ አንዱ የተቃወምነው ይህ ነው፡፡ ለዚህም መፍትሔ ይሆናል ያልነውን አቅርበናል፡፡ ከዚሁ ጋር የተቃወምነው አንቀጽ አንድ ቀን የቀረ ሠራተኛ የሥራ ውሉ  ይቋረጣል የሚለውን ነው፡፡ ይህም መሻሻል ያለበት አንቀጽ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ሌሎች በርከት ያሉ ጉዳዮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የሥራ ስንብት ክፍያን በተመለከተ በረቂቁ ላይ የሰፈረው ድንጋጌ ብዙ የሞገታችሁበት ጉዳይ ነው፡፡

አቶ ካሳሁን፡- የሥራ ስንብት ክፍያን በተመለከተ በነባሩ አዋጅ አምስት ዓመትና ከዚያ በላይ ያገለገለ ሠራተኛ ከአሠሪው ጋር ለመቆየት የሚያስችል ውል ከሌለ በቀር፣ ሥራውን የመልቀቅና የሥራ ስንብት ክፍያ የማግኘት መብት አለው፡፡ አሁን ግን 20 ዓመት አገልግሎት ቢኖረው በፈቃዱ ሥራውን ከለቀቀ የሥራ ስንብት ክፍያ አያገኝም ይላል፡፡ እኛ በብርቱ ተቃውመነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ አንቀጽ ሲካተት ምን ታሳቢ ተደርጎ ይመስልዎታል?

አቶ ካሳሁን፡- ከእነሱ የተረዳነው ሠራተኛው የሚለቀው የተሻለ ክፍያ ስላገኘ ነው የሚል ስሜት ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው የተሻለ ክፍያ አግኝቶ አይለቅም፡፡ አንድ ሠራተኛ ሥራ የሚለቀው የተሻለ ክፍያ ስላገኘ ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ ለመሆን፣ ትራንስፖርት እንዳይቸግረው ሊሆን ይችላል፡፡ ባነሰ ደመወዝም ቢሆን ቀረብ ወዳለ ቦታ ሊዛወር ይችላል፡፡ የተሻለ አግኝቶ የሚሄደው ጥቂት ነው፡፡ ስለዚህ ለጥቂት ተብሎ ብዙኃኑን የሚጎዳ አንቀጽ ነው፡፡ ስለዚህ የሥራ ስንብት ክፍያ ቢያንስ እንደ በፊቱ መቆየት አለበት ብለን እየተከራከርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዓመት ፈቃድ አሰጣጥ ላይ በአዲሱ ረቂቅና አሁን ባለው አዋጅ የሰፈረው ልዩነት እንዳለው ተጠቅሷል፡፡ በአዲሱ ረቂቅ ላይ የሰፈረው ብዙዎችን የሚያደነጋግር ነውም ይባላል፡፡ እስቲ የሁለቱን ልዩነት ያብራሩልኝ? የሠራተኞችን መብት ይነካል የተባለው ለምንድነው?

አቶ ካሳሁን፡- በሥራ ላይ ባለው አዋጅ አንድ ዓመት ያገለገለ ሰው 14 ቀናት የዓመት ዕረፍት ያገኛል፡፡ ከዚያ በኋላ በየዓመቱ አንድ አንድ ቀን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ነገር አሁን በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት ያገለገለ 14 ቀናት የዓመት ፈቃድ ያገኛል የሚል ነው፡፡ ይህ ማለት በነበረው አዋጅ አምስት ዓመት ያገለገለ የዓመት ዕረፍቱ 19 ቀናት ነው፡፡ አሁን 14 ቀናት እንዲሆነው የተፈለገው በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡ ከአምስት እስከ አሥር ዓመት ያገለገለ 16 ቀናት የዓመት ዕረፍት ያገኛል ይላል፡፡ ከ10 እስከ 15 ዓመት ያገለገለ ደግሞ 18 ቀናት የዓመት ዕረፍት ይኖረዋል ሲል፣ ከ16 እስከ 20 ዓመት ያገለገለ ሠራተኛ የዓመት ዕረፍቱ 20 ቀናት እንደሚሆን ነው በረቂቁ የተቀመጠው፡፡ ከሃያ ዓመት በላይ ከሆነ እስከ 30 ቀናት እንደሚያገኝ ጠቅሶ ይህ ከ30 ቀናት በላይ አይሄድም ነው የሚለው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ተግባራዊ ቢሆን እንደ ችግር የታያችሁ ምንድነው? ሥጋታችሁስ ምንድነው?

አቶ ካሳሁን፡- አንደኛ ሥራ ላይ ያሉት ሠራተኞች የዓመት የሥራ ፈቃዳቸው ከ30 ቀናት በላይ ሄዷል፡፡ ይህ ከሆነ እነዚህ ነባር ሠራተኞች ወደኋላ ሊመለሱ ነው ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ አንድ ሰው 20 ዓመት አገልግሎ የዓመት እረፍትህ 20 ቀናት ብቻ ነው ማለት አግባብ አይሆንም፡፡ በቀደመው አዋጅ በስድስት ዓመት የሚደርስበትን የዓመት ፈቃድ ቀናት አሁን በ20 ዓመት ነው የሚደርስበት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሰፊ ልዩነት ያለው ነው፡፡ ይህንን አንቀበልም ነው ያልነው፡፡ ይህም እንዳለ ሆኖ ደግሞ እስከ አምስት ዓመት ያገለገለ 14 ቀናት የዓመት ፈቃድ ይሰጠዋል የሚባለውም ቢሆን፣ በአዲሱ ረቂቅ ሌላ አስገዳጅ ነገር የተቀመጠለት ነው፡፡ ይህም ለሠራተኛው ከሚፈቀደው 14 ቀናት ውስጥ ሰባቱን ቀናት አሠሪው የሚያዝበት ሆኖ በረቂቁ መቀመጡ ነው፡፡ ሰባቱን ቀናት ሠራተኛው አያዝበትም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የሠራተኛው በሕግ የተፈቀደ የዓመት ዕረፍት ከሆነ አሠሪው የሚያዝበት ለምንድነው? ግልጽ ቢያደርጉልኝ?

አቶ ካሳሁን፡- ይህ ማለት ለምሳሌ አንተ ችግር ቢኖርብህ ከአሠሪህ ጋር ተነጋግረህ ፕሮግራም አድርገህ ሰባቱን ቀናት ብቻ ነው የዓመት ፈቃድ ብለህ የምትወጣው፡፡ ሰባቱን ቀናት ግን አሠሪው በፈለገ ጊዜ ነው የምትወጣው ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት አንተ ባልፈለግክበት ጊዜ የዓመት ፈቃድ ውጣ ልትባል ትችላለህ፡፡ በፈለግህ ጊዜ ደግሞ አትወጣም ልትባል ትችላለህ፡፡ ስለዚህ በራስህ የዓመት ፈቃድ ሰባቱ ቀናት ላይ አታዝም ብለው ነው ያመጡት፡፡ ይህ ከሆነ የዓመት ፈቃድ መብት አይደለም ማለት ነው ወደሚለው ይዋስድሃል፡፡ በእኔ መብት ላይ ለምን ሌላው ያዛል? ቀደም ብሎ የአሠሪው ሥራ እንዳይጎዳ ሠራተኛውና አሠሪው ተመካክረው የዓመት ፈቃድ ፕሮግራም በጋራ ያወጣል ይላል፡፡ አሁን ግን ይህንን ቆረጡትና ሰባቱን ቀናት በጋራ ያወጣሉ፡፡ ሰባቱ ላይ አሠሪው ብቻ ነው የሚለው መጣ፡፡ ይህ ፍፁም ሊሆን የማይችል ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የተለመደ አሠራር ምንድነው? የዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) ድንጋጌስ እንደ ስታንዳርድ የሚያስቀምጠው የዓመት ፈቃድ መጠን ምን ይላል?

አቶ ካሳሁን፡- አንድ ሠራተኛ አንድ ዓመት ካገለገለ 21 ቀናት የዓመት ዕረፍት ማግኘት የግድ ነው፡፡ በኮንቬንሽንም የተቀመጠው ይኼው ነው፡፡ ሌሎች አገሮችም የሚጠቀሙት ይህንን ነው፡፡ የዓመት ዕረፍት መነሻ 21 ቀናት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እንደየአገሩ ሁኔታ በዓመት ወይም በሁለት ዓመት አንድ ቀን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በእኛ አገር ግን መነሻው ራሱ 14 ቀናት ነው፡፡ አሁን ደግሞ እየተቆራረጠ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ተሰይመዋል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የነበረው አለመረጋጋት አሁን ተሻሽሏል፡፡ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲመት በኋላ የተሻለ ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ ስለመታየቱ እየተነገረ ነው፡፡ እናንተ ከለውጡ ምን ትጠብቃላችሁ?

አቶ ካሣሁን፡- የኢሠማኮ አባላት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ አሁን ዋናው ነገር ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ነው የምንፈልገው፡፡ ሁለተኛ በአገራችን ዴሞክራሲ እንዲኖር ነው የምንፈልገው፡፡ ሰው በአገሩ የማይፈልገውን ተቃውሞ፣ የሚፈልገውን ተቀብሎ የሚኖርበት፣ ይህንን ተናገርክ ተብሎ የማይታሰርበት፣ ስለመብት ተናገርክ ተብሎ ወደ እስር ቤት የማይሄድበት አገር ማየት ነው የምንፈልገው፡፡ መልካም አስተዳደር እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ መልካም አስተዳደር ከሌለ ምንም ነገር መሥራት አይቻልም፡፡ በተለይም ደግሞ ሌብነት በተባለው ላይ የጠነከረ አቋም አለን፡፡ ከዚህ በፊትም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ሌብነትን በመቃወም ሲታገሉ ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ ብንታገልም የሚታገሉን ኃይሎች ደግሞ ኃይላቸው ወይም ሥልጣናቸው ከፍተኛ ስለሆነ ብዙ ገፍተን አልሄድንም፡፡ በሠራተኛውም ሆነ በመላው ሕዝብ ተሳትፎ በሌብነት ውስጥ ያሉ አደብ የሚገዙበት ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ቢያንስ እስካሁን የበሉት ይበቃቸዋል፡፡ ከአሁን በኋላ እንኳን አደብ የሚገዙበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንፈልጋለን፡፡ አገራችን ሰላም ሆና በተለይም ደግሞ በኢኮኖሚ አሁን ከሚመዘገበው ዕድገት በላይ እንዲሆን እንሻለን፡፡ በጋራ ሠርተን የተሻለ አገር እንድትኖረን እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ብዙዎች የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመተንበይ ተቸግረው ነበር፡፡ እርስዎ በግልዎ ለውጥ ይመጣል ብለው አስበው ነበር? ከለውጡ በኋላስ ያለውን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ካሣሁን፡- ከአንድ ዓመት በፊት አሁን ያለው ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ ከአንድ ዓመት ወዲህ ግን ለውጥ ሊኖር እንደሚችል አስቤያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን እንዴት አሰቡ?

አቶ ካሣሁን፡- ምክንያቱም የሕዝብ ተቃውሞ እየበረታ ስለመጣ፣ ይህንን የሕዝብ ታቃውሞ ሊያስቆም የሚችል ነገር የለም፡፡ እንዲህ ዓይነት የሕዝብ ተቃውሞን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ሆነ በሌላ አዋጅ ልታስቆመው አትችልም፡፡ ለውጡ በሕዝቡ ተቃውሞ ሲመጣ በተለያየ መንገድ ነው፡፡ በትክክለኛው መንገድ የሚቃወም አለ፡፡ በሌላ መንገድም የሚቃወም አለ፡፡ ነገር ግን በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ይህ የግድ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ በእርግጥ እኔ በተለይ በኢሕአዴግ ውስጥ እንዲህ ያለ ለውጥ ይፈጠራል ብዬ አልገመትኩም፡፡ እንዲህ ዓይነት የመተጋገል ስሜት መጥቶ ኢሕአዴግ በዚህ ዓይነት መልክ ራሱን ይለውጣል የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን ለውጡ የተነሳው ከራሱ ድርጅት አባላት ስለሆነና ለውጥ ፈላጊዎች እዚያ ውስጥ ታግለው አሁን የሚታየው ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙዎቹ ለውጥ ሊኖር ይችላል ብለው ያስባሉ፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙ ተስፋ ሰጪ ንግግሮች አድርገዋል፡፡ አንዳንዶች ግን የምናምነው ለውጡ በተግባር ሲታይ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ አስተያየት ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ ካሳሁን፡- አሁን በተጀመረው መንገድ የሚኬድ ከሆነ ለውጥ ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተናገሩትን ሰምተናል፡፡ ንግግራቸው ሁላችንንም የሚያስማማ ነው፡፡ አሁን ንግግራቸውን በተግባር ማየት እንፈልጋለን የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አዎ እርሳቸው በተግባር መሥራት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን የእኔ ሥጋት እኛ ፈታኝ እሳቸው ተፈታኝ ሆነው መቅረባቸው ነው፡፡ ምክንያቱም እሳቸው ተናገሩ፣ ተግባራዊ የሚያደርጉት ሥራ አለ፡፡ በእኔ እምነት አብዛኛው ሥራ ያለው ሕዝቡ ዘንድ ነው፡፡ እሳቸው አቅጣጫና አመራር ነው የሚሰጡት እንጂ በእያንዳንዱ ችግር ውስጥ፣ በእያንዳንዱ መሥሪያ ቤት፣ ወረዳ፣ ቀበሌ ገብተው አይታገሉም፡፡ ለተግባራዊነቱ ሕዝቡ አብሮ መታገል አለበት እንጂ እሱ ውጤት ካመጣ በኋላ እኔ አግዛለሁ የሚባል ነገር የለም፡፡ ውጤት ለማምጣት በጋራ መሥራትና መተጋገዝ አለብን፡፡ መንገድና አቅጣጫ ሲደፈንብን አዎ ልንቸገር እንችላለን፡፡ መንገዱና አቅጣጫው ካለ ያንን አጠናክሮ፣ እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በላይ እንዲሠሩ መግፋት ያለብን እኛ ነን የሚል እምነት አለኝ፡፡ የተናገሩትን ወደ ተግባር እንዲለውጡ ሕዝቡ ተባብሮ መግፋት አለበት፡፡ መታገል ያለበት ሕዝቡ ነው፡፡ ከአንድ ወገን ብቻ በመጠበቅ ውጤት ሊመጣ አይችልም በጋራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም ለቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርባችሁ ነበር፡፡ ምላሽ ያላገኘንባቸው ጥያቄዎቻችን ናቸው ያላችኋቸውን ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ታቀርባላችሁ?

አቶ ካሣሁን፡- አዎ፡፡ ቀደም ብዬ ያነሳኋቸው ነገሮች ናቸው፡፡ የሕዝቡ መብት አልተከበረም ሲባል እኮ እኛም እዚያ ውስጥ አለን፡፡ በነፃነት የመደራጀትና የመደራደር መብት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይከበር ነው የምንለው፡፡ ይህንን ነው ያልነው፡፡ በአንዳንድ ድርጅቶች ይህ እስካሁን አልተከበረም፡፡ ችግር አለ፡፡ ይህንን የሚያስፈጽሙ አካላት ተጠናክረው እንዲሠሩ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እነዚህን ሰዎች ዓይተው ይመድቡልናል ብለን እናስባለን፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን መፍትሔ ይሰጡናል ብለን ነው የምናስበው፡፡ በአፈጻጸም ላይ ማለቴ ነው፡፡ ሌላውን እኛ እንሠራለን፡፡ በመንግሥት በኩል ግን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማስከበር፣ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅን የማስከበር፣ የወጡ ሕጎችና ደንቦችን ማስፈጸም የሚችል ኃይል መቀመጥ አለበት፡፡ እነዚህ የለውጥ ኃይሎች ካልተቀመጡ አሁንም እኛ ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡ እንታገላለን፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ሲወያዩ ለአገር የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ በጥናት የተደገፈ ፖሊሲ ማምጣት ትችላላችሁ ብለዋቸው ነበር፡፡ እናንተም ለሠራተኛው የሚሆን ፖሊሲ አምጡ የሚል ዕድል ብታገኙ ምን ዓይነት የሠራተኛ ፖሊሲ ይኑር ብላችሁ ታቀርባላችሁ?

አቶ ካሣሁን፡- የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፖሊሲ ግልጽና ግልጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የየትኛውም አገር ሠራተኞች የሚፈልጉት ለጭቁንና ለአብዛኛው ሕዝብ የሚቆም ፖሊሲ ነው፡፡ ምክንያቱም ለዚህ ኅብረተሰብ የሚሆን እንደ አገር ፖሊሲ መኖር አለበት፡፡ አሁን በፖሊሲ ደረጃ እንደ አገር የነበረው ፖሊሲ ለሠራተኛው ብዙም የሚታማ አይደለም፡፡ እንዲያውም እኛ በተለየ የምንፈልገው ልማታዊ ፖሊሲ ነው፡፡ እንደ ሠራተኛ በአገራችን ዴሞክራሲን የሚያከብር ልማታዊ መንግሥት ነው የምንፈልገው፡፡ ይህንን የምንፈልገው ሌሎች ፖሊሲዎች ለሠራተኛው ጥሩ ስላልሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ልማታዊ መንግሥትን በተለየ የምትፈልጉበት ምክንያት ምንድነው? ሌሎች የፖለቲካ አመለካከቶች ያላቸው ቢሆንስ?

አቶ ካሣሁን፡- ሌሎች የፖሊሲ አስተሳሰቦችና የፖለቲካ አመለካከቶች ለሠራተኞች ጥሩ ስላልሆኑ ነው፡፡ ሌሎች ፖሊሲ አራማጆችን ውጤታቸውንም ስላየን ነው፡፡ ሊብራሊዝምን በተመለከተ በዓለም ላይ የነበረውን ሁኔታ ዓይተናል፡፡ አሁንም እየመጣ ያለውን ችግር ዓይተናል፡፡ ከዚህ አንፃር የሚያዋጣው በትክክለኛ መንገድ ከተመራ ልማታዊ መንግሥት ነው፡፡ በልማታዊ መንግሥት ከሰማይ በታች በግልህ ታደርጋለህ የሚባል ነገር የለም፡፡ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን ይፈቅዳል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሠራተኞች ለምሳሌ በተለይ እኛ የመንግሥት ባንኮች የግል እንዲሆኑ አንፈልግም፡፡ ባንኮች ለውጭ ባንኮች እንዲሸጡ አንፈልግም፡፡ ምክንያቱም ፋይናንስ ማለት ጭንቅላት ነው፡፡ ጭንቅላትህ ከተያዘ መንቀሳቀስ አትችልም፡፡ ይህንን የምንቀበለው የኢሕአዴግ ፖሊሲ ስለሆነ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ ባደጉና ባላደጉ አገሮች በተግባር ያየነው ጉዳይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትና ከለላ ከሌለ ታች ያለው ደሃ ሕዝብ ይጐዳል የሚል እምነት ስላለን ነው፡፡ አሁን አንዳንዶቹ አገሮች ውኃ፣ መብራትና የመሳሰሉት በግል የተያዙ ናቸው፡፡ እነዚህ አገሮች ምን ዓይነት ጉዳት እንደ ደረሰባቸው እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የመብራት መክፈል አቅቷቸው ለአንድ ለሁለት ወር ጨለማ ውስጥ የሚያድሩ አሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ዋጋው ውድ በመሆኑ መክፈል ስላቃታቸው ነው፡፡ በእኛ ስናየው አሁን ባለው የሠራተኛ ደመወዝ ዋጋው ትንሽ ከፍ ካለ ችግር አለ፡፡ በመብራትና በውኃ ላይ የሚመጣውን ነገር መንግሥት እየቻለ ነው እንጂ፣ የግል ቢሆን የሚመጣብን አደጋ ከፍተኛ ነበር፡፡

እንዲሁም የባንኮች ሥራ ለውጭ አለመፈቀዱ ጠቅሞናል፡፡ እነዚህ የግል ባንኮች የተፈጠሩት በአገሬው ሰዎች ነው፡፡ ሀብት በብዙ ሰው እጅ ገባ ማለት ነው፡፡ የውጭ ባንኮች ይገባሉ የሚባል ነገር አለ፡፡ እኛ ይህንን አንደግፍም፡፡ ሌላው ቀርቶ የንግድ ስምምነቶች ሲፈረሙ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መሆን አለበት፡፡ እኛ ገና ታዳጊ አገር ነን፡፡ ለምሳሌ በወጪ ንግድ ከግብፅ፣ ከኬንያ፣ ከደቡብ አፍሪካ ጋር እንወዳደራለን ወይ? ይህንን ታሳቢ ያደረገ ጥንቃቄ የተሞላበት የንግድ ስምምነት ነው የማያስፈልገው፡፡ እንዲህ ያለ ስምምነት ውይይት እየተደረገበት ነው መፈረም ያለበት፡፡ ከዚህ በፊት በንግድ ሚኒስቴር ሥር እንዲህ ያሉ ስምምነቶችን የሚያይ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ የንግድ ምክር ቤት ነበር (ከንግድ ምክር ቤት ሌላ ማለት ነው)፡፡ ከንግድ ምክር ቤት፣ ከሙያ ማኅበራት፣ ከተቃዋሚና ከመሳሰሉት የተውጣጣ ነው፡፡ ይህ ስብስብ ሊፈረም በታሰበው የንግድ ስምምነት ላይ ውይይት ያደርግበትና አቅጣጫ የሚያስቀምጥበት አሠራር ነበር፡፡ ይወስናል ማለት ግን አይደለም፡፡ ስምምነቱ ከአገሪቱ ጥቅም አንፃር እየተመዘነ ይቀርብ ነበር፡፡ 

ሪፖርተር፡- እንዲህ ዓይነት አሠራር ነበር?

አቶ ካሣሁን፡- አዎ ነበር፡፡ እንዲያውም እኛ እንሳተፍበት ነበር፡፡ ያኔ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነበር፡፡ አቶ ግርማ ብሩ በነበሩበት ጊዜ ማለት ነው፡፡ ከአውሮፓ ጋር የሚደረግ የንግድ ስምምነት እንዲቆይ ያደረግነው ሐሳብ ሰጥተን ነው፡፡ ሐሳብ ሰጥተን ብቻ ሳይሆን ጥናት አካሂደን ነው፡፡ አሁን ብንፈርም ምን ሊመጣ እንደሚችል፣ ስንት ሠራተኛ ከሥራ ሊፈናቀል እንደሚችል ሁሉ አቅርበናል፡፡ ከጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ምን ያህል ሠራተኛ ሊፈናቀል እንደሚችልና ችግሩን የሚያሳይ መረጃ ሁሉ አቅርበናል፡፡ ስለዚህ ምርታችንን እስካስተካከልንና የተሻለ ነገር እስኪኖረን ድረስ ስምምነቱ እንዲዘገይ ተደርጓል፡፡ አሁንም ደግሞ የምንለቃቸውና የምናቆያቸው ነገሮች ካሉ ከሁሉም አቅጣጫ ተወያይቶ ለአገር ይጠቅማል አይጠቅምም? በዘላቂነት ምን እንጠቀማለን? ምን እንጐዳለን? ተብሎ በተነፃፃሪነት ታይቶ እንጂ ዝም ብሎ የንግድ ስምምነቶች መፈረም የለባቸውም የሚል እምነት አለኝ፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...